ከላይ ሆነን ስናይ – ገለታው ዘለቀ

ፕላም አይላንድ የተባለች የፓሲፊክ ውቅያኖስ ደሴት ላይ አንዳለሁ ከዚህ በፊት ኣጫውቻችሁ ነበር። ዘወትር ጠዋት ከመኝታየ ስነሳ በምእራብ በኩል ያለውን በር ከፈተ ኣድርጌ ዐይኖቼን ጣል አድርጌ ከፊት ለፊት የተንጣለለውን ውቅያኖስ አያለሁ። ይህ የምኖርበት ቤት ከውቅያኖሱ ጫፍ 50 ሜትር ኣካባቢ ነው የሚርቀው። የሚገርመው ታዲያ ውቅያኖሱ በቀን ሁለት ጊዜ አካባቢ ኣንዴ በጣም ይጠጋና ጢም ብሎ ሞልቶ ይታያል፣ ሰዓታት ይቆይና ደግሞ ወደ ኋላ ይሸሽና ዝቅ ብሎ ይታያል። በቀን ሁለት ጊዜ አካባቢ ውቅያኖሱ እንዲህ ይጫወታል። ይህ ሁናቴ ሃይ ታይድ ሎው ታይድ (High tide & low tide) እየተባለ ይጠራል። የሚገርመው ይህ ክስተት በየቀኑ ከሚለዋወጡ የኣየር ንብረት ክስተቶች ጋር የተያያዘ አይደለም። ብዙ ዝናብ ጥሎ ከተማው ተጥለቅልቆ ነገር ግን ውቅያኖሱ ከጫፉ ጎድሎ የተወሰኑ ሜትሮች ከምድር ጫፍ ላይ ወደ ኋላው ሸሽቶ ይታያል። ደግሞ በጠራራ ጸሃይ ጊዜ ድንገት ጢም ብሎ ሞልቶ ከደጃፍ ደርሶ ይታያል። ይህ ውቅያኖስ ሲሞቅ የሚሞቀው ሲበርድ የሚበርደው ኣይደለም ጎበዝ። ውቅያኖሱ ወደ ኋላ ወደፊት የሚያጫውተው ጉዳይ አንድ ከፍ ያለ የተፈጥሮ ህግ ነው። ይህ ህግ የጸሃይና የጨረቃ ስበትና የመሬት ዙረት ህግጋት ናቸው። ለነዚህ ህጎች እየተገዛ ነው ወዲያ ወዲህ የሚለው። ይህ ኣስደናቂ ክስተት ውቅያኖስን ተንተርሰው የተፈጠሩ ከተሞች ሁሉ የሚያዩት የዘወትር የአለማችን ክስተት ነው። ታዲያ እንደለመድኩት ዛሬ ማለዳ ስነሳ በምእራቡ በር በኩል ያለው በር ላይ ቆሜ ውቅያኖሱን ልታዘብ ቆምኩ። ዛሬ ደግሞ የማለዳዋ ጸሃይ ደምቃለች። ነገር ግን ውቅያኖሱ ጢም ብሎ ሞልቶ ከደጃችን ቀርቦ ታየኝ። ፎቶ አነሳሁትና High tide ………..ብየ ወደ ዘወትር የማለዳ ስራየ አዘነበልኩ።
plamisland scaledከዚህ የውቅያኖስ እንቅስቃሴ አንድ ነገር እማራለሁ። ከፍ ባሉ ህጎች ይተዳደራል። በየቀኑ የሚመጡ አካባቢያዊ ለውጦች የሚያወዛውዙት ኣይደለም። እንደ ወንዝ ደራሽ የለውም። የሰው ልጅም ለመርህ እንዲሁ ተገዢ መሆን አለበት…………። የማለዳውን ትዝብቴን ዘና ትሉ ዘንድ ካጫወትኳችሁ ዘንዳ ዛሬ ስላለኝ ወንድማዊ መልእክትና የልብ ሸክም ልንገራችሁ።
ሃገራችን ኢትዮጵያ የገባችበትን የጦርነት ኣዙሪት ሳስብ እጅግ ያሳስበኛል ይዘገንነኛል። የዚህ ጦርነት ዳፋ ደግሞ በተለይ ድሃውን ህዝብ ሰላሙን፣ ዳቦውን፣ ቤቱን ሁሉ ይነጥቃል። እጅግ ብዙው ህዝባችን ደግሞ ድሃ ነውና ይህ ህዝባችን ሰላሙን ፣ ዳቦውን፣ ቤቱን ሁሉ ያጣል ማለት ነው። በተለይ አማሮች፣ አፋሮች፣ ትግሬዎችና ኦሮሞዎች የዚህ ጦርነት ዳፋ ብዙ ጉስቁልናን አምጥቶባቸዋል። ዛሬስ ሃገራችን ጦርነትን የምትቋቋምበት ምንም ጎን የላትም። የዓለም ህዝብ ያቀርብ የነበረው እርዳታም እያለቀ ነው ተብሏል። በዚህ ጦርነት ላይ ተጨምሮ ሶማሌ ክልልና ደቡብ ኣካባቢ ድርቆች እያጠቁን ነው። በዚህ ጊዜ በፍጥነት ወደ ተኩስ አቁም ውሳኔ መግባትና ችግሮችን በሰላም መፍታት ግዴታችን ሆኑዋል። ከዚህ በፊት የነበሩ የስምምነት መድረኮች ኣልተሳኩምና ዘላለም ኣይሳካም ኣይባልም። ትናንት ጦርነት ተደርጎ ነበርና ዛሬ ስምምነት የለም ኣይባልም። ለሁሉም ጊዜ አለው ወገኖቼ። ኣማጽያንና መንግስት በኣለም ላይ ይዋጉና ደግሞ ይደራደራሉ። ይሄ በኣለም የታየ ነገር ነው። ደርግና ወያኔ ብዙ ጊዜ ተደራድረዋል። ሻእቢያና ደርግ ብዙ ጊዜ ተደራድረዋል። በተዋጊ ሃይሎች መካከል ድርድር ሁል ጊዜም ያለ ፖለቲካዊ ክስተት ነው። አሁንም ግዴላችሁም ለድርድር እንደገና አንድና ሁለት እድል መስጠት አይገድለንም። እንደገና ሰከን ብሎ የድሃውን ጉስቁልና ኣይተን መምከር ያስፈልጋል። ህወሃት የትግራይን ህዝብ ለጦርነት መስበቁን ያቁም። ህዝቡ በችግር መከራውን እያየ ስለምን ጦርነትን ትሰብካላችሁ? መንግስት ልበ ሰፊ ሆኖ ድርድርን ያስብ። ድርድር ኣይጠላም። የሚጠላው በድርድሩ ላይ የሚነሳው ሃሳብ ሃገር ኣፍራሽ ሲሆን ለማንም የማይጠቅም ሲሆን ነው። በድርድር ጊዜ ተቃውሞና ድጋፍ መልካም ነው። ነገር ግን ድርድር የሚባል ነገር ኣታሰሙን ማለት ጤነኛ ነገር ኣይደለም። የፖለቲካ ሃይሎችም ቢሆኑ ችግሮች በጠረንጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ ነው መግፋት ያለባቸው። ህዝቡን ምንም ፋይዳ ለሌለው ነገር ኣናስጨርስ። አማራና ትግሬ በወልቃይት ጉዳይ ለምን ይጫረሳሉ? ሃገሪቱ ብሄራዊ ምክክር ላደርግ ነው ከዚያም የህገ መንግስት ማሻሻያ አደርጋለሁ አያለች አይደለምን? መቼስ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ የዚህ ምክክር ውጤትና የመፍትሄ ኣሳብ ወልቃይትን ለትግራይ የሚሰጥ ነው ብየ አላምንም። የፌደራል ስርዓቱ ከምክክሩ በሁዋላ ማሻሻያ ሲያደርግለት ወልቃይትን ለአማራ የሚሰጥ ነው ብየ ኣላምንም። እኔ ከምክክሩ ማግስት የምጠብቀው ነገር ወልቃይት የኣማራም የትግራይም ኣትሆንም። ታዲያ ዛሬ አማራና ትግሬ ሲተላለቅ ለምን ዝም አንላለን? ከምክክሩ በሁዋላ ወልቃይት የኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው የምትሆነው። ወልቅይት ብቻ ኣይደለችም ኣዲስ ኣበባ፣ መቀሌ ፣ ባሀዳር ወዘተ ሁሉ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ቤቶች ይሆናሉ ብየ ኣምናለሁ። ታዲያ የምክክራችን መዳረሻ ወደዚህ ከፍ ያለ ጉዳይ የሚያደርሰን ከሆነ ዛሬ ኣማሮችና ትግሬዎች በወልቃይት ጉዳይ ሲጋደሉ ለምን ዝም እንላለን? ምክክሮች የሚፈቱትን፣ ስርዓታዊ ለውጦች የሚፈቱትን ችግር ይዞ ህዝባችን መተላለቅ የለበትም። በኣፋርና በትግራይ መካከል፣ በሶማሊያና በኣፋር መካከል በድንበር ጉዳይ ወገኖቻችን ለምን ይተላለቃሉ? ሃቀኛ ምክክር ስናደርግ እኮ የኣፋር ህዝብ ድንበሩ ሞያሌ ነው። የኣማራው ድንበር ሞያሌ ድረስ ነው። የትግሬው ድንበር ሞያሌ ድረስ ነው። ተመካክረን የኔ የኔ…… የሚባል ቀርቶ የእኛ ወደሚል ከፍታ ለመራመድ ያሰብን ሰዎች ዛሬ በዋዜማው በድንበር መደባደብ የለብንም። እኔ እሰከሚገባኝ ድረስ ጎንደር የኔ የኔ የሚለው የለውም። ባለፈው ጊዜ የሃገራችን ትግል ብሄር ተኮር ሆኖ በተነሳበት ወቅት የጎንደር ወጣት በየቦታው የሚፈሰው የኦሮሞ ደም ደሜ ነው ብሎ ሲነሳ የኦሮሞው ወጣት ከማዶ ሆኖ የአማራው ደም ደሜ ነው ብሎ ተነሳ። ይህ የሚያሳየው የኣዛምድ ፖለቲካ፣ የደም ሃረግ ፖለቲካ፣ በምድራችን ውስጥ ቦታ የለህም፣ ሃገራችን የሁላችን ናት፣ እጣ ፈንታችን ኣንድ ነው ማለት ነው። አማሮች የኔ የሚሉት የላቸውም። ትግሬው የኔ የሚል የለውም። ኦሮሞው የእኔ የሚል የለውም። ደቡብ፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻጉል፣ ሃረር፣ ሶማሊያ ሁሉም የሃገሩን ኣንድነት የሚወድ ህዝብ ነው። ጽንፈኛ ፖለቲከኞች ናቸው መከራ የሆኑን። ስለዚህ ፖለቲከኞች በሃገራችን ውስጥ ሰላም መጥቶ መተሳሰሪያ መርሆዎቻችንን ኣሻሽለን ወደ ተሻለ ልማትና ሰላም እንድናመራ መስከን ያስፈልገናል። ለሰሜኑ ጦርነት ሰላማዊ መንገድ ይፈለግለት። የኣማሮች፣ የትግረዎች፣ የደቡቡ፣ የኦሮሞው፣ የሶማሌው፣ የሁሉም ብሶት ያብቃ። ሰው ሰራሽ መከራው ያብቃና ገበሬው ከኣፈሩ ጋር ታግሎ በምግብ ራሱን ይቻል ቢያንስ በረሃብ አንቅጣው። ምክክር ውስጥ ስንገባ በሙሉ ልብና በቅንነት መሆን አለበት ። ምክክራችን እንዲሰምር ከላይ ሆነን ከፍ ብለን እንይ። የሰፈር ድንበር ጉዳይ ካብከነከነን እንደሃገር ጠንካራ ህብረት ለመገንባት እንቸገራለን። እግዚአብሄር ይርዳን።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.