በገባለት ቃሉ – አባትህ ለእኛ አባት፤
አንተ ለኛ ሞተህ – ልንድን ከሃጢያት፤
እኛን አድናለሁ – ብለህ ከመከራ፤
መስቀል ተሸክመህ – አትውጣ ተራራ::
በጨካኞች ጅራፍ – አይገረፍ ጀርባህ፤
ምስማር አይቸንከር – በጅና በግሮችህ፤
በጦር አይወጋ – አይበሳ ጎንህ፤
አትጠጣ ፍጹም – የሃሞት መራራ፤
አድናለሁ ብለህ – እኛን ከመከራ፤
መከራህ አይብዛ – መከራችን ላይቀር፤
ተንገላተህ አትሙት – አትሰቀል! ይቅር::
ተከባብሮ መኖር – አብሮ መብላት ቀርቶ፤
ጥላቻ፤ ጭካኔ – መከራ በርክቶ፤
ወንድማማችነት – ፍቅር መተባበር፤
አንድነት፤ ነፃነት – ፍጹም ጠፍተው ካገር፤
መቻቻል፤ ደግነት- ከሃገር ተሰደው፤
ግፍ በደል በርክቶ – ሞልቶ ፈሶ ጽዋው፤
ሰው ሆነን ሰው ካልሆን – ተፈጥረን ባምሳልህ፤
ከሰማየ ሰማይ – ወርደህ ከዙፋንህ፤
አፈር ለባሽ ገላ – ከንቱ ሥጋ ለብሰህ፤
አትሰቀል በቃ! – እኛን ላድን ብለህ ::
ይልቅስ ከሰሙህ_ እንዲህ ምከራቸው………!
እንደዚህ በላቸው_ ስልጣን ላዋስካቸው…. !
ስልጣን ተገን አርጎ – ቀምቶ የበላ፤
ለሥጋው አድልቶ – ወገኑን ያጉላላ፤
ዘረኝነት አርሶ – ቂም በቀል የዘራ፤
የሚያበዛ ትዕቢት – ሰው የሚያስፈራራ፤
ውሸት ያመረተ – በደል የከመረ፤
በግፍ የገደለ – ወህኒ ቤት ያጎረ፤
ጥላቻን አንግሶ – ፍቅርን ያኮሰሰ፤
ወንድሙን የገፋ – በደል ያነገሰ፤
ቁጣዬን አብዝቶ – መከራውን ያጭዳል፤
ሕዝቤን አታጉላሉ – ከንግዲህ ይበቃል !
ብለህ ንገራቸው………!
ስልጣን ላዋስካቸው……… !
ልቦና ቢገዙ_ ድንገት ቢመለሱ_ ወደ ሕሊናቸው ::
ግን !
የሕዝብህን ጩኸት – እየሰማ ጆሮህ፤
ስቃይ መከራውን – እያየኸው ባ’ይንህ
ሲካድ ሰብዕናው – ፈጥረኸው ባምሳልህ፤
ዝምታህ ከበዛ – ከዘገየ ፍርድህ፤
ኤሎሄ ! ኤሎሄ ! ላማ ሰበቅታኒ – ላ’ባትህ ልናገር፤
ቁም ስቅልህ ይብቃ!_ እኛ አልዳንምና – አትሰቀል ይቅር!!
ተጠየቅ ልጠየቅ !
( አሥራደው ከፈረንሳይ )
« በአገር በሃይማኖት፤ በሚስት የለም ዋዛ !
በአሞሌ አይለወጥ፤ በአራጣ አይገዛ !! »
ብሎ የዘመተው ፤
በአድዋ በማይጨው ፤
ለአገር ለነፃነት ሕይወቱን የሰዋው ፤
ለኛ ሲል የሞተው ፤
ድንበር ያስከበረ – ባጥንቱ ቸንክሮ ፤
ባ’ንድነት ያሰረ – በጅማቱ አክርሮ ፤
ቆዳው ተፈቅፍቆ – ብራና ተሌጦ ፤
ታሪኩ የተጣፈ – በደም ተበጥብጦ ፤
ሰንደቅ የሰቀለው – ባጥንቱ ሰክቶ፤
በሥጋ ወ ደሙ – በቃል ኪዳን ጠንቶ ፤
ለሰጠን አደራ – ለቃል ኪዳናችን ፤
ዛሬ ቢጠይቀን፤
ምንድነው መልሳችን ?!
በአሞሌ ለሸጥነው – ለነፃነታችን ፤
ለተቸበቸበው – ለባዕድ መሬታችን ፤
ለተሸራረፈው – ያገር ድንበራችን ፤
ለተሸረሸረው – ጥኑው ዕምነታቸን ፤
ለ’ኛ ሲል የሞተው ፤
በአድዋ በማይጨው ፤
ዛሬ ቢጠይቀን ፤
ምንድነው መልሳችን ?!
ለቃል ኪዳናችን – መፍረስ ወይ መጠበቅ ፤
መልሳችን ምንድነው ?_ ተጠየቅ ልጠየቅ ?!
ቢጠይቅ ታሪኩን ፤
ቢያነሳ አደራውን ፤
በደም የተጣፈ – ያ’ባት ኑዛዜውን ፤
ምንድነው መልሳችን ?!
ለሰጡን አደራ – ማረጋገጫችን ፤
ለ’ኛነት መግለጫ – የ’ኛነት ቃላችን ?!
ለቃል ኪዳናችን – መፍረስ ወይ መጠበቅ ፤
መልሳችን ምንድነው ?_ ተጠየቅ ልጠየቅ ?!