መጽሐፉን ተወው! እና ሰዉን አጥብቀህ ጠይቅ! (ሥልጣን እንዴት በስልት ይገኛል? አጠናኑ? አካሄዱስ?) – አሳፍ ሃይሉ

ብዙ የታሪክ ምሁራን ጥናትና ምርምራቸውን የሚጀምሩት ከወረቀት ነው፡፡ ከመጽሐፍ፡፡ ከታተሙ ምንጮች፡፡ ከሰነዶች ነው፡፡ ከቀጥተኛ ማስረጃዎች ያልተቀዱ የታሪክ ምርምሮች ተዓማኒነታቸው ያሽቆለቁላል፡፡ ምክንያቱ፡፡ ግልጽ መሰለኝ፡፡ ታሪክ ተረት ተረት አለመሆኑን ለማስረገጥ ነው፡፡

በእርግጥ አይታበልም አዎን፡፡ ታሪክ ሳይንስ ነው፡፡ የአጠናን ስልት አለው፡፡ ማስረጃዎች አሉት፡፡ ማስረጃዎችን የሚያነጥርበት የራሱ የተጠና መንገድ አለው፡፡ ታሪክ ተረት ተረት አይደለም፡፡ ወቸ ጉድ! እሺ ይሁን! ብለን ተቀበልን እሺ፡፡ ግን ታሪክ ፀሐፊዎች፡፡ በአንድ ትልቅ ነገር ተሸውደዋል፡፡

አብቹን ከሗላ ተመልከቱት:: ከፊት ያሉትን ከርብቶ ሁሉን ጠቅልሎ ይዟል::

የዓለም ሕዝብ ታሪክ የሚሠራውኮ መጽሐፎችን እያነበበ አይደለም፡፡ ወይም መጽሐፍን ስላነበበ አይደለም፡፡ በራሱ በሚያሳምነው እውነታ ነው የሚመራው የሰው ልጅ፡፡ ከራሱ የዕለት ኑሮ ነው የሚነሳው፡፡ በዙሪያው ካለው፣ ከጎጆው፣ ከማጀቱ፣ ከራሱ ፍላጎትና ኪሳራ፣ ወይም ከራሱ ዕምነትና እሳቤ ተነስቶ ነው – አንድን ነገር ለማድረግ የሚነሳሳው፡፡ ወይም የሚነሳው፡፡

እንጂ – የጎጃም ገበሬ በቀኃሥ ላይ ያመፀው – የማርክስና የኤንግልስን ወይ የሌኒንን የጭቁኖች አብዮት መጽሐፍ አንብቦ፣ ወይም ስላነበበ አይደለም፡፡ ሌት ተቀን በአለንጋው የሚጠብሰው የራሱ ኑሮ ነው ለአመጽ የሚያነሳሳው፣ እንጂ አንድ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ፈረንጅ መጽሐፍ ላይ ስለደቀደቀ ወይም ስለለፈለፈ አይደለም፡፡

አንድ የአሜሪካ የባርነት ታሪክ አጥኚ – የታሪክ ጸሐፊዎች የየሰዉን ጓዳና የእያንዳንዱን ሰው ሀሳብና ውጥን ሳይፈትሹ፣ እንዳስፈለጋቸው ከመጽሐፍና ከምሁራን ፖለቲከኞች ትንተና እየተነሱ፣ ታሪክን እንደ ልብ-ወለድ ባለ መልኩ፣ የራሳቸውን መጽሐፋዊ ምናብ ቀብተው የሚስሉት ነገር – በሳቅ ያፈርሰኛል ይላል፡፡

እና ምሳሌውን ለማስረዳት፣ የሰሜን አሜሪካ ሰፋሪዎች በወቅቱ ቅኝ ገዢያቸው በእንግሊዝ ሥር አንገዛም ብለው በሚያምጹበት ወቅት፣ በግብርና ይተዳደር የነበረና፣ በእንግሊዝ ላይ አምፆ የዋሺንግተንን ጦር የተቀላቀለን አንድ የአሜሪካ ገበሬ ከነዩኒፎርሙና ነፍጡ አቁሞ ይጠይቀዋል፡-

‹‹ለዚህ ለተነሳችሁለት የተቀደሰ የነፃነት ዓላማ እንድትሰለፍ ያነሳሳህ ነገር ምንድነው?››

ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ መልስ አላገኘም፡፡ ግራ መጋባት ብቻ፡፡ ከዚያ ሌላ ጥያቄ ያስከትልበታል፡-

‹‹የትግሉ መሪዎች የሰው ልጆችን ነጻነት የሚሰብኩ እንደ እነ ጆን ሎክ፣ እንደ እነ ሩሶ፣ እንደ እነ ቶማስ ፔይን፣ እንደ እነ ሙር፣ እንደ እነ… ያሉትን ታላላቅ የነጻነት ሃዋርያት ጽሑፍ ለነጻነት ትግላቸው እንዳነሳሳቸው ደጋግመው ይገልጻሉ፣ እና አንተንስ የእነዚህ ሰዎች ጽሑፎች አላነሳሱህም ለትግልህ?››

ሰውየው ጭራሽ ከበፊቱ ይበልጥ ግራ ተጋብቶ፣ ሰዋሰውን ባልጠበቀ ደንበኛ የገጠር እንግሊዝኛ ይመልስለታል፡-

‹‹ወንድሜ፣ ስለምን ወይም ስለማን እያወራህ እንደሆነ አላውቅም፣ ማንም አላነሳሳኝም፣ ማንበብና መጻፍም አልችልም፣ አንድ ነገር እፈልጋለሁ፣ የራሴ መሬት፣ የእንግሊዙ ንጉሥ ደሞ አይሰጠኝም፣ ጆርጅ ዋሺንግተን ግን እሰጥሃለሁ ብሎኛል፣ አምኜዋለሁ፣ ስለዚህ የምታየውን ጠብመንጃ አንግቤ እከተለዋለሁ፣ አለቀ፣ አከተመ፣ ሌላ አንተ ስለምትጠራቸው ሰዎች ሰምቼም አላውቅም፣ ለማወቅም አልፈልግም፣ ከእኔ የምታገኘው ይሄው ነው፣ እባክህ ሌሎችን ደግሞ ጠይቅ፣ ደክሞኛል ልረፍበት!››

ይህንን ጽሑፍ ስለ አሜሪካኖች የነጻነት አብዮት ‹‹ያልተነገሩ ታሪኮች›› በሚል ከታተመ መጽሐፍ ላይ ካነበብኩት ምናልባት ወደ ሶስት አሰርት ዓመታት ይሞሉታል፡፡ መጀመሪያ በሳቅ ነበር ያፈረሰኝ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ – አንድ ነገር በብዙ መጽሐፎች ላይ ስለሚገኝና ስለተጻፈ ብቻ – እውነቱ ያ እና ያ ብቻ ነው ብዬ ማመን እንደሌለብኝ ትምህርት ሰጠኝ፡፡ ሶስተኛ ደግሞ – አንድ ታሪክ ገንኖ ሲወጣ፣ እና መደበኛ ታሪክ ሲሆን፣ ሌሎች ያልተሰሙ፣ ጸሐይ ያልወጣላቸው፣ ተዳምጠው የቀሩ ታሪኮች ሊኖሩ እንደሚችሉም – ጥሩ ግንዛቤ ሰጠኝ፡፡

አራተኛና ዋናው ግን – ሁለተኛ ስለሆነ ሀገር ታሪክ ስጽፍ ወይም ሳስብ – የሀገሩን እውነታ ከምሁራን የመጽሐፍ ገጾች ጋር አቆራኝቼ የማሰብ ግዴታ እንደሌለብኝ ተገለጸልኝ፡፡ እና ብዙዎቹን ቲዎሪዎቼን በዚህ ዓይነት ዓይን-ገላጭ መጽሐፎች የተነሳ አሽቀንጥሬ ጣልኩ፡፡ ከቲዎሪዎች ተገላገልኩ፡፡ እና በቀጥታ ወደ ሰዉ፡፡ ወደ ጎጆ፡፡ ኳሷን ወደ መሬት፡፡ እንደ እኔ እምነት፣ ከመጽሐፍትም፣ ከሕዝብም፣ ከሁለቱም የተዛነቁ ታሪኮች ቢቀርቡልን – ለእውነታው ይቀርብ ነበር ባይ ነኝ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ክብሪት የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮት - (በያሬድ አይቼህ)

