‹‹አገራዊ ምክክሩ ታሪክ ላይ ብቻ መንጠልጠል የለበትም›› ባህሩ ዘውዴ (ኤመሬተስ ፕሮፌሰር)፣ የታሪክ ተመራማሪ

ሪፖርተር

የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ዘመናዊ ታሪክ በጥልቀት በመመራመር በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችንና መጻሕፍትን ለአንባቢያን በማበርከት ባህሩ ዘውዴ (ኤመሬተስ ፕሮፌሰር) ተጠቃሽ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቀው ያውቃሉ የሚባልላቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ተመራማሪው ባህሩ (ኤመሬተስ ፕሮፌሰር)፣ የዩኒቨርሲቲውን የታሪክ ትምህርት ክፍል በበላይነት በመምራት አገልግለዋል፡፡ በአገር ውስጥ የሚገኙ የሲቪክና ሌሎች ገለልተኛ የሙያ ማኅበራትንና ተቋማትን በመሥራችነትና በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች በማገልገል ይታወቃሉ፡፡ ለኅትመት የተዘጋጁ ጆርናሎችን በአርትኦት ሥራቸው፣ በተለያዩ መድረኮች በሚያቀርቧቸው የጥናት ጽሑፎቻቸው በብዙዎች ዘንድ ዕውቅናን አትርፈዋል፡፡ የታሪክ ሊቅና  ዕውቅ  ምሁሩ ላበረከቷቸው ጽሑፎች በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን፣ በቅርቡ ተመሥርቶ ወደ ሥራ እየገባ ያለው የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች  ማኅበር እንዲቋቋም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡  ሲሳይ ሳህሉ ከታሪክና ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ባህሩ ዘውዴ (ኤመሬተስ ፕሮፌሰር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ዘመናት በኢትዮጵያ ውስጥ የተጻፉና እየተነገሩ ያሉ የተለያዩ ገጽታዎች ያሏቸው ትርክቶች በሕዝቡ መካከል ቅራኔ ሲፈጥሩ ይታያሉ፡ እነዚህን ቅራኔዎቹ ለመፍታት  ሙከራ ነበር ወይ? ከነበረስ ከሒደቱ ምን መማር ይቻላል?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- የተፈታበትን መንገድ ከማየታችን በፊት ችግሩ እንዴት ተፈጠረ የሚለውን ማየቱ ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ሁለት ነገሮች መናገር ይቻላል። አንደኛው የፖለቲካ ጫና ነው፡፡

የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ታሪክን ለራሳቸው በሚያመች መንገድ ስለሚተረጉሙ፣ ይህ ነው አንዱ ለትርክት መፈጠር ምክንያት የሆነው። በታሪክ ባለሙያዎችና በፖለቲከ አቀንቃኞች መካከል ያለው የታሪክ አተረጓጎም የተለያየ ስለሚሆን ነው ቅራኔው የተፈጠረው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የጋራ የሆነን ታሪክ ለሕዝቡ፣ በተለይም ለወጣቱ ትውልድ የማስተማር ሒደት መቋረጥ ነው፡፡ ከአፄው ዘመን ጀምሮ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ በሚገቡበት የመጀመሪያ ዓመት፣ ስለአገራቸው እንዲያውቁ ተብሎ አጠቃላይ ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ ጂኦግራፊና የማኅበረሰብ ጥናትን ጨምሮ፡፡ ታሪክ የጠቅላላ ትምህርት አንዱ ዓምድ ነበር፡፡ እናም ብዙዎቻችን በዚህ ክፍለ ትምህርት ውስጥ ካለን ሰዎች ይህንን ትምህርት ያላስተማረ ሰው የለም፡፡ እንዲያውም ብዙዎቹ ምሩቃን በኋላ ላይ ሲያገኙን፣ የአንደኛ ዓመት የታሪክ ትምህርት  እንዳስተማርናቸው ያስታውሱን ነበር፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የተውኔት አውራ - የሀገር ባንዴራ።

ይህንን አጠቃላይ ትምህርት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስና ጥሩ ማስተማሪያም ለማድረግ፣ በ1980ዎቹ አካባቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ክፍለ ትምህርት ጥሩ የማስተማሪያ መጽሐፍ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡

እንደ አጋጣሚ ሆኖ አንዳንድ የፖለቲካ ወገንተኞችን የሚያስኮርፉ ወይም የሚያስቆጡ አንድ ሁለት ቃላት ወይም ጉዳዮች ስለነበሩ በዚህ ምክንያት መጽሐፉ ታገደ፡፡ ይህ እንግዲህ የመጀመሪያው የቁልቁለት ጉዞ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ደግሞ ይባስ ብሎ የአንደኛ ዓመት ትምህርት ታጠፈና ተማሪዎች ስለአገራቸው ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ የሕዝብ አመጣጥና አሠፋፈር፣ ወዘተ የሚሉ ጉዳዮችን ምንም ሳያውቁ ቀጥታ ወደ መረጡት ትምህርት እንዲሄዱ ተደረገ፡፡ ይህ ለተፈጠረው ችግር የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ምክንያቱም ወጣቱ ትውልድ ስለአገሩ ምንም ሳያውቅ የፖለቲካ አጀንዳዎች ሰለባ መሆን ጀመረ፡፡ የችግሩ አመጣጥ ይህ ነው፡፡ ችግሩን በመፍታት ረገድ በቅርቡ ሙከራ ተደርጓል፡፡ ይኸውም የትምህርት ሚኒስቴር ማለትም በወቅቱ የነበረው የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ ካርታ መሠረት፣ ጠቅላላ ትምህርት ለጀማሪ ተማሪዎች እንዲሰጥ በመደረጉ ታሪክም እንዲሰጥ ተወሰነ። ከዚያ ባለሙያዎች ተፈልገውና ተመርጠው አንድ ረቂቅ አዘጋጅተው፣ ያ ረቂቅ ደግሞ ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ክፍለ ትምህርቶች ግብዓት ተገኝቶበት ሲያበቃ በመጨረሻ የሚያወዛግብ አንድ ትንሽ ነገር ተፈጥሮ፣ ለአንድ ዓመት ተቋርጦ ሥራ ላይ ሳይውል ቀርቶ ነበር። አሁን ግን ያ ነገር ተስተካክሎ በዚህ ዓመት ለጀማሪ ተማሪዎች ይሰጣል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ይህ እንግዲህ የመፍትሔው አንዱ አካል ነው የሚሆነው። ምክንያቱም ዞሮ ዞሮ ወጣቱን ነው መቅረፅ ያለብን፡፡ ወጣቱን ስለአገሩ ታሪክ ካላስተማርነው ከትምህርት ቤት ሲወጣ ሌላ ምንም ታሪክ አያውቅም፡፡ በዚህም በዚያም በየቦታው የሚጻፈውን ብቻ ይዞ በፖለቲካ ድርጅቶች የሚራመደውን ሐሳብ ብቻ ነው የሚያስተጋባው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ካርቱም ለምትገኙ ስደተኞች በሙሉ - በሱዳን የሚገኙትን 5ቱን የወያኔ ሰላዮች/ ተላላኪዎች ይወቁ

ሌላው ደግሞ ችግሩን ለመቋቋም የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ከአንዴም ሁለቴ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ተመሥርቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ዘላቂነት አላገኘም። አሁን የሰላም ሚኒስቴር ባደረገው ትልቅ ድጋፍ የታሪክ ባለሙያዎች ተሰባስበው ለአራት ቀናት በኩሪፍቱ ዘግተው ተወያይተው፣ በመጨረሻ ‹‹የኩሪፍቱ ስምምነት›› በሚል ባለሦስት ዓምዶች ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ አንደኛው ማኅበሩ የሚያግባባ የታሪክ የሚጻፍበት መንገድ እንዲቀይስና ያለውን ውዥንብር ለማጥራት ጥረት እንዲደረግ። ሁለተኛ የአንደኛ ዓመት ማስተማሪያ መጽሐፍ ዳር ደርሶ ሥራ ላይ እንዲውል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ማኅበሩ እንደገና እንዲቋቋም የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ማኅበር ቢቋቋም እንደ አንድ ባለሥልጣን መናገርና ክብደት ያለው አስተያየት መስጠት የሚችል የታሪክ ተጠሪ ድርጅት ይኖራል ማለት ነው፡፡ በታሪክ ማኅበሩ አማካይነት መጻሕፍትን መገምገም ይቻላል፡፡ አንድ መጽሐፍ ስለታተመና በትልቅ አጀብ ስለተመረቀ ብቻ ትክክል ነው ማለት አይደለም፡፡ ማንም ሰው በገንዘቡ ማሳተም ይችላል፡፡ ነገር ግን ያ መጽሐፍ ዋጋ የሚኖረው ወይም ሚዛን የሚደፋው በባለሙያ ተገምግሞ፣ በአስተማማኝ መረጃ ላይ የተመሠረተ ትክክለኛ ታሪክ ነው ሲባል ብቻ ነው፡፡ በአገራችን ግን ይህ አልተለመደም፡፡ በመሆኑም የታሪክ ምሁራን ማኅበር ይህንን ለመፈጸም ትልቅ ኃላፊነትና ብቃት አለው፡፡ እናም በዚህ መልክ ወደፊት ተስፋ የምናደርገው ይህ ማኅበር ከጠነከረ እነዚህን ጉድለቶች ማስተካከል እንደሚችል ነው፡፡

ነገር ግን በአገራችን የማኅበራት ሕይወት ቀላል አይደለም፡፡ አቅምና ሀብት ያስፈልጋል፡፡ የሕዝቡን ድጋፍ ለማግኘት ትልቅ ዘመቻ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በአባላት መዋጮ ብቻ መንቀሳቀስ አይቻልም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ የውጭ ድጋፍና በተወሰኑ ሚኒስትሮችም የሚደረጉ ድጋፎች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ራሱ መደገፍ መቻል አለበት፡፡ በተለይ አንድ አገራዊ ታሪክ አለ ብሎ የሚያምን ሁሉ መደገፍ አለበት፡፡ እንግዲህ በዚህ መንገድ የተሻለ ተስፋ ይመጣል ብለን እናስባለን፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ አሁን ለምትገኝበት የፖለቲካ ቀውስ መሠረቱ የማዕከላዊ መንግሥትን ሥልጣን በተቆጣጠረው አካል ውስጥ የተነሳ የሥልጣን ሽኩቻ ነው የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ዳግም የቀውሱ መሠረታዊ ምክንያት ለዘመናት ያልተመለሰና የቆየ የብሔረሰቦች የፖለቲካ ጥያቄ ወይም መታረቅ ያልቻለ የፖለቲካ አቋም እንደሆነ የሚገልጹም አሉ፡፡ እርስዎ አሁን ያለው የፖለቲካ ቀውስ መሠረታዊ ምክንያት ምንድነው ብለው ያምናሉ?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- የሥልጣን ሽኩቻ ብቻ የችግሩ መንስዔ አይመስለኝም፡፡  በመሠረቱ የኢትዮጵያ ታሪክ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ የማንኛውም አገር ታሪክም እንዲሁ አልጋ በአልጋ አይደለም፡፡ በሒደት ውስጥ ብዙ ችግሮች ተፈጥረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሽርሽር መልክ አይደለም የተፈጠረችው። ዳሩ ግን ይኼ በቁርሾነት ተይዞ የጥላቻ ዓይነት ታሪክ ወይም የአንድ ወገን የታሪክ የማቀንቀን ነገር በስፋት ተራግቧል። እናም ዋናው ችግር ይኼ ነው። የታሪክ ባለሙያዎች ሆን ብለው ያለፈን ታሪክ አይደብቁም፣ ይህ ነገር ሆኗል፣ ያ ተደርጓል ይላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም አገሮች መንግሥታት ሲፈጠሩና አገረ መንግሥት ሲመሠረት በሕዝብ ውሳኔ ሳይሆን፣ እንደ ክፉ ዕድል ሆኖ በጦርነት ነው፡፡ እንግዲህ የታሪክ ባለሙያዎችና የፖለቲካ አራማጆች ልዩነት ምንድነው ሲባል፣ የታሪክ ባለሙያዎች የተፈጠረውን ክስተት ይመዘግባሉ፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች ያንን ለጊዜያዊ ፍጆታና ለማቃቃር ይጠቀሙበታል፡፡ በዚህም የተነሳ በታሪክ ባለሙያዎችና በፖለቲካ አቀንቃኞች መካከል ያለው ልዩነት ይኼ ነው፡፡ የታሪክ ባለሙያዎች አይደብቁም፣ የተደረገውን ነገር ሆኗል ብለው ሲያስቀምጡ ግን ጉዳዩ ለዘለዓለም ቁርሾ ሆኖ ማባላትና ማፋጀት አለበት ብለው አያምኑም፡፡ በተለይም የተለያዩ ብሔረሰቦች አንድ አገር አለን የምንል ከሆነና አንድ አገር እንገነባለን የምንል ከሆነ፣ ያንን እንደ ታሪክ መዝግበን እናልፋለን እንጂ አሁን እንደሚታየው ለመበጣበጥ፣ ለመጠላላት ወይም የጎሪጥ ለመተያየት ምክንያት መሆን የለበትም ነው የምለው፡፡

ሪፖርተር፡- የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን እየተመሠረተ ነው፡፡ ወደፊት ሊካሄድ በታሰበው የምክክር ሒደት ታሪክ አንዱና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ሊፈጠር የሚችልን ወገንተኝነት እንዴት ማረቅ ይቻላል፡፡ በተለይም ክፉውንም ደጉንም ጉዳይ አስታርቆ የሚሄድ ሕዝብ ከመፍጠርና ወጥ የሆነ አገራዊ ፍቅር ለመፍጠር ምን መደረግ አለበት?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- አንደኛ ነገር ሊካሄድ በታሰበው አገራዊ ምክክር ላይ ታሪክ ብዙ ጫና እንዲያሳድር አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም ታሪክ በታሪክ ባለሙያዎች ይዘገባል፣ የሚያነበው ሰው ያነበዋል፡፡ ምክክሩን በተመለከተ ብዙ አጀንዳዎች አሉ፡፡ ስለዚህ የሚሻለው እነዚህ አጀንዳዎች ላይ ማተኮር ነው፡፡ ይሁን እንጂ አለመግባባት እስካለ ድረስ ደግሞ በተለይ የታሪክ ባለሙያዎችና ሌሎች የፖለቲካ አቋም አለን የሚሉ ወገኖች ባሉበት፣ ራሱን የቻለ ምክክር ቢደረግ ይኼ ምናልባት ወደ ተሻለ አቅጣጫ ሊያስኬድ ይችል ይሆናል፡፡ በሌላ አገርም የተደረገው ይኼ ነው፡፡ ነገር ግን የታሪክ ባለሙያ ሲባል እውነተኛ ባለሙያ እስከሆነ ድረስ አውቆና ሆን ብሎ የፖለቲካ አቋም አያራምድም፡፡ በእርግጥ ሰው መቶ በመቶ ፍፁም መሆን ስለማይችል ሳያውቀው የተወሰነ ዝንባሌ ሊያሳይ ይችላል፡፡ በመሠረቱ ግን የታሪክ ባለሙያ የሙያ ግዴታ አለበት፣ ሚዛናዊ ለመሆንና የሁሉንም አቅጣጫ ለማሳየት፡፡

ሪፖርተር፡- አልፎ አልፎ የተዛባ ታሪክ ለሕዝብ የሚያቀርቡ ስላሉ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- እነሱን የታሪክ ጸሐፊዎች ወይም ባለሙያዎች አንላቸውም፡፡ የታሪክና የሌላው ዘርፍ መሠረታዊ ልዩነት ምንድነው ካልክ የተፈጥሮ ሳይንስን (እንደ ኬሚስትሪና ባዮሎጂ) የወሰድክ እንደሆነ ራሱን የቻለ ሙያ ነው፡፡ ሒደቱን ካልጨረስክና ስለባዮሎጂ ወይም ኬሚስትሪ በዚያ ሙያ ካልተካንክ በስተቀር፣ ዝም ብለህ ተነስተህ ልትጽፍ አትችልም። በዚህ ረገድ ታሪክ የተለየ ባህሪ ነው ያለው፡፡ አንድ ሰው የተወሰነ ቁንፅል መረጃ ይዞ ታሪክ ነው ብሎ ሊጽፍ ይችላል፡፡ እያወዛገበ ያለውም ይኼ ነው፡፡ እውነተኛ ታሪክ ጸሐፊ ግን በቁንፅል መረጃ ሳያመሳክር ወይም ሁሉንም ወገን ሳያይና ሳያመዛዝን አይጽፍም፡፡ ሁለት ዓይነት የታሪክ ጸሐፊዎች አሉ፡፡ አንደኛው የፖለቲካ ጫና ያለበት ታሪክ የሚጽፍ ሲሆን፣ ሁለተኛው የታሪክ ባለሙያ ሆኖ የሚጽፈው ታሪክ ነው፡፡ ሁለቱም የተለያዩ ናቸው፡፡ አሁን የተመሠረተው የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ይህን የታሪክ ልዩነት ለይቶ ማውጣት ይጠበቅበታል፣ ይችላልም፡፡

ሪፖርተር፡- የአገር ፍቅርንና ታሪክን እንዴት ይመለከቷቸዋል?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያውያን የአገር ፍቅር የሚያከራክር አልነበረም፡፡ ነገር ግን ከ20ኛው መቶ አጋማሽ ጀምሮ በተለይ የተማሪው ንቅናቄ የብሔረሰብ ጥያቄን ካነሳ በኋላ፣ ለረዥም ጊዜ ፀንቶ የቆየውን ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ የመጣል ሁኔታ ታይቷል፡፡ ያ ነገር ገፍቶ ገፍቶ አሁን ያለንበት ሁኔታ ላይ ተደርሶ፣ ኢትዮጵያ ስትፈርስ ማየት ያስደስተኛል የሚል ያውም ከመሀል አገር የኢትዮጵያ ዕምብርት ከሚባል ክልል መሰማት ተጀመረ፡፡ ይኼ በጣም አዲስና የሚሰቀጥጥ ነገር ነው፡፡ በተወሰነ ደረጃ በእርግጥ የብሔረሰቦች ማንነት በባህል፣ በቋንቋና በመሳሰሉ ጉዳዮች መታወቅ አለበት፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያዊነት ኪሳራ መሆን የለበትም፡፡ ኢትዮጵያዊነት ዋና ማዕቀፍ ሆኖ በዚያ ላይ ደግሞ በብሔረሰብ ማንነት፣ በባህልና በቋንቋ መኩራት፣ መከባበር፣ ወዘተ ላይ አስታራቂ ሐሳብ ማምጣት አለብን፡፡ ምክንያቱም ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በጣም የጦዘው ከኢትዮጵያዊነት በበለጠ የብሔረሰብ ማንነት ነው፡፡ የታሪክ ትምህርት ማስተማር መታጠፍም ለዚህ አንዱ ነፀብራቅ ነው፡፡ እናም የዚያን ሒሳብ እየከፈልን ነው ያለነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን የብሔረሰብ ማንነትን ሳንክድ፣ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነት የበላይ መሆኑን የምናሳይበት ደረጃ ላይ መድረስ አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት አሁን ያለውን የፖለቲካ ቀውስ ለመፍታትና ቁልፍ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮችና የፖለቲካ ልዩነቶች ላይ መግባባት ለመድረስና አገረ መንግሥቱን ለማፅናት፣ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የታቀደው አገራዊ ምክክር የሚስተዋሉትን የፖለቲካ ችግሮች ምን ያህል ይፈታል ብለው ያስባሉ?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- ስለዚህ እንግዲህ አሁን ምላሽ መስጠት አልችልም፡፡ ኮሚሽነሮች ተሰይመው ምን ያህል ነፃነት እንደሚኖራቸው፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ይኖራል አይኖርም፣ እነ ማን የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ ይሳተፋሉ፣ እነ ማን ዝግጁ ናቸው፣ ወዘተ ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁሉ መሟላት ስላባቸው አሁን ባለንበት ሁኔታ ተነስቶ መተንበይ ወይም አስተያየት መስጠት ያዳግታል፡፡

ሪፖርተር፡- አገራዊ ምክክሩ የሚካሄድበት ወቅት በተረጋጋ የፖለቲካ ከባቢ ውስጥ ባለመሆኑ፣ እንዲሁም የተመረጠ መንግሥት ሥልጣን ላይ ባለበት ወቅት የሚካሄድ በመሆኑ፣ ችግሮቹን ለመፍታት ምቹ ይሆናል ብለው ያስባሉ?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- በጣም ችግር ነው፡፡ ምክንያቱም ጦርነት በሰሜን የአገሪቱ ክፍል እየተካሄደ ነው፣ እስካሁን አላለቀም፡፡ በመሀል አገርም ሰሞኑን እንደምንሰማው ከፍተኛ የሰላም ዕጦት አለ፡፡ የተወሰኑ የፖለቲካ ድርጅቶች ሒደቱ ተዓማኒነት የለውም፣ ስለዚህ አንሳተፍም ብለው አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡ ከባድ ፈተና ነው፡፡ ይህ ምክክር አስፈላጊነቱ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡ ነገር ግን ነባራዊ ሁኔታው ምን ያህል አመቺ እንደሆነ ግን ጥርጣሬ አለ፡፡

ሪፖርተር፡- የምክክር ሒደቱ ስኬታማ ሊሆን የሚችለውና ውጤቱም በፖለቲካ ማኅበረሰቡ ዘንድ ቅቡልነት ሊያገኝ የሚችለው፣ ምክክሩ ሁሉንም ወገኖች ያካተተ የሽግግር መንግሥት ሲኖር ነው የሚሉ ሰዎች ይደመጣሉ፡፡ ከሌሎች አገሮች ተሞክሮና ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ይህን ጉዳይ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- ያ ሁሉ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ የሽግግር መንግሥትን ሐሳብ ማቀንቀን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ይህ መንግሥት ፈቃደኛ ከሆነና በቅን ልቦና የሚይዘው ከሆነ እሱን ማገዝ ነው የሚሻለው እንጂ፣ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ማለት ራሱን የቻለ ፈተና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ ፖለቲካ ቅራኔን የፈጠሩ ቀላል የማይባሉ የፖለቲካ ታሪኮች ተዓማኒነት የሌላቸው፣ ወይም ደግሞ አሁን ባለው ትውልድ የፖለቲካ ትርጓሜ ተሰጥቷቸው ለፖለቲካ ቅራኔና ቁርሾ ምክንያት ሆነዋል የሚሉ ልሂቃን አሉ፡፡ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ? ለምሳሌ በቀደመው ዘመን የአማራ ገዥ መደብ የፈጸማቸው ተብለው የሚነሱ የጭቆና ታሪኮችን አሁን አማራ ተብሎ ቅርፅና ስያሜ ላገኘው የፖለቲካ ማኅበረሰብ የመስጠት፣ የተቀረው ማኅበረሰብ ደግሞ ተፈጸሙ ከተባሉት ጭቆናዎች እኔ ንፁህ ነኝ ይላል፡፡ ይህንን ተቃርኖ እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- መጀመርያ ነገር የአማራ ገዥ መደብ ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱም ገዥ መደቡ ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተውጣጣ ነው የነበረው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ምናልባት አማራ ዋናው ቦታ ላይ መገኘቱ ካልሆነ በስተቀር አማራም፣ ትግራዋይም፣ ኦሮሞም፣ ሌሎችም በተለያዩ የታሪክ ወቅቶች የገዥ መደብ ሆነው አልፈዋል፡፡ ስለዚህ ከእንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ መላቀቅ ያስፈልጋል፡፡ አሁን አሁን በአማራ ላይ የሚደርሰው ግፍ አንዱም ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ያለግባብ አንድ ብሔረሰብን ነጥሎ የኢትዮጵያ ችግር መንስዔ ለማድረግ መሞከር ስህተት ነው፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ የአገዛዝ ታሪክ ውስጥ ሁሉም ተሳትፏል፡፡ በዘመነ መሣፍንት ጊዜ የነበረው የኦሮሞዎች ሚና ቀላል አይደለም፡፡ ትግራይና አማራ በተለያዩ ጊዜያት በሥልጣን ላይ ተፈራርቀዋል፡፡ እንደ እነሱ ደግሞ ሌሎች የብሔረሰብ አባላት በገዥ መደብ ውስጥ ተሳትፈዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ጉዳይ ሁኔታውን ወደ ያልሆነ አቅጣጫ የሚወስድ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይ ደግሞ ያም ሆነ ይህ ግፍ ተሠራ እንበል፣ አሁን በዚያ ላይ ማላዘን አለብን ወይ? ይህን ስናብሰለስልና ስናመነዥክ መኖር አለብን ወይ? ወይስ ከዚያ መውጣትና አዲስ ምዕራፍ መጀመር አለብን? ያለፈው አልፏል፡፡ እሱን ለታሪክ ጸሐፊዎች ትተን እኛ ግን አዲሲቷንና የተሻለችውን ኢትዮጵያ መገንባት አይሻለንም ወይ የሚል መሆን አለበት አቅጣጫው፡፡

ሪፖርተር፡- በአገራዊ  ምክክሩ የፖለቲካ ልሂቃኑ ታሪክን እየጠቀሱ ያለ መስማማት አዝማሚያ ቢያሳዩ ይህንን ቅራኔ ለመፍታት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- ይህ የምክክር ሒደት ታሪክ ከተጫነው እንደ መጥፎ ነገር ነው የሚታየው፡፡ ታሪክ እንደ አንድ ዘርፍ መታየት አለበት እንጂ በሁሉም ቦታ ሁሉን ነገር ፈጻሚ፣ ወይም አድራጊና ለምክክር ሒደቱ መሳካትና አለመሳካት ምክንያት መሆን የለበትም፡፡ ታሪክ፣ ታሪክ ነው፡፡ በቃ አለቀ፡፡ እርግጥ የምክክር ኮሚሽኑ ዓላማ ሲታይ የትምህርትና የታሪክ ግንዛቤ ያስፈልጋል፡፡ በታሪክ ላይ የተወሰነ ግንዛቤ ያስፈልጋል፡፡ በታሪክ ላይ የተወሰነ ምክክር ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን አገራዊ ምክክሩ ታሪክ ላይ ብቻ መንጠልጠል የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- ሌሎች በተመሳሳይ ሒደት ላይ የነበሩና ችግራቸውን በውይይት የፈቱ አገሮች እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ የሚችሉ ይኖራሉ?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- እንዲህ ዓይነት ችግሮች የኢትዮጵያ ብቻ አይደሉም፡፡ ታሪክ በብዙ አገሮች ላይ ችግር ጥሎ ሄዷል፡፡ ነገር ግን እንደ እኛ አገር እጅግ የከረረበት የለም፡፡ ለምሳሌ አሜሪካን ብታይ የባርነት ታሪክ ራሱን የቻለ አወዛጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን የምታያቸው የአፍሪካ አሜሪካውያን ታሪክ በባርነት የጀመረ ነው፡፡ ከባርነት በኋላ ነፃ ወጡ ተብሎ እንኳን እስካሁን ድረስ ብዙ መከራና ግፍ ይደርስባቸዋል፡፡ ‹‹የጥቁር ሕዝብ ሕይወት ዋጋ አለው›› (Black Lives Matter) የሚል እንቅስቃሴ እስካሁን ድረስ እያተስተጋባ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ እኛ አገር የፖለቲካ ውዝግብ የፈጠረበት ብዙ የለም፡፡ በሌላ በኩል ጀርመንን ውሰድ፡፡ በጀርመን ሒትለርን የመሰለ ጭራቅ የሆነ ስንት ሚሊዮን አይሁዶችን የገደለ መሪ ነበር፡፡ ነገር ግን ጀርመኖች ከዚያ በኋላ ስህተት ተሠርቷል ብለው አምነው ሙዚየም እስከ ማቋቋም ደርሰዋል፡፡ ወጣቱ ትውልድ ያ ዘመን የጥፋት ዘመን እንደነበር እንዲገነዘብ የሆሎኮስት (ዕልቂት) ሙዚየም እስከ ማቋቋም ደርሰዋል፡፡ ሩዋንዳን ስታይ ከዚያ ከጅምላ ጭፍጨፋ በኋላ አገራዊ ታሪክ እንዴት መጻፍ ይቻላል ብለው ኮሚቴ አቋቁመው፣ የውጭ ምሁራን ሳይቀሩ ተሳትፈውበት ሰፊ የሆነ ምክክር አድርገዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ምክክር በኢትዮጵያም ማድረግ ይቻላል፡፡ የእኛን ነገር ያከበደው የፖለቲካ ድርጅቶች ጫና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክን እየጠቀሱ አለመግባት እንዲፈጠር ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ እንደ አገር መቀጠል ይቻላል ወይ?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- እንግዲህ በተቻለ መጠን ፖለቲከኞች ታሪክ ላይ ያላቸውን ጫና መቀነስ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም የአንድ አገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወሰነው በታሪክ ሳይሆን፣ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ላይ ተመርኩዞ ነው፡፡ ለምሳሌ የኤርትራን ጉዳይ ስታይ፣ ኤርትራ የመገንጠል እንቅስቃሴ ስትጀምር በመሠረቱ የነበረው የፖለቲካ ጥያቄ ነው፡፡ ፌዴሬሽን ነበር፣ ፌዴሬሽኑ ፈረሰ፡፡ ፌዴሬሽኑ ከፈረሰ በኋላ መጀመርያ ፌዴሬሽን ይመለስልን ነበር የኤርትራውያን ጥያቄ፡፡ ከዚያ ነፃ እንሁን፣ በቅኝ ግዛት ሥር ነው የወደቅነው የሚል እንቅስቃሴ ተጀመረ፡፡ ይህ የፖለቲካ ጥያቄ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የታሪክ ባለሙያ ያልሆኑ የሻዕቢያ ደጋፊዎች አዲስ ታሪክ መፍጠር ጀመሩ፡፡ ይህም ኢትዮጵያና ኤርትራ በታሪክ በፍፁም አይገናኙም፣ የተለያየ ታሪክ ነው ያላቸው ብለው አክሱምንም የኤርትራ ታሪክ አካል አድርገው የሚያወሩበት ጊዜ ነበር፡፡ ይኼ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ምክንያቱም በመጨረሻ የኤርትራ ጉዳይ የተዳኘው በታሪክ ሳይሆን፣ በጦር መሣሪያና በፖለቲካ የበላይነት ነው። ከዚያ በኋላ ደግሞ ምን ተገኘ ስትል በጣም ትንሽ ነው፡፡ በተጨባጭ የምታነሳው ነገር የለም፡፡ ግን በመሀል ታሪክ ሰለባ ሆነ፡፡ የተጣመመ ታሪክ፣ መሠረት የሌለው ታሪክ፣ አንድ የነበሩ ሕዝቦችን የተለያዩ ሕዝቦች ናቸው ብሎ የሚያወራ የፈጠራ ታሪክ ተስፋፋ። ስለዚህ ፖለቲከኞች በፖለቲካ፣ የታሪክ ባለሙያዎች በታሪክ ላይ ቢያተኩሩ የተሻለ የወደፊት አቅጣጫ ይኖራል ብዬ አምናለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅርብ ዓመታት በፊት በተለይ የመንግሥት ለውጥ ተደረገ ከተባለበት ጊዜ በፊት ታሪክ እያነሱ አንዱ ወቃሽ ሌላኛው ተወቃሽ በመሆን ግጭቶች እዚህም እዚያም ይስተዋሉ ነበር፡፡ ለውጥ መጣ ከተባለ ወዲህ የሚታየውን አለመግባባትና ቁርሾ እንዴት ያዩታል?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- ከለውጥ ወዲህ ያሉ ግጭቶች መነሻቸው በእኔ ግምት ሦስት ናቸው፡፡ አንደኛው አንድ የሆነ ጠንካራ መንግሥት አለመኖር ነው፡፡ እንዳሻው ማሰርና መግደል ከሚችል መንግሥት ለዘብ ወዳለ ስትመጣ ትንሽ የመፍታታት ሁኔታ አለ፡፡ መንግሥት ደካማ ነው ብሎ መገመት አለ፡፡ ድሮ ከነበረው ቆንጠጥ የሚያደርግ ዓይነት ተወጥቶ ላላ ያለ ሥርዓት ሲመጣ፣ ምንጊዜም ማዕከላዊ መንግሥት መዳከሙ የማይቀር ነው፡፡ ሁለተኛው ሕወሓት ወደ መቀሌ ሸሽቶ ከመሸገ በኋላ ያለው ምንም እንኳ ትክክለኛው መረጃ ባይገኝም፣ አዲሱ ሥርዓት እንዳይረጋጋ ለመበጥበጥ የሚያደርጋቸው ዕርምጃዎች እንደነበሩ ከፍተኛ ግምት አለ፡፡ ሦስተኛ በተለይ ኦነግ ሸኔ ለምን እንዲህ ሊገን እንደቻለ በእውነቱ እንቆቅልሽ የሆነ ነገር ነው፡፡ የኦሮሚያ ክልል የራሱ ጠንካራ የፀጥታ ኃይል እያለው፣ ኦነግ ሸኔ እንዲህ እንዴት መግነን እንደቻለ ጥያቄ የሚያጭር ነው፡፡ ለሚታዩት ግጭቶች የተለያዩ ምክንያቶች አሉ እንጂ ከታሪክ ጋር የሚያያዝ አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- የተመሠረተው የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር በአገራዊ ምክክር ሒደቱ ምን ዓይነት ሚና ይኖረዋል?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- በመሠረቱ ማኅበሩ ብሔራዊ ምክክሩ እንዲሳካ ሙያዊ ግዴታውን ይወጣል፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ ለጋ ስለሆነና የገንዘብ አቅሙም ደካማ በመሆኑ፣ የሰው ኃይልም ችግር ስላለበት እንቅስቃሴው የተገደበ ነው፡፡ ከዚያም በላይ አባላቱ በተለያዩ ክልሎች ስለሚገኙ ኃላፊነቱ የሚወድቀው በአብዛኛው አዲስ አበባ ባሉት ላይ ነው የሚሆነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ለሕዝብ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር ይሠራል፡፡ ኮሚሽኑን እንግዲህ ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሥራ ሲጀምር በታሪክ ላይ ጥያቄ ከቀረበና እንድንሳተፍ ከተጠየቅን እንቢ አንልም፣ ፈቃደኛም ነን፣ ግዴታም አለብን።  ኮሚሽኑን ማጣጣል አያስፈልግም፣ ከመጠን በላይም ተስፋ ማድረግ አያስፈልግም፣ በሰከነ ሁኔታ መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ የአገረ መንግሥት ግንባታ ሒደት ፅኑ መሠረት ላይ ያልቆመ በመሆኑ፣ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓትና ባህልን መትከል እንዳልተቻለ ይገልጻሉ፡፡ በመፍትሔነትም ሕዝብና መንግሥትን የሚያስተሳስር ማኅበራዊ ውል መቀረፅ እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ እርስዎ እንደ አንድ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ በጥልቀት የመረመረ ተመራማሪ ይህንን የመፍትሔ ሐሳብ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌሰር ባህሩ፡- ማኅበራዊ ውል አሁን ባለው ሁኔታ መገለጫው ሕገ መንግሥት ነው። ኢትዮጵያ በመሠረቱ ከአንድ ፅንፍ ወደ ሌላ ፅንፍ ነው የሄደችው፡፡ የመጀመሪያው በተለይ በአፄውና በደርግ ዘመን በጣም የተማከለና ኢትዮጵያዊነቱ በጣም ጎልቶ የወጣ አንዳንዴም በተጋነነ ሁኔታ፣ ከዚያ ደግሞ ዥው ብሎ እንደ ፔንዱለም ወደ ሌላ ፅንፍ ነው የሄደው ወይም ሌላ ዋልታ ነው የረገጠው፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ ይልቅ ብሔረሰቦች የበለጠ ዋጋ አላቸው የሚል ነው፡፡ እናም አዲስ ማኅበራዊ ውል ሲባል አዲስ ሕገ መንግሥት፣ ኢትዮጵያን ማዕከል ያደረገ፣ ነገር ግን የብሔረሰቦችን መብት፣ ባህልና ቋንቋቸውን የሚያዳብርና የሚያከብር መሆን አለበት፡፡ ይህ ነው የሚታየኝ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share