July 1, 2022
25 mins read

በበርካታ ሱዳናውያን እየተተፋ ያለው ሌ/ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃንና በአል-ቡርሃን እየተነዳች ያለችው ሱዳን አሁናዊ ገጽታ – ጌታቸው ወልዩ (ከሜክሲኮ ባህረ-ሰላጤ)

290213355 576709827390478 7033014726745911103 nውድ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ-ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንደ ምን ሰነበታችሁ? በዛሬው ጽሑፌ የሱዳን ሉዓላዊ /ወታደራዊ ሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር አዛዥ የሆነው ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን በበርካታ ሱዳናውያን ምን ያህል እንደተጠላ፤ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እየተጠጋ ምን ያህል እንደሚፎክርና በአምባገነናዊ አገዛዙ ሥር ያለችው ሱዳን አሁናዊ ገጽታ ምን እንደሚመስል በአጭሩ አስቃኛችኋለሁና ለደቂቃዎች አብራችሁኝ ትቆዩ ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ።

ውድ ወገኖቼ፦ የሱዳን ሠራዊት ከጥቅምት 2013 ዓመተ-ምህረት አንስቶ፤ ቀላል፣ መካከለኛና ከባድ መሣሪያዎችን ታጥቆና ተደራጅቶ፤ በብረት ለበስ የቅኝትና የአሰሳ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ተቀናጅቶ፤ በግብጽ የጦርና መረጃ ኀይሎች የሳተላይት፣ የዘመቻ፣ ሎጂስቲክና ሌሎች ወታደራዊ ድጋፍ ተጎላብቶ፤ ታሪካዊ አጋጣሚዎችን እንደ ጥሩ መረማመጃ በመቁጠር፤ ጦርነት የማወጅ ያህል በሚቆጠር ሁኔታ በዓለም አቀፍ ሕግ ሊጣስ የማይገባውን የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛትን አልፎ (ጥሶ) በሰሜን ጎንደር በኩል እንዲገባ ትዕዛዝ ሰጭና አቅጣጫ አስቀማጭ ቀንደኛ የሱዳን ጄነራሎች መካከል፦ በግብጽ ትሮይ ፈረስነቱ የሚታወቀው ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃንን ግንባር ቀደሙ ነው።

የሱዳን ሠራዊት በሁለቱ አገራት ማለትም በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር አካባቢ ድልድይ እንዲገነባና ወታደራዊ ጦር ሰፈር እንዲመሠርት ትዕዛዝ በመስጠት፤ በርካታ ቁጥር ያላው የሱዳን ጦር ሆን ብሎ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲጠጋና የጸብ አጫሪነት ድርጊት እንዲፈጽም ዋነኛ ትዕዛዝ ሰጪውና በድርጊቶቹ ሁሉ ቀዳሚው ተጠያቂም ይኸው የሱዳን ሉዓላዊ /ወታደራዊ ሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር አዛዥነት ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣንን ጠቅልሎ የያዘው ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን ነው።

ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን:- ራሱ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ድንበር ላይ እየተገኘ የሱዳንን ሰንደቅ በመኪና ላይ በማውለብለብ፣ ቀኝ እጁን ከፍ አድርጎ መፈክር በማሰማትና ሠራዊቱን ለጸብ ጫሪነት በድንፋታ ስሜት በመቀስቀስ በእብሪተኝነቱ የሚታወቅ፤ የራሱንና ጋሻ ጃግሬዎቹን ሥልጣን ለማስጠበቅ የማይፈጽማቸውን ተግባራት በመናገሩ በበርካታ ሰላም ወዳድ ሱዳናውያን የሚናቅ፤ ከነቅጽል ስሙም “ጉረኛው ጄነራል” (boastful/braggart general) እየተባለ የሚጠራ፤ ለግብጽ ታይታ የሚፈራገጥ ሕዝብ እየተፋው ያለ በባዶ የሚንጠራራ ጄነራል ነው።

ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃንን ኢትዮጵያን ለማስፈራራት ከግብጽ መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሆን በሱዳን ግዛት ተደጋጋሚ ወታደራዊ ልምምድ እንዲካሄድ መመሪያ በመስጠቱ የሚኩራራና የሚያቅራራ፤ በግብጽ ያገኘውን ወታደራዊ ሥልጠና “በአገሬ ሱዳን በተግባራዊ ልምምድ አሳያለሁ!” በማለት በሥልጣን ተራራ ላይ ወጥቶ በጉራ የሚንጠራራ፤ የፖለቲካዊ ሕይወት ልምሻ ያጠቃው፤ ነገን ማየት የተሳነው፤ ጄነራል ነው።

-ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን፦ የሱዳን ወራሪ ሠራዊት በተለያዩ ጊዜያት ድንበር ላይ የነበሩ አያሌ ኢትዮጵያውያንን በተለይም በአካባቢው ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የምትልካቸውን ሰሊጥና ጥጥ የሚያመርቱ አርሶአደሮችን በወረራ በማፈናቀል፤ ወራሪው ሠራዊት ማጨጃ ማሽን ይዞ በመምጣት ሰሊጥን ጨምሮ የተለያዩ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች የግብርና ምርቶችን አጭዶ እንዲወስድ በማንአለብኝነት ትዕዛዝ በመስጠትም ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዝ ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም እያራመደ ያለ ጄነራል ለመሆኑ ግብሮቹ ምስክሮች ናቸው።

እንዲሁም ኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ ያሉ ነዋሪ ኢትዮጵያውያንና አርሶአደሮች ካምፖቻቸው በመወረራቸው፤ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ ካምፖቻቸውን በማውደም፤ ንብረቶቻቸውን በመዝረፍ፤ አርሶ አደሮች የራሳቸውን እርሻ እንዳያጭዱ እንቅፋት በመሆን ለተሄደው ርቀት ሁሉ ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን ተጠያቂ ነው። ለአብነት ያህል ቀደም ሲል ከጥቅምት 2013 ዓመተ-ምህረት ጀምሮ በሱዳን ሠራዊት ወረራ የተነሳ ድንበር ላይ ያርሱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን መካከል የተወሰኑት ሙትና ቁስለኛ እስከ መሆን መድረሳቸውን መጥቀስ ይቻላልና።

መታወቅ ያለበት በነጃፋር መሐመድ ኤል-ኒሜሪም ሆነ በየደረጃው በነበሩ የሱዳን ፈላጭ ቆራጭ መሪዎች የአገዛዝ ዘመን እንደተፈጸመው ሁሉ፤ ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ለሚፈልጉ ኀይሎች መጠለያ (ከለላ)ና መተላለፊያ በማዘጋጀት፣ ሥልጠና፣ ሌሎች የሎጅስቲክና ጦር መሣሪያዎች ድጋፍ እንዲያገኙ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድም፤ የሱዳን ሉዓላዊ /ወታደራዊ ሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር አዛዥ የሆነው ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን ስሙ በቀዳሚነት የሚጠቀስ እኩይ ጄነራል ነው።

በተለይም በኢትዮጵያ ታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታና ውሃ መሙላት ሂደት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ የሚያካሂዱትን ውይይትና አለመግባባት ሽፋን በማድረግ፤ በአገር ውስጥ የተነሳበትን ከባድ ተቃውሞና ችግሩ የተባባሰውን ቀውስ በከፊል ለማስተንፈስና ጥቂት ጊዜ ለመግዛት በማሰብ፤ የድንበር ጥያቄና ውዝግብ በማስነሳት፤ ቀጣናውን ለውጥረት ዳርጎ፤ የኢትዮጵያን ውስጣዊ አለመረጋጋት እንዲባባስ የሀሰትና የፈጠራ መረጃዎች በሱዳን ሚዲያዎች እንዲተላለፉና በኢትዮጵያ ላይ ዓለም አቀፋዊ ጫና እንዲጨምር ከግብጽ ጋር ተባብሮ በመሥራትም ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን የአንበሳውን ድርሻ እንደሚይዝ ፀሓይ የሞቀው እውነታ ነው።

እንደሚታወቀው ከሰኔ 15 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት ጀምሮ ደግሞ “በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ ሰባት ወታደሮችና አንድ ሰላማዊ ሰው በኢትዮጵያ ኃይሎች ተገድለውብኛል!” ስትል ሱዳን ውንጀላ ካቀረበች በኋላ፤ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ እርምጃዎች እንዲወሰዱ እና የሱዳን አዋሳኝ በሆኑ የኢትዮጵያ ድንበር አካባቢዎች መድፍን ጨምሮ በተለያዩ ከባድ መሣሪያዎች እንዲደበደቡ በማድረጉ ሂደት እንደ ሱዳን ጦር የበላይ ኀላፊነቱ ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን ትዕዛዝ ለመስጠቱ ምንም ጥርጥር አያሻውም።

በከባድ መሣሪያዎቹ ጥቃትም በግብርና ካምፖች ላይ ጉዳት ማድረስን ጨምሮ በሥፍራው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ነዋሪዎች እንደ ተለመደው በእርሻ ሥፍራዎች መደበኛ የእርሻ ተግባራት እንዳያከናውኑ መደረጋቸውን በማስመልከት የምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አንድ የሥራ ኀላፊን ዋቢ በማድረግ በርካታ የመገናኛ ብዙሐን በተለያዩ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች እየተገለጸ እንደሚገኝ ይታወቃል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓመተ-ምህረት (ጁን 27 ቀን 2022) ባወጣው መግለጫ፤ ተገድለዋል የተባሉት የሱዳን ወታደሮች በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በሱዳን ውስጥ የተያዙ ወታደሮች መሆናቸውን የገለጸ ሲሆን፤ የሱዳን ጦር አዛዥ የሆነው ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃንም ከኢትዮጵያ ጋር በቅርበት ወደሚዋሰነው ወደ ምሥራቅ ሱዳን አል-ገዳሪፍ ግዛት አምርቶ፤ ኢትዮጵያና ሱዳን በሚወዛገቡበት የአል-ፋሻጋ ሦስትዮሽ ማዕዘን ድንበር ተጠግቶ፤ ወታደሮቹን ለጸብ አጫሪነት መቀስቀሱን ራሱ የሱዳን ዜና አገልግሎት የቪዲዮ ማስረጃ መጥቀስ ይቻላል።

በቅስቀሳውም በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ላይ ሞቱ የተባሉትን ወታደሮች አስመልክቶ “ወንድሞቻችሁ ተሰውተዋል። እኛ ከእናንተ ጎን እንቆማለን! እንረዳችኋለን! ኀላፊነት አለብን! በማናቸውም መንገድ መብታችንን እናስከብራለን! መሬታችንን ሊነካ የሚመጣ ላይ እርምጃ እንወስዳለን!” በማለት “ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል!” እንዲሉ በከንቱ እስከ መፎከር ደርሷል።

ሊታወቅ የሚገባው ጉዳይ ግን እነሆ በነጄኔራል አል-ቡርሃን አምባገነናዊ አስተዳደር ሥር የምትማቅቀው -ሱዳን፦ ብዙ ሚሊየን ሱዳናውያን ለአገራቸው ሰላምና መረጋጋት መምጣት፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፈጠርና ፍትኅ መረጋገጥ ነግቶ በጠባ ሰላማዊ ሰልፍ የሚያጥለቀልቋት፤ ከአራቱም አቅጣጫ ረብሻና አመጽ እንደ ቅቤ የሚንጧት፤ ነግቶ በጠባ የብሔር ግጭት የጎን ውጋትና ጋንግሪን የሆነባት፤ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና ፍትህ ማጣት ያየለባት፤ ሰላምና መረጋጋት የታጣባት አገር ከሆነች ከራርማለች።

አዎ! በግብጽ ትሮይ ፈረስነቱ የሚታወቀው ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃንን እንደ እንዝርት የምትሽከረከረው ሱዳን፦ እጅግ በርካታ ዜጎች በጸጥታ ኀይሎች በአደባባይ የሚዋከቡባት፣ የሚደበደቡባትና የሚታፈኑባት፤ በግጭት ብዛት ብዙዎች ለእስር፣ ሙትና ቁስለኝነት የሚዳረጉባት፤ የዜጎቿ ፈተና በዝቶ ብሶታቸውና መከራቸው እንደ አሸን ፈልቶ፤ ቀዬያቸውንና አገራቸውን ጥለው የሚሸሹባትና ከአገር አገር የሚንከራተቱባት የስቃይና የድህነት አገር ከሆነችም ሰነባብታለች።

የሱዳን ሉዓላዊ /ወታደራዊ ሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር አዛዥነት ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣንን በማን አለብኝነት በተቆናጠጠው ሌተና ጄነራል አብድል ፈታህ አብድራህማን አል-ቡርሃንና ቢጤዎቹ ደካማ አመራር መከራዋን እየበላች ያለችው ሱዳን፦ የዳቦና ነዳጅ እጥረት እጅጉን የሰፋባት፤ የሸቀጦች ዋጋ ንረትና ግሽበት ከጣራ በላይ የሆነባት፤ ጉቦ፣ ሙስና (ንቅዘት)ና የሌቦች አገዛዝ የተንሠራፋባት፤ መልካም አስተዳደርና ፍትኀዊ አሠራር የራቃት፤ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥሰታ መንገዱ የጠፋባት፤ የተወሳሰበ ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ውስጥ ገብታ ግራ በገባው ፖለቲካዊ ሽኩቻ እንደ በርበሬ የምትታመስ አገር ከሆነችም አመታትን አንድ፣ ሁለትና ሦስት ብላ ቆጥራለች።

ሲቪል አስተዳደርን ማየት የማይሻው አል-ቡርሃን የሚሾፍራት ሱዳን፦ ከግብጽ ጋር ለአመታት እየተወዛገበችባቸው ያሉትን የ”ሀላዪብ ሦስት ማዕዘን” እና “ቢር ጣዊል” አካባቢዎች (Halayib Triangle and Bir Tawil) ጉዳይ መፍትሄ እንዲያገኝ በድፍረትና ቆራጥነት፤ በአገራዊና ሕዝባዊ ስሜት፤ የሚከራከሩ መሪዎች የናፈቋት፤ የኮርዶፋንና ዳርፉር ጥልፍልፍ ችግሮች እንቅልፍ ነስተው የእግር እሳት የሆኑባት፤ በመፈንቅለ-መንግሥት የሚገለባበጡ አምባገነን ጄነራሎች እንደ አበደች ኳስ የሚያጎኗትና የሚያጦዟት ሳታጣ ያጣች አገር መዝገብ ውስጥ የገባች አገር ከሆነች በርካታ ፈሪ አመታት አስቆጥራለች።

የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ሌተና ጄነራል ዑመር ሀሰን አልበሽር ከሥልጣን መንበራቸው ተመንግለው ወደ ዘብጥያ ከተወረወሩ በኋላ ወደ ሥልጣን የመጡት እነ ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን በተሳሳተ ኮምፓስ የሚነዷት ሱዳን፦ ከጥሩ ጎረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር ያለባትን የድንበር ውዝግብ በሰላማዊና መግባባት መንገዶች ለመፍታት የሚደራደሩ፤ ለሕልውናዋና ብሔራዊ ጥቅሟ የሚበጃትን የኢትዮጵያ ታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታን በእውቀትና ማስተዋል፤ በወዳጃዊነትና ቀና አመለካከት ተመልክተው የጋራ መግባባትንና ተጠቃሚነትን የሚዘምሩ፤ መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ምሁራንና ተመራማሪዎችን አጥታ በውሽልሽል ጎዳና የቁልቁሊት መንደርደሯን ከገፋችበትም ከራርማለች።

በዚህ የተነሳም ሱዳን፦ “መካሪ አጥታ፤ ዘወትር እንደ ቀለብ በያዘችው ወላዋይነትና ተንሸራታችነት አቋሟ ወደ ተሳሳተ ጫፍ ተገፍታ፤ በኢትዮጵያን ጠሏ ግብጽ መሪዎች በእኩይ መንገድ ተነድታ፤ በግብጽ ትሮይ ፈረስነቷ በከንቱ እየተጋለበች ወዴት እንደምትሄድ ግራ ተጋብታ፤ እንደ ገበቴ ውሃ በከንቱ እየዋለለች፤ የዐረቡ ዓለምና የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት መሆን ሲቻላት የስንዴ እርጥባንና በሴፍቲኔት ለዜጎቿ አንድ ዶላር ለማደል የረድኤት ድርጅቶችን ደጅ የጠናች አገር ሆናለች!” እያሉ በአፍሪካ ቀንድ፣ በሰሜን ምሥራቅና ምሥራቅ አፍሪካ ዙሪያ የተጠበቡ በሳል የጂኦ-ፖለቲካና ምጣኔ ሀብት ተንታኞችን ጨምሮ የወታደራዊ፣ መረጃና ደኅንነት ሹማምንት እና የቀጣናው ልኂቅ ዲፕሎማቶች የሚተቿት አገር ሆናለች።

“በኢትዮጵያ ታላቁ ኅዳሴ ግድብ ግንባታና ውሃ መሙላት ዙሪያ አለመግባባት የፈጠሩት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በተለያዩ ጊዜያት ውይይት ሲያደርጉ እንደ ሱዳን ሉዓላዊ /ወታደራዊ ሽግግር መንግሥት ምክር ቤት ሊቀመንበርና የሱዳን ጦር አዛዥነት ኢትዮጵያ የታችኛው ተፋሰስ አገሮችን ተጠቃሚ ጭምር ለማድረግ በሄደችባቸው መልካም ጉዞዎች ሁሉ የሱዳን ሉዓላዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ተጨባጭ ሚና አላበረከተም!” ሲሉ አያሌ ሱዳናውያን የሚወነጅሉት ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን፤ “የግብጽ ተጎታች የሆነ፤ በማን አለብኝነት ልቡ በከንቱ የገነገነ- ጄነራል ነው” በማለት በየቀኑ የውግዘት ናዳ እየተወረወረበት ይገኛል።

እናም! በአሁኑ ወቅት ብዙዎች ሱዳናውያን “General Abdel Fattah Abdelrahman al-Burhan is a servile of Egypt!” ማለትም:-“ሌተና ጄነራል አብድል ፈታህ አብድራህማን አል-ቡርሃን የግብጽ አገልጋይ/ ባሪያ ነው!” እያሉ የመፈክር ያህል ስሙን ደጋግመው እየጠሩ፤ እኩይ ግብሩን በአደባባይ ቆመው እነተናገሩ፤ ሲያወግዙትና ሲወቅሱት መስማት እየተለመደ መጥቷል።

ከሁሉ ከሁሉ ደግሞ ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን:-ሰላማዊ የሆነች ዴሞክራሲያዊት ሱዳን እንድትፈጠር ሱዳናውያን ያላቸውን ከፍተኛ ተስፋ፣ ፍላጎትና ስሜት ጠልፎ የወሰደና የሕዝብን አደራ የበላ ከሃዲ ጄነራል ነው።” (Abdel Fattah al-Burhan hijacked and betrayed the aspirations of the Sudanese people for a peaceful, democratic country” ተብሎ በቁሙ የአገርና ሕዝብ አደራ በልና ከሃዲነት መስጠሎ ካባ የለበሰ፤ በየዕለቱ በምስኪን ሱዳናውያን የተወቀሰ፤ አምባገነን ጄነራል ነው። ጎበዝ! በቁማችሁ “የአገርና ሕዝብ አደራ የበላ!” ከሚል ወቀሳና እርግማን የኢትዮጵያ አምላክ ይጠብቃችሁ!

በመጨረሻም በሕዝባዊ አመጽ ወደ አደባባይ እየወጡ ያሉ ሱዳናውያን ሕዝባዊ ድጋፍ የሌለው መንግሥት ከባህር እንደ ወጣ ዓሳ መሆኑን በመናገር፤ የሚከተለውን አገርኛ ምሳሌያቸው ከፍ አድርገው እያቀነቀኑ ይገኛሉ። “A big chair does not make a king.” ትርጉሙም፦ “ትልቅ ወንበር ንጉሥ አያደርግም ወይም አያሰኝም!” ማለት ነው። ሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን ከገባው እውነታው ይሄ ነው።

በማጠቃለያዬ፦ የአሁኑ የኢትዮጵያ ድንበር ከተማ መተማን አልፎ እስከ ምዕራብ ጎጃም መሸንቲና መራዊ የዘለቀ ረዥም የንግድ መስመር ግንኙነት የነበራት፤ በታሪካዊና ጥንታዊ ንግድ ማዕከልነቷ የምትታወቀው የሌተና ጄነራል አብዱል-ፈታህ አል-ቡርሃን የትውልድ ከተማ “ጋንዴንቶ -ሸንዲ” እንደ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ኢዛና አይነት ኀያል መሪዎች፤ ሰጥ ለጥ አድርገው መሬቷን ጭምር አፍ እንዳስያዟት፤ አል-ቡርሃን ጠንቅቆ ያውቃልና ፉከራውንና ጸብ አጫሪነቱን ቢያቆም ይበጀዋል! የሚል መልእክቴን ማስተላለፍ እወዳለሁ። ሠናይ ዘመን ለሁላችሁም። አበቃሁ።

በመጨረሻም ቸሩ እግዚአብሔር አገራችንን ይጠበቅልን!

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ አምላክ አገረ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

(ጌታቸው ወልዩ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
Go toTop