June 13, 2022
18 mins read

ዶክተር አብይ ስልጣን ይልቀቁ፣ የሽግግር መንግስት ይመስረትና ብሄራዊ መግባባት ይጀመር – ገለታው ዘለቀ

Abiy 90

Abiy 90ውድ ወገኖቼ ኢትዮጵያ ብሄራዊ መግባባት ያስፈልጋታል የሚለው ጥሪ የሁላችን ነው። ብሄራዊ መግባባት ሲባል ምን ማለት ነው? የሚለው ጉዳይ ላይ ግልፅነት እንደሌለ የገባኝ የምክክር ኮሚሽነሩ ሲናገሩ አድምጬ ነው። እያዘንኩ በትህትና  ይህንን ልበል……….።

ዋናው የምክክር ኮሚሽነር ሲናገሩ የምክክር አጀንዳ ከታች ከህዝቡ ነው የምናመጣው ስለዚህ ህዝቡን እያወያየን አጀንዳ እንሰበስባለን ወደ ሃያ ሺህ ስብሰባ እናደርጋለን ይላሉ። ገበሬውን ስናወያይ ችግሬ የማዳበሪያ ነው ሊል ይችላል ይህ ችግሩ ይመዘገባል ይላሉ ኮሚሽነሩ። ወጣቱ ችግሬ ስራ ማጣት ነው ሊል ይችላል ይህ ችግር ይመዘገባል ይላሉ ኮሚሽነር………።

እንደማየው የብሄራዊ ምክክር ፅንሰ ሃሳብ በምርጫ ከሚመጣ የመንግስትና የህዝብ ስራዎች ጋር ተምታቶባቸዋል። ይህ ኮሚሽን የህዝብን ችግር ሁሉ መዝግቦ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን እናድርግ? ለማለት የተቋቋመ መሆን የለበትም። የማህበረሰብ ችግር እኮ ሁል ጊዜም አለ። ገበሬው የራሱ ከግብርና ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉበት፣ ሃኪሙ ከስራው ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉበት፣ አስተማሪው ከትምህርት ጋር የተያያዙ ችግሮች አሉበት፣ ወጣቱ የስራ ችግር አለበት፣ ህዝቡ በኑሮ ውድነት እየተጠበሰ ነው፣ ኢንፍሌሽኑ ልጓም አጥቶ ይጋልባል ወዘተ. ይሁን እንጂ ይህ ኮሚሽን እነዚህን ችግሮች አዳምጦ ፓሊሲ ለመቅረፅ የተነሳ አይደለም። እነዚህ ሁሉ የህዝብ ችግሮች የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ከተዘረጋ በሁዋላ ፓርቲዎች የህዝቡን ችግሮች እያጠኑ አማራጭ ፓሊሲ እየቀረፁ በምርጫ ስልጣን እየያዙ ሲሄዱ በሚያድግ ዴሞክራሲና ልማት የሚቀረፉ ናቸው። ገበሬው ዛሬ ማዳበሪያ ተቸግሮ ቢሆን የተሻለ መንግስት ሲመጣ ለዚህ ችግሩ መላ ይሰጠዋል፣ በታሪካ አጋጣሚ ዋልጌ መንግስት ሲመጣ ደግሞ የማዳበሪያ ችግሩ እንደገና ሊመጣ ይችላል። ይህንን ችግር የምንቀርፈው በመድብለ ፓርቲ ስርዐት ነው እንጂ የብሄራዊ ምክክር ኮሚሽን በማቋቋም አይደለም። ከቶውንም የዚህ ኮሚሽን ስራ እንደዚህ አይደለም።

በአንድ ሃገር ብሄራዊ መግባባት የሚያስፈልገው በፓርቲዎች መካከል የሃሳብ ልዩነት ስለታየ አይደለም። በተለይ እኛ ብሄራዊ መግባባት  የሚያስፈልገን በዋና ዋና መተሳሰሪያ መርሆዎች ላይ ጽንፈኛ ልዩነት ስላለ፣  ምርጫ በማይፈታቸው ልዩነቶች ላይ ስለወደቅን፣  ወይም ችግሮቹን ለምርጫ ብናቀርብ በውጤቱ ለሃገር ህልውና እምቅ አደጋ ደቅኖ ስለመጣብን፣ በለሂቅ ክፍፍል በሃይል ህብረታችን ስለተመታና ስርዐቱ እገጭ እጓ ስለሚል ነው ብዬ አምናለሁ።  በኔሽን ግንባታ ላይ መሰረታዊ ችግሮች ስላለ ነው ብየ አምናለሁ።

ለምሳሌ በፌደራል ስርዓቱ፣ በፖለቲካው ሰልፍ፣ በባንዲራና በሌሎች ከፍተኛ መዋቅራዊና ስርአታዊ ትክሎች ላይ መግባባት የለም። ይሄ አለመግባባት በመድብለ ፓርቲ ስርዓት ውስጥ ጤነኛ ልዩነት አይባልም።  ስርዓቶች ቋሚ መሆን አለባቸው። ለስርዓት ተከላና ነቀላ ምርጫ ካደረግን አንዱ ሲያፈርስ አንዱ ሲተክል ሃገር መንግስት ሳይረጋጋ ይቀርና ችግር ውስጥ እንገባለን። ስለዚህ ከባድ የለሂቅ ክፍፍል በስርዓተ መንግስት ላይ ሲኖር የብሄራዊ ምክክር አሳብ ይነሳል።  ይህ የምክክር ኮሚሽን ግን የህብረተሰብን ችግር ሁሉ ልመዘግብ ነው ብሎ ከተነሳ በራሱ ተወሳስቦ የማይመለከተውን ሲያቦካ ከርሞ ይፈርሳል። ይህ ኮሚሽን ይህንን በማድረጉ የሚጠቅመው ነገር መንግስት ስልጣን ላይ ውሎ ያድር ዘንድ አስታማሚ መሆን ብቻ ነው።  የአሁን አያያዙም ይህንን ያሳያል። ሃገሪቱ ሃቀኛ መዋቅራዊ ጉዳዮችን አንስታ በወቅቱ እንዳትወያይ ምክክሩን ቡርቅቅ አድርጎ ዋናውን አጀንዳ ማዘናጋት ሃይ የሚባል ተግባር ነው። የማንነት ኮሚሽንና የብሄራዊ እርቅ ኮሚሽን በመንግስት ተጠልፈው ምንም ፍሬ ሳያሳዩ እንደፈረሱት አይነት ነው።

ስለዚህ በኢትዮጵያ ሁኔታ የምክክር ኮሚሽን ስራ በሚገባ ካልተበየነ ወደፊትም ወደ ምክክር ገብተን ችግሮችን ልንፈታ አንችልም።  በዚህ ሰዓት ሃገሪቱ በስርዓታዊ ሽብር ውስጥ ባለችበት ሰዓት አጀንዳዎችን  ሰብሰብ አድርጎ በመዋቅራዊ ጉዳዮች ላይ ለሂቁ፣  የፓለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ የሃይማኖትና የሲቪክ መሪዎች በፍጥነት ወደ ውይይት መግባት ነበር የሚያስፈልጋቸው።  ኢትዮጵያ ውስጥ ህዝብና ህዝብ ተጋጭቶ አያውቅም። በብሄሮች መካከል በባህል ግጭት የለም።  አንዱ ብሄር የኔ ምግብ ይጣፍጣል ያንተ አይጣፍጥም ብሎ ጦርነት አያደርግም።  ሌላው ብሄር የአንተ ልብስ አያምርም የኔ ያምራል ብሎ ጦርነት አይገባም።  ቡድኖች የሚጋጩት ኢንስትሩመንታሊስት ወይም ብሄርን መሳሪያ አድርገው የሚያጋጩ ፓለቲከኞች ሲበጠብጡት ብቻ ነው። ህዝቡ ፓርቲዎቹን ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ እያለ ተግባብተው እማራጭ ፖሊሲ እያመጡ እንዲመርጣቸው ነው የሚፈልገው።

እውነቱን ለመናገር በዚህ ሰዐት በኢትዮጵያ ውስጥ የብሄራዊ ምክክር አጀንዳዎች ግልፅ ናቸው። አጀንዳዎቹ አይደሉም የጠፉት። የምክክር ኮሚሽኑ አጀንዳ ፍለጋ ሃያ ሺ ስብሰባ ማድረግ የለበትም። የተቸገርነው አጀንዳ ሳይሆን በነዚህ አጀንዳዎች ላይ ሁሉን አቀፍ የሆነ ምክክር በጊዜው ማድረግ ነበር። ኮሚሽኑም ስራው ይሄ ሆኖ ሳለ የሃገሪቱን ምክክር ስራ ቡርቅቅ አድርጎ እያሰፋ ማወሳሰብ በእውነት ያሳዝናል። ይህ አካሄድ ለስልጣን ጥመኞች ጊዜ እየሰጡ እያስታመሙ ማኖር ነው አላማውና መቃወም ያስፈልጋል። የምክክር ኮሚሽን የሚቋቋመው ሃገራዊ ቀኖናዊ ችግሮችን ለመፍታት አይደለም። ቀኖናዊ ችግሮች በምርጫ በመድብለ ፓርቲ ስርዐት ይፈታሉ። የምክክር ኮሚሽን የሚያስፈልገው በሃገራዊ አይነኬ ዶግማዊ ጉዳዮች ላይ ለመግባባት ሃገርን በቋሚ ስርዐት ለማርጋት ነው።

ውይይት ወይም ምክክር ሲደረግ  በውጤቱ ሮድማፕ ለማዘጋጀትና ለህገ መንግስት ማሻሻያ የሚሆኑ ሃሳቦችን ማምረት ነበር። በዚህ ሂደት ላይ ህዝቡ በአጀንዳዎቹ ላይ፣ በውይይቱ ሂደት ላይ ቀጥተኛ አስተያየት የሚሰጥበትን መድረክ ማዘጋጀት በርግጥ ተገቢ ነው። መጨረሻ ሮድማፑን የሚያጸድቀው ግን ህዝብ ነው።  ይሁን እንጂ አጀንዳዎችን በማወሳሰብና በማንዘላዘል የምክክር ሂደትን ማጓተት ተገቢ አይደለም::

ለማናቸውም ዛሬም፣ ከዚህ በፊት እንደ ዜጋ ያጠናሁዋቸውን ብሄራዊ የምክክር አጀንዳዎች አካፍላለሁ።

ዋናው ጉዳይ ሃገራችን መቼም ቢሆን የምክክር ምእራፍን ወደ ጎን ትታ የረጋ መንግስት መስርታ ልትኖር አትችልም። ስለዚህ ሃቀኛ የምክክር ሂደት ውስጥ ስንገባ አጀንዳዎች እነዚህ ቢሆኑ ብሄራዊ ችግሮቻችን ይፈቱና ከዚያ በመለስ ያሉ የህዝብ ችግሮች በፖሊሲ እየታረቁ ይፈታሉ ብየ አምናለሁ። አጀንዳዎቹ የሚከተሉት ነበሩ።

  1. በህብረታችንወይምበአብሮነታችን ፍፁምነት ላይ ውይይት ያስፈልጋል ። ህብረታችንና የጋራው ቤታችን በምን ያህል አቅም ወይም በምን ያህል የአብሮነትና የወዳጅነት የቃልኪዳን ልክ ይታተ? የሚለው ዋና የምክክር አጀንዳ ነው። አሁን ያለው መተሳሰሪያ መርሆ የህብረታችንን ልክ በመገንጠል የወሰነው ሲሆን አሁን ይህንን የህብረት ልክ እንዴት እናሳድገው የሚለውን ቁልፍ ጉዳይ ነው :: ለዚህ ነው Toward a More perfect Union እያልኩ የፃፍኩት:: ውይይታችን የጋራውን ቤት ፍፁም ወደ ማድረግ እንዲሆን መወያየት ያስፈልጋል ::
  2. በቅርፀመንግስትላይ (Government Structure ) ምክክር ያስፈልጋል ። ቅርፀ መንግስት በምርጫ መንግስት ሲመጣና ሲሄድ የሚቀየር አይሆንም። በዚህ አንድ ኢትዮጵያን የመሰለ ቅርፀ መንግስት መስፋት አለብን። ይህ ጉዳይ ሀገሪቱ ፓርላመንታሪ ትሁን ወይስ ፕሬዝደንሺያል? የፌደራል ሥርዓቱ ምን መልክ ይያዝ? የመንግስት ቅርፁ ምን ይጨምር ምን ይቀንስ? ለምሳሌ የህገመንግስት ዳኛ ይኑር ወይስ እንዴት እንቀጥል ወዘተን ይመለከታል ::
  3. ብሄራዊማንነትንናየብሄር ማንነትን እንዴት እንንከባከብ።  በምን አይነት ምህዋር ይዙሩ? እንዴት ሳይጠላለፉ ይኑሩ በሚለው ላይ ምክክር ያስፈልጋል።  በማንነት ፖለቲካ ላይ ውይይት ያስፈልጋል::  Identity politics and Identity vote on the scale of democracy and justice መቀመጥ መመዘን አለበት::
  4. ብሄራዊምልክቶችንበተመለከተ መመካከር ያስፈልጋል። ባንዲራን መዝሙርን ወዘተ ይመለከታል።
  5. የመሬትላራሹጥያቄ ምክክር ውስጥ መግባት አለበት። የፓሊስ ቀጭን ጉዳይ አይደለም ይህ አጀንዳ።
  6. ያለፈመጥፎትውስታዎች እንዴት ይታዩ? (Past bad memories) የሚለውን ማንሳት ተገቢ ነው።
  7. ቋንቋናተግባቦትንበሚመለከት ውይይት ያስፈልጋል።  ይህ ጉዳይ የአንድ ፓርቲ ፓሊሲ ሳይሆን የቋንቋ አያያዛችን ላይ የጋራ አቋም መያዝ ይቻላል።

 

ይህንን ካልኩ በሁዋላ ግን ሁላችንም እንደምናየው ሃገራችን ሁለንተናዊ ደህንነቷ ዛሬስ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አደጋ ላይ ወድቋል። አድሮ የተሻለ ነገር የለም። መንግስት ይህ ሁሉ ችግር እየተፈጠረ ጣቱን ሌላው ላይ እየጠቆመ ከመኖር ባሻገር የፖለቲካ ለውጥ ለማድረግ አልፈለገም። የኢትዮጵያ ህዝብ ደርግ እንዲወድቅ የታገለው፣ ህወሃት እንዲወድቅ የታገለው እነዚህ መሪዎች ህዝቡን ከአንድ መከራ ወደ ሌላ መከራ እየዘፈቁ ስለሄዱ ነው። ዶክተር አብይ ህዝቡን በኑሮ ውድነትና በሰላም እጦት፣ በመፈናቀልና በመከራ ብዛት  ከደርጉና ከመለስ በልጠዋል። ስለዚህ ይበቃል። መንግስት ለሚከሰቱ ችግሮች ሁሉ ጣት መቀሰር አያዋጣውም። ይልቁን አሁን ዶክተር አብይም በክብር ስልጣን ያስረክቡና የተውጣጣ የሽግግር መንግስት ይቋቋም። ከዚያም ሃገሪቱ ወደ ብሄራዊ መግባባት ታዘንብል። ከፍ ሲል እንዳልኩት በምንም መልኩ ልንዘለው የማንችለው ምዕራፍ የብሄራዊ ምክክር ምዕራፍ ነው። ነገር ግን ዶክተር አብይ ብዙ ተቋማትን እንዳበላሹት ይህንን ተቋምም አበላሽተዋል። በዚህ ሁሉ ግን ሃገራችን ተስፋ መቁረጥ የለባትም። እንደ ሃገር የሽግግር መንግስት መስርቶ የጠዳ ብሄራዊ ምክክር ወደ ማድረግና ህብረትን  ፍጹም ወደ ማድረግ ማሻገር የዚህ ትውልድ ትልቅ የቤት ስራ ሆኖ ይታያል። እንደሚታየው በዚህ ወቅት በሃገራችን የውስጥ ጉዳዮች ላይ የውጪ ጣልቃ ገብነት አይሏል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በረጋ መንፈስ ያለ ውጪ ጣልቃ ገብነት ማስተካከል አለባቸው። ከአለም አቀፉ ኮሚኒቲ ጋር ያለን ግንኙነት ጨለምተኛ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ጠብቀን መራመድ ያስፈልጋል። በመሆኑም ነጻ የሆነ የሽግግር መንግስት መስርተን የፖለቲካ ለውጥ በማምጣት መረጋጋት ፈጥረን መተሳሰሪያ መርሆዎቻችንን ለማሻሻል ምክክር ውስጥ እንግባ። ለምክክር ሰላም ወሳኝ ነው። ጦርነቱ የሚያቆመውና ጊዚያዊ መረጋጋት የሚመጣው ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግስት ሲቋቋም ነው።

እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ

http://amharic-zehabesha.com/archives/125663

7 Comments

  1. አይ የሃበሻ ፓለቲካ ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ። ያኔ ስታጨበጭቡና ሆ ስትሉ እንዳልነበር አሁን ተገልብጣችሁ ከስልጣን ይውረድ የሽግግር መንግስት ይመስረት ስትሉ አታፍሩም። በመሰረቱ የሽግግር መንግስት የሚለው ቃል የሚያስጠላና ከአለፈው ታሪካችን ስንማር ሽግግር መሆኑ ቀርቶ መልክ እየቀያየሩ ሲፈትጉን እንደኖሩ ያመላክታል። በእኔ እምነት ችግሩ ያለው ማን በስልጣን ላይ አለ፤ ከእነማን ወገን ናቸው እያለን እየፈጠርን በምንጋግረው የክፋት እንጀራ ጭምር እንጂ በመሪዎቹ ላይ ብቻ ማላከክ ራስን ከተጠያቂነት ለማራቅ ነው። ችግሩ ያለው ከህዝቡ ነው። ህዝቡ በወያኔ የ 30 ዓመት ተንኮል በራፉ ላይ ቆሞ ሃገር ነኝ እያለ ሰንደቅ ሲያውለበልብ ይውላል። በዚሁ በክልል ፓለቲካና በብሄር ተኮር ሽብር እልፍ ሰዎች ሃብትና ንብረታቸውን፤ ህይወታቸውን አተዋል። ግን ዛሬም ያው ነን። በውጭም በውስጥም የምናቅራራው የተውሶ የህልም መሳሪያም ሆነ የእውኑን ታጥቀን አባረው፤ በለው ግደለው እያለን እንፎክራለን እናፏክራለን። ችግሩ ህዝቡ ነው መሪዎቹ አይደሉም። ሰራዊቱን ከትግራይ ያስወጣው የወያኔ ውጊያ አይደለም። የትግራይ ህዝብ በህቡዕና በግልጽ በተናጠልና በማበር በየሜዳው ስለገደለው እንጂ። የጽሞና ጊዜ ለመስጠት የትግራይ ገበሬ እንዲያርስ የተባልነው ሁሉ የወስላቶች ወሬ ነው። ወያኔን የሃበሻ ህዝብ የጠላው ከትግራይ ምድር ስለወጡ አይደለም። ሥራቸው የሳጥናኤል ስለሆነ እንጂ። ስለሆነም ያ ሰው፤ ያ ቡድን እንዴት ህዝባችን ያስተዳድራል ብሎ መጠየቅ እንጂ በዘሩና በቋንቋው ተተምኖ መጠላትም መወደድም የለበትም።
    የዶ/ር አብይ ከስልጣን መውረድ አንድም ፓለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ድል አያመነጭም። የባሰ ግርግርና ፓለቲካ እንጂ። ትላንት ለ 5 ዓመት ተብሎ ተመርጠው አሁን ጊዜአዊ መንግስት ይቋቋም ማለቱ ከወያኔ የክፋት ኮሮጆ የተዘገነ የፓለቲካ ብልሃት ይመስላል። ይህ ሲባል በጭፍን ጠ/ሚሩን እንደሚደግፉት እኔም እነርሱን ለመምሰል ስልፍ ይዤ አይደለም። ያለውን እውነታ ይምጣልን ከምትሉት ጋር በማነጻጸር እንጂ። ፓለቲካ ያለ ውሸት፤ ሃይማኖት ያለሸፍጥ፤ የተጓዙበት አንድም የዓለም ታሪክ የለም። ታሪክ ብለን የምናነበው እንደ ጸሃፊውና እንደተጻፈበት ዘመን ያገድዳል እንጂ። አስታውሳለሁ አንድ ጊዜ በውጭ ሃገር ነበርኩ። ሳናስበው የሰው ጎርፍ ከፊት ለፊታችን መፈክር አንግቦ ይነጉዳል። በጊዜው በስልጣን የነበሩትን ይውረድ እያለ እሳት ይለኩሳል መንገድ ይዘጋል እርስ በእርሱ ይነታረካል። በዚህ ጊዜ አንድ ጎኔ የነበረው ግብጻዊ ስማ ወንድሜ ከአመታት በፊት እነዚሁ ሰዎች ናቸው ሰውዬውን ስልጣን ላይ ያወጡት። አሁን ደግሞ ተገልብጠው የተገነባ ይንዳሉ አለኝ። ባጭሩ ያቺ ሃገር ዛሬ ሃገር አይደለችም። ወረበሎች የሚራወጡባት ምድር እንጂ። ትሻልን ትቼ ትብስን ይሉሃል ይሄ አይነቱ ነው። ከደርግ ክፋት የባሰ በኢትዮጵያ ምድር ይመጣል ብሎ አንድም ሰው ያሰበ አልነበረም። ግን አያቹሁት አይደል። ከሰው ተራ የወጣ ወያኔን አመጣ።
    ስለዚህ ችግሩ ከመሪዎቻችን ብቻ እንደሆነ አድርጌ እኔ አላየውም። ህዝቡ ራሱ ችግር አለበት። ስርቆቱ፤ ቅሚያው፤ ጠለፋው፤ በሴቶችና በድሃ አደግ ልጆች ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ፤ ማጭበርበሩ፤ ሰውን በመርዝና በመኪና እየገጩ መግደሉ፤ ከሌላ ክልል መጣ ብሎ ቤት ዘግቶ በእሳት ሰው ከሚያጋይ ቡድን እንዴት ባለ ሂሳብ ነው ፍትህ ይኖራል ብለን የምንጠብቀው? ወያኔ ለትግራይ ህዝብ ምን አመጣ? እልፍ የኦሮሞ ቱልቱላዎች ለኦሮሞ ህዝብ ምን አዲስ ነገር ፈጠሩ? ለአማራ ህዝብ ቆሚያለሁ የሚሉትስ ለዘመናት ለህዝቡ ያደረጉት እዚህ ግባ እሚባል ምን ተደረገ? መልሱ ምንም ነው። ራሱ በፓርላማ ውስጥ ቁጭ ብለው ይህን ጥያቄ ባቀርብ ሶሻል ሚዲያ ውስጥ ይቀባበሉታል ብሎ በማመን ስንት የሚጠየቅ እያለ ለግጭትና ለተገንጣይ ሃሳብ ቅድሚያ በመስጠት ጥያቄ ለጠ/ሚሩ የሚያቀርቡ ስንቶች ናቸው? እንታዘባለን። ከዚያ ወስላታው ሚዲያ ጠ/ሚሩና እክሌ ተፋጠጡ ይሉናል። ወይ መፋጠጥ አንድ አንድን እንዲበላው እየቀሰቀሱ እንደሆነ ይገባቸው ይሆን?
    የዚህ ጽሁፍ ጸሃፊ በኑሮ ውድነት፤ በሰላም እጦት፤ በህዝቦች ስቃይና በድርቅ ጠ/ሚሩን አጣጥሏዋቸዋል። የት ነው ጸሃፊው የሚኖሩት? ዛሬ የኑሮ ውድነት የሌለበት ምድር አለ? ስንኮንን በመረጃና ዓለም አቀፋዊ የፓለቲካና የኢኮኖሚ እይታን ይዘን ቢሆን የተሻለ በሆነ ነበር። ግን መጽሃፉ እውቀት ይበዛል ባለው መሰረት ዛሬ ሁሉ ዶ/ር፤ ፕሮፌሰር፤ ወዘተ ስሙ ላይ እየለጠፈ ሲዘላብድ ማየት የተለመደ ሆኗል። የህክምናው ዶ/ር ሥራውን ትቶ ሰው አንቂ የመድረክ ሰው፤ ኢንጂኒየሩ በተማረበት ሙያ ህዝብን እንደማገልገል የፓለቲካ ሰው ሆኖ ሃተፍ ተፍ ሲሉ ከማየት የበለጠ ውርደት የለም። የጠፋው ሰርቶ የሚያበላ እንጂ ለፍላፊ ምድሪቱ አጥታ አታውቅም። ቀንም ማታም፤ በሚዲያ መለፍለፍ፤ ባልተጨበጠ ነገር ላይ አየሁ ብሎ ማውራት። እንዲህ ባለ ሃገር ውስጥ ነው የሽግግር መንግስት የሚሉን። ምን አልባት በዋሽንግተን ዲሲ ታክሲ ነጂዎችን አሰባስቦ የአሜሪካ መንግስት ለጋዘጠኞች ካቀረቧቸው ወገኖች ጋር መዳበሉ የሚሻል ይመስለኛል። አሁን ላለችው ኢትዮጵያ ግን ጭቃም ተቀባች ጥላሸት የሽግግር መንግስት አያስፈልጋትም። ባለው እየመከሩና እየዘከሩ መጓዙ የሚሻል ይመስለኛል። በቃኝ!

  2. አቶ ገለታው ዘለቀ የባልደራስ የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ ናቸው። ባልደራስ የእስክንድር ነጋ ፓርቲ ማለት ነው። ዶ/ር ዐቢይ ሥልጣን ለቅቀው የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ሲሉ ማንን መተካት እንዳሰቡ ቢያስታውቁን ጥሩ ነበር። የዋጋ ግሽበት ዓለም አቀፍ መሆኑን ያወቁ አይመስሉም። ዶ/ር ዐቢይ እንዳመጡት አስመስለዋል። ከህወሓት ጋር ጦርነት ባይቆም ኖሮ አገራዊ ጉዳት ምን ሊሆን እንደሚችል፣ ህወሓት ያበላሸውን መጠኑን ጨርሶ የተገነዘቡ አይመስልም። ስለ መንግሥት ምሥረታ፣ አሁን ስላለንበት ሁኔታ ምኑንም የተረዱ አይመስልም። ከመጻሕፍት የቃረሙትን፣ በልምድ የማያውቁቱን ስንቱን ጫሩ። ጥሩነቱ በተለያየ ጊዜ ብዙ ስለሚናገሩና ስለሚጽፉ ማን እንደ ሆኑ አቋማቸውን ጭምር ማወቅ ይቻላል።

  3. The idea behind a transitional government is generally acceptable but its plausibility under the present conditions in the country needs deliberations on it. The Ethiopian politics is polarize and this has stood in the way of even discussions let alone a transitional government. The reality is that despite calls and wishes for an all party transitional phase, it has not materialized. The real and fake parties can not come together and agree to form a transitional government.

  4. After routing the forces of the derg Amhara government, the heroic Tigray forces under the leadership of the TPLF formed a transitional government with all the stake holders in the county. As known all over the world, the Tigray people have one of the oldest civilizations and longest history of democratic politics. Contrary to this, the Amhara and Oromo communities had not existed as nations or states ( are at the lower level of social development) but the TPLF created regions for them and allowed them self rule as part of its process of democratizing and developing them. Now the concern among the Tigrayans is whether the Oromos will be strong enough to defend and maintain their self rule.

    • Digital Tigraway – Let by gone be by gone. Do not dig up buried issues to create more fire and to have us kill each other unabated. Have you been in Tigray recently? Holed up in some Western country and glorifying past and present evil deeds of the TPLF is not going to help anyone. Living among a pluralistic society you still advocate hate and division among the Ethiopians. What a shame! Wake up and be part of the global community. Forget your fabricated past glory. Life is worth living when lived with others. Not just the ones in your circle and your ethnic groups.

      • Fascists like the guy using the alias Digital Tigraway are deranged persons and do not consider constructive ideas and advice like yours. Experts who know Tigray well state that it is the poorest region and can not sustain itself. The empty hubris the guy writes here is rubbish.

  5. Digital is the best illustration of a group that lied profusely, continued to lie and ended up believing its own lies. Look what hell such individuals and groups have put us through in the past 50 years. Check out these:

    “As known all over the world, the Tigray people have one of the oldest civilizations and longest history of democratic politics.”
    1. It is NOT known all over the world, unless by “all” is meant Dedebit.
    2. The oldest civilisation is not in Tigray, unless by Tigray is also meant Afar, Amhara, and the Nile Valley.
    3. “The longest history of democratic politics” can’t be true with only 27 years to talk of; democracy based on ethnicity is NO democracy; democracy that does not allow opposition parties and wins elections by 100% every time is NO democracy.
    4. “After routing the forces of the derg Amhara government” is a wish fulfillment. Derg had already collapsed internally of its own doing; there was a coup attempted. Read Fisseha Desta’s memoir. FYI, Fisseha Desta is from Adowa. Fast forward to 2020 where Tplf has amassed over a quarter of a million forces and the best equipment it looted while a ruling party. Within two weeks it was routed and its top leaders hunted down like wild beasts and liquidated and many surrendered. This happened less than two years ago and everyone, including Americans know it. Btw, Americans were the ones that helped Tplg ragtag army into Addis and Americans are still defending them!

    Do you now see, how one ends up believing own lies and thinks everyone will follow suit? What needs to happen to groups like this that are disjointed from reality? I think that is for psychiatrists and crime busters to investigate and resolve.

Leave a Reply

Your email address will not be published.

aklog birara 1
Previous Story

ኢትዮጵያን ለመታደግ ፋኖን በጅምላ ማሳደድ በአስቸኳይ ይቁም –  አክሎግ ቢራራ (ዶር)  

EDF
Next Story

  መንግስት በዐማራ ፋኖ ላይ የሚያደረገውን ዘመቻና ጥቃት አጥብቀን እናወግዛለን!

Latest from Blog

አስቸኳይ ህዝባዊ ጥሪ

July 24, 2024 ዓለማቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት Global alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገዜ ጎፋ ወረዳ ኬንቾ ሳቻ ጎዝዲ ቀበሌ በደረሰው የመሬት መንሸራተት የብዙ ወገኖቻችንን ህይዎት ማለፉን
Go toTop