መግቢያ
መቸም የሃገሬ ሰው ጥቅስና መፈክር ይወዳል። ነገር ግን ከጥቅሱና ከመፈክሩ ጀርባ ያለው መልዕክት ግን ሲተገብር አይታይም።
በየውይይት ታክሲው ፣ ባጃጅ ና በየቤታችን በኪሮሽ አየተከተቡ የተለጠፉ ብዙ ጥቅሶች አሉ። እኔ በልጅነቴ አክስቴ ቤት ግድግዳ ላይ ሁሌ ተፅፋ የምታነባ ጥቅስን ሳስታውስ ግርም ይለኛል፣ ጥቅሷም እንዲህ ትነበባለች “ፊርማና ወረቀት ጠፊ ነው ተቀዳጅ መተማመን ብቻ ይበቃል ለወዳጅ” ትላለች።
እቺ ጥቅስ ከልጅነቴ ጀምሮ በአዕምሮየና ልቤ ውስጥ ተከትባ መውደድና ታማኝነትን በልቤ አንግሳ እስከዛሬ እንድዘልቅ እረድታኛለች። የደጋገጎች፣ በእምነት ሙላት የተዋጁና የእውነተኛ ኢትዮጵያዊያን ቅኝታዊ መፈክር ስለሆነችም ይሆናል ልቤ ላይ ተከትባ ለዘመናት የዘለቀችው።
መቸም “ ጀሮ የማይሰማው ፣ ሆድ የማይችለው የለም” እንዲሉ የሰው ልጅ ከስሜታዊነት ርቆ ፣ ነገሮችን በአንክሮ አይቶ ፣ አገናዝቦና አሰላስሎ የሚሆነውንና እየሆነ ያለውን ማሰላሰል የግድ ይሏል።
በዚች አጭር ፅሁፍ በታላቋ የአምላክ ተስፋ ምድር ኢትዮጵያ በማሟረታችውና፣ በስሟ በመነገዳችው ከዚያም አልፎ ሊክድዋት የዳዱትንም ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለቻቸው ማሰላሰል ጠቃሞት አለው።
“ከኢትዮጵያ ሱሴ እሰከ ኢትዮጵያ አትፈርስም” የሚለውን መፈክር የሚያሰማው መንግስት፣ የመሪዎች አሽሙርና ሿሿ በዚህ አጭር ፅሁፍ ይዳሰሳል።
ኢትዮጵያ አትፈርስም የሚለው የሟርትና የጥቅመኞች እጓጉል መፈክርን በተመለከተ!
ይሄ የቂል መፈክር አንዳንዴ በደርግ ዘመን በባንዳዎች ይነበነቡ የነበሩትን ከአምላክ ጋር የሚያላትሙ መፈክሮችን ያስታውሰኛል ፣ ለምሳሌ “ ተፈጥሮን በቁጥጥራችን ሥር እናውላለን” የሚል የማሞ ቂሎ ተረት ተረት እንድናስታውስ የግድ ይለናል። አብዛኛው ህዝብ የተማረውም ፣ ፓለቲከኛውም ሳይቀር ይሄን የጅሎችና ጅላንፎዎች መፈክር በየመንገድ፣ በየቤቱና በየቢሮው ለጥፎ እንደ አቡነ ዘበሰማያት ይደግመው እንደነበር ሳስታውስ እስካሁን ይህ ክስተት ያስደምመኛል። ተፈጥሮን የሰው ልጅ በቁጥጥር ስር ማድረግ ይቻልዋልን? ብሎ የጠየቀም በዘመኑም አልነበረም።
አንባቢዎች የአጨብጫቢነት ብሃሪ ከትናንት ክስተት የተወረሰ የግንታግቶች መገለጫ እንጂ እንዲሁ የመጣ ማህበራዊ ዝቅጠት አይደለም።
- ይህን ላነሳ የተገደድኩት የአምላክ የተስፋ ሃገረ የሆነችው ኢትዮጵያየተለያዮ ፈተናዎች ቢደቀንባትም በሕዝቦቿ ተጋድሎና እምቢ ባይነት ተቋቁማ ፣ በነፃነቷ ታፍራና ተከብራ እየዘለቀች ነው ፣ ለወደፊቱም በእርግጠኝነት ያለጥርጥር ትኖራለች።
ሃገረ ኢትዮጵያ ካጋጠሟት ፈተናዎችና ግብ ግቦች መካከል የተወሰኑትን ለማየት እንሞክር :
