“ኢትዮጵያ የሚለውን የነጻነት ስም የማስጠበቅ የታሪክ አደራ አለብን!” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

ውድ የሀገሬ ልጆች፣

የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ወዳጆች፣

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጀግንነትና መሥዋዕትነት ክብሯንና ነጻነቷን አስጠብቃ የኖረች ሀገር ናት። ይሄን ወዳጅም ጠላትም ያውቀዋል። ድንበሯን ሊደፍሩ የሞከሩ አይበገሬ ክንዷን አይተዋል። ሊያስገብሯት የቋመጡ አቀርቅረው ተመልሰዋል። ክህደት ለፈጸሙባት ተገቢውን ትምህርት መስጠት፣ ከጀርባ የወጓትን አይቀጡ ቅጣት መቅጣትን ታውቃለች። ለሺህ ዘመናት የተጎናጸፈችው ነጻነትና ሉዓላዊ ክብር በችሮታ የተገኘ አይደለም። ያለ ዋጋ ነጻነትን አጽንቶ መጠበቅ አይቻልምና፤ ኢትዮጵያ የሚለው የነጻነት ስም የደም ዋጋ ተከፍሎበታል፣ ብርቱ ጀግኖች ሞተውለታል።

በታሪክ የምናውቃቸው አባቶቻቸው በአስተዳደርና በርእዮተ ዓለም ይለያያሉ፤ ለመብት፣ ለፍትሕና ለእኩልነት በነበራቸው አመለካከት ይለያያሉ። ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነት፣ ነጻነትና ሉዓላዊነት ባላቸው ቦታ ግን ልዩነት አልነበራቸውም። በቋንቋ፣ በብሔርና በጎሳ ብዝኃነት ቢኖራቸውም የአልደፈርምባይ ቆራጥነታቸው አንድ ያደርጋቸዋል። የግል ፍላጎታቸው የቱንም ያህል የተራራቀ ቢሆን፣ የጋራ ጠላት ሲመጣ ኢትዮጵያዊነት ከግላዊነታቸው በላይ ይቀመጣል።

ድሮም ሆነ ዛሬ የእያንዳንዳችን ፍላጎት፣ የሁላችንም ሕይወት ከኢትዮጵያ በታች ነው። እኛ ኖረን ኢትዮጵያ ከምትሞት እኛ ሞተን ኢትዮጵያ እንድትኖር እንፈልጋለን። የሁላችንም የሆነች፣ ነጻነትና ፍትሕ የሰፈነባት፣ በገናናነቷና በነጻነቷ በዓለም አደባባይ የምትጠራ ሀገር እንድትኖረን ምኞታችን ነው። ለኢትዮጵያ ትልቅ በመመኘት፤ ሀገራችን አንገቷ ቀና እንዲል በመፈለግ፤ ባለፉት ሦስት ዓመታት ዐቅማችን የፈቀደውን ሁሉ አድርገናል። ፖለቲካችን ከመገዳደል ወደ መተጋገል እንዲቀየር ታግለናል። ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በሰው ሀገር የሚንከራተቱት ሁሉ እንዲገቡ ለማድረግ ሞክረናል። ካለፈው በጎውን ወስደን ጥፋቱን በይቅርታ ለማረም ተንቀሳቅሰናል። “በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር” ብለን አዲስ ምዕራፍ ከፍተናል። የመለያየትና የጥላቻን ግንብ አፍርሰን የመደመርና ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ድልድይን ልንገነባ ቃል የገባነውን ወደ ተግባር ለመተርጎም ዐቅማችን የፈቀደውን አድርገናል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የብልጽግና ፓርቲ ኮንግረስ አብይ አህመድን ፕሬዝዳንትአድርጎ መረጠ

 

ኢኮኖሚው እንዲያገግምና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ፤ የዳኝነት ሥርዓታችን እንዲሻሻል፣ የሰብአዊ መብት አያያዛችን እንዲስተካከል፤ የውጭ ግንኙነት መርሐችን ጎረቤት ተኮር እንዲሆን ታግለናል። በዚህ መካከል እንደ ሰው በርትተናል። እንደ ሰውም ደክመናል። እንደሰው አልምተናል፣ እንደ ሰውም አጥፍተናል። በኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት፣ በኢትዮጵያ ክብርና በኢትዮጵያ ታላቅነት ግን ለአፍታም አዘንብለን አናውቅም።

ኢትዮጵያ የምታጓጓ ሀገር ናት። ከትናንትናዋ ይልቅ ነገዋ ታላቅ ነው። መከራ ማለፍ ነባር ችሎታዋ ነው። ይሄንን የገጠመንን መከራም እናልፈዋለን። ኢትዮጵያ ማሸነፏ አይቀርም። አሁን ኢትዮጵያን ለመታደግ የመጨረሻውን ፍልሚያ የምናደርግበት ጊዜ ላይ ነን። ጠላቶቻችን በውጭና በውስጥ ተቀናጅተው ዘምተውብናል። በአንድ በኩል ታሪካዊ ጠላቶቻችን በራሷ ፈቃድና በራሷ መንገድ ብቻ የምታድግ ኢትዮጵያ ላለማየት የጥፋት በትር ሰንዝረዋል። ኢትዮጵያ አፍሪካዊ በሆነ መንገድ ከተነሣች፣ ተነሥታም ካሸነፈች፣ ከዚህ በኋላ ለማንም የማትመለስ ትሆናለች። ይሄን አፍሪካዊ መንገድ ለማደናቀፍ ሁሉንም ዓይነት የክፋት መሣሪያዎች አሰልፈዋል። የውጭና የውስጥ ጠላቶቻችን የእነርሱን ብርታት በኢትዮጵያ ድካም ላይ ለመገንባት ተነሥተዋል። የኢትዮጵያ ፍላጎት ይዞ ማለፍ እንጂ ጥሎ ማለፍ አልነበረም፤ ለዚህ ነው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችን በዋናነት ጎረቤት ተኮር እንዲሆን ያደረግነው፤ ይህ ትግል የመላ ጥቁር ሕዝቦች ትግል ነው። ኢትዮጵያ አንበርክኮ ጥቁር ሕዝብን ለማሳፈርና አዲሱን የቅኝ ግዛት ቀንበር ለመጫን የሚደረግ ሤራ ነው።

ጥቁር ሕዝቦች የራሳችን ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነትና ክብር እንዳይኖረን ሆን ተብሎ የሚደረግ አንገት የማስደፋት ትግል ነው። ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተ ዘመቻ፣ ኢትዮጵያን በማንበርከክ ጥቁር ሕዝቦች የነጻነትና የአሸናፊነት አርአያ እንዳያገኙ የተከፈተ ዘመቻ መሆኑን ላስታውሳችሁ እወዳለሁ። ለጥቁር ሕዝብ ክብርና ልዕልና ስትሉ፣ በፓን አፍሪካ መንፈስ፣ ሁላችሁም ጥቁር ሕዝቦች፣ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቆሙ ጥሪ አቀርብላችኋለሁ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በቆቦና አራዶም ከተሞች ነዋሪዎች የህወሓት ኃይሎች ጥቃት ኢላማ ሆንን ሲሉ ይከሳሉ

በመጨረሻም ይህ ትግል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግል ነው። ልጆቻችን ሀገር እንዲኖራቸው የሚደረግ ትግል ነው። ልጆቻችን ክብርና ነጻነትን ለብሰው፣ በዓለም አደባባይ በኩራት ቀና ብለው እንዲሄዱ የሚደረግ ትግል ነው። በዓለም ላይ በክብር የምንጠራበት ስም እንዲኖረን የሚደረግ ትግል ነው። መኖር ወይም አለመኖራችንን የሚወስን ትግል ነው። ያለ ጥርጥር ግን እናሸንፋለን። ኢትዮጵያን ጠርቶ መሸነፍ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው።

ጊዜው ሀገርን በመሥዋዕትነት መምራት የሚያስፈልግበት ጊዜ ነው። ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ። ታሪክ ከሚያደንቃቸው የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ ለመሆን የምታስቡ ሁሉ ለሀገራችሁ ስትሉ ዛሬውኑ ተነሡ፤ ግንባር ላይ እንገናኝ፡፡ የእኛ መዝመት የሚፈጥረውን ክፍተት ከግንባር የቀሩት በሙሉ ዐቅማቸው ሸፍነው ይሠራሉ፡፡ በግንባር ያልተሰለፉ የክልልና የፌደራል አመራሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የልማትና አስተዳደር ሥራዎችን በሙሉ ዐቅማቸው ይከውናሉ።

ጎልማሶች በዘዴና በብልሃት አካባቢያቸውን እየጠበቁ፣ አረጋውያን እናትና አባቶች በጸሎት እየተጉ፣ ሁሉም ሰው ተባብሮ የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያረጋግጣል። ከዚህ በኋላ በሩቁ ተቀምጠን ተቺና አራሚ የምንሆንበት ጊዜ አይደለም። መደረግ ያለበትን እኛው ራሳችን እናድርገው። ለኢትዮጵያ ከእኛ በላይ ከየትም አይመጣም። ኢትዮጵያ የሚለው ስም የአሸናፊዎች ስም ነው፤ የነጻነት ምልክት ነው። አልጠራጠርም፣ የእኔ ትውልድ ለአሸናፊ ስሙና ለነጻነት ምልክቱ የሚጠበቅበትን ዋጋ ከፍሎ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በክብር መዝገብ ላይ በወርቅ ብዕር ያትማል።

አመሰግናለሁ!!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትሩር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ኅዳር 132014 .

https://fb.watch/9sSpjd07Oa/

2 Comments

  1. ሃገር ሲወረር ኑ ተከተሉኝ በማለት ግንባራቸውን ለጠላት ጀርባቸውን ለካሃዲ ያጋለጡ መሪዎች ኢትዮጵያ በፊትም ነበሯት አሁንም አሏት ወደፊትም ይኖሯታል። የጠ/ሚሩ ወደ ውጊያ አምድ መሄድና ያስተላለፉት መልዕክት ልቡን የማይነካው እውነተኛ የሆነ የኢትዮጵያ ልጅ ያለ አይመስለኝም። ከተገኘም ያው በወያኔ ዙሪያ ፍርፋሪ ለቃሚና እኖር ባይ በሰው ደም የሚነግድ ብቻ ነው። በመሰረቱ ሃገራችን በሚታዪና በማይታዪ ጠላቶች ተከባለች። በአንድ እጅ የሰላምና የእርቅ ጥሪ በሌላ እጅ የሳተላይትና የሌሎችም ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የበሬ ወለደ ወሬ እያወሩ የሚያስወሩት አሜሪካኖች ለዚህ የጥፋት ሴራ መሪዎቹ ናቸው። አሁን ደግሞ ብለው ብለው የሽብር ጥቃት በመዲናዋና በሌሎችም ከተሞች ሊፈጸም ይችላል ተጠንቀቁ ይሉናል። የሽብሩን ምንጭ ያውቁታል። ወያኔና ግብረ አበሮቹ ናቸው። የሚያሳዝነው ግን በዚህ ሁሉ የሴራ ትብታብ ውስጥ አሜሪካ ትርፏ ምን ይሆን? አሁን በራሺያ ዪክሬን (ክሬሚያ) በኩል እሳት የሚቆሰቁሱት አሜሪካኖች ሰውን በማጫረስ ምን እጃቸው እንደሚገባ ለማወቅ አይችልም። ዪክሬኖች አብሮ ለዘመናት የኖረውን የራሽያን ህዝብ ወዲያ ብለው አፍቃሪ አውሮፓ ከሆኑ ወዲህ ያተረፉት አንዳች ነገር የለም ከሰቆቃ በስተቀር። አሁንም የአሜሪካን አለንላችሁ በመስማት የሚያደርጉት መፍጨርጨር የትም አያደርሳቸውም። ለጉርብትና የቅርብ ጠላት ከሩቅ ወዳጅ ይሻላል።
    አሁን እንሆ ዪክሬን በቱርክ የተመረቱ ሰው አልባ ድሮኖችን በመጠቀም ራስዋን ለመከላከል የምታደርገው እርምጃ በአሜሪካ እሳት ማቀበልም እየተደገፈ ነው። ግን ከፍርስራሽ የተረፈችው ራሽያ ማንም የማይበግራት ሃገር እንደሆነች ያኔ ክሪሚያን ስትቆጣጠር ታይቷል። አልፎ ተርፎ አሜሪካኖች ታይዋንን ቻይና እንዳታጠቃልል የምንችለውን ሁሉ እናረጋለን እያሉ ሲደነፉ ሰው አምኖ መቀበሉም ይገርመኛል። የማይሆን ነገር ለሚስትህ አትንገር፡ አዎን የጦር መሳሪያቸውን ይሸጣሉ፤ አማካሪ ይመድባሉ። ፊት ለፊት ጦርነት ከቻይና ጋር ግን የማይታሰብ ሂሳብ ነው። ሌላም ብዙ ማለት ይቻላል። ግን በዚህ የአጅ አዙርም ሆነ የቀጥታ ፍትጊያ የሃበሻው ምድር መካተቷ እጅግ የሚያሸማቅቅ ነው። ጠ/ሚሩን ነገሩ አብቅቷል ውጣ፤ እኛ መጠለያ እንስጥህ እንዳሉት ክልዪ ልዪ ሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ጠ/ሚሩ ግን ይህ የማይታሰብ ነገር ነው በማለቱ ይኸው እንሆ በሚድያቸውና በውጭ ጉዳይ ፈጻሚዎቻቸው እልፍ ሴራ እየሰሩ ይገኛሉ። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ አስተሳሰብ በ60 ስሌት የተሳለ ነው። የጊዜውን መለወጥ ያላገናዘበ። ሽንፈትና ውርደቱን የሚዘነጋ። ሊቢያን አፈራርሰው አሁን አስታራቂ የሆኑት እነዚህ እብዶች ትርፋቸው ምን ይሆን? ዛሬ በየመን ላይ በሳውዲዎች የሚዘንበውን የመከራ እሳት አስታጣቂውና አፍላቂው አሜሪካ ራሷ ናት። ያው በዘይት በተገኘው ፔትሮ ዶላር የአሜሪካን የጦር መሳሪያ በገፍ የምትሸምተው ሳውዲ የሰው ልጆች መብት የማይከበርባት የመከራ ሳጥን ናት። ግን አይናቸው በነዳጅ የተሸፈነው አሜሪካኖች ሳውዲዎች ሃገራቸውን በ 911 ሲያወድሙ እንኳን የተደረገ ነገር የለም። ልብ ያለው ይህን ሁሉ ሊያስተውል ይገባል።
    ለጠ/ሚሩና አብረዋቸው ላሉ፤ ለሃገሪቱ መከላከያ ሰራዊትና ለሚሊሻው፤ ለፋኖዎች የምመኘው አንድ ነገርን ነው። ጠላትን ድል አድርጋችሁ፤ የከፋፋዪችን ሴራ አፍርሳችሁ የኢትዮጵያን ዳርና ድንበር አስከብራችሁ በህዝባችን በሆታና በደስታ ታጅባችሁ የምትመለሱበት ጊዜ ለማየት እጓጓለሁ። ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነው። በዚህም በዚያም እየተከፈላቸውና ስልጣን በማጣታቸው አኩርፈው የውሸት ታምቡር በጠ/ሚሩ ላይ የሚነፉ ሁሉ የሙታን ስብስቦች ናቸው። 99 መርፌ አንድ ማረሻ አይወጣውም። እናንተ ወስላቶች አፋችሁን ዝጉ። በጠ/ሚሩ አመራር ወያኔ ለአንድ ጊዜና ለመጨረሻ ጊዜ ይቀበራል። ህዝቡ ተነስቷል፡ ሰው ከውጭ ከውስጥ የሃገር ማዳን ጥሪውን ተቀብሏል። የእናቶችና የህጻናት እንባ ይታበሳል። ባንዲራችንም ከፍ ይላል። በቃኝ!

    • አረመኔዎች ለዘረፋ ስለሚዋጉ አያሸንፉም:: ኢትዮጵያ አሸናፊ ናት:: 400 ኪሜ የተለጠጠው የአረመኔ መንጋ በወረራቸው ቦታዎች ይቀበራል:: ጦርነትን እንደናፈቁ እኛንም ጎትተው ከተቱን አሁን ያለው ምርጫ ማፅዳት ብቻ ነው:: ተስፋ ሁፎችህ ሀቀኛና ኢትዮጵያዊ ስለሆኑ አከብራቸዋለሁ በርታ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share