April 22, 2022
4 mins read

በአርባ ምንጭ የባልደራስ አመራሮች እገታን በተመለከተ የፓርቲው ድርጅታዊ መግለጫ

bALDERAS Hባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲን አገር አቀፍ የማድረግ ራዕይ ሰንቆ በትላንትናው ቀን ሚያዚያ 12/2014 ዓ.ም. አርባ ምንጭ ከተማ የገባው የባልደራስ የልዑካን ቡድን 1ኛ. አቶ እስክንድር ነጋ የፓርቲው ፕሬዘደንት፣ 2ኛ. አቶ ስንታየሁ ቸኮል የፓርቲው የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ፣ 3. ጋዜጠኞቹ ጌጥዬ ያለው እና ወግደረስ ጤናው 4ኛ. የካሜራ ባለሙያ አቶ ሱራፌል አንዳርጌ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው እቅድ፣ ባልደራስን አገራዊ ፓርቲ ለማድረግ የሚጀመረውን የፊርማ ማሰባሰብ ንቅናቄ በአርባምንጭ እና በወላይታ ሶዶ ከተማ ለማስጀመር የነበረ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት ለሁለቱ ከተሞች አስተዳደሮች ጥያቄ ቀርቦ ከተፈቀደ በኋላ፣ “ከበላይ በመጣ ትዕዛዝ ” እንዲሻር ተደርጓል፡፡
ሆኖም፣ ህዝባዊ የአዳራሽ ስብሰባ ተከለከለ ማለት፣ የፊርማ ማሰባሰቡ ተከለከለ ማለት ስላልሆነ፣ የፓርቲው ልዑክ ቡድን ሚያዚያ 12/2014 ዓ.ም ወደ አርባ ምንጭ ተጉዞ፣ አገራዊውን የፊርማ ማሰባሰብ ሂደት በአርባምንጭ ከተማ አስጀምሯል፡፡ በዚህም መሠረት፣ የልዑካን ቡድኑ በከተማው ካሉ የድርጅቱ ደጋፊዎች ጋር በመሆን ከአዳራሽ ውጭ ፊርማ የማሰባሰብ ሥራውን አከናውኗል፡፡ አመሻሽ ላይ ግን፣ ፖሊስ የልዑካን ቡድኑ አባላት ያረፉበት ሆቴል ድረስ በመሄድ በቁጥጥር ስር አውሏቸው ወደ ሴቻ ፖሊስ ጣቢያ ወስዶ አስሯቸዋል፡፡ የልዑካን ቡድኑ ታስረው ያደሩበት ጣቢያ የመኝታ ቦታ የሌለው በመሆኑ፣ በከፊል ያለ ፍራሽ መሬት ላይ፣ በከፊል ደግሞ ቁጭ ብለው ለማደር ተገደዋል፡፡
በነጋታው የሴቻ ፖሊስ ጣቢያ የታጋቾቹን ቃል በመቀበል ላይ እያለ፣ ከበላይ ስልክ ተደውሎ ቃል የመቀበል ሂደቱ እንዲቆም ከተደረገ በኋላ ወደ ጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ እንዲወሰዱ ተደርጓል፡፡ ከዚያም በፖሊስ አጀብ ወደ አርባ ምንጭ አውሮፕላን ማረፊያ ተሸኝተው ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ተደርገዋል፡፡
በኦሮሞ ብልጽግና የሚመራው ይህ አፈና፣ አገራችን ምንም ዓይነት እውነተኛ የፖለቲካ አማራጭ ኃይል እንዳኖራት ለማድረግ ታቅዶ እንደሆነ ፓርቲያችን ይረዳል፡፡ ከትላንት አሳሪዎች ውድቀት ያልተማረው ተረኛው የኦሮሞ ብልጽግና መንግሥት በሚወስደው አፋኝ እርምጃ ፓርቲያችን ሳይሸማቀቅ፣ የጀመረውን አገር አቀፍ የማድረግ እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም የአገሪቱ ክልሎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማስገንዘብ እንወዳለን፡፡ የኦሮሞ ብልጽግና መራሹ መንግሥት የሚፈፀመው አፈና ፓርቲያችን የተነሳንለትን ዓላማ ከማራመድ የማያስቀረው መሆኑን ተገንዝቦ፣ የሚፈጽመውን ሕገ-ወጥ ተግባር እንዲያቆም እንጠይቃለን፡፡
ትግሉ ተጠናክሮ ይቀጥላል!
ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ
ሚያዚያ 13 ቀን 2014 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop