July 6, 2022
2 mins read

ጊምቢ ኤሎሄ ጊምቢ ቶሌ (ከአሁንገና ዓለማየሁ)

290684552 3309915649279615 7045677791337159006 n
ጊምቢ ኤሎሄ ጊምቢ ቶሌ
ትእዛዝ ወርዶ ከእገሌ
ከሥልጣኑ ሉያ ሃሌ
ለማይካድራ ጅኒ ቆሌ
መስዋእት ሊቀርብ
በንጹሕ ደም መቅጃ አኮሌ
ዱበርቶኒ ፊ ኢጆሌ**
ተጨፍጭፈው
በወለጋ ጊምቢ ፎሌ
ካንዲት ጎጆ አሥር ሞቶ
ለኦነግ ዛር ተሠውቶ
መሬት ጭረው እህል ዘርተው
የሚኖሩ ከብት አርብተው
የማይጽፉ ማያነቡ
ጥያቂያቸው
ወጥተው ወርደው ቤት ሲገቡ
ሰላም ዋለ ቤተሰቡ?
መጣ ቀረ ወይ ዝናቡ?
ብቻ ሆኖ
አራት ኪሎ የሚያውቃቸው
አራት ኪሎን የማያውቁ
እንደ ዶሮ ተከታትፈው
እንደ አውሬ እየታነቁ
እንዲያ ሲያልቁ
ያስተዳድር የተባለው
የመመከት ሥልጣን ያለው
በከፈሉት ግብር ሰብቶ
ባመረቱት ቀለብ ገዝፎ
ካገር ጠላት ዲናር ልፎ
ይሁዳኛ እየሳመ
ሲሰጣቸው አሳልፎ
ጊምቢ ሆና ጎልጎታቸው
ቤትልሄምም ራሷ ጊምቢ
መንደራቸው ድንገት ሆኖ
የቀያፋው ትልቅ ግቢ
አርብ ማልዳ ደርሶባቸው
የኛ ያሉት ወገናቸው
ጴጥሮስኛ ሲክዳቸው
በጥላቻ ጅራፍ ገርፎ
የሮም አሽከር ሲይዛቸው
በክላሽ ጥይት ተቸንክረው
ገና ሳትወጣ ነፍሳቸው
እጣ ወጥቶ በልብሳቸው
ንብረታቸው ሲከፋፈል
ለወራሪ / ጃርት ፍልፈል
አስገርፎ አሰቅሎ
ጲላጦስ እጁን ቢታጠብ
የሌለበት አስመስሎ
የፈሰሰው ደም የወሎ
ያለበደሉ ተገድሎ
በወለጋ ጸሐይ ተንኖ
ሰማይ ጠቅሶ እንደ አውሎ
ገና ይወቅ/ሳል ዘላለም
ገና ይጮ/ኻል ለሁሌ
ጊምቢ ኤሎሄ! ጊምቢ ቶሌ!

* አኮሌ = ማለቢያ ቅል፣ ጮጮ፣ የፈሳሽ ማስቀመጫ
** ዱበርቶኒ ፊ ኢጆሌ = ሴቶችና ልጆች

መታሰቢያነቱ በሰኔ ወር 2022 ዓ.ም. በወለጋ በአማራነታቸው ተለይተው በመንግሥት መራሽ ጭፍጨፋ በጭካኔ ለተፈጁት ሰላማውያን እና ንጹሐን ኢትዮጵያውያን ይሁን።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop