ዘግይቶ ባገኘነው ዜና: ለቸኮለ! ማክሰኞ ኅዳር 28/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

ለቸኮለ! ማክሰኞ ኅዳር 28/2014 ዓ.ም

ዘግይቶ ባገኘነው ዜና

ዓለማቀፉ ብሄራዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የአንደኛነት ደረጃ እውቅና እንደሰጠ ኮሚሽኑ ማምሻውን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል። ጥምረቱ ለኮሚሽኑ እውቅናውን የሰጠው፣ የጥምረቱ ገምጋሚ ኮሚቴ በኮሚሽኑ አደረጃጀት እና አሠራር ላይ ያካሄደውን ጥልቅ ግምገማ መሠረት በማድረግ ነው። ኮሚሽኑ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ውስጥ ሆኖም፣ በሀገሪቱ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስጥበቅ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ በመሆኑ እና አምና የታዩበትን ጉድለቶች በማስተካከሉ የአንደኛነት ደረጃ እንደሰጠው ዓለማቀፉ ጥምረት ገልጧል። ይኼው እውቅና፣ ኮሚሽኑ የዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ጥምረት አባል እንዲሆን እና ድምጽም እንዲሰጥ እንደሚያስችለው መግለጫው አክሎ አመልክቷል።

1፤ አማጺው ሕወሃት ታጣቂዎች በአማራ ክልል በጋሸና እና በሰሜን ሸዋ ዞን አንጾኪያ ከተሞች በቆዩባቸው ጊዜያት በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን በጅምላ እንደጨፈጨፉ እና የጅምላ መቃብሮችም እንደተገኙ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ሥዩም ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል። ታጣቂዎቹ በተጠቀሱት አካባቢዎች በርካታ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎችንም እንደፈጸሙ መረጃዎች እየወጡ እንደሆነ ተገልጧል። በአፋር ክልልም ታጣቂዎቹ በርካታ ሰላማዊ ሰዎችን እንደገደሉ ቢልለኔ በመግለጫቸው ያወሱ ሲሆን፣ በሁሉም አካባቢዎች የተፈጸሙ የቡድኑ ወንጀሎች በገለልተኛ አካል ወደፊት ይጣራሉ ብለዋል። አንዳንድ ምዕራባዊያን መንግሥታት የሕወሃት ታጣቂዎች በሁለቱ ክልሎች የፈጸሟቸው ከባድ ወንጀሎች ግድ ያላላቸው መሆኑ፣ በሰብዓዊ መብት ላይ ፖለቲካዊ አቋም መያዛቸውን እንደሚያሳይ ቢልለኔ አክለው ተናግረዋል።

2፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ለ2 ሚሊዮን ዕርዳታ ፈላጊዎች 28 ሺህ ሜትሪክ ቶን አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እንደመደበ እና ለጋሸና እና ላሊበላ ተረጅዎች ደም 5 ሺህ ኩንታል ምግብ እንደላከ የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪ ቢልለኔ ሥዩም በዛሬው መግለጫቸው አስታውቀዋል። በአፋር ክልልም ከ1.3 ሚሊዮን ዕርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ውስጥ ለተወሰነው ዕርዳታ እየተከፋፈለ እንደሆነ በመግለጫው ላይ ተገልጧል። ቢልለኔ ጨምረውም፣ ሕወሃት 900 ዕርዳታ ጫኝ የረድዔት ድርጅቶች ካሚዮኖችን ነጥቆ ታጣቂዎቹን ከቦታ ቦታ ሲያጓጉዝባቸው፣ አንዳንድ የውጭ መንግሥታት ዝምታን መርጠዋል በማለትም ወቅሰዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ዳግም የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ችግር እንዳይሆን ተደርጎ ይቀበራል ሲሉ ተመራቂ የአማራ ልዩ ኃይል አባላት ገለጹ

3፤ በአማራ ክልል የአማጺው ሕወሃት ታጣቂዎች ሰሞኑን በለቀቋቸው እና ገና በቁጥጥራቸው ስር ባሉ አካባቢዎች 7 ሚሊዮን ሕዝብ በምግብ እና መድሃኒት እጥረት ለከባድ ችግር ተጋልጦ እንደሚገኝ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ለሪፖርተር ጋዜጣ ተናግረዋል። በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ጎንደር እና በዋግኽምራ ብሄረሰብ ዞኖች ለዕርዳታ ፈላጊዎች እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የምግብ ዕርዳታ ማድረስ አልተቻለም። በተለይ ዋግኽምራ ዞን እና የሰሜን ጎንደር ዞን አንዳንድ አካባቢዎች ገና በሕወሃት ታጣቂዎች ስር በመሆናቸው፣ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊዎች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

4፤ የአሜሪካው ዓለማቀፍ የልማት ተራድዖ ድርጅት (ዩኤስአይዲ) በሰሜን ኢትዮጵያ ለጦርነት ተጎጅዎች ስብዓዊ ዕርዳታ ማቅረቡን አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። በሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ጎንደር፣ ምዕራብ ጎጃም እና ዋግኽምራ ዞኖች ለ2.6 ሚሊዮን ሰዎች የሕይወት አድን ዕርዳታ ለማድረስ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ድርጅቱ ገልጧል።

5፤ የእንግሊዙ ብሪቲሽ ሙዚዬም ከኢትዮጵያ የተዘረፉ 11 ቅዱስ ታቦታትን ለመመለስ ፍቃደኛ እንዳልሆነ ዘ አትላንቲክ የተሰኘው ድረገጽ ዘግቧል። ብሪቲሽ መዚዬም ታቦታቱን በዘላቂነት ለኢትዮጵያ ለመመለስ የእንግሊዝ ሕግ እንደማይፈቅድለት ገልጾ፣ ታቦታቱን ዘለግ ላለ ጊዜ በውሰት መልክ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መስጠት እንደሚችል ግን አስታውቋል። ሙዚዬሙ ታቦታቱን እንዲመልስ የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲጠይቅ ቆይቷል። በሙዚዬሙ ከሚገኙት ታቦታት መካከል 8ቱ ከ150 ዓመታት በፊት በመቅደላው ጦርነት ወቅት የእንግሊዝ ወታደሮች የዘረፏቸው ናቸው።

6፤ በጀርመን የኢትዮጵያዊያን ሰብዓዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ሥዩም ኃብተ ማርያም ባንድ የጀርመን ከፍተኛ ፖለቲከኛ ላይ ባቀረቡት ትችት ሳቢያ ክስ እንደተመሠረተባቸው ዶቸቨለ ዘግቧል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአንድነት/መድረክ የፖለቲካ ግንኙነት እና የጋራ እንቅስቃሴ ከመቀናጀት እስከ ግንባር ያለው አጠቃላይ ሁኔታ ግምገማ

ግለሰቡ የተከሰሱት ነገ ለሚሾመው አዲሱ የጀርመን መንግሥት ዕጩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የሆኑትን አናሌና ቤርቦክን ባለፈው መስከረም “ዘረኛ” ብለው በአደባባይ ሰልፍ ላይ በመጥራታቸው እንደሆነ ዘገባው ገልጧል። ሥዩም የጀርመን አረንጓዴ ፖርቲ ተመራጭ የሆኑትን ፖለቲከኛ “ዘረኛ” ያሏቸው፣ ፖለቲከኛዋ በቴሌቪዥን የምርጫ ክርክር ወቅት ጥቁሮችን የሚያዋርድ ቃል ተጠቅመዋል በማለት ነበር።

7፤ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ሴሪል ራማፎዛ አደገኛ የተባለእ ልውጥ የኮሮና ተዋሲ በደቡብ አፍሪካ መጀመሪያ መገኘቱን ተከትሎ ከአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች የበላይነት ስሜት የተጫናቸው እና ክብር ነክ የሆኑ የስልክ ጥሪዎችን እንዳስተናገዱ መናገራቸውን የሀገሪቱ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ፕሬዝዳንቱ የአንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች በቫይረሱ ሳቢያ በደቡብ አፍሪካ ላይ ስለጣሉት የጉዞ እገዳ በቅጡ ሊያናግሯቸውም ሆነ አስተያየታቸውን ለመስማት እንዳልፈቀዱ ጠቁመዋል። ልውጡ የኮሮና ተዋሲ “አሚኮርን” መጀመሪያ በደቡብ አፍሪካ እንደተገኘ ነበር በርካታ የአውሮፓ ሀገራት በደቡብ አፍሪካ ላይ የጉዞ እገዳ የጣሉት። ሆኖም የኅብረቱ አባል ሀገራት ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት ላይ የጣሉትን የጉዞ እገዳ ዛሬ ያላላሉ ተብሎ ይጠበቃል። [ዋዜማ ራዲዮ]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share