January 15, 2022
10 mins read

ከመንግሥት የሚጠበቅ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን በተመለከተ ከዓለም-አቀፋዊ የኢትዮጵያውያን ማሕበረ ሰብዓዊ ድርጅቶች የተሰጠ መግለጫ

ጥር 7 ቀን 2014 ዓ.ም.

የትግራይ ሕዝብ ነፃ-አውጭ ግንባር (ትሕነግ) ጥቅምት ፳፬ ቀን ፪ ሽህ ፲፫ ዓ.ም. በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን-ዕዝ ጦር ላይ ድንገተኛ የጥቃት እርምጃ በመውሰድ ከፍተኛ የአገር-ክኅደት ወንጀል ከፈጸመበት ጊዜ አንስቶ፣ በመንግሥት በኩል የተወሰዱትን እጅግ በጣም አደናጋሪ የሆኑ እርምጃዎችን፣ እንዲሁም ሊወሰዱ ሲገባ ችላ የተባሉትን ጭምር፣ በትዕግሥት እና በትዝብት የተመከተው የኢትዮጵያ ሠፊ ሕዝብ፣ በመሪዎቹ ላይ ያሳደረው እምነት እየነጠፈ እና እየሟሸሸ መሄዱን በሃዘኔታ እና በቁጭት እየተመለከትን እንገኛለን።

ኢትዮጵያችን በአገር-በቀል ጽንፈኛ አሸባሪ ቡድኖች እና በባዕዳን ጠላቶቻችን የተናበበ ዘመቻ ተወጥራ በተያዘችበት፣ በተዘመተባት እና ለጥቃት ተጋልጣ ዜጎቿ ለጅምላ መፈናቀል እና ለዘግናኝ እልቂት በተዳረጉበት አሣዛኝ ሁኔታ፣ በመንግሥት በኩል የታየው ድክመት እና ግልጽነት የጎደለው አሠራር፣ በአገር-ወዳድ እና ቅን-አሳቢ ኢትዮጵያውያን ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አሳድሯል።

በመጀመሪያ፣ ባለፈው ዓመት ሰኔ ሃያ-አንድ ቀን በመንግሥት በኩል የተወሰደውን ግብታዊ “የተናጠል የተኩስ ማቆም ፖለቲካዊ ውሣኔ” ተከትሎ፣ በአፋር እና አማራ ክልል ነዋሪዎች ላይ ታሪክ የማይረሳው ዘግናኝ ወንጀል ተፈጽሞአል፣ በንብረት ላይ መጠነ-ሠፊ ውድመት እና ዘረፋ ደርሶአል፣ እንዲሁም ከታዳጊ እስከ አዛዉንት ሴቶች ላይ አሰቃቂ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እንዲፈጸም እየሆነ ይገኛል።

ቀጥሎም፣ ከሰኔ ሃያ-አንዱ የተሳሳተ ውሣኔ ትምሕርት ካለመውሰድ በሚመስል መልኩ፣ መንግሥት ታኅሣሥ ፲፬ ቀን፣ “ድል ስለተገኘ እና ትሕነግ በወረራ ከያዛቸው የአፋር እና የአማራ ክልሎች ሙሉ-በሙሉ (100%) ተቸንፎ ስለወጣ” ጦርነቱን አቁሟል የሚል መግለጫ መስጠቱ፣ ኢትዮጵያውያንን እጅጉን አስገርሟል፣ አበሳጭቷል፣ አሳዝኗልም።

ይባስ ብሎም፣ ከአገራቸው ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የምዕራቡ ዓለም በአገራቸው ላይ የሚያደርገውን ተቀባይነት የሌለውን ጫና ለማውገዝ እና የአገራቸውን ክብር ለማስጠበቅ በዓለም-አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ባሉበት እና በትሕነግ ወረራ ምክንያት የተፈናቀሉ እና የተጎዱ ወገኖቻቸውን ለመርዳት በተሠማሩበት ጊዜ፣ አሁንም ባልታሰበ መልኩ፣ በከፍተኛ ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው እስር-ቤት የሚገኙ በአሸባሪነት የተፈረጀባቸው ድርጅት አባል የሆኑ ግለ-ሰቦች እንዲፈቱ መወሰኑ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አንጀት የሚቆርጥ፣ በመንግሥት ላይ አመኔታ ያሚያሟሽሽ እና እጅጉን የሚያሳስብ ክስተት ሆኖ ተግኝቷል። በይበልጥ አሳሳቢ ያደረገው ደግሞ፣ የውሣኔው ያልተጠበቀ መሆን ብቻ ሳይሆን፣ ከጀርባው የታዘለ የማይታሰብ ጉድ ይኖራል የሚል ግምት መኖሩ አጠራጣሪ አለመሆኑ ነው። ለዚህም፣ በመንግሥት በኩል በማብራሪያ መልክ የሚሰጡ ምክንያቶች እርስ-በርስ የሚጣረሱ እና ትርጉመ-ቢስ መሆናቸው ጥርጥሬውን ምክንያታዊ ሊያደርገው በቅቶአል።

