ወይፈን ሆይ ነቃ በል!

ጅብና ጥንብ አንሳ በላም ላይ ዶልተው፣
ተካፍለው ሊበሏት ቆራርጠው ዘልዝለው፣
ለሰላሳ ዓመታት ተማክረው ተስማምተው፣
ጅቡ ባለስልጣን ጥንብ አንሳ አሽከር ሆነው፡፡

በልቶ እማይጠግብን ጅብ ግፉ ጣለውና፣
ጥንብ አንሶች አረፉት ስልጣኑን ያዙና፡፡

በስልጣን ዘመኑ ሆዱ የሰፋው ጅብ፣
እንዴት ይዋጥለት ዳረጎት መቀበል፣
ጥንብ አንሳ ተሚባል ተድሮው ጥሩ አሽከር?

ጥንብ አንሶች ተጅቡ በስልጣን ተጣልተው፣
ስንት ወይፈን አስፈጁ ላምን አዳኝ መስለው፡፡

ጅብ ሰክሮ ሲመጣ አተላውን ቅሞ፣
ጥንብ አንሳን ሊያወረደው ተስልጣን ዠልጦ፣
ወይፈንና ኮርማ አዳነው ተዋግቶ፣
ለላሚት ጥንብ አንሳው ተጅብ ይሻል ብሎ፡፡

ነገር ግን ጥንብ አንሳ የድሮው ጅብ አሽከር፣
ለጊዜውም ቢሆን ስልጣኑን ሲስያከበር፣
ለጅብ መኖር ሲፈቅድ ተወንዙ ባሻገር፣
መናቆር ጀምሯል ተወይፈን ኮርማ ጋር፡፡

ጥንብ አንሳ እርግቦችን ጅብ በግ እንደማይሆን፣
ከሰላሳ ዓመት ውጪ ማን ይንገርህ ወይፈን?

የሰላሳ ዓመቱ ታሪክ ሲመረመር፣
ጆፌ ትርፍራፊ ጉርሻ ለመቀበል፣
ስንቱን ወይፈን ኮርማ በጅብ አስበልቷል፡፡

እባክህ ወይፈን ሆይ ዛሬ እንኳን ነቃ በል፣
ጅብና ጥንብ እንሳ የተጣሉ ቢመስል፣
እውነት አይምሰልህ እንዳትንዘላዘል፣
ለአያሌ ዘመናት በአንድ ማድ በልተዋል፣
ላሟን በጦር ወግተው ደሟን ጠጥተዋል፣

ዛሬም የጥንብ አንሳ ተጅብ ጋር ድርድር፣
አንተኑ ዳግመኛ በጅብ ለማስወረር፣
መሆኑን አጢነህ አካኬ ዘራፍ በል፣
አንድ ላይ ከትመህ ምከርና ዘክር፣
በቀንድህ በሻኛህ ክብርህን አስከብር፡፡

በላይነህ አባተ ((abatebelai@yahoo.com)
ታህሳስ ሁለት ሺ አስራ አራት ዓ. ም.

ተጨማሪ ያንብቡ:  ባለታላቅ ታሪክ ነኝ ኢትዮጵያዊ - እስፋው ረጋሳ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share