ለሶስት ሽህ ዘመን የተዘመረላት፤
ጀግኖቹ ልጆቿ ከጥንት የሞቱላት፤
ድርሳነ ቅዱሳን ስሟን ያወደሷት፤
የሰው ነጭ ከጥቁር የተፈጠረባት፤
እስላም ክርስትያኑ ተፋቅሮ ያለባት፤
በአድዋ ገድሏ ዓለም የቀናባት፤
የአሜሬካ ቁጣ ሁሌ እሚዘንብባት፤
የድሃ ጉልበቷን እጅግ የሚፈሩት፤
በተንኮል ዱላቸው የሚቀጠቅጧት፤
የሰማዩ ጌታ ሁሌ እሚጠብቃት፤
የፅናት ምሳሌ የአፍሪካ ኩራት ፤
ቀስተደመና ነች ኢትዮጵያን አትንኳት።
እወቁት-ብዙ ሲቀጠቀጥ ምስማርም ይጠብቃል፤
ጠላት ሲበዛበት ኢትዮጵያዊ ፅናት እያደር ይፈካል፤
ልማደኛው ክንዷም ሃያልን ያስፈራል፤
ማመን ካቀታቸው አድዋዊ ፅናት ብዙ ይናገራል።
ያንኪው አሜርካ በእጅጉ ጠግቧል፤
ጉልበትና ትዕቢት ጀግንነት መስሎታል፤
ሃይል የፈጣሪ መሆኑን እረስቷል።
ተረስቶት ከሆነ እኛው እናውራለት፤
ሶማሊያ ዘምቶ ሲጎተት እራቁት፤
አፍጋሃን ገብቶ ሲወጣ በውርድት፤
ይሄ ሁሉ ሃፍረት አልሆንካለው ትምህርት፤
ይግባ ኢትይጵያ ይንቦራጨቅበት፤
መቸም አይሰለቸው መከናነብ ውርደት።
እንኳን በዚህ ዘመን እያለን አየር ሃይል፤
ጥንትም በቀስታችን እጆቹን ሰጦናል፤
በጎራዲአችንም ትጥቅ አስፈትተናል፤
የሐባሻን ጀብዱ ክንዳችን ያውቀዋል።
ሃብሻ ፅኑ ነው ውጣ ውረድ ያውቃል፤
በድርቆሽ ጉልበቱ ሽህ ማይል ይጓዛል፤
በፈረስ ባሕያ ጣሊያንን ረቷል፤
የጤፍ ጉልበታችን ማክዶናልድ እረቷል፤
ብቂላ ያለጫማ ነጩን አሸንፏል፤
ቆርጦ ለተነሳ እምነት ከወኔ ጋር ሚሳይል ያከሽፋል።
ሃያሉ አሜሪካ ሕገ-አራዊት ሆኗል፤
ሃይል የፈጣሪ መሆኑን እረስቷል፤
መዓቀብ በመጣል አገር ያሸብራል፤
ድሃን እያስራበ ስገዱልኝ ይላል፤
መዓቀብ በመጣል ሚረታ መስሎታል::
አይጉድ አማሪካ እጅጉን ተኩራርቷል፤
የትእቢት ሙቀቱ ገንፍሎበት ታይቷል፤
ይሄው እራሽያ የጥጋብ ፊኛውን አስተንፍሶለታል፤
ቻይና ከታከለች ውድቀቱ ይፈጥናል፤
ኢትዮጵያም በነርሱ ሰላሟ ይሰፍናል።
በባንዳና እፉኝት ብዙ ተነክሳለች፤
በባዕድ ጠላቶች ብዙ ተጠቅታለች፤
ይህም ሁሉ ሆኖ በአይበገሬነት በፅናት ቆማለች፤
ጥላቷን በቋንቋው ድባቅ እየመታች፤
በእግዚአብሔር ቸርነት እየተጠበቀች፤
በአድዋ ጀግኖች በክብር ኖራለች።
ጠፋች ሲሏት ፈክታ አለች እስከዛሬ እየተዘከረች፤
ወደፊትም ትኑር እንደ አዲስ አበባ ሁሌም እያበበች፤
ትኑር ኢትዮጵያዬ-በአዲሱ ትውልድ እየተሞገሰች፤
በዓድዋዊ ፅናት ቆማ ትኖራለች፤
የጥቁር ሰው ኩራት አድዋ ሕያው ነች።
ሰማነህ ታምራት ጀመረ April 2, 2022, Ottawa Canada