February 18, 2014
12 mins read

ተራ ኢትዮጵያዊ መሆናችንን አንናቀው ! ግርማ ካሳ

አገሬን ለቅቄ ስደት የጀመርኩት በ1984 ነዉ። ኢሕአዴግ ስልጣን በጨበጠ በአንድ አመቱ። ከአስራ አራት አመታት በኋላ ለአንድ ወር ጉብኘት ቦሌን ረገጥኩ። እሑድ ቀን ፣ ግንብት ሰባት 1997 ነበር።

ከዚያ በፊት ብዙም የፖለቲካን ነገር አልከታተለም ነበር። ምርጫ እንደሚደረግ፣ ቅንጅት ሕብረት እየተባለ የምርጫዉ ዘምቻ እንደተጧጧፈ ያወኩት ትኬት ከቆረጥኩ በኋላ፣ ከምርጫዉ 15 ቀናት በፊት ነበር። በአጭሩ አባባል፣ በአገሬ ዉስጥ እየተደረገ ከነበረዉ ሁኔታ የተለየዉ፣ ዲስኮንቴክትድ የሆነ ነበርኩ ማለት ይቻላል።

በወቅቱ የነበረዊ አንጻራዊ ዴሞክራሲ አስደሰተኝ። ቅንጅት አዲስ አበባን ሙሉ ለሙሉ አሸነፈ። ከሌሎች ቦታዎች የሚመጡም ዉጤቶች ቅንጅቶችን የሚያስደስት ነበሩ። በዚህ ጊዜ ችግሮች መፈጠር ጀመሩ። ኮሮጆ መቀየር የመሳሰሉት። አገሪቷ ወደ ቀውስ መግባት ጀመረች።በየቀኑ ጋዜጦችን እገዛለሁ። (አዲስ ዘመንን ግን ገዝቼ አላወቅም) የምወዳት ቡና ቤት ነበረች። ካፌ ማሩ ትባላለች። ቡናዬን ይዤ ጋዜጦችን አነባለሁ። አንድ ቀን እንደለመድኩት ገዝቼ ሳገላብጥ፣ ሁሉም የአንዲት ሴት ልጅን ፎቶ፣ በትልቁ አውጥተዋል። በቆምኩበት እንባ ይፈሰኝ ጀመር።

የአሥራ ስድስት አመት ወጣት ነበረች። በኮተቤ አካባቢ በተነሳዉ ሕዝባዊ ሰላማዊ ተቃዉሞ፣ ከኢሕአዴግ ታጣቂዎች በተተኮሰ ጥይቅ ተመታ የወደቀች። ሽብሬ ደሳለኝ ትባላለች። የዘጠና ሰባቱ ምርጫ የመጀመሪያዋ ሰላባ። ይሄን ጊዜ የ23 አመት ሴት፣ ምናልባትም የልጅ እናት ትሆን ነበር። ሽብሬን መቼም ቢሆን አልረሳትም። ስምንት አመት ቢሆነኡም፣ በርሷ ላይ የተፈጸመው፣ ትላንት እንደተፈጸመ አድርጌ ነዉ አሁን የማስበው።

ጋዜጦቹን አንብቤ እንደጨርስኩ፣ ወደ ሜክሲኮ በእግሬ አመራሁ። ሌላ አስደንጋጭና አሳዛኝ ክስተት የዚያኑ ቀን አጋጠመኝ። ነጭ መስታወት ቢጤ በፊታቸው ባደረጉ ፖሊሶች፣ የተግባረ እድ ተማሪዎች ይደበደቡ ነበር። በሰደፍ ሲመቷቸው በአይኔ በብረቱ ተመለከትኩ። ዉስጤ ተቆጣ። «እንዴት ዜጎች በአገራችዉ እንደ ከብት ይደበደባሉ ? » አልኩ። ያኔ ወሰንኩኝ።

እርግጥ ነዉ፣ እኔ ላይ የደረሰብኝ ነገር የለም። በአሜሪካን የስደት ኑሮ ጀምሬ፣ በሁሉ መስክ ደህና ሁኔታ ላይ ነዉ ያለሁት። እግዚአብሄር ይመስገን። ነገር ግን አሜሪካ እና ኢትዮጵያ አንድ ስላልሆኑ፣ በኢኮኖሚ እንደ እኔ ለምን አይሆንም ባልልም፣ እኔ እንደ ኢሚግራት በአሜሪካን አገር ያለኝን መብትና ዲግኒቲ፣ ጥቂቷን እንኳን ወገኖቼ በአገራቸው ማጣቸውን ሳሰበዉ ዉስጤ ቆሰለ። ያንንም መቀበል ከበደኝ። ኢትዮጵያ ዉስጥ የሰብአዊ መብት እንዲከበር ፣ ዜጎችን የመደብደብ፣ የማሰር፣ የማፈናቀል ተግብራት እንዲወገዱ፣ ዉጤት ያምጣም አያምጣም፣ ማድረግ ያለብኝ ሁኑ ለማድረግ ወንንኩ። ለራሴ ቃል ገባሁ።

በብዙ ሺሆች እንደሚቆጠሩ የቅንጅት ደግፊዎች፣ እኔም የቅንጅት ድጋፍ ማህበራትን ተቀላቀልኩ። ምርጫ ቦርድን በመጠቀም፣ የ«ቅንጅት» ሕጋዊ ስም ለነ አየለ ጫሚሶ ቡድን ፣ ገዢው ፓርቲ በመስጠቱ፣ ቅንጅቶች በቅንጅት ስም መንቀሳቀስ ስላልቻሉ «አንድነት» የሚል ስም ይዘው ትግሉን ቀጠሉ። የቅንጅት ድጋፍ ማሀብራትም ወደ አንድነት ድጋፍ ማህበራት ተቀየሩ። የቅንጅት ወራሽ የሚባለዉን አንድነትም መደገፍ ቀጠልን።

የአንድነት ፓርቲን በመደገፍ የማደርጋቸውን አንዳንድ ተግባራት የታዘበ፣ ቅንጅትን ይደገፍ የነበረ አንድ ወዳጄ «ተቃዋምዊዎች የሚረቡ አይደሉም። ለምን ጊዜህን በነርሱ ላይ ታጠፋለህ ? ያኔ ስትደክመለት የነበረዉ ቅንጅት እንኳን ፈራርሶ የለም እንዴ ? » አለኝ።
ይህ አባባል ብዙዎች የሚሉት አባባል ነዉ። ብዙ ጊዜም ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ እንዲህ አይነት አስተያየቶች አንብቢያለሁ። «ቅንጅት ፈርሷል» የሚለዉን አባባል ግን በጭራሽ አልቀበለም። የቅንጅት ስም ላይኖር ይችላል። አሁን «ቅንጅት» ላንል እንችላለን። ያኔ የቅንጅት መሪ የነበሩ፣ ያኔ በነበሩበት ሁኔታ ላይኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ያኔ ቅንጅትን ቅንጅት ያሰኘው፣ ከምርጫ ቦርድ የተገኘ ስም፣ ወይንም መሪዎቹ አለነበሩም። ሕዝቡ ለነጻነት፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሰብአዊ መብት መከበርና ለኢትዮጵያዊነት የነበረዉን ግለትና ጥማት ማመላከቱ እንጂ። የቅንጅት ነገር፣ በዋናነተና በቀዳሚነት የተገናኘዉ ከሕዝብ ጋር ነበር። ስለዚህ «ቅንጅት ፈርሷ”» ማለት «ሕዝብ ተመችቶታል፤ ሕዝብ ደልቶታል፣ ሕዝቡ መብቱ ተከበሮለታል …. » እንደማለት ነዉ።

አሁንም የሕዝቡ ጥያቄ ያኔ የነበረዉ ጥያቄ ነዉ። አሁንም ህዝብ «የፍትህ ያለ ፣ የሰላም ያለህ፣ የሕግ በለያነት ያለህ፣ የመልካም አስተዳደር ያለህ» እያለ ነዉ። አሁን ሕዝብ «የዘር ፖለቲክ አልፈለግም፣ ኑሮ ተወደደ፣ ቀንበር በዛብኝ ፥» እያለ ነዉ።
ለምሳሌ ያኔ በቅንጅት ስም ይደረግ የነበረዉ እንቅስቃሴ አይነት፣ በሚሊዮኖች ለነጻነት ድምጽ በሚል እንቅስቃሴ ሥር ኢትዮጵያ ዉስጥ እየተፋፋመ ነዉ። የአንድነት ፓርቲ እና መኢአድ በባህር ዳር ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተዋል። የሚሊየምም ድምጽ ለነጻነት ክፍል ሁለት በቅርቡ ይታወጃል ተብሎ ይጠበቃል። መርሳት የሌለብን ደግሞ፣ እነዚህ አገር ቤት ያሉ ወገኖቻችን፣ ይህን አይነት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት፣ እየታሰሩ፣ እየተደበደቡ፣ ከሥራቸው እየተባረሩ ወዘተረፈ ነዉ። ፈረንጆች እንደሚሉት፣ “They are not talking the talk; they are walking the walk”::

ያኔ ቅንጅትን ስንደገፍ የነበርን፣ በጥቂት መሪዎች ስህተት፣ ተስፋ ቆርጠን ፣ ኢሕአዴግን እንደ ግዙፍና የማይነቃነቅ አድርገን ማየት የጀመርን፣ ከትግሎ ጎራ የሸሸን በጣም ብዙ ነን። ትግሉን የጎዱ፣ የሕዝቡን ኃይል አሳንሰው፣ ተስፋቸዉን በሌሎች አገሮች ላይ የጣሉ ግለሰቦችንና የፖለቲክ መሪዎች ላይ በማተኮር ወደ፣ ወደ ኋላ የተጎተትን ብዙ ነን። ነገር ግን ዋጋ እየከፈሉ ያሉትን፣ እነ እስክንደር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ፣ ርዮት አለሙ፣ ናትናኤል መኮንን የመሳሉትን እናስብ እላለሁ። ተስፋ መቁረጥ፣ በቀላሉ አቅጣጫችንን መቀየር፣ ሌሎችን ደካም ማለት፣ እጅ አጣምሮ እያወሩ መቀመጥ ቀላል ነዉ። የአላማ ጽናት ኖሮ፣ የደከሙትን እያገዙ፣ የሥራ ሰው መሆን ግን ከባድ ነዉ።

እንግዲህ በቅንጅት ወቅት አኩሪና ትልቅ ሥራ እንሰራ ለነበርን፣ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቼ፣ እንደገና ጽናቱ ይኖረን ዘንድ፣ አክብሮት የተሞላበትን ጥሪዬን አቀርባለሁ። «አንተ ምንድን ነህና ነው እንደዚህ አይነት ጥሪ የምታቀርበው ? ልትሉኝ ትችላላችሁ። አዋ የፖለቲካ ፓርቲ መሪ ወይንም የአንድ ድርጅት ሃላፊ አይደለሁም። እንደ ማናችሁም ፣ አንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ነኝ። ነገር ግን አንድ ነገር አውቃለሁ። እንደኔና እንዴናናት ያሉ ተራ ኢትዮጵያዉያኖች ናቸው ለኢትዮጵያ መፍትሄ የሚሆኑት። በዳያስፖራ ያሉ በሜዲያዉ የምናያቸውና የምንሰማችደው ጥቂት የታወቁ ሰዎች ሳይሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተራ ኢትዮጵያዉያን ሲንቀሳቀሱ ነው የኢትዮጵያን ትንሳኤ ማወጅ የምንችለው።

ዉድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣ ወደ ቀድሞዉ ቦታችን ተመልሰን፣ ከስሜትና ከጥላቻ በጸዳ መልኩ፣ ሕዝባችን መብቱ እንዲከበር የሚያደርገዉን ትግል እንደገፍ። ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁን !

የሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ ፌስቡክ ላይክ በማድረግ፣ እየተሰራ ያለዉን ነገር ይከታተሉ። የአንድነት ድህረ ገጽን በመጎብኝት የገንዘብ ፣ የሃሳብ ድጋፎዎትን ያበርክቱ።
https://www.facebook.com/MillionsOfVoicesForFreedomUdj
http://www.andinet.org/

Latest from Blog

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

ከሃይለገብርኤል   አያሌው የኦቦ ሲራጅና የወይዘሮ ፉንታዬ ልጅ ጃዋር መሃመድ ትላንትን ዛሬንና ነጋችንን ሊያሳይ የሚችል መጽሃፍ አዘጋጅቶልናል:: በእውነቱ መጽሃፉ ሊነበብ በሚችል የሃሳብ ፍሰት ተቀንብቦ በአነጋጋሪነቱ ቀጥሏል:: ጃዋርን እና የቄሮን ትውልድ በቅጡ ለመረዳት መጽሃፉ ማንበብ

የጃዋር የፖለቲካ ጅዋጅዌ! “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ’’

ጥር 2 ቀን 2017 ዓ/ም   January 10, 2025  በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡ ቤተ ሰብ፡ ወዳጅ ዘመዶቻችሁን ያጣችሁ: ልጆቻችሁን የቀበራችሁ፡ አካልችሁን ያጣችሁ፡ የተሰነዘረውን ብትር በመከላከል ላይ ያላችሁ፡ያለፈቃዳችሁ በመንግሥት ተጽእኖ ወደመግደልና

በኢትዮጵያዊነታችሁ፡ በኦርቶዶክሳዊ እምነታችሁ፡ በአማራነታችሁ፡ በአማረኛ ተናጋሪነታችሁ፡ በተሰነዘረባችሁ ብትር፡

January 10, 2025
መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ ¹⁵ የምድርም ነገሥታትና መኳንንት ሻለቃዎችም ባለ ጠጋዎችም ኃይለኛዎችም ባሪያዎችም ጌቶችም ሁሉ በዋሾችና በተራራዎች ዓለቶች ተሰወሩ ፥ ¹⁶ ተራራዎችንና   በላያችን ውደቁ በዙፋንም ከተቀመጠው ፊት ከበጉም ቍጣ ሰውሩን ፤ ¹⁷ ታላቁ የቁጣው ቀን  መጥቶአልና ፥ ማንስ ሊቆም ይችላል ? አሉአቸው ። ራእይ 6 ፤  15_17 ይኽ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ። የኢየሱስን ልደት ሰናከብር የየሐንስ ራእይን ማንበብ ጠቃሚ ይመስለኛል ። ምክንያቱም በመጨረሻው ዘመን

ከኢየሱስ የፍርድ ቀን በፊት በህሊናችን ውስጥ ፍቅርን ለማንገስ እንጣር 

የምጣኔ ሀብታዊ ፍጥ፣ የፖለቲካ፣ የእውነትና የሰብአዊ መብት ታጋይ፣ የአመኑበትን ነገር ለመናገር እንደ ፖለቲከኛ በቃላት ሳያሽሞነሙኑ ቀጥታ የሚናገሩት የሀገሬ ኢትዮጵያ ታላቅ ሰው ነበሩ “ዘር ቆጠራውን ተዉት፤ የአባቶቻችሁን ሀገር ኢትዮጵያን አክብሩ!”  አቶ ቡልቻ ደመቅሳ

ሀገር ወዳዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ

January 6, 2025
Go toTop