ለቸኮለ! ቅዳሜ ታኅሳስ 30/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ ፕሬዝዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጀኔራል ብርሃኑ ጁላ በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የፊልድ ማርሻል ማዕረግ እንደሰጡ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዐቢይ አሕመድ አቅራቢነት፣ በጠቅላላው የአንድ ፊልድ ማርሻል፣ 4 የሙሉ ጀኔራልነት፣ 14 የሌትናል ጀኔራልነት፣ 12 የሜጀር ጀኔራልነት እና 58 የብርጋዴር ጀኔራልነት ማዕረጎችን ጨምሮ 101 ከፍተኛ መኮንኖች የማዕረግ ዕድገት ተሰጥቷቸዋል። የሙሉ ጀኔራል ማዕረግ ያገኙት፣ ጀኔራል አበባው ታደሠ፣ ጀኔራል ባጫ ደበሌ፣ ጀኔራል ሐሰን ኢብራሂም እና ጀኔራል ጌታቸው ጉዲና ናቸው። የማዕረግ ዕድገቱ የተሰጠው በኃይል አመራር እና በውጊያ የላቀ ጀብዱ ለፈጸሙ መኮንኖች እንደሆነ ተገልጧል።

2፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሀገሪቱ ጦር ሠራዊት የወታደራዊ ማዕረግ ደረጃ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል። በወታደራዊ ማዕረግ ማሻሻያው መሠረት የፊልድ ማርሻል ማዕረግ በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍተኛው ወታደራዊ ማዕረግ ሆኖ የተጨመረ ሲሆን፣ ማዕረጉ 5 ኮከቦች ይኖሩታል። በወታደራዊ ማዕረግ ምልክቶች ላይ ደሞ በዘንባባ ምትክ ጋሻ እና አንበሳ አዲሶቹ ምልክቶች ሆነው ተመርጠዋል። በኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ታሪክ እስከ ትናንት ድረስ ከፍተኛው ወታደራዊ ማዕረግ ባለ አራት ኮከብ ሙሉ ጀኔራል ማዕረግ ነበር።

3፤ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ የኢትዮጵያ መንግሥት የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ በርካታ እስረኞችን መፍታቱን በአድናቆት እንደሚያዩት በጽሕፈት ቤታቸው በኩል አስታውቀዋል። ጉተሬዝ አክለውም፣ በሰሜን ኢትዮጵያ ከዓመት በላይ የዘለቀው ግጭት ባስቸኳይ እንዲቆም፣ ተፋላሚ ወገኖች ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እና በሀገሪቱ ሁሉን ዓቀፍ ብሄራዊ ውይይት እና የእርቅ ሂደት እንዲጀመር ጥሪ አቅርበዋል። በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ከሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅርብ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ዋና ጸሃፊው አክለው ገልጸዋል። ጉተሬዝ ይህን ያሉት፣ መንግሥት ትናንት የኦፌኮ፣ ባልደራስ እና የሕወሃት የቀድሞ አመራሮችን ከእስር ሲፈታ ለይቅርታ እና ብሄራዊ ዕርቅ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ መግለጹን ተከትሎ ነው።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ምን ይባላል ? መንፏቀቅ ወይስ መንፈቅፈቅ !! -ማላጂ

4፤ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ነገ በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ “የሚሊዮኖች ጉዞ” በሚል መሪ ቃል እንዲካሄድ የታቀደው ሰልፍ ለሌላ ጊዜ መተላለፉን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ኤጀንሲው ሰልፉን ለምን ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ እንዳስፈለገ እና ሰልፉ ወደፊት መቼ እንደሚካሄድ ማብራሪያ አልሰጠም። ሰልፉ በመንግሥት ጥሪ መሠረት ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገራቸው የገቡ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አንዳንድ ምዕራባዊያን መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩትን ያልተገባ ተጽዕኖ ለማውገዝ የታለመ ነበር።

5፤ መንግሥት ትናንት ምኅረት ያደረገላቸው የኦፌኮ እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ አመራሮች ከወህኒ ወጥተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደተቀላቀሉ አስታውቀዋል። ከኦፌኮ ጃዋር ሞሐመድ፣ በቀለ ገርባ እና ደጀኔ ጣፋን ጨምሮ በጃዋር ሞሐመድ መዝገብ የተከሰሱ ሌሎች እስረኞች በሙሉ ተፈተው ቤታቸው ገብተዋል። ከባልደራስ ፓርቲ ደሞ የፓርቲው ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ እና ምክትል ሊቀመንበሩ ስንታየሁ ቸኮል ዛሬ ከፓርቲው አባላት እና ደጋፊዎች ጋር በአካል እንደተወያዩ እና ፓርቲው ባሁኑ ወቅት ቅድሚያ ትኩረቱ የሀገር አንድነትን ማስጠበቅ እንደሆነ መግለጻቸውን ፓርቲው አስታውቋል። መንግሥት የሕወሃት የቀድሞ አመራሮች የሆኑትን ስብሃት ነጋን፣ ቅዱሳን ነጋን፣ አባዲ ዘሙን፣ ሙሉ ገ/እግዚአብሔርን እና ኪሮስ ሐጎስን ጭምር ከእስር መፍታቱን ገልጧል።

6፤ የተመድ ጸጥታው ምክር ቤት በሱዳን ቀውስ ላይ በቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ በዝግ ስብሰባ ሊመክር እንደሆነ የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ዘግቧል። ምክር ቤቱ በሱዳን ቀውስ ላይ እንዲመክር ስብሰባውን ከጠሩት የምክር ቤቱ አባላት መካከል አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ኖርዌይ እና አየርላንድ ይገኘበታል። በሱዳን የተመድ ተወካይ ቮልከር ፔርዝ ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሐምዶክ በፍቃዳቸው ከሥልጣናቸው ከለቀቁ ወዲህ በሀገሪቱ ስላለው ሁኔታ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ዘገባው ገልጧል። ሱዳን እስካሁን አዲስ ጠቅላይ ሚንስትር አልተሾመላትም። [ዋዜማ ራዲዮ]

ተጨማሪ ያንብቡ:  ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ለቪኦኤ ቃለምልልስ ሰጡ | ስለአንዳርጋቸው ጽጌ፣ ስለኦሮሞ ሕዝብ ተቃውሞ፣ ስለሚያደርጉት ጥንቃቄ ተናገሩ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share