January 15, 2022
1 min read

ጥልመት ይብቃ – ውነቱ ደሳለኝ

ጣይ የወጣ መስሎኝ
ማልጄ ደስ ብሎኝ
ፈንጥዤ ቦርቄ
ፈክቼ ደምቄ፤
ምነው አሁን ከፋኝ
ገለማ ከረፋኝ
ገና ሳልጠረቃ
ጨነገፈ አበቃ።

ይህ የሀገሬ ጀግና
ሥመ_ጥር ገናና
ለሦስት አስርት ዐመት
ሲ’ቀላ ሲበለት
ሲኖር ተኮድኩዶ
ሲነጉድ ተሰድዶ፤
ይህን ለማርክሻ
ዋገምትና ፋሻ
መላ ምነው ጠፋው
ዘዴ ምነው ራቀው?
ማቆሚያ ብልሃቱ
ማስወገጃ ስልቱ።

ጥልመት ከነገሰ ስንጠብቅ ጣይቱን
መከራና እንግልት ካበራየው ቤቱን
ሰቆቃው ካየለ ከጠፋለት ለከት
ከይህ በላይ የትአል እየኖሩ መሞት?

እንግዲያስ!

መውዜሬን አምጡልኝ ወዲህ በሉ ጦሬን
የእናቴን የአባቴን የአያት ቅድመ አያቴን
ቃል አለብኝና ዘለአለም እንዳይፈርስ
ህያው ሆኖ እንዲኖር አንድም ሳይፋለስ
ፍንን ብዬ ልሂድ እንደ አንበሳ ደቦል
ምንሽሬም ያግሣ ቀለሄም ይንበልበል
ደሜም ይሁን ጅረት አጥንቴም ይከስከስ
ነፍሴም ሰማይ ትውረስ ስጋዬም ትቀደስ።

እውነቱ ደሳለኝ
ጥር 7 2014 ዓ ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop