March 10, 2014
39 mins read

የሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ አሳሳች መረጃዎችና የተምታታ አስተያየት

በመሠረቱ ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ ስለ አብዮቱ “ እኛና አብዮቱ “ የሚል መጸሐፍ ጻፉ የሚል
ዜና ስሰማ ፣ መጸሐፋቸው እንደ ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለማርያም መጸሐፍ በቅጥፈት የተሞላ
አይሆንም ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር ፡፡ ግን ሳይሆን ቀረ ፡፡ በነገራችን ላይ የሻምበሉን መጸሐፍ ገና
አላገኘሁትም ፣ ነገር ግን አንድ ወዳጄ ከምዕራፍ 13–16 ያሉትን ገጾች ፎቶ ኮፒ አድርጎ ስለሠጠኝ
አየተገረምኩኝ አነበብኳቸው ፡፡ ሻምበሉን ምን ነካቸው ብዬም እራሴን ጠየኩኝ ፡፡ ደራሲው
በትምህርታቸው እንዳልገፉ ይገባኛል ፡፡ ሆኖም ግን በትምህርት ያለመግፋት ትንታኔ ላይ ችግር
ይፈጥር እንደሆን እንጂ ፤ “ በእጅ የገባን መረጃ ” አሳስቶ ማቅረብ ከምን ሊመነጭ እንደሚችል
ፈጽሞ ሊገባኝ አይችልም ፡፡ ፍቅረሥላሴ መረጃው በእጃቸው ከሌላቸው አርፈው መቀመጥ አለባቸው
እንጂ ባልሆነ ማስረጃ አንባቢን ማሳሳት የለባቸውም ፡፡ መረጃው በእርሳቸው በኩል መቅረቡ ደግሞ
የበለጠ አደገኛ የሚያደርገው ፣ ግለ-ሰቡ በደርግ ውስጥ በከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩ ሰለሆኑ
መረጃው አላቸው ተብሎ ስለሚገመት ነው ፡፡ ዕውቀት መቸም በሁለት መንግድ እንደሚገኝ
ይታወቃል ፡፡ አንደኛው መንገድ ቀጥተኛ የሚባለው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ቀጥተኛ ያልሆነው መንገድ
ነው ፡፡ ቀጥተኛ የምንለው ፣ በራሳችን ተመክሮ የምናገኘው ዕውቀት ሲሆን ፣ ቀጥተኛ ያልሆነው
ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ተመክሮ የሚገኝ ነው ፡፡ እኝህ ደራሲ ግን ከሁለቱም የታደሉ አይመስለኝም ፡፡ የጻፉት መጸሐፍ በራሳቸው ዘመን ያውም ቁልፍ ተዋናኝ ሆነው በተሳተፉበት ወቅት ስለተከናወነ
ጉዳይ ከመሆኑም በላይ ፣ ስለወቅቱም የሚያወሱ መጸሐፍቶች በብዛት ተጽፈው ይገኛሉ ፡፡ አንዳንድ
ጉዳዮች ሊረሱ ስለሚችሉ ደራሲው መረጃዎችን ከነዚህ መጸሐፍቶችና ከምርመራ መዝገቦች ላይ
ማግኘት ይችሉ ነበር ፡፡ እርሳቸው ግን ይኸንን ሁሉ መቸገር የፈለጉ አልመሰለኝም ፡፡ እስቲ ትዝብቴን
እርሳቸው ከፍ ብየ በጠቀስኳቸው ምዕራፎች ውስጥ ካቀረቧቸው አስተያቶች አንዳንዶቹን እየመዘዝኩ
በመኢሶን ድርጅት ዙሪያ ባቀረቡት ነጥቦች ላይ ብቻ በማተኮር አስተያየቶቼን ለማቅረብ ይፈቀድልኝ ፡፡
I. የመረጃ ስህተቶችን በተመለከተ
ሀ – የሕዝብ ድርጅት አባላትን በተመለከተ
በሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ መጸሀፍ የቀረበልን የተሳሳተና ያልተሟላ መረጃ (
ገጽ 230 )
1 . አቶ የወንድወሰን ኃይሉ
2 . አቶ መሥፍን ካሱ
3 . ዶ/ር ሰናይ ሌኬ
4 . ዶ/ር ነገደ ጎበዜ
5 . አቶ ኃይሌ ፊዳ
