የአማራ ክልል መንግስት ተማሪዎችን ሰልፍ ከለከለ «ተማሪዎች ሰልፎች እንዳያደረጉ ለምን ተከለከሉ?» – ዓለምነው መኮንን

በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞን በአማራ ክልል ተወላጆች ላይ ሰሞኑን የተፈፀመን አሰቃቂ ግድያ በተመለከተ የተለያዩ አካላት ሐዘናቸውን በተለያዩ መንገዶች ሲገልጡ ቆይተዋል። በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች፤ ባህር ዳር እና አዲስ አበባን መጥቀስ ይቻላል፤ የመንግስት የፀጥታ ኃይላት ሐዘናቸውን ለመግለጥ የወጡ ሰልፎችን ለመበተን ሙከራዎችን ሲያደርጉና በአንዳንድ ተማሪዎች ላይም ድብደባ መፈጸማቸውም ተዘግቧል።
ዛሬ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መግለጫ የሰጡት የአማራ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ «ተማሪዎች ሰልፎች እንዳያደረጉ ለምን ተከለከሉ?» በሚል ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፦ «ከሰልፍ ጋር ተያይዞ በሰልፍ ስሜትን መግለፅ ችግር ያለበት አይደለም፣ የተፈፀመው ችግር ሰልፍ ያስወጣል፣ ያስቆጣል፣ ስሜት ያስይዛል ግልፅ ነው፤ ነገር ግን አንዳንድ ኃይሎች ይህንኑ ዓላማ መጀመሪያ ዜጎቻችንን እንዲህ እየጨፈጨፉ የአማራ ሕዝብ ሰልፍ እንዲወጣ ይፈልጋሉ። ዜጎቻችን እየጨፈጨፉ የአማራ ሕዝብ ወደ አመፅ እንዲወጣ ይፈልጋሉ። አመፁን ተጠቅመው ሌላ ብጥብጥና ግርግር እንዲፈጠር ይፈልጋሉ፤ ይህ በመረጃ የተረጋገጠ ነው። ለዚህ እንዳንዳረግ መጠንቀቅ አለብን» ብለዋል። አክለውም፦ «አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ የታዩ ምልክቶች፣ መልዕክቶቹ ጤነኞች አይደሉም። መልዕክተኞች አሉ እዛ ውስጥ። አብዛኛው ሰው ስሜቱን ለመግለፅ ሊሆን ይችላል ግን በጣም ጥቂቶች ደግሞ ሰርገው የሚገቡ አሉ። ወደ ሰልፍ ከተገባ በኋላ ይህንን ስሜት መጠቀም ይፈለጋል። ስሜት ነው የሚመራህ ሰልፍ ላይ ደግሞ። ይህን መጠንቀቅ ያስፈልጋል» በማለት ሰልፎቹ የተከለከሉበትን ሁኔታ ለማብራራት ሞክረዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር ለመደራደር ተደራዳሪ አባላትን ይፋ ባደረገበት በዚህ ወቅት ሕወሓት ለአዲስ ዙር ጦርነት እየተዘጋጀሁ ነው ማለቱ እየተወራ ነው በሚለው ጥያቄ ዙሪያ አቶ ግዛቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ሕወሓት የጦርነት መግለጫ ሲያወጣ እንደኖረ፣ አሁንም ሊያወጣ ይችላል። የአማራ ክልል ግን ከምንጊዜውም በላይ ለሰላም ዋጋ ይሰጣል ብለዋል። አቶ ግዛቸው፣ አንድ ሆኖና ተጠናክሮ ራስን መከላከል መዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል። መንግስት ለክልሉ በሚሰጠው አቅጣጫና የክልል ተግባር የሆነውን እንሠራለን፣ ሕዝቡ የደጀንነት ተግባሩን ያጠናክር፣ አይዘናጋ ሲሉም አሳስበዋል። በክልሉ የተጀመረው ሕግ የማስከበር ተግባርም ውጤታማ በመሆኑ ወደ ኋላ ሳይመለስ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በተያያዘ ዜና፦ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የከሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ በትግሉ ተስፋሁን ማምሻውን ለዶይቼ ቬሌ እንዳስታወቁት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ምክር ቤት ካስተላለፋቸው ውሳኔዎች መካከል አንዱ የባለሦስት እግር ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴን የምሽት ስምሪት መግታት ነው።
በዚህም መሰረት ከተፈቀደላቸው ወጪ ማነኛውም በተለምዶ ባለሶስት እግር ተሸከርካሪዎች (ባጃጆች) ከዛሬ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ እንዳይንቀሳቀሱ ተወስኗል ብለዋል፡፡
ከተጠቀሰው ሰዓት ውጪ ሲንቀሳቀስ በተገኘ ባጃጅና አሽከርካሪ ላይ እርምጃ እንደሚወሰድበት ከተማ አስተዳደሩ ማስጠንቀቁንም አቶ ተስፋሁን አመልክተዋል፡፡ስለጉዳዩ ያነጋገርናቸው አንዳንድ የባጃጅ አሽከርካሪዎች ውሳኔውበእለት ገቢያችን ላይ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ መንግስት የከተማዋን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ሌሎች አማራጮችን መውሰድ ነበረበት በሚል ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡
ዘገባ፦ ዓለምነው መኮንን፤ ዶይቸ ቬለ (DW) ከባህር ዳር
ተጨማሪ ያንብቡ:  ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ያየሰው ሽመልስ በጸጥታ ኃይሎች ተያዙ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share