አቻምየለህ ታምሩ_የታሪክ ተመራማሪ!
የታሪክ ተመራማሪው እና ተንታኙ አቻምየለህ ታምሩ የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያወጣውን መግለጫ — “ከፍትፍቱ አጉርሱኝ ከመረቁ [ግን] ጾመኛ ነኝ!” እንደማለት ነው ሲል የሚከተለውን ሰፋ ያለ ምላሽ ሰጥቷል:_
የፋሽስት ወያኔ የሃይማኖት ክንፍ “የሀገረ ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” የሚል ሰም በሰጠው ድርጅት በኩል ከወደ መቀሌ በትግርኛ ቋንቋ ያወጣውን መግለጫ አነበብኩት።
“የሀገረ ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን”ተብዮውን የፋሽስት ወያኔ የሃይማኖት ክንፍ ያልኹት “የሀገረ ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” ለማቋቋም የመሰረት ድንጋይ የተጣለው በፋሽስት ወያኔ መሆኑና ፋሽስት ወያኔ ሲፈጠር ጀምሮ የነበረ ፕሮጀክት መሆኑ ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት ክንፉ በትግርኛ ቋንቋ ያወጣው መግለጫም በቤተ ክርስቲያን ስም ከመሰጠቱ በስተቀር ፋሽስት ወያኔ በዋናው ጽሕፈት ቤቱ በኩል ከሚያወጣቸው መግለጫዎች ጋር ምንም ልዩነት የሌለው በመሆኑ ጭምር ነው።
ፋሽስት ወያኔ ራሱን ማሌሊት ነኝ እያለ በገብረ ኪዳን ደስታ በኩል ግን የማሌሊቶች ቤተክርስቲያን ለመቋቋም ሲንቀሳቀስ የነበረ ጉድ ነው። እነሆ ያ እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቶ የማሌሊቶች ቤተ ክርስቲያን ስለመቋቋሙ ከወደ መቀሌ ሰምተናል!
መግለጫው በበርካታ የቂል ተረቶች፣ ነውረኛ ዲስኩሮችና አስቂኝ ጥያቄዎች የተሞላ ነው።
የፋሽስት ወያኔው የሃይማኖት ክንፍ አክሱምን ማዕከል ያደረገውን የኢትዮጵያ ቀደምት ስልጣኔ የትግራይና የትግሬ ብቻ ለማድረግ ያልሞነጨረው ቅራቅንቦ ተረትና የፕሮፓጋንዳ ዲስኩር የለም።
መግለጫው ስለ አክሱም ስልጣኔና ስልጣኔ የትግራይና የትግሬ ብቻ እንደነበር የታወቀ ነው ይላል።
የመግለጫው ጸሐፊዎች የአክሱምን ስልጣኔ ስልጣኔው በነበረበት ወቅት ላልነበሩት ለትግሬና ለትግራይ ለመስጠት ያን ያህል ሲኳትኑ አክሱም ውስጥ ዛሬም ድረስ ቆመው የሚገኙት የድንጋይ ላይ ጽሑፎችና በቁፈራ የተገኙ የጥንት ሳንቲሞች ስለ አክሱም ስልጣኔ ባለቤቶች ማንነት ከያዙት ማስረጃ ጋር መቃረናቸው ግድ አይሰጣቸውም።
በአክሱም ዘመን የነበረው ስልጣኔ ባለቤቶች፣ የንጉሠ ነገሥት መንግሥቱ ልዩ ልዩ ክፍሎች፣ ነገዶችና አሰፋፈራቸው እዚያው አክሱም ውስጥ በቆሙና በተቀበሩ ድንጋዮች አልፎም እስከ ደቡብ አረቢያ ድረስ በውጭ አገር ቋንቋዎችና የአገር ውስጥ ቋንቋዎች በሆኑት በግዕዝና በአማርኛ ቋንቋ ተጽፏል።
ስለዚህ ታሪክ ማስረጃ የሚሻ ቢኖር የአክሱምን የድንጋይ ላይ ጽሑፎችና የጥንት ሳንቲሞች በቦታው በመገኘት ከ110 ዓመታት በፊት ያጠናው ጀርመናዊን የታሪክ ፕሮፈሰር ኢኖ ሊትማን እ.ኤ.አ. በ1913 ዓ.ም. “Deutsche-Aksum Expedition” በሚል ርዕስ በአራት ቅጾች ያሳተመውን መጽሐፍ ማንበብ ይችላል።
አክሱም ውስጥ በሚገኙት የድንጋይ ላይ ጽሑፎችና ሳንቲሞች ላይ የአክሱም ስልጣኔ ባላቤቶች እነ ማን እንደሆኑ ዛሬም ድረስ የሚገኙ የልዩ ልዩ ነገዶች ስም ተጠቅሰዋል።
በዚህ የነገዶች ስም ዝርዝር ውስጥ ትግሬ ወይም ትግራይ የሚል የነገድም ሆነ የአካባቢ ስምና ዝርዝር የለም።
በሃይማኖት ስም መግለጫ ያወጡት “የሀገረ ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” ካድሬዎች ትግሬንና ትግራይን የአክሱም ስልጣኔ ብቸኛ ወራሽ ሲያደርጉ በማይዋሽበት ዘመን እየኖሩ አክሱም ውስጥ የቆሙት የድንጋይ ላይ ጽሑፎችና ተቆፍረው የተገኙ ሳንቲሞች ያስተዛዝቡናል ብለው ለመጠንቀቅ ባይሞክሩ እንኳን ያን ያህል ውሸት መድፈራቸው በፈጣሪያቸው ዘንድ ያስጠይቀናል ብለው የማይፈሩ ግብዞች ናቸው።
የአክሱምን ስልጣኔ ጨምሮ የትኛውም የኢትዮጵያ ሥልጣኔ የየትኛውም ነገድና ሃይማኖት አይደለም። የኢትዮጵያ ስልጣኔ ሁሉ ባለቤቱ ከአንድ ነገድና ሃይማኖት በላይ ነው።
የትኛውም ነገድና ሃይማኖት የትኛውምንም የኢትዮጵያን ሥልጣኔ በብቸኛነት የራሱ የሚያደርግበት የታሪክም ማስረጃ ሊያቀርብ አይችልም። በሌላ አነጋገር የኢትዮጵያ የሆነ ሁሉ ባለቤቱ ከአንድ ነገድና ሃይማኖት በላይ ነው።
የአክሱም ታሪክና ስልጣኔ በነገድ ይከፋፈል ቢባል የማይሆነው የትግሬና የትግራይ ብቻ ነው።
ማዕከሉን አክሱም ያደረገው የኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥልጣኔ በብቸኛነት ከትግሬም ሆነ ከትግራይ ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም።
ማዕከሉን አክሱም ከተማ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት በነበረበት ወቅት ዛሬ ትግራይ ተብሎ የሚታወቀው አካባቢም ሆነ ትግራይ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ትግሬ የሚባል ሕዝብ አልነበረም።
በነገራችን ላይ የአክሱም ታሪክ የትግሬ ሥልጣኔ እንደነበር የሚያሳይ አንድ እንኳን ብጣሽ የታሪክ ማስረጃ [የድንጋይ ላይ ጽሑፍና በቁፋሮ የተገኘ የአርኪዮሎጂ ማስረጃ] አለኝ የሚል የትግሬ ብሔርተኛ ፕሮፈሰርና ዶክተር ቢኖር ውለታ ከፋይ መሆናችንን ከወዲሁ ማሳወቅ እንወዳለን!
በቤተ ፋሽስት ወያኔ ነውር የሚባል ነገር ስለሌለ የፋሽስት ወያኔ የሃይማኖት ክንፍ የግዕዝን ስነ ጽሑፍ የትግሬና የትግራይ ሊያደርገው ይቃጣዋል።
ትግርኛ የግዕዝ ፊደል ከተፈጠረ ከሺ ዓመታት በኋላ የግዕዝን ፊደል ተጠቅሞ መጻፍ የጀመረ ቋንቋ ነው። እንደ አማርኛ ሁሉ ትግርኛም ከግዕዝ ፊደል ተውሶ ስለሚጽፍ ግዕዝን ትግሬ የፈጠረው አያደርገውም።
በስነ ልሳን ረገድም ከትግርኛ ቋንቋ ይልቅ ኤርትራው ውስጥ ዛሬም ድረስ የሚነገረው ትግረ ቋንቋ ለግዕዝ ይቀርባል። በቤተ ወያኔ እሳቤ መሰረት ግዕዝ የነገድ ቅርበት ይሰጠው ከተባለ ኤርትራ ውስጥ ላለው ትግረ [ትግሬ አላልኹም] እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ትግሬ አይቀርብም።
እንግዲህ! የፋሽስት ወያኔ የሃይማኖት ክንፍ የኢትዮጵያን ስልጣኔ የአክሱም ስልጣኔ ብቸኛ ባለቤት ያደረገው ትግራይና ትግሬ ያዋሰው አድርጎ ያቀረበው ትግሬም ሆነ ትግራይ የአክሱም ስልጣኔ በነበረበት ወቅት ባልነበሩበት ነው።
ጥያቄው የፋሽስት ወያኔ የሃይማኖት ክንፍ ካድሬዎች ኢትዮጵያዊ አይደለንም ብለው “የሀገረ ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” ከመሰረቱ የኢትዮጵያን ስልጣኔ፣ የኢትዮጵያን ፊደል፣ የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ሃይማኖት ለምን አብረው አይጠሉትም?
ሌላው “የሀገረ ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” በሚል ስም በወጣው መግለጫ ከምናገኛቸው አስቂኝ ጥያቄዎች አንዱ ኢትዮጵያን ምግብ፣ መድኃኒት፣ የስልክ፣ የውኃ፣ የመብራትና የባንክ አገልግሎት ባስቸኳይ ለ[ሀገረ] ትግራይ እንድታቀርብ የጠየቁበት ማስጠንቀቂያ አዘል ጥያቄ ነው።
ኢትዮጵያዊ አይደለንም ብለው ከኢትዮጵያ በመገንጠል የራሳቸው የሆነን “የሀገረ ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” ካቋቋሙ አገራቸው ያልሆነችውን ኢትዮጵያን ምግብ፣ መድኃኒት፣ የስልክ፣ የውኃ፣ የመብራትና የባንክ አገልግሎት ባስቸኳይ ለ[ሀገረ] ትግራይ እንድታቀርብ ለምን ይጠይቃሉ?
ባጭሩ የፋሽስት ወያኔ የሃይማኖት ክንፍ ካድሬዎች “የሀገረ ትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን” ካቋቋሙና ኢትዮጵያን ከጠሉ ሁሉን መጥላት እንጂ ኢትዮጵያን እየጠሉ “ከፍትፍቱ አጉርሱኝ ፤ ከመረቁ [ግን] ጾመኛ ነኝ” እንዳለው አይነት ቂላቂልነት የኢትዮጵያ የሆነውን ለምን ይወዳሉ? የተለየን ነን ብለው ኢትዮጵያ ከጠሉ የኢትዮጵያ የሆነውን ሁሉ አብረው ለምን አይጠሉትም? ኢትዮጵያን ከጠሉ የኢትዮጵያን ነገር ለምን ይወዱታል? እስቲ ጠይቁልን?!