6 . ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ
7 . አቶ አሰፋ መድሀኔ
8 . አቶ እሸቱ ጮሌ (ዶ/ር መባል አለበት)
9 . ዶ/ር መለሰ አያሌው
10 . አቶ ተስፋዬ ሸዋዬ
11 . አቶ ባሮ ቱምሳ
12 . ዶ/ር በዛብህ ማሩ
13 . አቶ ዮሐንስ አድማሱ ናቸው ፡፡ ( አቶ ዮናስ አድማሱ ለማለት ፈልገው
መሰለኝ ) የሚገርመው ነገር ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምም “ትግላችን” ብለው ባሳተሙት መጸሐፋቸው ላይ ቁጥሩን ወደ 11 ዝቅ አድርገውታል ፡፡ ሰዎቹ
ወይ ጃጅተዋል ፣ አለበለዚያም የማስረጃ ጥቅሙ ስለማይገባቸው ፣ አቀራረቡ ላይ
ደንታቢስ ናቸው ማለት ነው ፡፡ ስለዚህ አንባቢ የነርሱን ሥራ በሚያነብበት ወቅት
በጥንቃቄ ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር እያመሳከረ መሆን ይኖርበታል ፡፡
በአቶ አንዳርጋቸው አሰግድ “በአጭር የተቀጨ ረጅም ጉዞ” የቀረበልን ትክክለኛና
የተሟላ መረጃ (ገጽ 296 )1 . አቶ ኃይሌ ፊዳ
2 . ዶ/ር ፍቅሬ መርዕድ
3 . ዶ/ር ከድር መሐመድ ( በኋላ ላይ ወደ ኢሉ አባቦራ የሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤት
የተዛወረ )
4 . አቶ መስፍን ካሱ
5 . ዶ/ር ነገደ ጎበዜ
6 . አቶ ባሮ ቱምሳ
7 . አቶ ዮናስ አድማሱ
8 . ዶ/ር ሠናይ ልኬ
9 . አቶ ሸዋንዳኝ በለጠ
10 . ዶ/ር እሸቱ ጮሌ
11 . ዶ/ር መለስ አያሌው
12 . ዶ/ር አሰፋ መድኀኔ
13 . አቶ ተስፋዬ ሸዋየ
14 . ዶ/ር በዛብህ ማሩና
15 . አቶ የወንድወሰን ኃይሉ – ከነዚህ ውስጥ ዶ/ር እሸቱ ጮሌና አቶ ዮናስ
አድማሱ ከጽሕፈት ቤቱ እንደተሰናበቱ ፣ በምትካቸው ዶ/ር ንግሥት አዳነና ዶ/ር ዓለሙ
አበበ ተጨምረዋል ፡፡ ከነዚህም ሌላ በኋላ ላይ የአፋር ነፃነት ንቅናቄ መሪ አባል የነበረው
አቶ ዩሱፍ ያሲን የጽ/ቤቱ አባል ሆኗል ፡፡ ለ – ከአዲስ አበባ ህቡዕ የገቡትን የመኢሶን አባሎችን በተመለከተ
በሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ የቀረበልን ያልተሟላና የተሳሳተ መረጃ ( ገጽ 342-3 )
1ኛ ቡድን ፡- በጎጃም በር በሱልልታ በኩል ለመውጣት የሞከረ ፤
 ኃይሌ ፊዳ የቡድኑ መሪ (በነገራችን ላይ ህቡዕ ስንገባ ቡድን መሪ የሚባል
አልነበረንም ፡፡ ደራሲው ከየት እንዳመጡት አላውቅም ፣ ምናልባት በወታደር
ዓለም ውስጥ ያለ ቡድን መሪ መንቀሳቀስ አይቻልም መሰለኝ ?)
 ዳንኤል ታደሠ
 ዶ/ር ከበደ መሸሻ ( የዶ/ር ከበደ አባት ሥም ፣ መሸሻ ሳይሆን መንገሻ ነው )
 ደረጀ ዓለማየሁና ጥቂት የመኢሶን ካድሬዎች ፡፡ 2ኛ ቡድን ፡- በወለጋ በኩል ሊወጣ የሞከረ ፤
 ተፈራ ገ/ፃዲቅ የቡድኑ መሪ (ግለሰቡ ስማቸው ተፈራ ገ/ፃዲቅ ሳይሆን ፣ዶ/ር
ተረፈ ወልደፃድቅ ነው፡፡
 ዳነቢ ዲሳሳ የተፈራ ገ/ጻዲቅ ሚስት ( ደንቢ ዲሳሳ እዚህ ቡድን ውስጥ
አልነበረም )
 አማረ ተግባሩ
 መርዕድ ከበደ
 ኃይሉ ገርባባና ሌሎች የመኢሶን አባላትና ካድሬዎች ፡፡ ( ኃይሉ ገርባባ በዚህ
ቡድን ውስጥ አልነበረም ፡፡ እርሱ ከወለጋ ካድሬዎች ጋር ነው የወጣው )
3ኛ ቡድን ፡- በጂማ መስመር ለመውጣት የሞከረ ፤
 ኃይለሥላሴ ወ/ ገሪማ የቡድኑ መሪ
 በለጠ ወትሮና ሌሎች የመኢሶን አባላት ፡፡ 4ኛ ቡድን ፡- በሲዳሞ በኩል ለመውጣት የሞከረና በከፊልም ቢሆን የመትረፍ ዕድል
የገጠመው
 መስፍን ካሱ የቡድኑ መሪ
 ዶ/ር ንግሥት አዳነ ( ከዚህ ቡድን ጋር አልነበሩም ) ደስታ ታደሰ (ከዚህ ቡድን ጋር አልነበሩም )
 ዳዊት አሰፋ
 አበራ የማነአብ
 አንዳርጋቸው አሰግድ ናቸው ፡፡ በዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ተሟልቶ የቀረበ
ወደ ጫንጮ የተጓዙ ጓዶች
 አቶ ኃይሌ ፊዳ
 ዶ/ር ከበደ መንገሻ
 አቶ ዳንኤል ታደሠ
 አቶ አያሌው ወልደ መድህን
 አቶ አበበ ኃይሌ
 አቶ የራስወርቅ አድማሴ
 አቶ ደረጀ ዓለማየሁ
 አቶ ዳንኤል (የትግል ስም ፣ ሾፌር ሆኖ ያገለገለ)
 ደንቢ ዲሳሳና ምትኩ ተርፋሳ ባካባቢው የሕዝብ ድርጅት ጽ/ቤት ባልደረባ
ስለነበሩ ከዚህ ቡድን ጋር አብረው ነበሩ ፡፡ ወደ አምቦ የተጓዙ ጓዶች
 ዶ/ር ተረፈ ወልደፃድቅ
 ወ/ሮ አጥናፍዓለም ይማም ( የዶ/ር ተረፈ ባለቤት )
 አቶ ከበደ ደሪባ
 አቶ እዮብ ታደሠ
 አቶ መርዕድ ከበደ
 አቶ አማረ ተግባሩ
ወደ ከንባታና ሀዲያ የተጓዙ ጓዶች
 አቶ ደስታ ታደሰ
 ዶ/ር ንግሥት አዳነ
 አቶ ኃይለሥላሴ ወልደገሪማና
 አቶ ኤፍሬም ዳኜ ሲሆኑ ፤ አቶ በለጠ ሙቱሮ ከአዲስ አበባ የሔዱ ሳይሆን ፣
እዛው የአውራጃው የሕዝብ ድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት ሠራተኛ የነበሩ ናቸው ፡፡ ወደ ሲዳሞ የተጓዙ ጓዶች
 አቶ አበራ የማነአብ
 አቶ አንዳርጋቸው አሰግድ
 አቶ መስፍን ካሱ
 አቶ ግርማ ሥዩም
 አቶ ዳዊት አሰፋ
አቶ ጋሻው ታደሠ ናቸው ፡፡ የሚገርመው ነገር ሌ/ኮ መንግሥቱ ኃይለማርያምም ሆኑ ሻም / ፍቅረሥላሴም፣
መኢሶኖች የተገደሉት በገበሬዎች እንጂ በኛ አይደለም ብለው ሽምጥጥ አድርገው ይዋሻሉ ፡፡ ዕውነቱ ግን ፣
የኢትዮጵያ ገበሬ እኛን ስለደበቀን ብቻ አብሮን ከመታሰርም አልፎ በድብደባ ተሰቃይቷልም ፡፡ አብዳላ ሶኔሳ
የኢትዮጵያ ገበሬዎች ማኀበር ፕሬዘዳንት ሆኖ በአብዮት አደባባይ ገበሬውን ወክሎ ንግግር ባደረገበት ወቅት
በንንግግሩ ላይ ደርግን ስለእኛ ድንገተኛ መሰወር የጠየቀው ጥያቄ ፤ “ እነዚያ እንደሱካር ይጣፍጡን የነበሩት
ልጆቻችን ወዴት ገቡ “ ብሎ ነበር ፡፡ ከንግግሩ ቆርጣችሁ ካላወጣችሁት በማስታወቂያ ሚኒስቴር ቤተ- መጸሐፍት ይገኛል ፡፡ በከንባታና ሀዲያ የተሸሸጉት ጓዶችም የተያዙት እርሶ እንደሚሉት በገበሬዎች ሳይሆን ፣መንገድ መሪዎቹ በከተማው የሠዐት እላፊ ለውጥ መደረጉን ባለማወቃቸው የተነሣ ፣ በወቅቱ ከተማውን
በሚጠብቁ የከተማው ፖሊሶችና በቀበሌ ጠባቂዎች ነው ሊያዙ የቻሉት ፡፡ ከዚያም ገበሬዎቹም ጓዶቹም
አብረው ተይዘው አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ነው ፣ ሁለቱን ማለትም ዶ/ር ንግሥት አዳነንና አቶ ደስታ
ታደሠን ከእስር ቤት ( ከከርቸሌና ከ4ኛ ክፍለ ጦር ) አውጥታችሁ ከነ ጓድ ኃይሌ ፊዳ ጋር አብራችሁ
የገደላችኋቸው ፡፡ ሀቁ ይኸው ነው ፣ የናንተም የምርመራ ሠነድ ቢፈተሸ ይኼንኑ ሀቅ ነው የሚመሰክረው ፡፡ ለምን የእናንተን ወንጀል በገበሬው ላይ እንደምታሳብቡ አይገባኝም ፡፡ እረስተውት ነው እንጂ ፣ በወቅቱ
ያስተላለፋችሁት ትዕዛዝ እኮ በተገኙበት ይገደሉ የሚል እንጂ እጃቸውን በሠላም ከሠጡ ያዟቸው የሚል
አልነበረም ፡፡ አንድ ቀን ይኸም የሕትመት ብርሃን ማየቱ አይቀርም ፡፡ እናንተ ያኔ የሚታያችሁ የነበረው
የተማረውን ክፍል አስወግዳችሁ ሥልጣን አለተቀናቃኝ መጨበጣችሁ ነው እንጂ ፣ አገሪቷንና አብዮቱን
ይዛችሁ ገደል መግባታችሁ አልታያችሁም ፡፡ አሁንም ለሠራችሁት ወንጀል ንሰሀ የገባችሁ አይመስለኝም ፡፡ ይኼ እንግዲህ ቀላሉን ነገር መረጃ ማቅረብን በተመለከተ የቀረበውን የግብር ይውጣ ሥራ ለማመልከት ስል
ያቀረብኩት ነው ፡፡ ይህችን ሰነድ አሰባስቦ መልክ በማስያዝ ማቅረብ ያቃታችሁ አገርን የመምራት የሚያህል
ኃላፊነት እንዲት ተሸከማችሁ ? እስቲ ደግሞ አስገራሚውንና እርስ በእርሱ የሚጣረሰውን ትንተናቸውን
እንመልከት ፡፡ መኢሶን ለምን እራሱን
ከኢማሌድህ አገለለ ? ለዚህ ጥያቄ ሻምበል ፍቅረሥላሴ የሠጡት መልስ የሚከተለውን ይመስላል ፤ “ የአገራችን ጠላቶች የከፈቱብንን የተቀናበረ ጦርነት በምን ዘዴ እንመክት ? አደጋውንስ እንዴት አድርገን
እናስወግድ ? ብሎ ከመመካከርና ጠንክሮ ከመቆም ይልቅ መኢሶን አብዮቱን በመክዳት ለመሸሽ ውሳኔ
ለማድረግ በመጋቢት ወር 1969 ኮንፈረንስ ጠራ ፡፡ የኮንፈራንሱ ተሳታፊዎች በአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ
በስፋት ከተወያዩ በኋላ “ ከደርግ ጋር የመሠረትነው ትብብር ተቋርጧል ፣ የትግል ለውጥም አድርገናል “ የሚል ውሣኔ አሳለፉ ካሉ በኋላ ፤ ከአብዮቱ “የሸሸንበትን” ምክኒያት ግን በሁለት ከፍለው ያቀርቡታል ፡፡ “ አንደኛው ምክኒያት መኢሶን በአቋራጭ በብልጣብልጥነት ሥልጣን በአጭር ጊዜ እጨብጣለሁ ብሎ የቀየሰው
ዘዴ ተግባራዊነት እየራቀ መምጣቱ ፣ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የመኢሶን መሪ ካድሬዎች ፈሪና ድንጉጥ
መሆናቸው ነው “ በማለት ይደመድማሉ ፡፡ እስቲ የሻምበሉን ግምቶች አንድ ባንድ እንመልከታቸው ፡፡ ይህ
መኢሶን ባቋራጭ በብልጣብልጥነት ለሥልጣን ያበቃኛል ብሎ የቀየሰው ዘዴ ምን ይሆን ? እርሳቸው አዋጁን
ይጠቅሱታል እንጂ አንብበውትም የሚያቁ አይመስለኝም ፡፡ ይህ ገጽ 231 ላይ የጠቀሱትን አዋጅ አንብበውት
ቢሆን ኖሮ ፣ ሥልጣንን በተመለከተ የመኢሶንን ዕቅድ አዋጁ ላይ ያገኙት ነበር ፡፡ አዋጁ የሥልጣን ጥያቄን
በተመለከተ ፤ “ የሠፊው ሕዝብ ትግል ተደራጅቶና ገፍቶ አብዮታዊ ሕዝባዊ ግንባሩ እንደተቋቋመ በትግል
ውስጥ የተሳተፉት የግንባሩ አባል ፓርቲዎችና የፖለቲካ ድርጅቶች ከሚያቀርቧቸው ምልምሎች መሀከል
ሕዝቡ በሙሉ ነፃና ምሥጥራዊ በሆነ ምርጫ እንደራሴዎቹን መርጦ የመንግሥቱን ከፍተኛ ሥልጣን
ወደሚይዘው አብዮታዊ ሸንጎ ይልካል ፡፡ የሕዝቡ ወኪሎች አጥንተው ባፀደቁት ሕገ-መንግሥት መሠረት
የመንግሥቱ መዋቅሮች ፣ ዘርፎችና የሥልጣን ክፍፍሎች ተወስነው በወዝ-አደሩ ፓርቲ መሪነት ሕዝባዊ
ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ይቋቋማል ፡፡ “ ነው የሚለው ፡፡ እንግዲህ ይኼ አዋጅ ገና በ1968 ዓ/ም ለሕዝብ
አብረን ቃል የገባንበት ነበር ፡፡ አዋጁ የመኢሶን የሥልጣን መወጣጫ አቋራጭ መንገድ ሊባልም አይገባም ፡፡ እናንተ ግን በደርግ ውስጥ የነበሩትን ተቀናቃኞቻችሁን በግድያ ካስወገዳችሁ በኋላ ፣ አዋጁን ወደ ጎን በማለት
እኛን የወንጀላችሁ ተባባሪ በማድረግ ሥልጣን ያለሕዝብ ይሁንታ ለመቆናጠጥ ፈለጋችሁ ፡፡ እኛም ከሕዝብ
ጀርባ በሚዶለት ሴራ ተባባሪ አንሆንም በማለታችን ልታጠፉን ተነሳሳችሁ ፡፡ በግልጽ እንገላችኋለን እስከማለት
ደረሳችሁ ፡፡ ያወጣነው አዋጅ ስለሥልጣን ሽግግር የሚለው በሕዝብ ይሁንታ ፤ “በወዝ-አደሩ ፓርቲ መሪነት
ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ይቋቋማል” እንጂ ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና ከፍተኛ ሲቪል
ቢሮክራቶች ተባብረው ኢሠፓን ይመሠርታሉ አልነበረም ፡፡ እናንተ ግን ያደረጋችሁት ይኸንኑ ነው ፡፡ አንድ
ፓርቲ ሳይሆን መድበለ ፓርቲ መቋቋም አለበት የተባባልነውንም ሽራችሁ ፣ ሕዝቡም ምርጫ እንዳይኖረው
አንድ ፓርቲ ብቻ ይበቃል በማለት ወሰናችሁ ፡፡ የጉዳችሁ ጉድ ደግሞ ሕዝቡ ከናንተው መሀከል እንኳን
የፈለገውን ግለሰብ እንዳይመርጥ ፣ የአንበሳና የጎሽ ምልክት ያላቸውን ትታችሁ ፣ ዝሆን ምልክት ያለውን
ብቻ ምረጡ አላችሁ ፡፡ ሻምበል ፣ ተዲያ መኢሶን እዝህ ጭምልቅ ውስጥ ለምን አብሮን አልገባም ብለው ነው
“ መኢሶን ከአብዮቱ ሸሸ “ የሚሉን ? ከአብዮቱ የሸሸው የ1968 ቱን አዋጅ የሻረ እንጂ ለአብዮቱ ተግባራዊነት
በፅናት የታገለው መኢሶን ሊሆን አይችልም ፡፡ ለመሆኑ አብዮት ማለት ደርግ ማለት ነው ብሎ የነገሮት
ማነው ? እናንተ የወር ደሞዘተኞች ሆናችሁ የንጉሡን ሥልጣን ስትንከባከቡ ፣ መኢሶን እንደ ፖለቲካ
ድርጅት የንጉሡን ሥርዐት ለመለወጥ ከውስጥም ከውጭም ይታገል እንደነበር አለማወቆን ከመጸሐፎ
ተረድቻለሁ ፡፡ ለእርሶ የፖለቲካ ድርጅቶች የተቋቋሙት በናንተ የግዛት ዘመን ይመስሎታል ፡፡ ሌላው አስቂኝ
ነገር ደግሞ “መኢሶን የሸሸው የሱማሌን ጦር ፈርቶ ነው” ያሉት ነው ፡፡ እርሶ ያለፍርሀት ምንም የሚያውቁትነገር ያለ አይመስለኝም ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ከየገጠሩ ተመልምሎ የመጣውን የሚሊሺያ ጦር ፣ የመኢሶንን
ያህል በቅርብ የምታውቁት አይመስለኝም ፡፡ የመኢሶን ጓዶች ከምልምል ሠራዊቱ ጋር አብረው በመሠልጠን
ወደ ጦሩ ግንባር ለመዝመት ጥያቄ ባቀረቡ ጊዜ እምቢ ማለታችሁን እረሱት ? እስቲ ስለዚህ ጉዳይ የእርሶው
ድርጅት አባል የነበሩት ገስጥ ተጫኔ ምን እንደሚሉ አብረን እንመልከት ፡፡ ገሥጥ “ነበር” ብለው በሰየሙት
የመጀመሪያው መጸሐፋቸው ገጽ 269 ላይ ፤ “ የሶማሊያን ወረራ ለመመለስ በታጠቅ ጦር ሠፈር እየሰለጠነ
በነበረው ሚሊሻ ሠራዊት ውስጥ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የኢማሌድኅ አባል ድርጅቶች የደርግን ፈቃድ ጠየቁ ፡፡ በግልም ሊቀ መንበር መንግሥቱን ተለማመጡ ፡፡ በተለይ መኢሶን ብዙ ወትውቶ ነበር ፡፡ “ ካሉ በኋላ
መኢሶን ፤ “ … አሰርጎ ያስገባቸው ካድሬዎቹም ተመንጥረው ወጡ ፡፡ “ ይላሉ ፡፡ መኢሶን ከሠራዊቱ ጋራ
እንዳይቀላቀል ይከልከል እንጂ ፣ የአብዮታዊ ሰደድ ፣ የወዝ ሊግና የማሌሪድ ካድሬዎች በጦሩ ከምፕ ውስጥ
እንደልባቸው ሲፈነጩበት እንደነበር ገስጥ ተጫኔ በዚሁ ገጽ ላይ ያብራራሉ ፡፡ መኢሶን ከጦሩ ጋር አብሬ
ልዝመት አለ እንጂ ከአገር ጉደይ ሸሽቶ አያውቅም ፡፡ ሻምበል ወደዱም ጠሉም ሀቁ እንግዲህ ይኸው ነው ፡፡ ሥልጣን ከሕዝብ ይሁንታ ውጭ አንፈልግም ማለታችንንም አሌ እንዳይሉ ፣ ይህን በተመለከተ አቶ ተስፋዬ
መኮንን “ ይድረስ ለባለታሪኩ “ ብለው ጥቅምት 1985 ያሳተሙትን መጸሐፋቸውን ገጽ 243ን ይመልከቱ ፡፡ ገስጥ ተጫኔም “ነበር” ብለው በ1996 ዓ/ም ያሳተሙትን መጸሐፍ ገጽ 270 ቢመለከቱ አቶ ተስፋዬ ያሉትን
ነው የሚያረጋግጡት ፡፡ ስለዚህ የራሳችሁን ሥልጣን ባቋራጭ የመያዝ ጉጉት የመኢሶን ዘዴ ነው አትበሉ ፡፡ ለሕዝብ በአዋጅ ቃል የገባችሁትን ያጠፋችሁት እናንተ እንጂ መኢሶን አይደለም ፡፡ ለነገሩ መኢሶን ከመደብ
ባህሪያችሁ በመነሳት ይኸንኑ እንደምታደርጉ ገና በ1968 ዓ/ም ግንቦት 11 ቀን ባወጣው በሰሕድ ቁጥር 40
አማካኝነት ለሕዝብ ፤ “ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ይህን ፕሮግራም ከሥራ ላይ ሊያውል አይችልም ፡፡ ስለዚህም ደርጉ የቀድሞ ወላዋይነቱን ካስቀረ ፤ የዚህን መለስተኛ አዋጅ ሥራ ላይ መዋል የሚያግዙ
እርምጃዎች በመውሰድ የሠፊውን ሕዝብ ትግል ሊያገለግል ይችላል ፡፡ ሠፊውን ሕዝብ ተክቶ ግን ይህን
ፕሮግራም ከሥራ ላይ ሊያውል አይችልም ፡፡ የዚህ መለስተኛ ፕሮግራም ታሪካዊ ቦታ ለአገራችን ችግሮች
ዛሬውኑ መፍትሔ ስለሚያስገኝ አይደለም ፡፡ ሠፊው ሕዝብ ለነዚህ መፍትሔዎች እራሱ እንዲታገል ለማንቃት
፣ ለማደራጀትና ለማስታጠቅ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ነው ፡፡ “ ሲል አስታውቆ ነበር ፡፡ ስለዚህ
ሻምበል የሥልጣን ጥመኝነቱ እናንተን የሚመለከት እንጂ መኢሶንን አይደለም ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ያስቀመጡት
መላ ምቶ ደግሞ እኛ “ከአብዮቱ የሸሸነው” የሱማሌን ጦር ስለፈሩ ነው ነው የሚሉት ፡፡ ሻምበል ምን ነካዎት
? መኢሶኖች እኮ ባዶ እጃችንን “ ታጋይ ይሞታል ፣ ትግል አይሞትም “ እያልን ከፀረ-አብዮተኞች ጋር
እንደታገልን እርሶም ሳያውቁት በመጸሐፎ ውስጥ መስክረውልናል እኮ ፡፡ ከሸሸን ያኔ ነበር የምንሸሸው ፡፡ እስቲ
በመጸሐፎ ገጽ 318 ላይ ስለእኛ ያሉትን ላስታውሶት ፡፡ “ እነዓለማየሁ በደርግ ውስጥ ያካሔዱት ሰላማዊ
መፈንቅለ-መንግሥት በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያስገኝልናል ብለው የጠሩት ሕዝባዊ ስብሰባ ተቃራኒ ውጤት
አስገኘ ፡፡ መኢሶን ቀስቅሶ ወደ አደባባይ ላወጣው ሕዝብ አቋሙን ለማሳወቅ ጥሩ አጋጣሚ ስለተፈጠረለት
ተጠቀመበት ፡፡ በቀላሉ የማይታይ ኃይል እንደሆነም አሳየ ፡፡ በአደባባይ የታየው የተቃውሞ እንቅስቃሴ
የነዓላማየሁን ቡድን ሲያሳስብና ስጋት ላይ ሲጥል ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱንና ደጋፊዎቻቸውን ያበረታታና የልብ
ልብ የሰጠ ነበር ፡፡ “ ብለው ነው የመሰከሩልን ፡፡ እናንተ ወኔያችሁ በከዳችሁ ወቅት መኢሶን የሕዝብን
ድጋፍ በመተማመን ብቻ ባዶ እጁን ከነዓለማየሁ ኃይሌ ጋር ተጋፍጦ እርሶም እንዳመኑት ስላበረታታናችሁና
የልብ ልብ ስለሠጠናችሁ ፈሪ ይሉናል ፡፡ ምን ያድርጉ እርሶ ማሰብ የሚችሉት ፈሪና ደፋር በሚሉ ቃላቶች
ብቻ ስለሆነ ፣ ስለኛ ጀግንነት ሊመሰክሩ አይችሉም ፡፡ ሻምበል ፣ ” ሌባ እናት ልጇን አታምንም “ ይባላል ፡፡ እርሶም ፍርሀቶ መረን የለቀቀ በመሆኑ የተነሳ እኛም እንደ እርሶ ፈሪ መስለን እንታዮታለን መሰለኝ ፡፡ ፈሪ
መሆኔን በምን አወክ ? ይሉኝ ይሆናል ፡፡ ማን እንደነገረኝ ለማወቅ ብዙም አይጨነቁ እርሶው እራሶ ኖት
በመጸሐፎ ውስጥ ያሰፈሩት፡፡
ሌ/ኮ ፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም እርሶን እንደማይተናኮሎት በብዙ አጋጣሚዎች አሳውቀዎታል ፣ እርሶ ግን
ከፈሪነቶ ብዛት የተነሣ አምነዋቸው ሊረጋጉ አልቻሉም ፡፡ ከሚገደሉት ማህል በስህተት እንደተደለደሉና በኮ/ል
ዳንኤል አስፋው አማካኝነት ከሞት እንደተረፉ በመጸሐፎ ተርከውልናል ፡፡ ይህ እንግዲህ እርሶ በሌ/ኮሌኔሉ
በክፉ ዐይን እንደማይታዩ ሊያረጋግጥሎት በተገባ ነበር ፡፡ እርሶ ግን ሊቀመንበሩ ከእልቂቱ የተረፋችሁትን ፣
በአዳራሽ ሰብስበው ስለጉዳዩ ሊያስረዷችሁ በፈለጉ ጊዜ ገና እንደተሸበሩ ነበር ፡፡ አስቲ ሁኔታውን እንዴት
እንደገለጹት ላስታውሶት ፡፡ በመጸሐፎ ገጽ 326 ላይ ፤ “ ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ወደ አዳራሹ ሲገቡ
ከመቀመጫችን ተነስተን ተቀበልናቸው ፡፡ የተረጋጉ ይመስላሉ ፡፡ ከወትሮው ይበልጥ ተኮሳትረዋል ፡፡ ፊታቸው
አስፈሪ ነው ፡፡ የወሰዱትን እርምጃ ስለምናውቅ ትኩር ብለን ዐይናቸውን የመመልከት ድፍረት አጣን ፡፡ ወዘተ.” ብለው ፍርሀቶ ገደብ የለሽ እንደ ነበር አስረድተውናል ፡፡ እኔ የምለው ፣ አልነካህም ከተባሉ በኋላ
ምንድነው እንደዚህ መንፈሽፈሽ ? ወታደር አይደሉም እንዴ ? እተፋፋመ ውጊያ ውስጥ ቢገቡ ምን ሊውጦትነው ? ሌላው የገረመኝ ነገር ደግሞ ስለ እነ መቶ አለቃ ዓለማየሁ ኃይሌ ማልቀስ የነገሩን ነው ፡፡ ምነው
የእርሶን በአራት ማዕዘን የወረደውን እንባ ዘነጉት ? ያውም መትረፎን ካረጋገጡ በኋላ ፡፡ ሻምበል ፣ መኢሶን
እንደናንተ የለት የለቱን እያሰበ ብቻ የሚጓዝ ድርጅት አልነበረም ፡፡ እናንተ አታነቡም እንጂ ፣ መኢሶን
በትግሉ ወቅት ከአብዮቱ ካፈገፈጋችሁ ጥሏችሁ በሚያመቸው መንገድ እንደሚታገል ቀደም ሲልም ነግሯችሁ
ነበር ፡፡ እናንተ ግን የእኛን ህቡዕ መግባት ከአብዮቱ እንደመሸሽ ቁጠራችሁት እንጂ የትግል ስልት ለውጥ
መሆኑን አልተረዳችሁም ፡፡ መኢሶን የሚከተለውን የትግል ስልት ሚያዚያ 30 ቀን ፣ 1968 ዓ/ም ባወጣው
የሠፊው ሕዝብ ድምፅ ቁጥር 39 ላይ የሚከተለውን ብሎ ነበረ ፤ “ መኢሶን በፕሮግራሙ መግቢያ ላይ
እንደገለጸው ፣ ለነዚህ አበይት ዓላማዎቹና በጠቅላላው ለፕሮግራሙ ሥራ ላይ መዋል … ያለአንዳች
ማወላወል ፤ በምሥጢርና በይፋ ፤ በሕጋዊ መንገድና በሕገ-ወጥነት ፤ በሠላማዊ መንገድና በአመፅ ፤
እንደጊዜውና እንደሁኔታው በሚለወጥ ታክቲክ ፤ ምንም ጊዜና ምንም ሁኔታ በማይለውጠው ቆራጥነትና
ታታሪነት የሚታገሉ አብዮታዊያንን አስተባብሮ ለኢትዮጵያ ሰፊ ሕዝብ ነፃነትና አንድነት አሰልፏል ፡፡ የኢትዮጵያ ጭቁኖች የሚያደርጉትን ትግል ዳር እስከ ዳር አስተባብሮ ፤ የተጣራ አብዮታዊ አመራር ለመስጠት
በጭቁን ሕዝቦችና በታሪክ ፊት የተቀበለውን አደራ እስከ መጨረሻው ይጠብቃል ፡፡ ጭቁኖች በትግላቸው
እንደሚገፉ ፤ በትግል እሳት የተፈተኑ አባሎቹ አብዮታዊ ግዴታቸውን ለመፈጸም ወደኋላ እንደማይሉ ሙሉ
እምነት አለው ፡፡ “ ከዚህ መግለጫ የምንረዳው ነገር ቢኖር ፣ መኢሶን የሶማሌ ጦርነት ከመምጣቱ ቀደም
ብሎም የትግል ስልት ለውጥ ሊያደርግ እንደሚችል ማሳወቁን ነው ፡፡ ስለዚህ የትግል ስልት ለውጥ ማድረጉ
እርሶ እንደሚሉት ድንገተኛና ከፍርሀት ጋር የተያያዘ አልነበረም ማለት ነው ፡፡ በተለይ እናንተ ከጥር 30 ቀን
፣ እሰከ የካቲት 4 ቀን ፣1969 ዓ/ም ድረስ ዝግ ስብሰባ አድርጋችሁ ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱን ባለሙሉ
ሥልጣን ከአድርጋችሁ በኋላ ፤ በ1968 ዓ/ም በአዋጅ ለሕዝብ የገባነው ቃል ኪዳን እንደተሻረ ምንም ጥርጥር
አልነበረንም ፡፡ ከዚያ በኋላማ በአገሪቱ ጉዳይ አለኛ ማን አለ በማለት ለያዥ ለገራዥ አስቸግራችሁ ነበር ማለት
ይቻላል ፡፡ የሚገርመው ነገር እኛን ለማጥፋት ከተባበራችሁ በኋላ እርስ በርስ ደግሞ መጨራረሳችሁ ነው ፡፡ እርሶ ግን ለሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሥልጣን ስጋት ስላልነበሩ ወዳጅ ጓደኞቾ ሲያልቁ ከዚህ ሁሉ
መአት አመለጡ ፡፡ በጦር ሜዳ ውሎ ልምድ የነበራቸውን የጦር መኮንኖች እንድ ባንድ አጠፋችኋቸው ፡፡ መድረክ ላይ የሚሠራ ትያትር ይመስል እነመጋቢ ሃምሣ አለቃ ለገሠን የሠሜን ጦር አዛዥ አድረጋችሁ
ሾማችሁ ላካችሁ ፡፡ አንድም ጥይት ሳይተኩሱ የሠሜን ግንባሩን ጥለው ተመለሱ ፡፡ እኝህ ሰው
በሕይወታቸው የመቶ ጦር እንኳን መርተው አያውቁም ፡፡ ባህር ኃይሉንም ፣ ፖሊስ ሠራዊቱንም በበታች
ሹማምንቶች አስያዛችሁ ፡፡ በዚሁም የከፍተኛ መኮንኖችን ሞራል ገደላችሁ ፡፡ በመጨራሻም አገሪቷን አሁን
ለወደቀችበት ሁኔታ ዳረጋችኋት ፡፡ ይኸው ነው እንግዲህ ሻምበል የናንተ ሥራ ፡፡ እስካሁን የመኢሶንን
አመራር የሚተቹ ግለሰቦች የመኢሶን አመራሮች የወጣላቸው ምሁራን ናቸው ፣ ለአብዮቱም ከፍተኛ አስተዋፆ
ማበርከታቸው አሌ አይባልም ካሉ በኋላ ፣ የሚያዥጎደጉዱት ስድብና ወቀሳ ነው ፡፡ ኢሕአፓና እነመንግሥቱ
ኃይለማርያም መኢሶንን በቅብብሎሽ በመግደልም ፣ በማሰርም ካዳከሙትና ፣ አገሪቷን አሁን ላለችበት ሁኔታ
ከዳረጓት በኋላም የሚወቅሱት መኢሶንን ነው ፡፡ በዚህ ዐይነት በአገራችን ስህተት የሚሠራው ምሁሩ እንጂ
መሀይሙ አይደለም ማለት ነው ፡፡ እኔ እርሶን ብሆን ፣ ይኸንን ሠርቻለሁ ብዬ መፎከር ይቅርና ቀና ብዬም
ሰው አላይም ነበር ፡፡ እርሶ ግን ባለፈው ጥፋቶ የተፀፀቱም አይመስሉም ፡፡ በዚሁ ላብቃ ፡፡

መርዕድ ከበደ

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop