ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ እስካሁን ያለበት አለመታወቁ እንዳሳሰባቸው ቤተሰቦቹ ገለፁ

ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ እስካሁን ያለበት አለመታወቁ እንዳሳሰባቸው የገጣሚው ቤተሰቦች ገለፁ።

 

ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ባሳለፍነው ማክሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2014 ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ፈረንሳይ ለጋሲዮን ከሚገኘው ጊዮርጊስ ምግብ ቤት ” ትፈለጋለህ?!” ተብሎ እንደተወሰደ እህቱ ሰላም በቀለ ወያ ተናግራለች።

ማክሰኞ ዕለት ሰሌዳ በሌላቸው ተሸከርካሪዎች ውስጥ በነበሩና ሲቪል በለበሱ የፀጥታ አካላት ታፍኖ መወሰዱ እንደነገሯት ያስረዳችው ሰላም፤”በፌዴራል እና በየአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቢሮ እንዲሁም በየካ ክ/ከተማ ውስጥ በሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎች ብንጠይቅም አድራሻው ሊገኝ አልቻለም“ ስትልም በማህበራዊ ሚዲያ ባስተላለፈችው የቪዲዮ መልዕክት ተናግራለች።

እህቱ አክላም “ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ወደ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን መሄጃ ባለ ፖሊስ ጣቢያ በዕለት መዝገብ አስመዝግበናል” ብላለች።

እናት እና አባቱ በድንጋጤ መታመማቸውን የገለፀችው ሰላም፤ እናቱ ጽጌ ገ/እግዚአብሔርም “ልጄ የት ነው ያለው?” ሲሉ አገር እና ሕዝብን መጠየቃቸውን ተናግራለች።

በመጨረሻም የወንድሟን ድምፅ ከሰማች ሦስት ቀናት እንዳለፉትና ያለበት አለመታወቁ መላው ቤተሰቡን ለከፍተኛ ጭንቀት እና ድንጋጤ መዳረጉን በመግለፅ፤ ጥፋተኛም ከሆነ በህግ አግባብ እንዲጠየቅና እንዲቀጣ ጠይቃለች።

– ምንሊክ ሳልሳዊ


Belay Bekele Weya
እርር ድብን አርጎ ፣ አንጀቴን ሚያቆስለኝ
መርጦ እየገደለ ፥ “መርጦ አልቃሽ” የሚለኝ!!!


ለግፍ ጥያቄ ፣ “በቃ!” ነው መልሱ
መፍትሔ አይኖርም ፣ እያለቀሱ !
——————————————————————
በጀግኖች ሀገር ላይ ፣ ለፈሪ ቀን ወጥቶ
“ጀግና ነኝ” ይለናል ፣ ንፁሃንን ፈጅቶ !!!
————————————————————
ሀቻምና በኦነግ ፣ አምና በወያኔ
ዘንድሮ በሸኔ
ሰበብ እያረጉ ፣ ያርዱኛል አቅደው
እኔን ካልገደለ
ሚኖር አይመስለውም ፣ የመጣ የሔደው።
።።
የመጣ የሔደው
ህመምህን ሳይሽር ፣ ቁስልህን ሳያክም
ሬሳህ ላይ ቆሞ
ማን እንደገደለህ ፣ ሊያስረዳህ ሲደክም
እንዳልቀረ አውቀህ ፣ ይቀራል ያልከው ግፍ
ወይ ለመኖር ታገል ፣ ወይ ሞትህን ደግፍ!!!
—————————————————————
በየቦታዉ ታርደህ ፣ ደምህ የትም ፈሷል
ጅምላ መቀበሪያ ፣ ጉድጓድህ ተምሷል
በየ ደረስክበት ፣ ሞትህ ተደግሷል
ይህንን እያወክ
ቀን በቀን ማላዘን ፣ ምን ይጠቅማል ለቅሶ?!
ትመር እንደሆነ ፣ ምረር እንደ ኮሶ!
——————————————————————
እያመመው መጣ “እያመመው መጣ
እያመመው መጣ ” እያመመው መጣ
ደሜ ባይገደብ ፣ ግፉ ባያባራ
ሁለት ስም አለኝ ፣ በሀገሬ ስጠራ
ስኖር “ኢትዮጵያዊ” ፣ ሲገድሉኝ “አማራ!”
———————————————————-
ዝናብ ባይኖር እንኳን
ቆስጣና ሰላጣ ፣ ችግኙን ትከሉ
አይቀርም በኔ ደም ፣ በኔ እምባ መብቀሉ !
—————————————————————
“መግደል መሸነፍ ነው” ፥ ብለው የነገሩን
በጅምላ በጅምላ ፣ አርገው ከሚቀብሩን
ምነው ማሸነፍን ፣ ሞተው ቢያስተምሩን?
———————————————————–
ልጄ…
ዝናብ ባይሰጥ እንኳን ፣ ሰማይ ተቆጥቶ
ችግኝ ለመትከል ፣ ተስፋ አትቁረጥ ከቶ።
አይቀርም ማደጉ ፣ የሰው ደም ጠጥቶ !
——————————-
ይነጋል ባልነው ቀን ፣ ጨለማው ገነነ
“አሻጋሪ” ያልነው ፥ አሸባሪ ሆነ !
=——————————————————-
አራት ዓመት ሙሉ
በወለጋ በኩል ፣ ጅምላ ስንቀበር
ለምን መንግስታችን
ዘመቻ አልጀመረም ፣ ህግ ለማስከበር?!????
እንጃ!
————————————————————-
ተጨማሪ ያንብቡ:  "የአዲስ አበባን የወደፊት እጣ የሚወስነው ሕዝቡ ነው" | ቃለምልልስ የኦነግ ከፍተኛ አመራር አቶ ኦዳ ጣሴ ጋር

1 Comment

  1. Dictator abiy amed,

    FREE BELAY BEKELE WOYA!!!!!
    Bekele is a hero whose thinking and life style transcends the rampant disease in contemprary Ethiopia-ETHNICISM.

    STOP AMHARA GENOCIDE IN ETHIOPIA!!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share