የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ የምሥረታ ወርቅ ኢዮቤልዩ ሲፈተሽ (ፕሮፈሶር ኀይሌ ላሬቦ)

የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ዘንድሮ የምሥረታውን የወርቅ ኢዮቤልዩ ማለትም ዐምሳኛውን ዓመት [በአ.አ. 1972-2022] በማክበር ላይ ይገኛል። በዓሉ የሚገልጥልን ነገር ቢኖር፣ የአገራችን ሕዝብ ከታሪክ መማርም ቀልብ መግዛትም እንደተሳነው ነው ብል ስሕተት አይመስለኝም። ገለልተኝነትን በተላበሰ የታሪክ መነጽር ብናየው፣ ኢሕአፓ ልክ እንደሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይና [ሕወሓት]  የኦሮሞ ነጻነት ግንባር [ኦነግ]፣ ዛሬ መወገዝ፣ መሰደድና ከሥረመሠረቱ መጥፋት ያለበት ሽብርተኛ ድርጅት እንጂ እንደዚህ በአደባባይ ስሙ በክብር መጠራት የሚገባው አይደለም። አዞ የተባለው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ቡድን አካልና ጭንጋፍ እንደመሆኑ፣ ከ፲፱፻፷ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ በኢትዮጵያ በየዘርፉ ለተከሠተው የሐሰት ታሪክ ስርጭትና የርእዮተዓለም ቀውስም ሆነ ላስከተለው ኢሰብኣዊ ተግባር፣ ማለትም አሁን በኦሮሚያም ሆነ በትግራይ በሌሎችም ክልሎች ጭምር፣ በከፍተኛ ደረጃ ከሚጠየቁት ዋነኞቹ አንዱ ኢሕአፓ እንደሆነ አይካድም።

EPRP 1

የአዞም የኢሕአፓም የጡት አባቶቻቸው የኤርትራው ነፃ አውጪ ድርጅቶች ሲሆኑ፣ የነዚህን ሕልም እውን ያደረጉት ደግሞ ኢሕአፓና ሕወሓት እንደሆኑ አይካድም። ኢሕአፓ በኅብረብሔርነት፣ ሕወሓት በጐሣነት ላይ የተመሠረቱ የማይጣጣሙ ድርጅቶች መስለው ቢታዩም፣ በዓላማቸውና በርእዮታቸው ግን የማይለዩ መሆናቸው ማወቅ ያስፈልጋል። ዋና ዓላማቸው ሥልጣን ሲሆን፣ የተጠቀሙትም  የጡት አባቶቻቸውን የመገንጠል ጥያቄ በኢትዮጵያ የጭቁን ብሔሮች ሽፋን ለማስፈጸም እንደሆነ ድርጊታቸው ይመሰክራል። ሁለቱም ከተማሪዎች እንቅስቃሴ በተዋሱት፣ “ብሔር፣ ብሔረሰቦች  የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብት እስከመገንጠል” በሚል መርህ ዙርያ የተሰባሰቡ ሲሆኑ፣ ልዩነታቸው የትኛው አስቀድሞ ይተግበር በሚለው ላይ ብቻ ነው። ኢሕአፓ “ትግሉ ሊሠምር የሚችለው በኅብረብሔራዊ ድርጅት ሲመራ ነው” ሲል፣ ሕወሓቶች፣ “የለም፤ በቀዳሚነት የተለያዩ ጭቁን ብሔር፣ብሔረሰቦች በየራሳቸው ድርጅት አማካኝነት ትግላቸውን ጀምረው፣ ከዚያ በኋላ የኅብረት ግንባር ሲፈጥሩ ነው” ይላሉ። ስለዚህ ሁለቱ የሚለዩት በስልት እንጂ በርእዮተ ዓለም ወይንም በእኩይ ተግባራቸው አይደለም።

ሁለቱም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያንቋሽሹ፣ አባቶችንና ታሪክን የሚያዋርዱ፣ በአጉል ትምክህትና ትዕቢት ያበጡ፣ የማይስማማቸውን በጭካኔ ከማረድም ወደኋላ የማይሉ፣ ለሥልጣንና ለገንዘብ ሲሉ አገር ከመሸጥ ወይንም ከጠላት ጋር ወግነው የገዛ አገራቸውን ከመውጋት ዐይናቸውን የማያሹ፣ ብዙ ‘ኢሰብኣዊ” ወይንም “አሬመኔኣዊ”ና “ባንዳዊ” ተግባሮች የፈጸሙ እንደሆኑ ደጋግሞ ታሪካቸው ይመሰክራል። ከኢሰብኣዊ ተግባራት መካከል የጌታቸው ማሩ አገዳደል ሊጠቀስ ይችላል። አቶ ክፍሉ ታደሰና አቶ ተስፋይ ደበሳይ የሽብር ተግባራቸውን የተቃወመውን የድርጅቱ የፓለቲካ ቢሮ ተለዋዋጭ አባል የነበረውን አቶ ጌታቸውን ከገደሉት በኋላ፣ ራሱን፣ እጁንና፣ እግሩን፣ ሌላውን አካላቱን ቈራርጠው በጆንያ ከትተው ይዘውት ሲሄዱ ተይዘው ሁለቱም ሸሽተው እንዳመለጡ ሻምበል ተስፋዬ ርስቴ በ“ምስክርነት” መጽሐፋቸው ይነግሩናል። ይኸ ዐይነት ጭካኔ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ መሬት ሲፈጸም፣ የመጀመርያው ሳይሆን አይቀርም። የኢሕአፓን ባንዳነት ድርጅቱ በሱማሌ ወረራ ወቅት የፈጸመው ክህደት ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። ወረራውን መደገፍ ብቻ ሳይሆን፣ በወቅቱ ከሱማሌው መሪ ሲያድ ባሬ ወደዐምስት ሚሊዮን ብር ወደድርጅቱ እጅ እንደገባ ይነገራል። ኢሕአፓ ይኸንን አስነዋሪ ድርጊት እንደለመደው ቢክድም ዓለም ያወቀው ፀሓይ የሞቀው የአደባባይ ምስጢር ከመሆን አላመለጠም።

ኢሕአፓና ሕወሓት በኢትዮጵያ ጥንታዊነትና ታላቅነት አያምኑም። በነሱ አስተያየት፣ ዓለም የሚደነቅበት፣ የመላው ዓለም ጥቊር ሕዝብ የሚኰራበት፣ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው፣ ከአፄ ምኒልክ ሲሆን፣ ሌላው ትርክት የደብተሮች ፈጠራ ነው። ከስድስት ሺ ዓመታት በላይ ያስቈጠረውን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የርስበርስ መወላለድ፣ በአምቻና በጋብቻ መገማመድ፣ በባህልና በሀብት መቋደስ፣ በቋንቋና በሃይማኖት መተሳሰር ምንም ዋጋ አይሰጡም። ኢትዮጵያ ለነሱ፣ “አንድ አማራ በተባለ ጨቋኝ ብሔረሰብ ወረራ የተቋቋመች፣ መቶ አምሳ ዓመት የማይሞላ ታሪክ ያላት አገር ናት። በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያ፣ አማራው በሁሉም ዘርፍ የበላይነቱን ይዞ የሚገዛባት፣ አማራ ያልሆነው ብሔረሰብ ግን፣ በግፍና በገፍ የሚማቅባት እስር ቤት በመሆኗ፣ ፈርሳ፣ጨቋኝና ተጨቋኝ በሌለበት መልኩ፣ እነሱ በምናባቸው በቃዡት አምሳል በአዲስ መልክ መገንባት ይኖርባታል” ይላሉ።

በዚህም አቋማቸው ኢሕአፓና ሕወሓት የጠቅላላው ጥቁር ሕዝብም ሆነ እንደነጻነቱ አረቦን ትታይ የነበረችው የኢትዮጵያ ጠላት የሆነው የአውስትሪያ ቄሣራዊ ሥርዐት አቀንቃኝ (ኢምፔርያሊስት) የባሮን ፕሮቻስካ ታማኝ ደቀመዛሙርት መሆናቸውን ያስረዱናል። የፓለቲካ ቋንቋቸውም ሆነ፣ ራእያቸውና ስልታቸው እንዳሉ የተቀዱት እሱ ኢትዮጵያ በመላው ዓለም ለተዘረጋው ለነጭ ዘር የበላይነትና ዐምባገነንነት ስጋት እንዳትሆን ነጮች አገሪቷን እንዴት አድርገው ማጥፋት፣ ግዛቶቿንም መበታተን ይገባቸዋል ሲል ከደረሰው “ኢትዮጵያ የባሩድ ቤርሚል” ከሚለው መጽሐፉ እንደሆነ አያጠራጥርም።

ይሁንና፣ ኢሕአፓ በነዛው የሐሰት ወኔ ቀስቃሽ ስብከቱ፣ በአገር ፍቅር ስሜት የነደደውን፣ ዘመናዊ ትምህርቱን ከአገራችን ነባር ታሪክም ሆነ፣ ሥርዐትና ወግ ማጣጣም ያቃተውን፣ የቦዘኔውንና የሕልመኛውን፣ እንዲሁም የግልቱንና የገልቱን ወጣት ቀልብ በሰፊው ሊስብ እንደበቃ አይካድም። እልፍ አእላፋት ንጹሓን ኢትዮጵያውያንም ድርጅቱ ለሥውር ዓላማው ሲል በፈጠረው ነጭ ሽብር የተባለ የግድያ መፈክሩ ሰለባ ሁነዋል። የራሱም ተከታዮች ክፉ ድርጊታቸው ባስከተለው በቀይሽብር ጦስ ለእንግልትና ለእልቂት ሲዳረጉ፣ከመሪዎቹ መካከል ጥቂቶቹ ራሳቸው በከፈቱት ጦርነት ቢሞቱም፣ ብዙዎቹ ግን፣ዕቅዳቸው ሲባክንና ሲመክን፣ እንደምንደኛ እረኛ ጀሌዎቻቸውን በጠላላ ሜዳ ጥለው፣ ጓዛቸውን ጠቅልለው፣ ወደውጭ አገር እንደፈረጠጡ፣ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ስለሆነ እዚህ መድገም ተገቢ አይመስለኝም።

ኢሕአፓ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳከም፣ ቢቻልም ለማጥፋት፣ ከተነሡት ድርጅቶች አንዱ ቢሆንም፣ የቋመጠው ሥልጣን ግን የውሃ ሽታ ሁኖ ቀርቶበታል። በለስ የቀናለት ልክ እንደኢሕአፓ፣ በኤርትራ ነፃ አውጭ ድርጅቶች፣ በተለይም በሻቢያ ትዝላትና እንክብካቤ ያደገው ሕወሓት ቢሆንም፣ የማታ ማታ እሱንም ለአፄ ምኒልክ ቤተመንግሥት ያበቃው በቀዝቃዛ ጦርነት ፍጻሜ ላይ በአዲሱ የዓለም ኀይሎች አሰላለፍ ብቸኛዋ የዓለም ዘበኛ ሁና የቀረችው አሜሪቃ ናት። ሕወሓት መላዋን ኢትዮጵያን የመግዛት ዕድል እንደገጠመው፣ በጌታው በአሜሪቃና በተጨባጭ በአገሩ ሁናቴ ተገፋፍቶ፣ የኅብረብሔርነት ሽፋን ለመስጠት ሲል ኢሕአዴግ የተባለ የዳቦ ስም በመስጠት የመርሀግብሩ አስፈጻሚዎች እንዲሆኑ በየክልሉ የየብሔራቸው ምስለኔዎቹ እንዲሆኑለት አስተማማኝ ናቸው ያላቸውን መልምሏል። ይኸ የወያኔ አወዳሽና አጐንባሽ የጐጠኞች፣ የአገርና የወገን ካጆች ክበብ የሞላው በሌላ ሳይሆን በኢሕአፓ አባላት እንደሆነ ለመረዳት ሌላውን ሁሉ ትቶ እነታምራት ላይኔን የመሳሰሉ ያሉበትን ግዙፉን የአማራን ክልል ብቻ መመልከቱ ይበቃል።

ኢሕአፓዎችና ጀሌዎቻቸው ብዙውን ጊዜ አጉራ ሲጠናባቸው፣ እንደመከላከያ የሚያነሡት ለእምነቱ ሲል የደርግን መድፍ ሳይፈራ በመቋቋም በጦር ሜዳ ላይ ሕይወቱን የሠዋውን የወጣት ብዛት ነው። የዚህን አስተሳሰብ ፈር ከተከተልን መዘዙ አስፈሪ መሆኑ አይካድም። ከፍተኛ ጥፋትና ውድመትም ሊያመጣ ይችላል። በአሜሪቃን የርስበርስ ጦርነት ጥቁሮች ጭንቅላታቸው ከዝንጀሮው ስለማይበልጥና ከሰው ልጅ በታች ስለሆኑ ከነጭ ዘር እኩል ሊታዩ አይችሉም ብለው ጦርነት የቀሰቀሱት የጥምረት መንግሥት (ኮንፌዴራሲ – Confederates) ኀይሎች፤ የአንድመቶ ዐሥርሺ አንድመቶ (110,100)  ሰዎችን ሕይወት በከንቱ በጦር ሜዳ ላይ ሠውተዋል። የሟቾቹ ቁጥር በመላው የአሜሪቃን ታሪክ ወደር የሌለው እንደሆነ ይታወቃል። ይኸም ሌላው ከፍተኛ ውድመትና ምስቅልቅል ሳይቈጠር ማለት ነው። ታዲያ የአንድነት (ዩኒዮኒስት – Unionists) ኀይል መድፍ ስላላስፈራቸውና ብርቅ ሕይወታቸውን ስለሠው ብቻ የባለጥምረት መንግሥት ኀይሎች በራእያቸውና በዓላማቸው ትክክል ነበሩ ማለት ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ከሚሉት ዐይነት ወግ ይመሳሰላል። የኢሕአፓም ሁናቴ ከዚህ አይለይም።

ኢሕአፓዎች የተካኑበት ሌላም መስክ አለ። ሐቁ ሲነገራቸው አንዲት ብጣሽ ዐረፍተነገር እንኳን መዝዞ በማውጣት ሐሰቱ ከምን ላይ እንደሆነ ሳይገልጡ ጽሑፉን በጭፍኑ የውሸት ታሪክ ነው በማለት ማጥላላትና መኰነን አንዱና ዋነኛው ነው። ከዚያም ባለፈ ጸሓፊውን መሳደብ፣ ያልሆነ ስም በማውጣት ወይንም ከወራዳ ድርጅት ጋር በማያያዝ ማሸማቀቅ እንደሃይማኖታቸው ቀኖና አድርገው ይዘውታል፤  ሁለተኛ ባሕርያቸው እስከሚመስል ድረስ። ርግጥ፣ እውነት ትመርራለች። አንጐልና ቅንነት ያለው ሰው ግን በሆነ ባልሆነ መመጻደቁን ትቶ ብትመርም፣ ብታሳዝንም ብትከብድም እውነቱን በጀ ብሎ ይቀበላል፤ ይማራል፣ ይታረማልም። አጉራ ሲጠናበት አጠናና ተጠያቂነት የጐደለው ግልብ ሐተታ የሚጠበቀው ከጅልና ከጥራዘ ነጠቅ ብቻ ነውና።

በገዳይነቱና በጭካኔው ኢሕአፓ ከሕወሓት አያንስም። በማንኛውም መመዘኛ ከደርግ ይከፋል እንጂ አይሻልም ማለት ይቻላል። ይሁንና ሕወሓት ሥልጣን እንደጨበጠ ለቀድሞ የሽብር አጋሩ ለኢሕአፓ የዋለው ከፍተኛ ውለታ ቢኖር የቀይ ሽብር ፈጻሚዎችን ለፍርድ አቅርቦ ሲቀጣ፣  በኢሕአፓ ለተጨፈጨፉት የነጭ ሽብር ሰለባዎች ግን ደንታም አልሰጠም። ታሪክ ረስቷቸው ደማቸው ደመከልብ ሁኖ ቀርቶ ዛሬም የፍትህ ያለህ እያሉ እንደጮሁ ናቸው። ፍትህ የአሸናፊዎች ደንገጡር ናት ካልተባለ በስተቀር ለነሱም መልስ ሊሰጣቸው ይገባል። እነዚህ የሞቱት ኢሕአፓ በራሱ ቀስቃሽነት በጀመረው በነጭ ሽብር መሆኑ ይታወቃል። ታዲያ ኢሕአፓ ቅንጣት የምታክል ልቦና ካለው፣ በዚህ የውደመት ተግባሩና ታሪኩ ማፈርና መጸጸት ሲገባው መኩራትና ሽር ጒድ ማለት ለትዝብት፣ ከዚያም ባሻገር በድርጅቱ ሰለባዎችና እሱም ባደረሰው በአገሪቷ ቊስል ዕንጨት ስደድበት ለማለት ካልሆነ በስተቀር ፋይዳው ግልጥ አይደለም።  የፍልስፍና አባት እንደሆነ የሚነገርለት ሶቅራጢስ “ያልተፈተሸ ሕይወት መኖር ብላሽ ነው” ያለው ዘይቤ የኢሕአፓና የተከታዮቹ  ዕጣ ፈንታ ሁኖ ከቀረ ቈይቷል። ከታሪኩና ከድርጊቱ ጋር ለመታረቅና ለመጣጣም የማይፈልግ ድርጅት ዐቅመቢስ ከመሆን ባሻገር ፋይዳቢስም እንደሆነ የሕይወት አመክሮ ይነግረናል። በዚህ ዕይታ ኢሕአፓ እያከበረ ያለው የሕያዌነቱን የወርቅ ኢዮቤልዩን ሳይሆን የሞት ተዝካሩን ነው ማለት ይቻላል። ገና ከጥንስሱ የሞተ ነበርና። ይኸም የድርጅቱ ህልውናና ማንነት ትክክለኛ መግለጫ መሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም።

“ከታሪክ መድረክ – ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ትናንትናና ዛሬ” ከተሰኘው መጣጥፌ የተቀነጨበ። መሉዉን መጣጥፍ ለማንበብ ከፈለጉ በዚህ ያገኙታል። ማስፈንጠርያውን ይጫኑት።  https://www.academia.edu/82676278

10 Comments

 1. ፕሮፌሰር ሀይሌ በውነት የምክር መለኪያ ነህ ይሄ አንዴ ተነቦ የሚታለፍ ሳይሆን ተደጋግሞ የሚነበብ ነውና ኢህአፓን በተመለከተ ወድፊትም ወደሁዋላም ወደግራም ወደቀኝም ተጉዘህ ቁልጭ አድርገህ አስቀምጠህልናል። ዛሬም ተገልብጠው በየቦታው አቅማቸው ሲደክም በብእር ብልጣብልጥነቱ ያላለቀባቸው አሸናፊውን ግፈኛ ስርአት በመጠጋት አገርን ጤና ይነሳሉ ያሬድ ጥበቡ፣ታምራት ላይኔ፣ብርሀኑ ነጋ፣አንዳርጋቸው ጽጌ የመሳሰሉት ላብነት ይጠቀሳሉ። እናመሰግናለን የነጠረ ምሁራዊ ጽሁፍ ነው

 2. መቸም ይህች አገር በታሪክ አዋቂነት ስም የማይወዱትን ሁሉ በጅምላ () ማውገዝ እንጅ ከአንድ ነገር አገራውና ዓለም አቀፋይ ነባራዊ ሁኔታ () እያነበቡና እያናበቡ ለትውልድ ማሳወቅ (ማስተማር) የሚፈልግና የሚችል ምሁር መናጢ ደሃ ከሆነች ቆየች። የሚገርመው ከግማሽ መቶ ክፍለ ዘመን በኋላም ይህ ትውልድ ከዚያ ትውልድ( ከኢህአፓ) ስህተትና ጥንካሬ በሚገባ ተምሮ የራሱን ታሪክ እንዲሰራ ከማሳወቅ ይል ኢምሁራዊ በሆነ እጅግ ደምሳሳ የትንታኔ ድሪቶ ትውልድን ማደናገር በጣም ያሳዝናል። መቸም ኢህአፓ አይወቀስ እና የአሁኖቹ ኢህአፓዎች ደግሞ ምንም አይነት ፋይዳ ያለው የፖለቲካ ሥራ ሳይሠሩ የእድሜን ርዝማኔ ብቻ እያሰቡና ወደ ፊት የማያራምድ ዲስኩር እየደሰኮሩ መቀጠላቸው ትክክል እንዳልሆነ መተቸት አይገባም የሚል ጤነኛ ሰው አይኖርም። ኢህአፓንና ከጥንት እስካሁን በጎሳ ፖለቲካ እየሠከሩ የዘር ፍጅት ካካሄዱትና እያካሄዱ ካሉት ድርጅቶች ጋር አንድ አርጎ ማየት ግን የምሁርነት ድንቁርና ወይም የጭፍን ጥላቻ ጋግርታምነት እንጅ ሌላ ሊሆን አይችልም ። የታሪክ ምሁርነት በእንዲህ አይነት እጅግ ደምሳሳና ጨርሶ የሰለጠነ ፖለቲካ አስተማሪነት የሌለው የትንታኔ ድሪቶ አሁን ላለው ችግር ጨርሶ መፍትሄ አይሆንም።
  እናም እባካችሁ ምሁሮቻችን ይህ ትውልድከቀደመውትውልድ ጥፋትና ልማት እየተማረ የራሱን የታሪክ ድርሻ እንዲወጣ በቅጡ ምከሩት እንጅ አሁንም ያለፈውን ትውልድ እየወቀሰና እየከሰሰ ራሱ ግን የቁም ሙት ሆኖ እንዲቀጥል አትፍረዱበት!!!

 3. TG “የትንታኔ ድሪቶ አሁን ላለው ችግር ጨርሶ መፍትሄ አይሆንም” መሳደብ ማሸማቀቁ እንዳለ ሁኖ አንድ የሚነበብ አይን የሚስብ ጽሁፍ ለእይታ አቅርበህ ታውቃለህ? እንግዲህ ታሪክህ የተነገረው ያንተ ከሆነ ፕሮፌሰሩ እንዳለው ማሸማቀቁና ስድቡ ቀርቶ አንድ ፍሬ ያለው ነገር ብታመላክተን ጥሩ ነበር፡፡ ፕሮፌሰሩን መቼም በዚህ አታማውም ጎግለህ የሰራውን መመልከት ነው፡፡ በተረፈ ብሽሽቁ ያለፈውን አትንኩብኝ የሚለው ነገር ለድርጅቶቹም ሆነ ለሃሳቡ ተሸካሚዎች የሚበጅ ባለመሆኑ የሌላንም ሃሳብ ለመስማት መዘጋጀት መልካም ይመስላል፡፡ የሚገርመው ፕሮፌሰሩም በጽሁፉ ይህ ሊመጣ እንደሚችል ጠቁሞ ነበር፡፡

 4. In terms of building Ethiopia, there is nothing positive to be said of the EPRP. On the other hand, in terms of destroying Ethiopia, EPRP has a role in both the Derg’s and the TPLF’s dismantling of the nation. It would have not been possible for TPLF to put the Ethiopian people in general and the Amhara people in particular in the current state of affairs without the complicity and assistance of former EPRP members. Well put, professor.

  ይኸ የወያኔ አወዳሽና አጐንባሽ የጐጠኞች፣ የአገርና የወገን ካጆች ክበብ የሞላው በሌላ ሳይሆን በኢሕአፓ አባላት እንደሆነ ለመረዳት ሌላውን ሁሉ ትቶ እነታምራት ላይኔን የመሳሰሉ ያሉበትን ግዙፉን የአማራን ክልል ብቻ መመልከቱ ይበቃል።

  We appreciate the courage of the valiant EPRP Ethiopians but we cannot deny that the organization was a tool of the enemies of Ethiopia, as its actions had spoken loudly.

  What the new generation should learn from the history of the EPRP is to understand that African politics has more remote players and movers than the eye beholds.

 5. መሬት ለአራሹ ዲሞክራሲ ለህዝቡ ብሎ ለህይወቱ ሳይሳሳ የታገለ የተሰዋ ትውልድን በጅምላ የሚኮንኑ በጣም የሚያሳዝኑ ፍጡራን ናቸው:: በዚያ ትውልድ ሃገር ቤትም ሆነ ሰሜን አሜሪካና አውሮፓ ከተመቸ ሃገር ወደምድራቸው መጥተው የታገሉ የተሰዉ በሁለቱም መስመር የነበሩ ታጋዮች ስራቸው ዘወተር ሲታሰብ ይኖራል:: በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በቅኝ ግዛት የተያዙ ህዝቦችን ነጻ ለማውጣት የቅኝ ገዥዎቹ ወዳጆች ምእራባዊያንን ጭምር ሲፋለም የነበረው የማርክሲዝም ፍልስፍናን አንጋፋው ታጋይ ኔልሰን ማንዴላና መሰሎቹ ታጋዮች መጠቀማቸውን ታሪክ ይመሰክራል:: በዚያ ትውልድ ትግልና መስዋእትነት መሬት ላራሹ መሆኑ ከሰው በታች ይቆጠሩ ይናቁ የነበሩ ህዝቦች መከበራቸው የማያስደስተው ህሊናውን የሸጠ ብቻ ነው:: የሚሰራ ይሳሳታል በትግል ወቅት የሳቱ በሁሉም ሃገሮች ይገኛሉ:: በሃገራችን በሳል የታሪክ ጸሃፊዎች ፕ/ር ባህሩ ዘውዴ ከነገስታቱ ቤተሰቦችና የደርጉ ፍስሃ ደስታ ጭምር የሰጡትን ምስክር ይህ ጸሃፊና እዚህ የሚያውድሱት ብዚያ ትውልድ ስም የተጻፉትን የሁለቱን እንስቶች የታደለችና የሌሎቹ የጄነራል ተፈሪ ባንቲ ልጅ እጮኛ የጻፉትን ዋቢ ጠቅሳለሁ:: የዚያ ትውልድ ክቡር ስራ የገባር ህዝቦች ግፍ በዶ/ር ሃዲስ አለማየሁ በፍቅር በወንጀለኛው ዳኛ የዘዘከረላቸው ህዝቦች ግድ የሚለው ሁሉ ይዘክረዋል ከሃምሳኛው ወደሰቧአምስተኛው መቶኛው በክብር ይቀጥላል::

 6. አዎ! ቀደም ሲል የሰነዘርኩትን እደግመዋለሁ! አንድን ጉዳይ ከተከሰተበት (ከተፈፀመበት) ጊዜ እና አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተጨባጭ ሁኔታ (the very objective reality) አንፃር መርምሮና ተገንዝቦ እና እጅግ ስሜታዊ ከሆነ የጭፍን ጥላቻና ውግዘት ራስን ተቆጣጥሮ ገንቢ ለሆነ የትውልድ ቅብብሎሽ በሚጠቅም አቀራረብ የሰላ ሂስ ማሄስ የትክክለኛ ምሁራዊ ባህሪና ሚና ነው።
  ዶ/ር ላሬቦን በአካል ባላቃቸውም በፅሁፎቻቸውና አልፎ አልፎ በሚሰጧቸው ቃለ ምልልሶች አውቃቸዋለሁና በአጠቃላይ ምሁርነታቸው ላይ ጥያቄ ማንሳት አልፈልግም። ትክክልም አይደለም።
  ይህ ማለት ግን “እገሌ/ሊት እኮ ዶ/ር ወይም ፕሮፌሰር ወይም ባለሥልጣን ወይም የቲዎሎጅ ሊቅ ወይም ጳጳስ ወይም ፓስተር ወይም ሸህ ፣ ወዘተ ነውና/ናትና እርሱን/እርሷን መተቸት ነውር ወይም ብልግና ነው” ወደሚል እጅግ ስሜት የማይሰጥ መከራከሪያ ሊወስደን አይገባም ። በዚህ ፈፅሞ አልስማማም!
  እንዲያውም እኮ አገራችንን የሁለንተናዊ እና የተደጋጋሚ ውድቀት ሰለባ ካደረጓትና እያደረጓት ካሉ ዋነኛ ምክንያቶች አንዱ ይህ “የአይነኬነት” ክፉ ባህልና ባህሪ ነው። ለዚህ ደግሞ ከጥንት እስካ ዛሬ ዋነኛ ሰለባ ምሁር ነኝ የሚለው የህብረተሰብ ክፍል ነው። አዎ! የአገራችን እጅግ ትልቁ ፈተና እኮ ዓለማዊውንም ሆነ መንፈሳዊውን ትውልዳዊ ድክመት በገንቢነትና በሚዛናዊነት መርምሮ ፣ ጎጅውን ከጠቃሚው ለይቶ ፣ የሚጠቅመውን ለግብአትነት በመውሰድ እና የሚጎዳውን ደግሞ እንዳይደገም በማድረግ ረገድ ወደ ፊት መራመድ የሚያስችል መንገድ የሚሳይ መጥፋቱ ነው።
  “ዶክተር ላሬቦን ለማወቅ የትምህርታቸውን የጀርባና የአሁን ምንነት ማወቅ ነው” የሚለው አስተያየት ትክክል ነው ። ይህ ማለት ግን “ዶክተሩ እንከን አልባ ናቸውና እርሳቸውን መተቸት አቅምን አለማወቅ ወይም አጉል መዳፈር ነው” ለማለት ከሆነ ወይ በራሱ የለየለት ድንቁርና ነው ወይንም ደግሞ ጨርሶ ስሜት አይሰጥም።
  እየተነጋገርን ያለነው ዶክተሩ በኢህአፓ ላይ በሰነዘሩት ወቅትንና ሁኔታን ከግምት ውስጥ ያላስገባና በእጅጉ ደምሳሳና በአንድ አይነት ጭፍን ምሬት የሚንተከተክ አቀራረብ ለዚህ በከፍተኛ ፈተና ላይ ለሚገኝ ትውልድ አስተማሪነቱ እምብዛም አይደለም በሚለው ሃሳብ ላይ ነው እንጅ ለምን ኢህአፓን ተቹ በሚል አይደለም። እደግመዋለሁ ፤ ስለ ዶክተሩ የትምህርት ጀርባና አሁንነት አይደለም በፍፁም አይደለም እየተነጋገርን ያለነው።
  የዚህ አስተያየቴ ዓላማ ዶክትሩን ዝቅ አርጎ የማየት ጉዳይ ሳይሆን በዚህ ፅሁፋቸው ውስጥ የታጨቀው እጅግ ደምሳሳና በአንዳች አይነት (ራሳቸው በሚያውቁት ምክንያት) የስሜት ትኩሳት የሚንተከተክ የጅምላ ፍረጃና ውግዘት ሀ) ለራሳቸውም አይጠቅምም ለ) እውነተኛና ትውልድን በቅጡ የማስተማር እሴትነትም አይኖረውም ሐ) ለእውነተኛና ሚዛናዊ የታሪክ ግምገማና አረዳድም ብዙ አይጠቅምም መ) የሰከነ ፣ ሚዛናዊ የሆነና ገንቢነት ያለው ትውልዳዊ መማማርንም አያበረታታም ። እንዲያውም አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ የሚገኝ ውልድ ያለፈውን በማውገዝ (blaming the past) ራሱንእየደለለ የሸፈጠኛ ገዥዎች የመከራ ቀንበር ተሸካሚ ሆኖ እንዲቀጥል ነው የሚያደርገው ።
  በአጠቃላይ ያለፈውን በቅጡና በገንቢነት መርምሮ የእና ብዙ ፋይዳ ያለው የፖለቲካ ሥራ ሳይሠሩ እድሜ የሚቆጥሩ የአሁኖችን ኢህአፓ ነን ባዮች ገንቢ በሆነ ሂስ መተቸት ትክክል ቢሆንም እጅግ በጣም ደምሳሳ (ጅምላ) የሆነና በግልብ ስሜት የታጨቀ ፍረጃና ውግዘት ግን የትክክለኛ ምሁራዊ ትርጉምና እሴትነት ይጎድለዋል ። ይህ ደግሞ ለራሳቸው ለዶክተሩም የሚመጥን አይመስለኝም።
  በተረፈ ግን በየትኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን ሃሳብና አቋም ላይ አስተያየት ለመስጠት የግድ ሊቅ መሆንን አይጠይቅምና “ደግሞ አንተ እሚሉ ዶክተሩን ተች” የሚል አይነት ትችት ወይ የለየለት ድንቁርና ነው ወይንም ደግሞ እያወቁ መደንቆር ነውና አይጠቅምም!

  • TG ርንድን ነገር ኩተከሰተበትና አገራዊ ሁኔታ ይላል ትችት ያ ማለት በጊዜ ተገድበው ያልሆነ ትንታኔና መፍትሄ መስጠታቸውን መስክረህባቸዋል። የምሁር፣የመሪ፣የፕላንና ፕሮግራም መለኪያው ዘመን ተሻግሮ ትክክል ብይን አስረግጦ የሚኖር እንጅ ያበደውን አለም ተከትሎ የሚያብድ መሆን አልነበረበትም። ወዳኽህ ሞረቴው ስለ መሬት ላራሹ ጥያቄና ስኬት አንስቷል በጣም ያስቃል በውቀቱ የኢትዮጵያ ህዝብ 23 ሚሊዮን ነበር ኢትዮጵያውያንን ከመግደል የተሻለ ፕሮግራም መንደፍ አያስፈልግም ነበር? ያንን እነ ዶክተር ምናሴ ለማ አድርገውት ነበር ኢትዮጵያን ያቆሙ ማለቅ ስላለባቸው ውጤቱ ዛሬ ያየነውን ሁናል። ይመችህ አቦ ምን አገባኝ

 7. አቶ ሃይሌ ላሬቦ አብደሃል? ከነጨራሹ ጨረቅህን የጣልክ ትመስላለህ። ለምን ትዋሻለህ? ለምን በማታዉቀዉ ገብተህ ትፈተፍታለህ? በዚያ ጊዜ አንተ ከሚሲዮኖች ፍርፋሪ ከመልወቀም ሌላ ስለተማሪዉ እንቅስቃሴ ምን ታቃለህ? በህይወትህ ለዲሞክራሲ ትግል ምን ያደረግከዉ አስተዋጽኦ አለህ? አዎሮፓ መጥተህ ይህንንም ያንንም እየኮረጅክ ድግሪ ያዝኩ አልክ። አሜሪካ እኮ እናቃለን። 7ና 10 ተማሪ ሰብስባችሁ አዳራሽና ዛፍ ስር አስተማርን እያላችሁ ፕሮፌሰር ሆንን ትላላችሁ። ወይ ፕሮፌሰር? ተራ ሴርቲፊኬት የያዘ ሰዉ እንዳንተ አይቀደድም። ዕድሜ ልክህን መሃኢም ሆነህ ትኖራለህ። ሰማይታት ጀግኖችን ለቀቅ አድርጋቸዉ። እግዚአብሔርን ካወቅክ እርሱ ይፍረድብህ፡ ግን አታዉቀዉም። መሃይምና ወንጀለኛ ፕሮፌሰር።

 8. ሃይሌ ላሬቦ አብደሃል? ከነጨራሹ ጨረቅህን የጣልክ ትመስላለህ። ለምን ትዋሻለህ? ለምን በማታዉቀዉ ገብተህ ትፈተፍታለህ? በዚያ ጊዜ አንተ ከሚሲዮኖች ፍርፋሪ ከመልወቀም ሌላ ስለተማሪዉ እንቅስቃሴ ምን ታቃለህ? በህይወትህ ለዲሞክራሲ ትግል ምን ያደረግከዉ አስተዋጽኦ አለህ? አዎሮፓ መጥተህ ይህንንም ያንንም እየኮረጅክ ድግሪ ያዝኩ አልክ። አሜሪካ እኮ እናቃለን። 7ና 10 ተማሪ ሰብስባችሁ አዳራሽና ዛፍ ስር አስተማርን እያላችሁ ፕሮፌሰር ሆንን ትላላችሁ። ወይ ፕሮፌሰር? ተራ ሴርቲፊኬት የያዘ ሰዉ እንዳንተ አይቀደድም። ዕድሜ ልክህን መሃኢም ሆነህ ትኖራለህ። ሰማይታት ጀግኖችን ለቀቅ አድርጋቸዉ። እግዚአብሔርን ካወቅክ እርሱ ይፍረድብህ፡ ግን አታዉቀዉም። መሃይምና ወንጀለኛ ፕሮፌሰር።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

290684552 3309915649279615 7045677791337159006 n
Previous Story

ጊምቢ ኤሎሄ ጊምቢ ቶሌ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

291479160 623167242707868 8396677107010763832 n
Next Story

ጠ/ሚ/ሩ በፓርላማ “በቀጣይ የሚያሰጋን አዲስ አበባ ነው” በማለት የወለጋን አጄንዳ ለማስቀየር ሞከሩ!!

Go toTop