መስፍን ወልደማርያም
መጋቢት 2005
በቀልድ ልጀምር፤ አንድ ጮሌ የአስመራ ልጅ የእኔ ተማሪ ነበር፤ አንድ ጊዜ የጂኦግራፊ ክፍል ተማሪዎች አንድ ጃፓናዊ አስተማሪ ለመሸኘት ግብዣ አድርገው ነበር፤ በግብዣው ላይ የጠቀስሁት ነገረኛ የአስመራ ልጅ (የአስመራ ልጅ የምለው ላርቀው ፈልጌ እንዳይመስላችሁ፤) በአስተማሪዎች ላይ ቀልድ ያሰማ ነበረ፤ ስለኔ ሲናገር፤– መስፍን ወልደ ማርያም የቢሮውን በር ሁልጊዜ ክፍት አድርጎ የሚቀመጠው ለምንድን ነው? ይልና እሱው ሲመልስ፣ በሩን የመዝጋት ሌሎች ዘዴዎች ስላሉ ነዋ! ቀልዱ ለእኔ እንደገባኝ ፊቱን ስለሚያኮሳትር ሰዎች በሩን አልፈው እንዲገቡ አይጋብዝም ማለት ነው፤ በዚያን ጊዜ እኔም እየሳቅሁ እንደተናገርሁት የሱን ፈሪነት በእኔ መልከ-ክፉነት መደበቁ ነው፤ ቀልዱን ያመጣሁበት ምክንያት ወያኔ ለነጻነት የቆመ መስሎ ለመታየት ሳንሱር የሚባለውን የሚታተሙ ጽሑፎችን በቅድሚያ የማስፈተሽ ቀንበር በሕግ አነሣ፤ ሰዎች እውነት መስሎአቸው ቅሪታቸውን እያነጠፉ ጋዜጦችና መጽሔቶችን ማሳተም ጀመሩ፤ ጋዜጦች እንደአሸን ፈሉ፤ መጻሕፍት ታተሙ፤ ጥቂት ቲያትሮችም ታዩ፤ ዘፈኖች ተመረቱ! ነገር ግን የግል ራድዮና ቴሌቪዥን እንዲሁ የብዙ ሰዎች ሕልም ሆኖ ቀረ፤ ብዙ ሰዎች ብዙ ገንዘብ ከሰሩ፡፡
በሕዝቡ ዘንድ የነጻነት ፍቅር እየለመለመ መሄዱን ሲያየው ወያኔ ሆዱ ተንቦጨቦጨ፤ እንቅልፍ እያጣ ሄደ፤ ቀስ በቀስ ግራ እጁን በሕገ መንግሥቱ ላይ ጭኖ በቀኝ እጁ ጎራዴውን መዘዘ፤ ቀስ በቀስ፣ አንድ በአንድ የተለያዩ መብቶችን ለማስከበር የቆሙትን አንቀጾች ሁሉ አስተኛቸው፤ በተገላቢጦሽ መብቶቻቸውን የሚጠይቁ ሰዎችን፣ ስለመብቶች የሚጽፉ ሰዎችን፣ መብቶችን ከጥቃት ለመከላለከል የቆሙ ድርጅቶችን፣ ከወያኔ አመለካከት ውጭ የሆኑ ሰዎችን ሁሉ መንግሥት በመገልበጥ ሴራ፣ ወይም በሽብርተኛነት እየያዘና እያሰረ በመክሰስና በማስፈረድ የማፈን እርምጃዎችን ሁሉ አጠናከረ፤ አንዲህ ያለውን አፈና ማየትና መስማት እየተለመደ መጣ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በሽብር ስም የሚካሄደው ጥቃትና የሰብአዊ መብቶች ረገጣ እንኳን እኛንና በሽብር ላይ ዓለም-አቀፍ ጦርነት ያወጁትን አሜሪካኖችንም እያስደነገጠ ነው፤ የዓለም የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ሁሉ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ በምሬት እየጮሁ ነው፤ ጋዜጠኞች፣ የሠራተኞች ማኅበሮች፣ የፖሊቲካ ቡድኖች ጭጭ እንዲሉና ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ መንገዱ ሁሉ እየተዘጋባቸው ነው፤ በትግራይ አብርሃ ደስታ የሚባል ወጣት የአፈናውን ድቅድቅ ጨለማ ጥሶ በመውጣት ስለጻፈ አፈናና ማስፈራራት ደረሰበት፤ ‹‹ጭቆናን ስላጋለጥሁ የሕዝብ ጠላት ተባልሁ›› ይላል፤ በቅርቡ እንኳን ሰማያዊ ፓርቲ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የጠራው የራት ግብዣ እንግዶቹ በተጠሩበት ሰዓት ተሰርዞ ተመልሰዋል፤ ለግራዚያኒ ስለሚሠራው ሐውልት የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ የሞከሩ ኢትዮጵያውያን ታሰሩ፤ እነዚህን ኢትዮጵያውያንን ያሰሩትን ምን እንላቸዋለን? እንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ምን የማያሳስር ነገር ሊኖር ይችላል?
የአፈናውን ነገር እነእስክንድር ነጋ፣ እነርእዮት ዓለሙ፣ ውብሸት ታየ … ይመሰክራሉ፤ ለመሆኑ ወደዘጠና ሚልዮን የሚሆን ሕዝብ ያላት አገር ስንት ጋዜጣ፣ ስንት የራድዮ ጣቢያ፣ ስንት የቴሌቪዥን ጣቢያ አላት? ኤርትራ ሦስት የራድዮ ጣቢያዎችና ስድስት ጋዜጦች፣ ጂቡቲ ሦስት የራድዮ ጣቢያዎችና አምስት ጋዜጦች፣ ኬንያ አሥራ ስምንት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ ከሠላሳ በላይ የራድዮ ጣቢያዎች፣ ዘጠኝ ጋዜጦች አሉት፤ ትናንት የተፈጠረው ደቡብ ሱዳን እንኳን ሁለት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች፣ አምስት የራድዮ ጣቢያዎች፣ አምስት ጋዜጦች አሉት፤ ኢትዮጵያ ያላትን እናውቃለን፡፡
ሰንጠረጅ አንድ
የኪስ ስልክ (ሞባይል) እድገት
እ.አ.አ. | 2008 | 2009 | 2010 | 2011 |
አገሮች | ሞባይል ለ100 ሰዎች | |||
በደቡብአፍ |
91 |
93 |
100 |
127 |
ኢትዮጵያ |
2 |
5 |
8 |
17 |
ኬንያ |
42 |
49 |
62 |
65 |
ሱዳን |
29 |
36 |
42 |
56 |
ኤርትራ |
2 |
3 |
4 |
4 |
ሶማልያ |
7 |
7 |
7 |
7 |
ጂቡቲ |
13 |
15 |
19 |
21 |
ምንጭ፡- የዓለም ባንክና የዓለም ቴሌኮሚዩኒኬሽን ድርጅት
የአፈናውን ልክ በሁለቱ ሰንጠረጆች ማየት ይቻላል፤ ለንጽጽር የቀረቡት አገሮች የአፍሪካ ቀንድ ጎረቤቶች ናቸው፤ ነገር ግን ላቅ ያለ ግብ ለማመልከት ደቡብ አፍሪካ ተጨምሮአል፤ ለምሳሌ የኪስ ስልኩን ብንወስድ በደቡብ አፍሪካ በመጀመሪያው ዓመት እአአ በ2008 ለአንድ መቶ ሰዎች 91 የኪስ ሰልኮች ነበሩ በ2011 ለመቶ ሰዎች ወደ አንድ መቶ ሃያ ሰባት ደረሱ፤ ይህም አንዳንድ ሰዎች ከአንድ በላይ የኪስ ስልክ አላቸው ማለት ነው፤ከጎረቤቶቻችን መሀል ኬንያ በ42 የኪስ ስልኮች ለአንድ መቶ ሰዎች ጀምሮ በአራተኛው ዓመት ላይ ወደስድሳ አምስት ማደጉ ይታያል፤ ሱዳንም ከሃያ ዘጠኝ ተነሥቶ በአራተኛው ዓመት ወደሃምሳ ስድስት አድጎአል፤ ጂቡቲም ከ13 ጀምራ ወደ 21 ገብታለች፤ ትልቅዋ አገር ኢትዮጵያ በሁለት ጀምራ ከአራት ዓመታት በኋላ ለመቶ ሰዎች አሥራ ሰባት የኪስ ስልኮች አስቆጥራለች፤ በአፍሪካ ቀንድ በኪስ ስልክ የመጨረሻውን ዝቅተኛ ቦታ የያዘች አገር ትልቅዋና በዓመት ከአሥራ አንድ ከመቶ በላይ እድገት ታስመዘግባለች የሚባልላት ኢትዮጵያ ነች፡፡
ሁለተኛው የአፈናው መገለጫ የኢንተርኔት አገልግሎት ነው፤ በኬንያ በ2008 ከአንድ መቶ ሰዎች ውስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚ የነበረው 42 ሲሆን በ2011 ወደ ስድሳ አምስት አደገ፤ በኤርትራ ከ4 ወደ 6 ሲያድግ፣ በኢትዮጵያ አላደገም፡፡
እነዚህ ሁለቱም የመረጃና የእውቀት መተላለፊያ ዘዴዎች ለማናቸውም እድገት ቁልፍ መሆናቸው አያጠራጥርም፤ በተለይም ለነጻነትና ለእውቀት እድገት አስፈላጊዎች በመሆናቸው ለአምባ-ገነኖች እንደጠላት መሣሪያ የሚቆጠሩ ናቸው፤ ችግሩ እውቀት አለነጻነት አይገኝም፤ ነጻነትም አለእውቀት አይገኝም፤ እውቀትና ነጻነት ተነጣጥለው አይገኙም፤ ስለዚህም ነጻነትን ለመግደል የፈለገ እውቀትንም ይገድላል፤ ስለዚህም አምባ-ገነኖች ሞባይልንና (ተንቀሳቃሽ ወይም የኪስ ስልክ) ኢንተርኔትን ማፈን ዋና ተግባራቸው ያደርጉታል፤ በዚህም ምክንያት ሕዝቦቻቸውን በድንቁርና ያዳፍናሉ፤ በደሀነት ያሰቃያሉ፤ በዘመናችን ዋናው የአውቀት መተላለፊያ ኢንተርኔት ነው፡፡
ሰንጠረጅ ሁለት
የኢንተርኔት አገልግሎት እድገት
ደቡብ አፍሪካ የገባው ለንጽጽር ነው፤ |
ምንጭ፡- የዓለም ባንክና የዓለም የቴሌኮሚዩኒኬሽን ድርጅት
የኢንተርኔት አገልግሎት በቅርቡና በርካሽ ወይም በነጻ ከተገኘ ብዙ ሳይለፉ ምንም ዓይነት እውቀት ሊገኝ ይቻላል፤ በሠለጠኑት አገሮች በአንዳንድ ቡና ቤቶች ነጻ የኢንተርኔት አገልግሎት ይገኛል፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በኢንተርኔት ለመጠቀም ደህና ገቢ ያለው መሆን ያስፈልጋል፤ከደሀነት ለመውጣትም ሀብታም መሆን ያስፈልጋል!