አሁን ይሄን ሁሉ ያስወራኝ ይህ እጅግ ታዋቂ መጽሐፍ ነው፡፡ መጽሐፉን የጻፈው የበርካታ ዶክትሬት ዲግሪዎች ባለቤት የሆነውና በሙያ መስኩ የታሪክ ተመራማሪ የሆነው ፕሮፌሰር ዊልያም አለን ነው፡፡ ይህ መጽሐፉ በ1965 ዓመተ ምህረት ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታተም – የዶክትሬት ዲግሪው ማሟያ የጥናት ጽሑፉ ነበር፡፡ ማለትም መጽሐፉ – የደራሲው – የዩኒቨርሲቲ ዶክቶራል ዲዘርቴሽኑ ነው፡፡

መጽሐፉ የጀርመንን አንዲት ከተማ ነዋሪዎች በማጥናት፣ የአዶልፍ ሒትለር ናዚ ፓርቲ፣ እንዴት ወደ ሥልጣን ሊወጣ እንደበቃ ይመረምራል፡፡ የሚመረምረው ግን መጻህፍትን እያጣቀሰ አይደለም፡፡ ከነዋሪው አፍ ቃለመጠይቆችን እያደረገ ነው፡፡ እንዴ?

ተመራማሪው እውነተኛ መልሶችን ከሚጠይቃቸው ሰዎች አንደበት እንደሚያገኝ እንዴት ገመተ? ማን የልቡን አምኖ ይነግረዋል? እየሰለላቸው ቢሆንስ? በኋላ ላይ የናዚ ደጋፊ ተብለው መከራ ቢወርድባቸውስ? ተስፋ-ቢስ ስለሆነ የተሸነፈና የተቀበረ ኃይል ማን ነው እውነቱን የሚመሰክረው?

አስበው፣ ዊልያም አለን ይሄን ምርምር ሲሠራ፣ ናዚ አፈር ድሜ ግጧል፡፡ ሂትለር አካሌን በአሲድ አቃጥላችሁ፣ በምሽጌ ጓሮ ቅበሩኝ ብሎ፣ ከተቀበረ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ከሂትለር አካል የተገኘው የመንገጭላው አጥንት ብቻ ነው፡፡ እርሱንም ይፋ ያደረጉት የሂትለር መንገጭላ በእጃቸው ያለው የራሺያ ኬጂቢዎች ነበሩ፡፡ ያውም ከስንት ዓመታት በኋላ፡፡

እና ሁሉም የናዚ ነገር አክትሞለታል፡፡ ናዚን ደግፈህ የሆነ ሃሳብ ከተናገርክ፣ በምዕራቡም በምስራቁም በርሊንን ሁለት ቦታ ተቀራምተው የሰፈሩት የኔቶና የዋርሶ ባለድሎች ዓይናቸውን ሳያሹ ቀንድህን ሰብረው ይጥሉሃል፡፡ እና እንዴት ነዋሪዎቹ ስለ ናዚ የሆድ-የሆዳቸውን ሊነግሩት ቻሉ?

አሳምኗቸው ነው፡፡ እንዴት አሳመናቸው? በጀርመንኛ! አቀላጥፎ በሚናገረው ጀርመንኛው፡፡ ጀርመኖችን ከመኮነንና እንደ አውሬ ከመቁጠር በተቆጠበ አስተያየቱ፡፡ ራሳቸውን በሚመስለው ቁመናና መልኩ፡፡ በዓይነ-ውሃው፡፡ እና በሰጣቸው ቃልኪዳን፡፡ በገባላቸው ቃል፡፡ አሳመናቸው፡፡ ጥናትና ምርምሩ ለዩኒቨርሲቲ ብቻ ምርምር የሚውል የዶክትሬት ጥናት ሆኖ ይቀራል፡፡

ይህ ሲባል፣ የተጠያቂዎቹ ማንነት ሙሉ በሙሉ በምስጢር ይያዛል፡፡ ሌላ ቀርቶ የከተማዋ ማንነት እንዳይታወቅ ‹‹ታልስበርግ›› በሚል የምስጢር ስም ይጠራል፡፡ የግለሰቦችን ማንነት የሚጠቁሙ ማናቸውም ልዩ ምልክቶችና ፕሮፋይሎች ጥብቅ-ምስጢር ተደርገው ይያዛሉ፡፡ ሰነዶች ላይ የሰፈሩ አሻራዎችና ስሞች ሁሉ ይፋቃሉ፡፡ ከእግዜር በቀር – እሱም በሁሉም ሥፍራ ስላለ ነው – ቃለመጠይቆቹንም ሆነ ጥናቱን – ከራሱ ከዊልያም አለን በቀር – ማንም አያይም፡፡

ሰዎቹ፡፡ ጀርመኖቹ፡፡ የዚህች በህቡዕ ስም ስሟ የተከተበች ከተማ ነዋሪዎች፡፡ ይህን ዕጩ-ዶክተር አመኑት፡፡ ደሞ በኢሊኖይስ፣ ሚችጋን፣ ሚኔሶታ፣ ኒውዮርክ፣ ወዘተ ባሉ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የቀላወጠ ብቻ አልነበረም፡፡ በበርሊን ዩኒቨርሲቲ፣ በሮቲንገን ዪኒቨርሲቲ፣ በራሳቸው የጀርመኖች ታሪክ ልቡ-ጠፍቶ ዕድሜውን የባጀ ብሩህ ተመራማሪ ነው፡፡ ቃሉን ሰጣቸው፡፡ አመኑት፡፡ እና ልባቸውን ሰጡት፡፡

ጥናቱ በመጨረሻ ተጠናቀቀ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በወረቀትና በመጻሕፍት ብቻ ለተለከፈው (ወይም ለቆረበው) የምዕራቡ ዓለም የታሪክ ጥናት መስክም፣ አዲስ ዓይነት ‹‹ኦራል ሂስትሪ›› (የቃል ታሪክ አጠናን) የሪሰርች ሜተዶሎጂ ያስተዋወቀ – ለምዕራቡ ዓለም የምርምር ተቋማት ‹‹ዓይን ገላጭ›› ምርምር ተባለ፡፡ ብዙዎችንም ጉድ አሰኘ፡፡ እስካሁንም ጉድ እንዳሰኘ ነው፡፡ በአሜሪካ የፖለቲካ ታሪክ አጥኚ ሆነህ፣ ይሄንን የዊልያም ሸሪዳን አለንን የናዚ የሥልጣን አረካከብን መጽሐፍ ሳታነብ ተመርቀህ አትወጣትም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የይቅርታ ፖሊቲካና የፍትሕ ነጻነት ወቅታዊ ችግራችን - ቁጥር 2 - ባይሳ ዋቅ-ወያ

ብዙዎች የሂትለርን አይዲዎሎጂ አጥንተዋል፡፡ ብዙዎች የሂትለርን የፖለቲካ አስተሳሰብ ምንጮች ተንትነዋል፡፡ ብዙዎች የናዚ ፓርቲን አመሠራረትና እንቅስቃሴ ታሪክ እስከ መቀበሪያው ድረስ ተከታትለው መጽሐፍ አሳትመዋል፡፡ ለናዚ የቀረቡ የፍልስፍና አስተምህሮቶችን፣ ደራሲዎችን፣ ምሁሮችን፣ ርዕዮተ ዓለሞችን ተንትነዋል፡፡ የጀርመንን የኢኮኖሚ ሁኔታ ዳስሰዋል፡፡

የውጪ ተጽዕኖዎችን፣ የማርክሲስቶችን ተጽዕኖ ከሩብ-ከተሙን እያሉ እንደ ወርቅ ሚዛን ላይ አስቀምጠው ለክተዋል፡፡ የአይሁዳውያን ጥላቻ (አንታይ ሴሜቲዝም) በጀርመን የተወለደው መቼ ነው፣ የተስፋፋውስ፣ የፋፋውስ፣ ምክንያቱ፣ አካሄዱ፣ እያሉም አጥንተዋል፡፡ ሁሉም በመጽሐፎች ገጾች ተሸክፈው ተቀምጠዋል፡፡

ይሄ ጉጉ ተመራማሪ ዊልያም አለን ግን – ድንገት ሁሉንም መጽሐፎችና ሀገራዊ ትንታኔዎች እርግፍ አድርጎ ጣለና – ወደ ሰዉ ጓዳ ዘልቆ ገባ፡፡ ከመጽሐፍ ገጾች ሳይሆን፣ ከራሱ እውነታ እየተነሳ አውቆትም ይሁን ሳያውቅ የአዶልፍ ሂትለር ደጋፊ የሆነውን ህዝብ ለመጠየቅ ዝቅ ብሎ ወደግለሰቦች ማጀት ገባ፡፡

ብዙዎቹ እንደሚነግሩት – እና በዚህ መጽሐፍ እንደምናገኘው – ብዙዎቹ – ሬዲዮ ከመስማት፣ ወይ ጋዜጣ ከማንበብ – ወይ አፍ የሚያስከፍቱ፣ እሳት ከትናጋቸው የሚተፉ፣ የፖለቲካ ተናጋሪዎችን ስብከት ከመስማት ውጭ – ለናዚነት ያበቃቸውን መጽሐፍ ያነበቡ አይደሉም፡፡ ዓለም ናዚነትነትን ከሄግል መጽሐፎች፣ ከሂደልበርግ መጽሐፎች፣ ከኒች መጽሐፎች፣ ወዘተ ሊመዝዝ ይውተረተራል፡፡ ናዚነት ግን – ከመጽሐፍ አልተቀዳም፡፡

የናዚነት ምንጩ – የዕለት ተዕለት ኑሮ ነው፡፡ ናዚነት የተቀዳው ከትልቅ የርዕዮተ ዓለም ሀይቅ አይደለም፡፡ ከተራ የዕለት ተዕለት ፍትጊያዎችና ከኑሮ ብሶቶች ውስጥ፣ ከትንንሽ ስም-የለሽ የሰፈር ልቦች ውስጥ ተፈልቅቆ የወጣ፣ የቁጣና የፀብ መንገድ ነው፡፡ ናዚዝምን የፈጠሩት ትናንሽ የየመንደሩ የብሶትና የጥላቻ ኩሬዎች ናቸው፡፡ ናዚዝም የተስፋፋው በቃል ነው፡፡ በዓይን ነው፡፡ በከዘራና በምላስ ነው፡፡

እገሌና እገሊትን እያለ፡፡ ኦቶ እከሌና ኦቶ እከሌ እያለ፡፡ ቀስ በቀስ፡፡ የያንዳንዱን ነዋሪ በር አንኳኳ፡፡ መጀመሪያ የቀበሌውን፡፡ የየወረዳውን ከአስሩ ሶስቱን ድምጽ፡፡ ቀጥሎ ከአስሩ ሰባቱን ድምጽ፡፡ በመጨረሻም ከአስሩ አስሩንም የምርጫ ድምጽ፡፡ ጠቀለለ፡፡ እና በመጨረሻ ይህ ከያካባቢው የተጠረቃቀመ የየወረዳው ኩሬ ውሃ ተጠረቃቅሞ – ሀገርን – ጀርመንን – ድብን ባለ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ – ሙሉ በሙሉ ጠቀለለ፡፡ የናዚ Seizure of Power ታሪኩ ይኸው ነው፡፡

በኋላ ይህ ጥናትና ምርምር ብዙ አድናቂዎችን አፈራ፡፡ ብዙዎች Oral Historyን ለማጥናት ከአውሮፓና አሜሪካ ወደየሀገሩ ፈለሱ፡፡ የአሜሪካን መንግሥት የውጭ ፖሊሲ ፔዳጎጂ የሚያማክረው የሃርቫርድ የታላላቅ ምሁራን ጉባዔ – በዚያው ዊልያም አለን ይህን መጽሐፍ ባሳተመበት – በ1965 (በጎርጎሮሳውያን አቆጣጠር) የየሀገሩን እውነታ ለማወቅ – የካልቸራል ዳይቨርሲቲና የኦራል ሂስትሪ ዓለማቀፍ ምርምር እንዲደረግ አሳሰበ፡፡ ፖሊሲ ሆነ፡፡ በየዩኒቨርሲቲዎችም ተተገበረ፡፡

በመጨረሻ የዚህች የናዚዎች መፈልፈያ ከተማ ስም ተደረሰበት፡፡ በድብቅ ስም ‹‹ታልስበርግ›› ይባል እንጂ እውነተኛ ስሙ – ‹‹ኖርዛይመር›› – ነው፡፡ ኖርዛይመር – በጀርመን የሳክሶኒ ግዛት ፈንጠር ብላ የምትገኝ አንዲት አነስተኛ ከተማ ነች፡፡ በገቢዋ አስተማማኝ፡፡ ሰዎች ከብዙዎቹ የጀርመን ግዛቶች በላይ ጥሩ ገቢ እያገኙ፣ የተረጋጋ ሠላማዊ ኑሮ የሚኖሩባት ከተማ ነበረች፡፡ ግን የጀርመን ኢኮኖሚ እያዘመመ ሲሄድ፣ ኖርዛይመርም ትኩሳቱ ደረሳት፡፡

ናዚዎች ገና እግራቸውን ወደ ኖርዛይመር ከተማ ሲተክሉ የመረጡት – በእውቀቱ የታፈረ፣ በሙያው የተከበረ፣ በጭምትነቱ ሁሉም ያወቀው – አንድ ሰውን ነበር፡፡ እርሱ ሁለት ጓደኞችን አፈራ፡፡ ሶስት ሆኑ፡፡ ሶስቱ ጥቂት ሰዎችን አፈሩ፡፡ እያለ እያለ – በሰው ትውውቅ አንዱ ሌላውን እየጋበዘ፣ የየራሳቸውን ሳምንታዊ የጥናትና የድራፍት ግሩፕ መሰረቱ፡፡ ከዚያ በትምህርት ቤቶችና በኮሌጅ ወጣቶች ላይ አተኩረው – በአንዳንድ በዓላት ላይ ሃሳቦቻቸውን ማስተላለፍ ጀመሩ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ግን ለምን ?  - አረጉ ባለህ ወንድሙነህ

የኖርዛይመር አብዮተኞች እንደ ሰጎን ጭንቅላታቸውን አሸዋ ውስጥ ቀብረው በእርጋታ ሥራቸውን ሲወጥኑ፣ ሂትለር ደሞ አሉ የተባሉ አፈኞችን መርጦ፣ ሰው በየተሰበሰበበት በማሰማራት፣ እና የአባላት የብር መዋጮ በየምሽት ድራፍት ቤቶች በመሰብሰብ፣ በባቫሪያ ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች በልጦ፣ በህዝቡ ለመሰማት፣ በአፉ፣ በምላሱ፣ በጭንቅላቱ፣ በሁለነገሩ እየተሟሟተ ነበር፡፡

በጣም የሚያስቀው የኖርዛይመር ናዚዎች ከሂትለር ናዚዎች ጋር ግንኙነት መስርተው፣ ለሰዉ ዓላማቸውን የሚሰብክ ‹‹ኃይለኛ ተናጋሪ ሰው›› ለአንድ ስብሰባ ዕድሜ ይላክልን ብለው ሲጠይቁ፣ የንግግር አበል፣ ማደሪያ፣ ቀለቡን፣ ወዘተ ወጪዎች የመቻል ግዴታቸውን የሚወጡት ራሳቸው ነበሩ፡፡ ያ ሳንቲም ደግሞ በቀላሉ አይገኝም፡፡

ያንን ሳንቲም በመዋጮ ለማግኘት ሲሉ – ተማሪዎችን ተወት አድርገው፣ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን፣ ደሞዝተኞችን፣ ሠራተኞችን ወዘተ ዒላማ ማድረግ ጀመሩ፡፡ ጨላ ሲጠረቃቀምላቸው – ሰባኪ (የናዚ ወንጌላዊ!) ይላክልን ብለው መልዕክት ይሰዳሉ፡፡ አሪፍ፣ የሰዉን ቀልብ የሚስብ ርዕስ መርጠው፡፡ ይላክላቸዋል፡፡ አዳዲስ ነፍሳትን ይማርክላቸዋል፡፡

አንዳንዴ – እነዚህ ናዚዎች ጴንጤዎችን ሁሉ ይመስሉኛል፡፡ ሲስተማቸው ማለቴ ነው፡፡ የሚገርመኝ፣ ሀይለኛ የባላንጣ ፓርቲ ተናጋሪ ሲመጣባቸው፣ በጥቅምም በጉልበትም አባብለው፣ ወደራሳቸው የማምጣት ሁሉ ልማድ ነበራቸው!!

ይህን ስል ብዙ ነገሮች ተግተልትለው መጡብኝ፡፡ እና የመጽሐፍ ትርክቴን አናጠቡኝ፡፡ ሳልናገራቸው ያለማለፍ ችግር አለብኝና ተናግሬ ጨዋታችንን ላብቃ፡፡ ቀጣዩንና ዋናውን ናዚነትን ወደ ሥልጣን ያመጣው ስልት (ወይም ስልቶች) ምንድን ነበሩ? የሚለውን በክፍል ሁለት እመለስበታለሁ፡፡

እና ጴንጤዎች ነበሩ ትዝ አሉኝ ያልኩት? (ፕሮቴስታንቶች ማለቴ ነው – ለአጠራሩ ከይቅርታ ጋር!)፡፡ የዚያኔ የጀርመን NSDAPዎች የሚጠቀሙት፣ ልክ የእኛ ሀገሮቹ ጴንጤዎች የሚጠቀሙትን ዓይነት ሲስተም ነው፡፡ የታወቁ ሰዎችን ወደራሳቸው ያዞሩና፣ ብዙ መነጋገሪያ ይፈጥራሉ፡፡ በብዙዎች አዕምሮ ይወሳሉ፡፡ ብዙ ተከታይም ያተርፋሉ፡፡

ጴንጤዎች ለምሳሌ የታወቁ የኢትዮጵያ ዘፋኞችን – ለምሳሌ – ሙሉቀን መለሰን፣ ወይ ሒሩት በቀለን ወደራሳቸው እንደሚማርኩት ማለት ነው፡፡ ወይ ዘማሪት ዘርፌን ወደ ጴንጤነት ቀይረው – ብዙ ነፍሶችን ትማርክላቸዋለች፣ የሰው ጆሮ ትገባለች፡፡ ከሐይማኖት ጋር ግንኙነት ስላለው አይደለም፡፡ እነዚህን መንፈሳውያን ተወዳጆች ከናዚ ጋር እያነጻጸርኩም አይደለም፡፡ ሲስተሙን – መንገዱን በራሳችን ምሳሌ አቅልሎ ለማሳየት ነው፡፡

ወደ መጽሐፉ አልመለስም ብያለሁ አሁን፡፡ ሌሎች ሁለት ምሳሌዎች ደግሞ ትዝ አሉኝ፡፡ ለምሳሌ – በንግግሩ ኃይለኝነት የታወቀ የስልጤ ተቃዋሚ የነበረውንና፣ ኢህአዴግ በምኑም በምኑም አማልሎ የራሱ ቱባ ካድሬ ያደረገውን የእኛውን አቶ ሬድዋን ከማልን አስበው!

ወይ ከቅንጅት መሪነት ራሱን ወደ አፍቃሪ-ኢህአዴግ ተቃዋሚነት ተርታ ያፈገፈገውን እንደ አቶ ልደቱ አያሌው፣ የመሳሰለውን አንደበተ-ርቱዕ ፖለቲከኛ ተመልከተው፡፡ ብቃታቸው የሚገርም ነው፡፡ ዝውውራቸው የሚገርም ነው፡፡

በቃ የጥንቶቹ – ዊልያም ሸሪዳን አለን የመረመራቸው የኖርዛይመር ናዚዎች – ያደርጉ የነበሩት ልክ እንደዚህ ነበር፡፡ የሰው ዓይን የሚገቡ፣ የሰው ጆሮ የሚያስከፍቱ፣ የሰው አፍ የሚያረጥቡ ደመ-ግቡ እና ዓይነ-ግቡ ተናጋሪዎችን ይመርጣሉ፡፡ ወደራሳቸው ይመለምላሉ፡፡ እና ብዙ ወጣቶችን በሃሳብ ወደራሳቸው ለመማረክ ይጠቀሙባቸዋል!

የሚያዘዋውረኝ፣ ወይ የሚመለምለኝ አገኝ ይሆን? (በነጻ ዝውውር! ስለ እግዜር፣ አትለፉኝ – ማለት አማረኝ!)

ትርክቴን ለመጨረስ ከሰሞኑ እመለሳለሁ፡፡

ለዛሬ አበቃሁ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share