ስለዚህ፣ ውድ አገራችን የምትገኝበትን እጅግ ፈታኝ ጊዜ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት፣ ከተደቀኑ ሥጋቶች መታደግ ይቻል ዘንድ፣ በአገር-ውስጥም ሆነ ከአገር-ውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ መንግሥታቸው በሚሠራው ሥራ ሁሉ ግልጽነት እና ተጠያቂነት እንዲኖረው፣ በከፍተኛ የኃላፊነት መንፈስ እና ቁርጠኝነት አበክረው በመጠየቅ፣ ያላቸውን የትውልድ ባላደራነትን እና ሚና እንዲወጡ እና በተግባር እንዲያዉሉ አጥብቆ ማስገንዘብ ያስፈልጋል።

ስለሆነም፣ በተለይም ለሚከተሉት ጉዳዮች መንግሥት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ፣ ወገኖቻችን አበክረው እንዲጠይቁ እናሳስባለን፤

  1. መንግሥት በእስር ላይ የነበሩ እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁ ድርጅቶች መሪዎችን በድንገት ከእስር እንዲፈቱ ያደረገዉን ውሣኔ እንዲሽር እና፣ በተጨማሪም ትሕነግን እና ሌሎችንም የሽብር ድርጅቶች በቀጣይነት ስጋት እንዳይፈጥሩ፣ ለአንዴ እና ለመጨረሻ እንዲያጠፋ፤
  2. የአገርን ደኅንነት እና ዘለቄታዊ ጥቅም በሚጎዳ ሁኔታ፣ በጊዚያዊ የፖለቲካ ስሌት አሸባሪ ቡድኖችን ለማግባባትም ሆነ የውጭ ኃይሎች የሚያሳድሩትን ጫና ለማባበል፣ መንግሥት ምንም ዓይነት እርምጃዎች እንዳይወስድ። በተለይም ትሕነግ በጉልበት ይዞአቸው በነበሩት፣ እንደ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት እና ራያ በመሳሰሉት ቦታዎች የሚኖሩት ስዎች ጥቅምና መበትን ሊጎዳ የሚችል ምንም አይነት ዉሳኔ ለመስጠት መንግሥት እንዳይከጅል፤
  3. ከአሁን በፊት ለተፈጸሙ ጥፋቶች እና ለተሠሩ ስህተቶች መንግሥት እውቅና ሰጥቶ ኃላፊነት እንዲወስድ እና ሕዝብን ይቅርታ እንዲጠይቅ። በይበልጥም፣ ሃዘኑን በውስጡ ይዞ መልሶ ለመቋቋም በመውተርተር ላይ ያለው የአማራ እና የአፋር ክልሎች ሕዝብ ለዳግም ፍዳ እየተዳረገ በመሆኑ እና ወደፊትም እንዳይሆን፣ ያለ-አንዳች ማመንታት እና ያዝ-ለቀቅ በሌለበት ሁኔታ፣ አስቸኳይ ወታደራዊ እርምጃ መንግሥት እንዲወስድ።

በመጨረሻም፣ በአገሪቱ በየጊዜው የሚከሰቱትን ሁኔታዎች በጽሞና እየተከታተልን፣ ለሁኔታዎቹ ተመጣጣኝ መልስ ለመስጠት ከምንጊዜውም ይበልጥ በቁርጠኝነት የተዘጋጀን መሆናችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ልናረጋግጥ እንወዳለን።

ፈራሚ ድርጅቶች

  1. Adwa Great African Victory Association (AGAVA)
  2. Amhara Heritage Society of Minnesota (AHSM)
  3. Association of Concerned Ethiopians in the Diaspora (ACED)
  4. Association of Former Army Officers (AFAO)
  5. Consortium of Ethiopian Civil Society Organizations (TIBIBIR)
  6. Ethiopian Dialogue Forum (EDF)
  7. Ethiopian American Development Council (EADC)
  8. Ethiopian Veterans Association (EVA)
  9. Ethiopiawinnet – Council for the Defense of Citizen Rights (E-CDCR)
  10. Global Alliance for the Right of Ethiopians (GARE)
  11. Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause (GAJEC)
  12. Global Amhara Coalition (GAC)
  13. Major Lemma Woldetsadik Memorial Foundation
  14. Menelik Hall Foundation (MHF)
  15. Network of Ethiopian Scholars (NES)
  16. Radio Yenesew Ethiopia
  17. Selassie Stand Up, Inc.
  18. The Ethiopian Broadcast Group
  19. Vision Ethiopia (VE)
  20. Worldwide Ethiopian Civic Associations Network (WE-CAN)
  21. Yeamara Hizb Sirchit

 

ግልባጭ

  • ክብርት ወ/ሮ ሳህለ-ወርቅ ዘውዴ፣ ፕሬዘደንት
  • ክቡር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር
  • ክቡር አቶ ደመቀ መኮንን፣ ም/ጠቅላይ ሚኒስትር እና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር
  • ክቡር አቶ ታገሠ ጫፎ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ
  • ክቡር አቶ አገኝሁ ተሻገር፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ
  • ክብርት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ፣ የፈደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዘደንት
  • ክቡር ዶ/ር ጊዲዎን ጢሞቲዎስ፣ ፍትሕ ሚኒስትር
  • ክቡር አቶ አዎል አርባ፣ የአፋር ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር
  • ክቡር ዶ/ር ይልቃል ከፋለ፣ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop