ተደብቃ ታረግዛለች፣ ሰው ሰብስባ ትወልዳለች – አስቻለው ከበደ አበበ

ያኔ ልጅ ሳለን ደርግ ስልጣኑን በሚያጠናክርበት የመጀመሪያው አመታት ከሱዳን መንግስት ጋር የነበረን ግንኙነት ትዝ ይለኛል፡፡ የሱዳኑን መሪ ጃፋር ኒሜሪ፣ ወንድም ተብለው ከፍ ከፍ ይደረጉ ነበር፡፡ በኋላ አብዬቱ በጥሩ አይኑ አላያቸውም መሰል፣ ከየሰፈሩና ት/ቤቱ በተውጣጡ ወጣቶች “ኒሜሪ የተነፈሰ ጎማ ነው፡፡” የሚል መፈክር በአብዮት አደባባይ ደርጉ ሲያስፎክር ዋለ፡፡

ይህ የልጅነት ትዝታዬ ከአርባ አመታት በኋላ  ቀልቤን በትውስታ የገዛው የፌድራሉ መንግስት በአስራ አምስት ቀን ጦርነት መቀሌ የገባ ግዜ ነው፡፡ ጠ/ሚ ለዚያ ድል የሱዳን መንግስት(የጀነራል አልቡርሃን) መንግስት ድንበር በመዝጋት ላደረገው አስተዋጾ አመሰገኑ፡፡ ውሎ ሳያድር ግን የሱዳን መንግስት ወራሪ ነው ተባለ፡፡

አል ቡርሃን በበኩሉ ጠ/ሚ አብይ ና እና ግዛትህ ጠብቅና ያዘ ስላለኝ ነው የገባሁት አለ፡፡ ጠ/ሚ ድንበራችሁን ጠብቁ ነው ያለኩት እንጂ የኢትዮጵያን መሬት ውረሩ አላለኩም አሉ፡፡ አልቡርሃን እንደ ኒሜሪ የተነፈሰ ጎማ ነው ባይባልም የግብጽ ተላላኪ የሚለው ቅጽል ስም ተሰጥቶት እንሰማለን፡፡

እርግጥ ነው ወያኔ/ ኢህአዲግ ኢትዮጵያ ታሪካዊ የሚባል ጠላት የላትም ደርግ የፈጠረላት እንጂ ይለን ነበር፡፡ በኋላ ግን፣ ፕሮጅቸት ኤክስ የተባለውን የህዳሴውን የአባይ ወንዝ  ግድብ  ሲጀመር፣ ግብጽን ታሪካዊ ጠላት ያደርግ ጀመር፡፡

መቼም አልቡርሃን ህጻን ልጅ አይደለም፡፡ እሱ እንኳን ፖለቲካ ባያውቅ የሚያማክሩት የውስጥም የውጭም ሰዎች አያጣም፡፡ ጦርነቱ በፈነዳ ግዜ የህወሃት ትግራይ ሰራዊት የተሻለ አቅም እንዳለው ያውቃል፡፡ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ ካልሆነ በምን ነገር ላይ ተመርኩዞ ጠ/ሚ አብይን  ሊያናግራቸው ይችላል? ጠ/ሚ ቢሆኑ በአስቸኳይ የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ሆነው እገዛውን ለማግኘት ካልሆነ ለምን ደውለው ያናግሩታል?

ይህ ካልሆነ ጠ/ሚ የአይአዎ ፖለቲካዊ ቋንቋ ዘይቤ ተጠቅመው የችግር አፈታት ቅደመ ተከተላቸው እንደራሳቸው አቋም የሚወሰን ሆኖ፣ አደናብረውት ሊሆን ይችላል፡፡ግራም ነፈሰ ቀኝም ነፈሰ እርዳታውን ፈልገው ነበር አግኝተውማል፡፡

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግስትና የትግራይ ክልል ጦርነት ከተካሂደ በኋላ በዚሁ ጦርነት የተሳተፉ ኃይሎችን ብናነሳ፤ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን እንዲሁም የክልል የሆኑት የትግራይ፣ አማራ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ኦሮሚያ…ልዩ ኃይሎችና ሚኒሻዎች በተዋረድ ይገኛሉ፡፡

በእነዚህ ኃይሎች ውስጥ በውስጥ ያደፈጠ “ታላቁ” ክልላችን የሚል ሃሳብ ይዘው ነበር ወደ ጦረነቱ የተገባው፡፡ ታላቋ ትግራይ ኤርትራን ልትጠቀልል ትፈልጋለች፡፡ ታላቋ ሱማሊያ ኢትዮጵያን፣ ጂቡቲንና ኬንያን፣ እንዲሁም ታላቋ ኦሮሚያ ሙሉ ምስራቅ አፍሪካን፣ በኤርትራውያን ዘንድም ይሁን  በአማራው ዘንድ ያሉ ብዙ ወጥተው የማይታዩ ነገር ግን የጥንት ግዛታችን ይህን ያክል ነበር የሚሉ አመለካከቶችም አሉ፡፡ አፋርም ቢሆን በኤርትራ፣ኢትዮጵያና ጅቡቲ የሚገኝ ህዝብ ነው፡፡

እንግዲህ እንዚህን አሰተሳሰቦች በብሔር ማንነት ላይ በህገመንግስት ደረጃ ፋፍተው እንደተያዙ ነው ጠቅምት 24፣ 2013 ላይ ጦርነቱ የፈነዳው፡፡ ጠ/ሚ አብይ አህመድ ጦርነቱን ለአንድ አመት ያክል ከተካሄደ በኋላ “ በዚህ ጦርነት ከሁሉ በላይ ትግራይ ተጎድታለች፡፡ እምንገነባትም እኛ አማሮቹና ኦሮሞዎች ነን…” ብለው ተናግረዋል፡፡ የሳቸው ንግግር ደግሞ የነ ጀነራል ፃድቅንና የነደብረጽዮን ንግግር ቅጂ ሆኖ ነው የተሰማው፡፡

ጠ/ሚ ይህን ከተናገሩ ዘንዳ ጥያቄ ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ያኔ የኢትዮጵያ ሰራዊት መቀሌን ሲይዝ የቤት ለቤት ፍተሸውን የካሄድነው በሰለጠነና ልዩ ሰራዊት ነው፡፡ ምክነያቱም ተራ ወታደሩ ምናልባት እቃ እንዳያነሳና እንደይሰርቅ  በሚል ሀሳብ  አስበን ብለው እኚሁ ጠ/ሚ ነግረውንም ነበር፡፡ ታዲያ ትግራይን ማን አወደማት?

እርግጥ ነው በሰሜን ዕዝ ላይ ህወሓት በወሰደው ጥቃትና በማይከድራ በደረገው ጭፍጨፋ ሰራዊቱ በከፍተኛ ቁጣ ነው ወደጦርነቱ የገባው፡፡ የኤርትራ ጦር ሰራዊትም ከሃያ አመት በፊት የተደረገበትን ቂም የዞ ነው ወደ ትግራይ ጦሩን ያዘመተው፡፡ የትግራይ ልዩ ሰራዊት በባደሜ ጦርነት ግዜ ባረነቱ-ኤርትራ ላይ ከፍተኛ ግፍ ፈጽሞ ነበር፡፡ ከተማውን ዘርፈዋል፣ ማማሳይ እንጨት እንኮን ሳይቀር ወደ ትግራይ ጭነዋል፡፡ ከብቶችን ረሽነዋል…

በዚያን ግዜ በአለምአቀፍ ደረጅ የተሰየመው የካሳ ፍርድ ቤት ይህንኑ የኤርትራ – ባረንቱ ጥፋትና ሻቢያ ጦርነቱ ሲነሳ አሰብ ወደብ ላይ ከያዘው የኢትዮጵያ እቃዎች ጋር በማመዛዘን ለኤርትራ በተወሰን ሚሊዮን ዶላሮች የሚበልጥ ካሳ እንዲከፈል ፈርዷል፡፡ ካሳ ክፍያው ግን አልተፈጸመም፡፡

እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የጦርነትና ውጊያን ልዩነት ማጤን፡፡ በትግራይ ዙሪያ የሚደረገው ታላቅ ጦረነት በትናንሽ የውጊያ ድሎች አስርሽ ምቺው ሲጭፈርበት ነገር ግን ነገሩን ለአንዴና ለመጨረሽ ግዜ መፍታት ሳይቻል እሰከ አሁን ግዜ ድረስ የዘለቀው፡፡ ለዚህ ሁሉ የህዝብ መከራ ተጠያቂው ደግሞ በቅድመ ተከተሉ የመጀመሪያ ረድፍ ላይ የሚገኘው ህወሓት ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የወያኔን የማያባራ ጥፋት በማስቆም ሂደት መሟላት ያለባቸው ወሣኝ ቅድመ ሁኔታዎች! - አንድነት ይበልጣል -ሐዋሳ

ወደ ጀነራል አልቡርሀን እንመለስና አንድ ጥያቄ እናንሳ፡፡ ለምንድን ነው ጀነራል አልቡርሃን በአማራ በኩል ያለውን የሱዳን ይገባኛል መሬት የወረረው? ለምን በሁመራ በኩል ያለውን፣ ያን ግዜ የትግራይ ክልል አካል የነበረውን መሬት ያልነካው ብለን ብንጠይቅ መልሱን እናገኛለን፡፡ ያውም አብይ ጋር፡፡ አብይ ጦረነቱ ከመጀመሩ በፊት አንድ ቀን በፊት ለህውሃት በብሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ልኮም ነበር፡፡

አብይ የመጀመሪያው የጦርነት ምእራፍ እንዳበቃ ግን ጀነራሎቹን በድለላ ቃል ሲናገራቸው ሳተናው፣ ድል ቁርሱ….እያለ ሽነገላቸው፡፡ ጦርነቱን ወያኔ በመልሶ ማጥቃት ሸዋ አድርሶ ሲመልሰው ደግሞ ወያኔ በጀነራሎቹ አካውንት ገንዘብ እያሰገባ ነው ብሎን ነገረን…ግን ለምን? ይህ እንግዲህ ማሸማቀቂያ  ይሁን  ወይንስ ሌላ ግዜ  የሚፈታው ነገር ይሆናል፡፡

እዚህ ላይ ጀነራል ተፈራ ማሞም ማንሳት ግድ ይላል፡፡ እንደኔ እምነት ከሆነ ጀ/ል ተፈራ የታሰረው አብይን ማዋጋት አይቸልም ብሎ ስለተናገረ ነው፡፡ እንዴት ማዋጋት ይችላል? የድድዳዳ ኮድ ኦፊሰር የነበረ ሰው ነው፡፡ የወታደራዊ መገናኛና በኋላ ደግም የስለላ ሰራታኛ የነበረ ሰው ነው፡፡ ፎቶ ልብሱ አብይ ግን፣ እኔ ስለ ዘመትኩ ነው ድል የተገኘው ብሎ ቁጭ አለ፡፡

ፕ/ት ኢሳያስ የጦርነቱን ሁኔታ አስቀድመው ተናግረው ነበር፡፡ የወያኔ ጦር ወደ ሸዋ እየገፋ በሄደ ቁጥር ከደጀኑ እየራቀ ስለሚመጣ ይመታል፡፡ ይኸው ነው የሆነው፡፡ እዚህ ላይ የፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላን ንግግር መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡

ደሴና ኮምበልቻ ከመያዙ በፊት ትንንሽ ከተሞችን መልቀቅ ሰትራተጃዊ ማፈግፈግ ስለሆነ እባካቸሁ ስራችንን እንስራበት ተውን ብለው ነበር፡፡ ሙሉ ወሎ ሲጠፋ ግን ምን እንዳሉ አላውቅም፡፡ በየትኛው ሚሊተሪ ሳይንስ ከተጠያቂነት እነደሚድኑ ባናውቅም ጠ/ሚ ግን ፊልድ ማርሻል አድርገዋቸዋል፡፡

ወይስ እስከ ወሎ- ሸዋ የተለጠጠው ጦርነት ሁን ተብሎ የተደረገ ይሆንን? ይህ ወያኔን ለማሸነፍ የተሰራ የጦርነት ስትራተጂ ከሆነ ደግሞ፣ ወሎ፣ጎንደር፣ሸዋና አፋር ሊካሱ ይገባቸዋል፡፡ በብዙ ቢሊዮንን የሚቆጠር ነብረት ጠፍቷል፣ ብዙም ሕዝብ አልቋል፡፡ የኦሮሚያም ይሁን የደቡብ ክልል …ይህ የጠፋውን ቦታ መልሶ ለማልማት ወጋ መክፈል አለበት፡፡ አለበለዚያ ግን የብልጽግናው አብይ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡ ለእርሰዎ ስልጣን ሲባል የሚጠፋ ሃገር እንደሌለ ማወቅ ይገባል፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን ጠ/ሚ አብይ ከጀነራል አልብሩሃን ጋር የተነጋገሩትን አናውቅም፡፡ ትግራይ ብር ሲልኩም ሆን ከወያኔ መሪዎች ጋር ያደርጉ የነበረው የስልክ ንግግር ስለምን እነደነበረ እንኳን ለህዝቡ አብረዋቸው ላሉ ሰዎች ግልጽ የሚያደርጉላቸው ነገር አልነበረም፡፡በዚህ ፖለቲካዊ ዝሙት የተፈጠረ የመአት ልጅ ደግሞ ሃገሪቱን ከድጥ ወደ ማጡ እለት እለት ሲገፈትራት ይታያል፡፡ በግል ወስነው በሚያደርጉት ነገሮች ችግር ሲነሳ ጩኸቱን ይቀጥላል፡፡ ተደብቃ ታረግዣለች፣ ሰው ሰብስባ ትወልዳለች ይሉሃል ይሄ ነው፡፡

በመቶዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ቤተመንግስት ሄደው ጠ/ሚ አብረዋቸው ፑሽ አፐ ከሰሩ ቦኋላ ወታደሮች ትንሽ የመብት ጥያቄ ነው የጠየቁት ሌላው የፌስ ቡክ ግርግር ነው ብለው ዶ/ር አብይ መግለጫ ሰጡ፡፡ቦኋላ ግን መፈንቅለ መንግስት ነው ብለው አረፉት፡፡ ወታደሮቹንም በወታደራዊ ፍርድ ቤት ቀጡ፡፡

ከዚያም የሪፓብሊካን ጋርድ ስልጠና ተጀመረ፡፡ የዚህ ጦር ኃላፊነት ከጠ/ሚ ጀምሮ የመንግስት ባለስልጣናትን መጠበቅ ነው፡፡ ይሄ ጦር ግን በትግራይ ክልል በተደረገው ጦርነት ተሳትፏል፡፡ ጠ/ሚ በቅርቡ እንደነገሩን ወለጋ ላይ ከኦነግ ሸኔ ጋር ሲታኮስም ነበር፡፡

አንድ በወያኔ/ኢህአድግ ግዜ የነበር ታሪክ ላጫውታቸሁ፡፡ ሞስሊም ተማሪዎች ተደራጀተው እስክሪብቶ ይዘው ”ኢስላም ሰላም “ የሚል መፈክር ይዘው ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ፡፡ ከዚያም ኢህአደግ ተሰብስቦ እንዴት መረጃው ለኛ ሳይደርሰን ሰለፍ ሊያደረጉ ሞከሩ ሲል ጠየቀ፡፡ በግዜው በነበረኝ መረጃ ጭራሽኑ ደህንነቱ ፖሊስን መረጃ አምጡ እያለ ያሰጨንቃቸው ጀመር፡፡ የስራ ጎራ መደበላለቅ ይሉሃል ይሄ ነው፡፡

ወያኔ በአዲስ አበባ ላይ  ከሚሊተሪ ወደ ፖሊስ የተመለሱ ወታደሮችን ኮማንደር እያለ ሾሞ የኢትዮጵያ ጉዳይ ነገር ሁሉ ለእነሱ ተጠቅልሎ እንደተሰጠ በማሰብ ይሰራ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የጎራ መደበላለቅን አስከተለ፡፡ የሚሊተሪው ደህንንት መርካቶ ልብስ ሺያጭ ላይ የሉ ነገዴዎችን ማሰርና መሰወር ጀመረ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በፊት የበቀለን ጅራት በዃላ የበቀለ ቀንድ በለጠው! - አገሬ አዲስ

ሶስስት ወይም አራት አስርቤት የነበራቸው ጄነራሎችም ነበሩ፡፡ ሰው ጠፍቶ ሲፈለግ አከሌ ጋር እንዳለ ይጠየቅ እስከሚባል ደረሰ፡፡ የሀገር ውስጥ ደህንነቱና የብሄራዊው ተናበው የማይሰሩ፣ በየመጠጥ ቤቱ ሲሰክሩ፣ እኔ ወዲ እንትና እይተባባሉ ጦር መሳሪያ ይማዘዙ ጀመር፡፡ ከአዲሳባ ድረስ በማክ መኪናዎች የሚመጣን ሃይልን  አስከ መጠጥ ቤታቸው ሱሉልታ ድረስ እየጠሩ ይፈናከቱ ጀመር፡፡ ዝቅጠት ውደቀትን ይቀድማል እንዲሉ፣ የሚሆነው ሆነባቸው፡፡

ወያኔ/ ኢህአዲግ የዚህን ያህል ለመዝቀጥ  ሃያ ሰባት አመት ፈጅቶበታል ለጠ/ሚ አብይ ብልጽግና ግን አራት አመት ብቻ፡፡ ያው የብልጽግና ስብስብ ተረፈ ኢህአድግም አይደል? የማን ዘር ጎመን ዘር እንዲሉ፡፡

በአብይ ዘመን በጸጥታ መዋቅር ውስጥ ያሉት በዋነኛነት የፌድራሉ ጦር፣ፌድራል ፖሊስ፣ የየክልሉ ፖሊሶች፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚኒሻዎች ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ደህንነቱና የብሔራዊ ደህንቱም አብረው የሚሰሩ ናቸው፡፡

የአብይን ግዜ ለየት የሚያደርገው በጭንቅ ግዜ ና ድረስልኝ ተብሎ የመጣና አሁን ደግሞ የሚገፋው ኢመደበኛው የሚባለው ኃይል፣ ፋኖ በአማራ በኩል መኖሩ ነው፡፡ እንዲሁም ጠ/ሚ አብይ በፌስቡካቸው ላይ ፖስት ባደረጉት መሰረት በስም የልጠቀሱት ኢመደበኛ ኃይል  በኦሮሚያ ይገኛል፡፡

ይህ በኦሮሚያ የሚገኘው ኢመደበኛ ኃይል በአሁኑ ሰዓት በቄለምና ቶሌ ወለጋ ውስጥ አማሮች ላይ ጄኖሳይድ እየፈጸመ የሚገኘው ማለት ነው፡፡ ከበፊትም ጀምሮ በአጣዬ፣ ደቡብ፣ ወሎ፣ ምንጃር፣ አሪሲ ሻሸመኔ…በመንግስት የሚደገፉ የኦሮሞ ኃይሎች፣ የመንግስትን አምቡላንስ፣ መኪናዎች የሚጠቀሙና በኦሮሞ የመከላከያ ሰራዊት የሚደገፉ ኃይሎች አማራውንና ሌላውን ሲገሉና ሲያፈናቅሉ ቆይተዋል፡፡

ለማ መገርሳና አብይ ያደራጇቸው ወታደራዊ ክንፎች እንደነበሯቸው ሲነገር ቆይቷል፡፡ በቅረቡ ምንጃር ላይ የኦሮሚያ ልዩ ኃይል የነበረ ሰው ሙሉ የመንግስት ሪሶርስን ተጠቅሞ ወደ ከተማ  ሲገባ በነዋሪዎችና ሚሊሻዎች በተወሰደበት እርምጃ ተገድሎል፡፡ የዚያን ግዜ የኦሮሚያ ጸጥታ አማካሪ የሆኑት ጀነራል ኃይሉ ጎንፍ እንተያያለን ፉከራቸውን ፎክረው ነበር፡፡

ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን የፀጥታ መዋቅር ይዘው የሚንቀሳቀሱ ሶስት- አራት ቡድኖች ተፈጥረዋል፡፡ አሁን ለነዚህ ቡድኖች መሪና ኃለፊ እየተገኘላቸው ይመስላል፡፡ የኦሮሚያው ብልጽግና ታየ ደንደና ዶ/ር አንጋሶ አቶ ሺመልስ አብዲሳ ነው ይሉናል፡፡

የእዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂው አቶ ሺመልስ አብዲሳ ቢሆን እንኳን፣ ጠ/ሚ አብይ ከተጠያቂነት እንዴት ሊያመልጡ ይችላል፡፡ አንድ ወንጀል ሲሰራ ወነጀሉን የሚሰራ ቀጥተኛ ተሳታፊ ቡድን አለ፡፡ ሌላው ዝም ብሎ የሚያየውም ደግሞ ተጠያቂ ነው፡፡ ፈረንጆቹ (Crime by commission and crime by omission ) የሚሉት አይነት መሆኑነው፡፡

ይህ ድብልቅልቁ የወጣ አካሄድ ለኦሮሞው ምንም አይጠቅመውም፤ እንዲያውንም ኦሮሞን አራት ቦታ ከፍሎ ሊያባለው ይችል እንደይሆን እንጂ፡፡ ለኦነግ ሸኔ ለሚሉት ካውንተር ኢንስረጅንስም ሆኖ የተፈጠረ ኃይል አይደለም፡፡ ሌሎች ትጥቅ ፈተው ሲገቡ፣ መንግስት ኦነግን ከነትጥቁ ወደ ሀገር ቤት ሲያስገባ አስመራ ላይ ምን እንደተነጋገሩም አናውቅም፡፡ ሁሉ ነገር ከህዝብ ተሸሸጎ ነው የተደረገው፡፡ ውጤቱ ግን ታለቅ ጥፋትና ጄኖሳይድ ሆኗል፡፡ ታላቁን ነውጥና እልቂት ግን በሌለበት ለህዝቡ በጩሀት ሊያካፍሉ ይሞክራሉ፡፡  ተደብቃ ታረግዛለች፣ ሰው ሰብስባ ትወልዳለች ማለት ይህም አይደል?

የአስመራና አዲስ አበባ ግንኙነት ተቋማዊ ቅርጹ አለመታወቅም አራሱን የቻለ ችግር ሆኗል፡፡ የኤርትራ ኃይሎች እዚህ ላይ ሊሰሩ ይገባል፡፡  አብይ ወደ ስልጣን እንደመጣ አብዛኛው ሰው ደስ ብሎት ተቀብሎት ነበር፡፡ ኤርትራውም፣ ትግሬውም …ዶ/ደ ደብረ ጽዮን፣ ፕ/ት ኢሳያስና ዶ/ር አብይ ሆነው የሁመራን መንገድ ሲከፍቱ፣ ጦርነት ሊያበቃለት ይሆን ያልን ስንቶቻችን ነበርን?

ጠ/ሚ አብይ ነገሮችን ሁሉ ከህዝብ ለምን እንደሚደብቁ ግራ ያጋባል፡፡ ይህ ግልጽ አለመሆን ደግሞ  ደጋፊዎቻቸውን ከእሳቸው ከማራቅ ባለፈ ሃገሪቷ ላይ የትምምን ፖለቲካ እንዳይሰፍን ምክነያት ሆኗል፡፡ ፍይል ወዲህ ቅዥምዥም ወዲያ እንደሚባለው እሳቸው የሚናገሩት ሌላ የሚሆነው ሌላ፡፡ ይህ ደግሞ ለሤራ ፖለቲካ አካሄድ አጋልጦቸዋል፡፡ አውነትም ይመስላል፡፡

ጠ/ሚሩ አንድ ነገር ተናገሩ ማለት መዓት ይከተላል፡፡ አሁን ደግሞ ወልቃይትንና ራያን የሚጠብቀው የኦሮሞ ወታደር ነው ይሉናል፡፡ አልጠብቅምስ ካለ… ወታደሩን በኢትዮጵያ ቁመና አደራጅተናል ሲሉ ከርመው በብሔር መልሰው ይለያዩታል፡፡ እንዲህ ያለው አካሄድ ጠ/ሚ አብይ ለኢትዮጵያ ፕላን ቢ እንዳላቸው ያሳያል፡፡ አንዲህ ካልሆን እንዲያ የሚል አይነት አካሄድ ማለት ነው፡፡ እንደዚያ ካልሆነ ለምን በወታደሩ መካከል ልዩነት ለመፍጠር ተፈለገ፡፡ ወደ ግል ስልጣናቸው የሚመጣ ኃይል ካለ የወታደሮች እርስ በእርስ ግድያና አመጽን(Mutiny) እንዲፈጠር ሃሳብን በማጫር (Initiate) በማድረግ አስቀድሞ መከላከልን የያዙ ይመስላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ዘር ማጥራት ወይስ ኢህአዴግን ማፍረስ ? (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ )

ኦሮሞ በባህሉ አንድ ነው ቢባልም በአበላሉ፣ በአዘፋፈኑ፣በአስተዳደራዊ ይዞታውና አካሄዱ… ይለያያል፡፡ የወለጋውና የጂማው ኦሮሞ በንጉስ ሲገዛ የነበረ ነው፡፡ የሃረሩ ደግሞ ሶማሌ አቦ ብሎ የታገል ነው፡፡ አይ.ኤፍ. ል. ኦ(Islamic Front for the Libration of Oromiya) ያሉ ድርጅቶችን ማሰብ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ላይ የውስጥም ይሁን የውጭ የራሳቸው ፍላጎት ያላቸውን ትልልቅ አቅም ያላቸው ድርጅቶች የቀጥታና ስውር እጅ ሲታሰብ ዛሬ ኦሮሚያ ላይ አማራወ፣ጉራጌው፣አገዉ፣ጋሞው…ነው የሚጋደለው፤ ነገ ግን እርስ በእራሱ ይሆናል፡፡

በመጨረሻም አንድ ነገር ብይ ነገሬን ልቋጭ፡፡ የመጀመሪያ የሪፓብሊካን ጦር ምረቃ ላይ ይመስለኛል አንዲት ሴት የደረገችውን ትእይንት ለአንድ እዚህ ሃገር ላለች ወታደር ቀመስ ሴት ፈረንጅ በግዜው አሳይቻት ነበር፡፡

ወታደሯ ወደ ፊት ተጎንብሳ ሁለት እጆቿን በእግሯ ስር በማሳለፍ፣ ጭንቅላቷን ከመቀመጫዋ ስር ብቅ አድርጋ ወደ ኋላ እያየች፣ በእጆ በያዘችው ሽጉጥ በርቀት የተሰቀለን ጀበና ስትመታ የሚያሳይ ትእይንት ነበር፡፡

“የምን አባል ነች?” አለችኝ፡፡ የሪፓብሊካን ዘብ ብዬ መለስኩላት፡፡

ከት ብላ ስቃ “ታደያ ይሄ ምንን ያረጋግጣል?” አለች፡፡

“ምንአልባት በለተመቻች ሁኔታም ውስጥ ሆኖ ኢላማን አለመሳት፡፡” አልኳት

የሄኔ “አይህ አንዳንድ ፌሚኒስት ጸሐፊዎች ቢያያት ሌላ ትርጉም ነበር የሚሰጡት“ አለች ፡፡ እኔም ንግግሯ ገባኝ፡፡

እንዲህ ያሉ ፌሚኒስት የሆኑ ሴቶች አንድ ግዜ መጽሐፍ ጽፈው፣ ሚሳኤልም ሆነ ጥይት የሚሰራው በወንድ ብልት ቅርጽ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሁን ተብሎ የወንድን የበላይነት ለመግዘፍ ነው ብለው ተከራከሩ፡፡ የወንዶቹ መልስ ግን የሚሳኤሉ ማስፈንጠሪያ መርከብ የእናንተን አይደለም ወይ የሚመስለው ሆነ መልሳቸው፡፡

ቀጠለች “በእናንተ ሃገር ያለው ፌድራሊዝም ኢቲኒክ ነው አይደል?” አለችኝ፡፡ አወንታዬን ከሰባት አመት በፊት ከለኝ ተሞክሮ ጋር አያይዤ ነገርኳት፡፡

አንዳንዴ ሚኒስትሮች እገሌ የሚባለው ሰው ሴኩሪቲ ይመደብልኝ ብለው የበሔራቸውን ተወላጅ የሚያሰመድቡበትን አግባብ እንደነበረም ጨምሬ አዓወትኳ፡፡ ይሄኔ “ሃገራችሁ አምባገነን መንግስት የመሆን እድሏ ትልቅ ነው፡፡” አለችኝ፡፡

እውነትም ከዚያ በኋላ የሃገራችን ሁኔታን ስመለከት፣ ወደና ፈቅዳ ወደ አምባገነንነት እያመራች ነው፡፡ ይኸውም ድቅል አምባገነን(Hybrid Dictatership)የሚባለውን አይነት ነው፡፡ በዚህ አምባገነንነት ውስጥ ምርጫ ይፈቀዳል፡፡ ስልጣን በታማኘነት እንጂ በችሎታ አይሰጥም፡፡ የግለሰብ የበላይነት ይነግሳል ፡፡ የፓርቲ የበላይነት በምነም መልኩ ይጠበቃል ሌሎች ተፎካካሪ ፓረቲዎች እንዳሉ ማለት ነው፡፡ በከፋፍለህ ግዛው ተቃዋሚዎችን እርስ በእርስ ያባለላል…

ብቻ አሁን ሃገራችን ውስጥ የምናየው ነገር ሁሉ ይከናወናል፡፡ ይህንም መንገድ አብይ ሁን ብሎ ቲዎሪውን አጥነቶና አስጠንቶ እየተገበረው ይገኛል፡፡ እነ አባ ቶረቤም ይሁን የመንግስት የሆነው ኦነግ ሽኔ ጠላቶችን ከፋፍሎ ለመምታት በመንግስት የተፈጠሩና ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ አደረጃጀቶች ናቸው፡፡ በዚህ አካሄዳቸውም ህዝብን እየቆሉና እያመሱ ይገኛሉ፡፡

ሰው ሞተም ሲሏቸው አሜሪካ ውስጥ በዚህ ዓመተ ምህረት በተለያዩ ሁኔታዎች ሃያ ሺህ ሰው ተገደሏል ይሉናል፡፡ እንደዛማ  ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ በለፈው አንድ አመት ከሰኔ እስከ ሰኔ የሞተው ሰው ቁጥር ወደ አንደ ሚሊዮን ይጠጋል፡፡ እስኪ እንቁጠረው በትግራይና ፌድራል ጦረነት ያለቀው ሰው፣ እሱን ተከትሎ በመጣው ርሃብና ዕርዛት የሞተው፣ በየ ቦታው የሚገደለው ሕዝብ በተለይ አማራው …

የአሜሪካ ህዝብ ቁጥር 329,500,000 ሲሆን  የኢትዮጵያ የህዝብ ቁጥር ደግሞ 120,000,000 ነው፡፡ ለሃያ ሺው በሬሾው በኢትዮጵያ አንጻር ቁጥር ሲሰራለት 7280 ሰው ይደርሳል ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ያክል ሰው ቢሞት ኖሮ እውነት ነው የአሜሪካው ምሳሌ ይሰራ ነበር፡፡ ግን እኮ አንድ ሚሊዮን ሰው ነው የሞተው፡፡ ያ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነው ሞት አሜሪካው ከነበረው ሞት 137 እጥፍ ያደርገዋል፡፡ አበቃሁ!

 

አስቻለው ከበደ አበበ

ሜትሮ ቫንኩቨር ካናዳ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share