- በጀርመን አፍሪካን የመቀራመጥ እጀንዳ ጥንስስ ተጠምቆ ፣ በፋሽሽቶች መንግስታት ጋሻ ጃግሬነት ተቀብቶ ሃገራችን ሊቀረምጥ የገባው ሰላቶው ጣሊያን ፣
- የኢትዮጵያን አባይ ውሃ በነፃ ያለተቀናቃኝ በባለቤትነት ለመኮምኮም የሚመኙት የግብፅ / ምስር/ና የሱዳን ሽርባዎች ከብዙዎቹ፣
- ሰሞኑን ደግሞ ከላይ በተጠቀሱት ታሪካዊ ጠላቶቻችን ተጠንስሶ ፣ ኢትዮጵያ ሳትፈልግ በተፈጠሩባት የእንግዲህ ልጆች ተተብትቦ ታይቶ ባማይታወቅ መልኩ የሃይማኖት ጦርነትና ግጭት ለመፍጠር ከታሪካዊዋ፣ የስልጣኔ ፈር ቀዳጅና የኢትዮጵያ አምሳል ከሆነችው ጎንደር በማስነሳት ወደ መላ ኢትዮጵያ እንዲሰፋፋ ተሞከረ። ነገር ግን ቀናተኛውና የማያቀላፋው የኢትዮጵያ አምላክ እንዴት ይሄን ሰይጣናዊ ሙከራ እንዴት እያኮላሸው እንዳለ ስናይ ዘይገርም የሚያሰኝ ነው፣
- የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶችሁሉ ሞክረው ያልቻሉትን በአንድ ተራ ሽፍታና ግብረች አበሮች ተደናብሮ “ ኢትዮጵያ አትፈርስም” እያሉ በየኢምባሲውና በተገኘው ቦታ ሁሉ ይህን የሞኝ ዘፈን እየደጋገሙ መዝፈኑና ማላዘኑ አንድም ታላቅዋን ሃገረ ኢትዮጵያ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ለማድረግ ከማሰብ የተነሳ ወይም ኢትዮጵያን በቅጡ ስለማያውቋት ፣ የኢትዮጵያን የረጅም ታሪክና ኩነት ባለመረዳታቸው ነው ለማለት ይቻላል ።
- በኢትዮጵያ ፀበል የተጠመቁ አዲስ የኢትዮጵያ ፍልስፍና አቀንቃኞችና ጅምር ኢትዮጵያዊ አማኒያን ለማለት ይቻላል ወይም ካድሬዎች “ኢትዮጵያ ሱሴ ወይም ኢትዮጵያ አትፈርስም” ቢሉ አፍላ ኢትዮጵያዊ ከመሆናቸው የተነሳ ይህን መሰል መፈክር እንደ ሞሞ ቂሎ መፅሃፍ ቢደጋግሙት አይፈረድባቸውም። ኢትዮጵያ በደንብ ላጣጣማት ጣዝማ ማርና ውብ ሃገር ናት። ጠንካራም የማትበገር የአምላክ የቃል ኪዳን ሃገር ናት።
እኔ ባደኩበት መንደር እናት ልጅ አዝላ ድግስ ቤት ስትታደም የምትጠጣውንና የምትበላውን በአንቀልባ ላዘለችው ልጅ “እንዳይደቃው” ተብሎ እናት በእጣቷ የበላችውንና የጠጣችውን ሁሉ ታቀምሰዋለች።
በእንደዚህ አይነት ቀመር ኢትዮጵያዊነትን በአንቀልባ ሳለን ጀምሮ እያጣጣምን ላደግን የአማራ ልጆች ይህ አካሄድና መፍክራዊ ጉሽምታ አንድም ፌዝ ወይም ሟርት ሲሆን ሌላኛው የዋሃንን ለማታለል የተቆመረ ቁማር ነው ብለን እናገናዝበዋለን፣ እንገመግመዋለን።
ታላቁ የፊልም ባለሙያና አዘጋጅ ጎንደሬው ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ ታፈረ ” ኢትዮጵያ በአንተ አልተሰራችም፣ በአንተም አትፈርስም፣ አንተ ትፈርስ እንደሆን እንጂ” ብለዋል ፣ እውነት ነው! ታላቁ አባታችን።
የነ “ኢትዮጵያ ሱሴ” የታች አምናው ቅዥት!
መቸም አንዳዴ የአገሬ ሰው “ነገርን ከስሩ፣ ውሃን ከጥሩ” ይላሉ። ትናንት “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ያሉት ፣ ዛሬ ዛሬ ጠፍተዋል። የጠፉት ወይም ሱሱን ተወጥተውት ፣ ከሱሱ ተላቀው ይሆናል ፣ ያለዚያም በሌላ መፈክር ሊመጡብን ብየ አስቤ ነበር። አረ ! እረስቸው መጡብን አይደል እንዴ!
የሃገሬ ሰው አንዳንዴ ወይ ግራ ገብቶታል ወይም ቋንቋ ጠፍቶታል። ሱስ ማለት በፈረንጂኛው “ Addiction “ የሚለው ተቀራራቢ ትርጉም ይሰጠዋል።
የሰው ልጅ የመጠጥ ሱስ፣ የሲጋራ ሱስ፣ የጉቦ ሱስ ወ.ዘ.ተ. ሱስ ሊይዘው ይችላል። ሱስ ደግሞ በአምላክ ዕርዳታ ፣ በፀሎት፣ በሐኪም እርዳታ ሊቀንስ ወይም ሊቆም ይችላል።
ስለዚህ ውስጠ ወይራ የቃሉን ስምና ወርቅ ሳይገላልጡ “ ኢትዮጵያዊነት ሱስ” ነው ስለተባለ ብቻ አብሮ ማጨብጨቡና መነውለል አግባብ አይደለም፣ ጉዳዩ ወዲህ ነውና ። ይህ አይነቱ የአስመሳዮች መፈክር ኩሸት መሆኑም እየታየ መጥቷልና።
ኢትዮጵያውያነት መንፈስ ነው። እንደሰሞነኞቹ አንዴ የምንለብሰው ፣ ሲያሻን አውልቀን የምንጥለው የፋሽን ወይም ቁስ /Matter/ አይደለም።
ኢትዮጵያ ጠላቷ በዝቶ ልትታመስ ትችላለች፣ ህዝቦቿ በእኩያን ሊጎሳቆሉ፣ ሊሰደዱና ሊሞቱ ይችላሉ። ነገር ግን ኢትዮጵያን ደጋግመው ስለጥሯትና ስላቆለጳጰሷት፣ በፍቅሯ ልንብሰለሰል እንችላለን ነገር ግን የኢትዮጵያዊነት ሱስ ይዞን ስንፈልግ የምንምጋት ሲመቸን ደግሞ ሰለቸሽኝ ብለን የምንተዋት አይደለችም። ኢትዮጵያ በቃችን የሚሉትም ሆነ በአፍላ የኢትዮጵያነት ፍቅር ተነድፈው “ኢትዮጵያ ፣ ኢትዮጵያ” የሚሉት ቢቻል እንደ አማራ ሕዝብ መንፈስና ማንነት አድርገዋት እንዲኖሩ እንመክረለን።
እንደ ቡናና አረቂ “ፉት፣ፉት” ብለው ችግሩ ሁሉ ወደሰገባው ሲገባ ፣ በሌላ አጀንዳ መጥተው በቃሽን እንዳይሉ። የሰሞነኛው አባዜ ቡዳ እንደ በላው ሰው ትላንት ስሟን ሊጠሯት ይቀፋቸው የነበሩ ቡድኖች ፣ ኢትዮጵያ የአማራ ብቻ ናት ብለው እንዳልነበር ፣ የብሄር መጎናፀፊያቸውን አውልቀው “ኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያ “ እያሉ መዘመራቸው እሰየው የሚያሰኝ ሲሆን በዚህ አጋጣሚ ያዝልቅላችሁ እንላችዋለን። ጠንቀቅ ኋላ እንዳአምናና ታች-አምናው እንዳንተዛዘብ። የፍርድ ቀን አለና “መጠንቀቅና ብልህ ሆኖ መጓዝ ለሃገርም ሆነ ለራስ ይበጃል” እንላለን።
ኢትዮጵያ ካንተ / ካንቺ ምን ትሻለች?
ኢትዮጵያ በራሷ ሚስጥር ናት። ይሄን ያልኩበት ምክንያት ተደጋጋሞ ቢገለፅም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ፍንትው ብሎ እየታየ ነው።
ኢትዮጵያ በራሷ የስበት ኃይል /Gravitational force / ያላት የቀለድባትን ፣ የእግዚአብሔር የተስፋው ምድር ስለሆነች “ከኢትዮጵያ በፊትና በላይ እኔን አምልኩኝ” ብሎ ለተወጣጠረ ማንም ይሁን ማን ወደላይ አጉና በአፍ ጢም የምትደፋ መገነጢሳዊ ኃይል ያላት ሃገር ናት።
ኢትዮጵያ እንደዘመኑ የአካል መመርመሪያ የሕክምና መሳሪያ ስካን /Scan/ የውጭና የውስጥ ሆድ ዕቃና አካል መርምራና ዐይታ ለሷ ባለህና በምትሰጣት ፍቅር ልክ አክማ የምታድን ውብ ሃገር ናት።
ተፃራሪዋ ከሆንክ ደግሞ አዋርዳና ዕርቃንህን አስቀርታ እንደተለከፈ ውሻ እያዛበረች ድምጥማጥህን የምታጠፋ ምትሃተኛ ሃገርና ምድር ናት።
ባለፉት አምሳ አመታት በውሸት፣ በሤራና አንድነቷን የተፈታተኗትን አይነኬ ነን ብለው ያሰቡ ባለሥልጣኖችና ሃገሮች እንዴት መቀመቅ እንደከተተች ስንመረምር አጃየብ የሚያሰኝ ነው።
በብሄር ከፋፍሎ ሊበጣጥሳት ያሰበውን ወያኔና መሪዎችን፣ ከዚህ በፊት በኮሚኒስት ፍልስፍና ያመሳትን የደርግ መንግስት እንዴት አወጣጥራ፣ ታግሳ ፣ በአባቶችና በብፁሃኖች አስመክራ “አሻፈረን” ሲሉ በተራ ሽፍታ እንዴት አዋርዳ እንዳሽቀነጠረችና አንገታቸውን እንዳስቀረቀረች ትዝብቱን ለአንባቢ እተወዋለሁ።
የደፈራትን ሶማሊያ ተስፋፊ ቡድን ፣ “የአፍሪካ ህብረት ከመናገሻው አዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሃገሬ ትሪፑሊ ተንቅሎ ካልገባ” ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ያለችውን ሊቢያና መሪዋን ጋዳፊን ፣ ከሕውሃት ጋር የዶለቱትን ሶሪያ ወ.ዘ.ተ. በአምላክ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ቁጣ ፣ በጠባቂወቿ መላእክት ሰይፍና ሃይል እንዴት እንዳይነሱ ሆነው እንደተመቱ አሁንም ልብ ያለው ልብ ይበል ጀሮ ያለው ይስማ ያሰኛል። ሰሞኑን ደግሞ ስሟን በክፉ ያነሷትን፣ የሸረቡባትን፣ ያመሷትን፣ በላይ ልብሷ ማደፍና ጊዚያዊ መጎሳቆሏን አይተው የተዛበቱባትን እንዴት እያተረማመሰች እንዳለች የአደባባይ ሚስጥር ነው።
ይህን ተንተርሶ ኢትዮጵያ የእውነት ምድር ናት። እውነት ደግሞ በውስጡ እምቅ የሆነ ትርጉም አለው። እውነት ቃል ነው፣ ቃል ሲባል ፣ አሱ አምላክ “የእውነት መንገድ” እኔ ነኝ ብሏል ። እውነት ፍቅርን ፣ አንድነትን ፣ መተሳሰብንና ሰላምን ትሰብካለች። እነዚህ ተዛማች ቁልፍ ሰንሰለቶች ካልተፃመሩና ከእውነት ጋር ካልትዋህዱ፣ እውነት በርሷ ለመቆም ይቸገራታል።
የምንናገራቸው፣ የምንፅፋቸው፣ የምናደርጋቸው፣ የምናረቃቸው ህጎች በሙሉ አንድነትን፣ሰላምን ፣ ፍቅርንና መተሳሰብን የሚያሳልጡና ከዕውነት ጋር የተጎዳኙ መሆን እንዳለባቸው የግድ ይሏል። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በራሷ የነበረች፣ያለችና ለወደፊቱ እንደ እግዚአብሄር ፍቃድ እውነት ሁና የምትኖር የእውነት ምልክት ናት።
ስለዚህ የማያዋጣውን ህሳቤና በሴራ የተተበተበ መፈክር ትተህ የእውነት ኢትዮጵያዊ ሁነህ ቅረባት፣ የምትሰጣትን እንጅ የምትሰጥህን ሃታስብ፣ ኢትዮጵያ ሽንገላ አትወድም፣ እውነትን ግን አጥብቃ ትወዳለች።
ኢትዮጵያን በመፈክር አዥጎድጉደህ የምታባብላት ሃገር አይደለችም ! ለምን ቢሉ? በታላቁ መፅሃፍ ቅዱስ ከአርባ ስምንት ጊዜ በላይ ፣ በቁራኑ ኪታብ የትየለሌ ጊዜ ተቀኝተውላታል ፣ በመዙማ ቅላፄ አሽሞንሙነው ገልፀዋታልና።
ማጠቃለያ
እንደሚታወቀው “ኢትዮጵያ ሱሴ” ነው የሚለው ትዕርክት አባይ በርሃ አቋርጦ ጣና ላይ ሲያስገመግም አንጀቱ ያልተንፈሰፈሰና ጮቤ ያረገጠ አልነበረም ። የአማራን ስስ ልብ ያማለለው ይህ ፅንሰ ሃሳብ ”ኦሮ-አማራ” የሚል ምእናባዊ መፈክር አጎናፅፎ ሕዝብን ከሕዝብ ጋር አስተቃቀፈ።
ይህ ፅንሰ ሃሳብ በውስጡ ያያዘው ተስፋ ፣ የመታረቅና የመወዳጀት ህሳቤ ለሁለቱ ወንድምማማች ህዝቦች የሚበጅ ነበር። ነገር ግን ውስጡ በመርዝ የተለወስ ስለነበረ የፅንሰ ሃሳቡን ተቀባይ የአማራ መሪዎችን በላች፣ ብዙ አምባ የሚሆኑ አምባዎችንና የትየለሌ አሳምነው ሊያሳምኑ የሚችሉ ትውልድ አሻጋሪዎችን በላች፣ ይበለጥ ሕዝብን አቃቃረች።
የሰሞነኛው “የኢትዮጵያ እትፈርስም” የራስን ወንበር ለማደላደል የተዜመች ነጠላ ዜማ መፈክር ለአያሌ ህዝቦች ደም መፍሰስ ምክንያት ሁና እንደጉም ተነነች። በማይሆን፣ ሊሆን በማይችልና ከዕውነታ በራቀ መፈክር ሃገርና ህዝብን አንሸግል።
አነሳስህ እንዲያምር አወዳደቅህም የከፋ እንዳይሆን ኢትዮጵያን በቅጡ አሳምረህ ያዛት፣ አትሸግላት።
ኢትዮጵያን አትስረቃት ፣ ከሰረቅካት ፣ መጨረሻ እርቃንህን ታስቀርሃለች፣ የአምላክ የተስፋ ሃገር ናትና። በችግሯ ጊዜ በጊዚያዊነት ድሃ ብትመስልህም ፣ ዕልቆ መሳፍርት የሌለው ሃብትና ፀጋ ያላት ምድር ናት። “ነግ ለኔ” ብለህ ተራመድ። በሌላ እንዲደርስ የሻትከውና የዘራህው ክፉ ሃሳብ ከበቀለ ለአንተም ይተርፍሃል።
“ሃገሬ ኢትዮጵያ ፣
ጋራሽ ሸንተረሩ
ልምላሜሽ ዕፁብ ነው
ነፋሻሽ አየሩ ።”
ተብሎ የተቀኘላት
በራሷ ምሉህ ፣ ሚስጥር የሆነች ሃገር ናት ፣ ጠንቀቅ አርገህ ያዛት ።
ከተዘራ አሰጉ
ከምድረ እንግሊዝ።