“ዘጠኝ ቦላሌ…” ከይኸነው አንተሁነኝ

ከይኸነው አንተሁነኝ

የክህደት ቁልቁለት አሉ ታላቁ ምሁር!!! የክህደት ውርስ የበቀል ዛር እያስጎራ፣ የሚሆነውንም የማይሆነውንም እያስቀባጠረ ሃያ አንድ ዓመት እያንደረደረ ወርውሮ እዚህ ያደረሰው ሕወሃት ስለመድረሱ እንጅ ወደ ፊት ስለሚሆነው ወይም ስለሚያደርገው ከግምት በላይ የሚያውቀው ነገር ያለ አይመስልም። አውቃለሁ ብሎ ያቀዳቸው ተማከርኩ ብሎ ያወራቸው ሁሉም እንዳይሆን እንዳይሆን እየሆኑበት መሆኑ ይሰማል። ብዙ የተነገረለት ስንት የተባለለት ”የሕወሃቱ የእድገት ትራንስፎርሜሽን”ም ብዙም እንዳልጨበጠ የሚወራው ሳይሆን እየሆነ ያለው የምድሩ ላይ እውነት እያሳበቀበት ነው። ወትሮም ያልነበረው የሁለት አሃዝ ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ፉከራም ወደ ሗላ እየባረቀ ”ለነዚህ ያህል ዓመታት ሁለት አሃዝ ተከታታይ እድገት ለምን ድህነትንና ስደትን በመጠኑ እንኳ ሊቀርፍ አልቻለም?” የሚለውን የዓለም ማሕበረሰብ ጥያቄ ባልተሳከረ መልኩ ለመመለስ ለሕወሃት አስቸጋሪ ሆኖበታል። ምክንያቱም የኑሮ ውድነቱ፣ ርሃብ እና ችግር የሚያንገላታው የሕዝባችን ቁጥር፣ የተማረ የሰው ሃይል ስራ አጥነት እንደጉድ መጨመር፣ ሁሉን አቀፍ ስደት ለመናገር ከሚያስቸግር በላይ መሆን እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከምንም ጊዜ በላይ ዋጋው  ረክሶ የታየባቸው ዘመናት በሙሉ በሕወሃት የአገዛዝ ዘመን በተለይም ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት አመጣሁ እያለ በሚለፍባቸው በነዚሁ ዓመታት ነበርና ነው። ለዚህም ይመስላል የዘንድሮው የሕወሃት የኢኮኖሚ እድገት ትንበያ ለዓመታት የሙጥኝ ያላትን ያችን ጉደኛ አስራ አንድ ቁጥር ለቆ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ወዳስቀመጡት የእድገት ትንበያ አሃዝ ለመድረስ ወደ ታች የተምዘገዘገው።

መብትን የመጠቀም ጉዳይም ጥንቅቅ ብሎ በሕወሃት ጉያ ገብቶ ከተቆለፈበት ቆየ። ሕወሃቶች የዓለምን ማሕበረሰብ ጩኸት በመፍራት ወይም ለፖለቲካችን ይጠቅሙናል ብለው ለይስሙላ ከተዋቸው በጣት የሚቆጠሩ ፀሐፊዎችና ተናጋሪዎች በቀር ማንም እንዳይጽፍ እጁን አስረዋል፣ እነዳይናገር አፉን ለጉመዋል በስርአት አንዳያስብም  በተለያዩ መንገዶች ህሊናውን ቶርች በማድረግ ሕዝባችንን እያደነዘዙት ይገኛሉ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ጃዋር መሐመድ ተከበብኩ ካለ የሚገደለው አማራ ነው፣ ከአብይ ጋር በስልጣን ከተጣሉ የሚገደለው አማራ ነው

በፖለቲካው ረገድም እውቅና አግኝተው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉ የፖልቲካ ፓርቲዎች ሕዝባቸውን ሰብስበው ማነጋገር፣ ሰላማዊ ሰልፍ ጠርተው ባንድ ጉዳይ ላይ ጥያቄ ማቅረብ፣ ለሕዝባቸው ለሀገራቸው ይበጃሉ ይጠቅማሉ ያሉዋቸውን ሃሳቦች አቅርበውና አጸድቀው የሀገሪቱ ሕግ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት በጠባቡ ሕወሃት በሽብርተኛነት እያስወነጀለና እያስቀጣ መሆኑን በዚህ ሰአት ማብራራት ለቀባሪው አረዱት እንዳይሆን ትቸዋለሁ።

ሕወሃት በተከተለው የተንጋደደ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ ሕዝባችን በኑሮ ውድነት ተመታ፣ በርሃብ በስደት ተንገላታ፣ ብዙው የበይ ተመልካች ሆነ፣ ልመና ማሳፈሩ ቀርቶ ደንብ እየሆነ መጣ፣ ስርቆት የጀግንነት መለኪያ እንጅ የማሕበረሰብ ጠባሳ መሆኑ ተረሳ፣ ማንኛውንም የቢሮ ስራ ለማስፈጸም እንደ ባላባቱ ስርአት እጅ መንሻ የመጀመሪያው ተመራጭ መንገድ እየሆነ መጣ፣ ከራስ ይልቅ ለሕዝብ ከእኛ ይልቅ ለሀገር ያሚል ሕሊና እንዲጠፋ ክረምት ከበጋ ተሰራ፣ ባጠቃላይ ሕወሃት መራሉ የወደቀ ራዕይ የሌለው ተስፋው የደበዘዘ የተነገረውን ዝም ብሎ የሚቀበል እንጅ ለምን ብሎ የማይከራከር ትውልድ ለመፍጠር ተጋ። የተሳካለትም ይመስላል። ሌላው ዓለም በዳቦ ሂሳብ ላይ አምስት ሳንቲም ስትጨመር ሀገሩን በሙሉ በሰልፍ ሲያተራምስ እየታየ በሀገራችን የሚወርደው ይህ ሁሉ የመብት ረገጣና አድሎ፣ ግርፋቱና እስራቱ ሕዝባችንን አደነዘዘው እንጅ አላስነሳውምና። ይህ የሕዝባችን ዝምታም ሕወሃት በያዘው የመከፋፈል መንገድ እነዲገፋበት ሁሉንም የስልጣን ቦታ በራሱ ሰዎች እንዲቆጣጠር አደረገው እንጅ የአመራር አንጀት አልፈጠረለትም።

ከአዲስ አበባ እስከ መቀሌ ከአዋሳ ናዝሬት እስከ ባህርዳር የህወሃቱ ገዥዎችና ጀሌዎቹ የአገዛዝ ወንበራቸው ላይ ቢያፈጡም የሻጉራ መተያየታቸውን ግን አላቆሙም- ዘጠኝ ቦላሌ… መሆኑ ነው ነገሩ ። የአመለካከት ልዩነት ጥቂት እንዴው ትንሽ ከመስመር የወጣ ቡድንተኝነት ከተገኘም ከሕወሃት የግል አብዮት ሃዲድ ማስፈንጠሪያ በስርአት ያልተተገበረው የይስሙላው መተካካት ተግባር ላይ ይውላል። ስልጣን ዘመድ ወገን የለውም ያባላል ያጫርሳል። ሕወሃት ለዚሁ ለማይረባ ስልጣን ስንቱን አራግፎ እዚህ እንደደረሰ እራሱ ያውቀዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአላሙዲ ፌደሬሽን የኢትዮጵያውያኑን ፌዴሬሽንን የገነጠሉትን ከአመራርነት አባረረ

በሂወት የሌሉትም ሆኑ አሁን ነፍስ ይዟቸው የሚነገታገቱት ሕወሃቶች ሀገር ለማጥፋት አንድ ሆነውታግለው ለእንብርታቸው የተጋጩ፤ አብረው እየዋሉ የማይተማመኑ፤ እየተሻሹ የሚገፋፉ፤ እየተሳሳቁ የሚጠራጠሩ፤ ከሀገራችን አልፈው ምስራቅ አፍሪካን ሕወሃት ሕወሃት ያሸተቱ። ምላሳቸው ከዶለዶመ ራዕያቸው ከወየበ በሗላ ባቅም ማነስ ከተሰናበቱበትና ከዘራ ከጨበጡበት ወጣት ተተኪዎችን ረስተው ባባራ እድሜ   የስልጣን ወንበር ናፍቆት ያነቃቸው የሙት መንፈስ የጠራቸው የዘመናችን ጉዶች ናቸው። ባሁኑ ወቅት ስለ ሀገር የሚነገር ስለ ሕዝብ የሚሰራ መልካም ራዕይ የላቸውም ሕወሃቶች ከመቧደንና መተራመስ ከመጋባትና መፋታት በቀር።

ይህ ወቅት ታዲያ ሕዝባችን ከገባበት የሞራል ውድቀት እንዲወጣ ብሔራዊ መነሳሳት በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰበክበት ወቅት መሆን አለበት። ይህ ጊዜ እጅ ለእጅ ተቃቅፈን፣ ልብ ለልብ ተሳስረን፣ ሃሳብ ለሃሳብ ተቆራኝተን ቀን ከሌት አንድነትን እንድንዘምር የሚሰራበት መሆን ይገባዋል። ይህን ታዲያ ሀገር እየመራሁ ነው የሚለው ሕወሃት እንዳይከውነው የራሱ ተፈጥሮ ስልጣን ሙስና ቡድንተኝነትና ዘረኝነት ከጋረደው የሕዝባችንን ሁሉን አቀፍ ሰቆቃ ለመመከትና የተሻለ ራዕይ እንዲኖረን ለማድረግ ኢትዮጵያዊ ነኝ የምንል ዜጋዎች ሁሉ ይህን ጨቋኝ አገዛዝ በማስወገድና ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ስርአትን በመገንባት ሀገራችንን ማዳን ሕዝባችንንም ማጽናት ይጠበቅብናል። አበቃሁ።

Share