ለቸኮለ! ቅዳሜ ጥቅምት 20/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ የመንግሥት ኮምንኬሽን አገልግሎት ከቀትር በኌላ ባወጣው መግለጫ የደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ደሴ በመከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ስር መሆኗን አስታውቋል። ዓለማቀፍ ዜና ወኪሎች አማጺዎች ከተማዋን ተቆጣጥረዋል በማለት ያሠራጩት መረጃ ሐሰት እንደሆነም መግለጫው አክሎ ገልጧል። መከላከያ ሠራዊት ደሴን ለመቆጣጠር ከኩታበር፣ ቦሩ ሥላሴ እና ሐይቅ አቅጣጫ ከተንቀሳቀሱ የሕወሃት ተዋጊዎች ጋር እየተፋለመ እንደሚገኝ የገለጠው መግለጫው፣ ስለ ውጊያው ያልተጣራ መረጃ የሚያሰራጩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል። ዓለማቀፍ ዜና ወኪሎች የከተማዋን አንዳንድ ነዋሪዎች በእማኝነት በመጥቀስ፣ አማጺዎቹ ወደ ከተማዋ እንደገቡ፣ የመንግሥት ወታደሮች ከማለዳ ጀምሮ በከተማዋ እንደማይታዩ እና የከተማዋ ኤሌክትሪክ አቅርቦት እንደተቋረጠ ዘግበው ነበር።
2፤ የመንግሥት ቃል አቀባይ የሆኑት የኮምንኬሽን አገልግሎት ሚንስትሩ ለገሠ ቱሉ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ በወገን ጦር ላይ የሠራዊቱን እንቅስቃሴ በማገድ ለሕወሃት የሚሰሩ ቅጥረኛ ወይም “ባንዳ” ኃይሎች አሉ ሲሉ ከሰዋል። መከላከያ ሠራዊት ከሚመራው የዕዝ ሰንሰለት ውጭ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ውጤት ሊያስገኙ እንደማይችሉ ተገንዝበው ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያሳሰቡት ቃል አቀባዩ፣ ሁሉም ወገን በመንግሥት ዕዝ ስር ውስጥ ገብቶ ሕወሃትን እንዲፋለም አሳስበዋል።
3፤ አማጺው ሕወሃት ተዋጊዎቹን ከአማራ እና አፋር ክልል እንዲያስወጣ እና ወደ ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተማ የሚያደርገውን ግስጋሴ እንዲገታ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። የሕወሃት ተዋጊዎች በከተሞች ላይ ከባድ መሳሪያዎችን ከመተኮስ እንዲቆጠቡ ያሳሰበው መግለጫው፣ ሁሉም ወገኖች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ጥሪ አድርጓል። ለትግራይ ክልል ተረጅዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዳይቀርብ መንግሥት እገዳ እንደጣለ ቀጥሏል ሲል የወቀሰው ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ፣ አሁንም ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታ ለተረጅዎች እንዲገባላቸው እንዲፈቅዱ ጠይቋል።
4፤ ፌደሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችን የክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ውጤት በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ምክር ቤቱ የሕዝበ ውሳኔውን ውጤት ያጸደቀው፣ ምርጫ ቦርድ ስላካሄደው ሕዝበ ውሳኔ እና ስለ ውጤቱ የሰጠውን ማብራሪያ አዳምጦ ከመረመረ በኋላ እንደሆነ ምክር ቤቱ አክሎ ገልጧል። በሕገ መንግሥቱ መሠረት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የፌደሬሽኑ 11ኛ አባል ክልል የሚሆነው፣ የደቡብ ክልል ምክር ቤት በመጭው ሰኞ በሚያካሂደው አስቸኳይ ጉባዔ ሥልጣኑን ሲያስረክብ ነው። የሥልጣን ርክክቡ ሲጠናቀቅ፣ አዲሱ ክልል ከደቡብ ክልል ተነጥሎ ራሱን የቻለ ክልል በመሆን ከሲዳማ ክልል ቀጥሎ ሁለተኛው ይሆናል።
5፤ ፌደሬሽን ምክር ቤት በዛሬው ስብሰባው የፌደራሉን የድጎማ በጀት ድልድል እና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ቀመር ዝግጅትን በሚመለከት የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ እንዳጸደቀ ምክር ቤተ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ምክር ቤቱ የውሳኔ ሃሳቡን ያጸደቀው፣ የድጎማ በጀት እና የጋራ ገቢዎች ክፍፍል ቋሚ ኮሚቴዎች ባቀረቡት የ2014 ዓ.ም ዕቅዶች ላይ ከተወያየ በኋላ ነው። ምክር ቤቱ አሁን በሥራ ላይ ያለው የድጎማ በጀት እና የጋራ ሃብት ክፍፍል ቀመርም ማሻሻያ ሳይደረግበት ባለበት እንዲቀጥል በአብላጫ ድምጽ መወሰኑንም አመልክቷል።
6፤ የኖርዌይ የስደተኞች ካውንስል በኢትዮጵያ እንዳይንቀሳቀስ የተጣለበት እገዳ ለሁለት ወራት እንደተራዘመ ድርጅቱ በድረገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ረድዔት ድርጅቱ በመንግሥት ውሳኔ ማዘኑን ገልጦ፣ እገዳው ለምን እንደተራዘመ ለመረዳት ከባለሥልጣናት ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ገልጧል። መንግሥት ባለፈው ሐምሌ በድርጅቱ ላይ የሦስት ወር እገዳውን የጣለው፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሐሰተኛ መረጃዎችን እንዳሰራጨ እና ለአንዳንድ የውጭ ሀገር ዜግነት ላላቸው ሠራተኞቹ አስፈላጊውን ሕጋዊ የሥራ ፍቃድ እንዳላሟላ በመጥቀስ ነበር።
7፤ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ጌታ ፓሲ ዛሬ የሐዋሳ ኢንዱስትሪያል ፓርክን እንደጎበኙ ኢምባሲው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። አምባሳደሯ የፓርኩ ባለሃብቶች ማኅበር አመራሮችን እና የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ፋብሪካዎች ሠራተኞችን ያነጋገሩ ሲሆን፣ የፋብሪካዎቹ ሠራተኞች የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ምርቶች ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ አሜሪካ የሰጠችው ዕድል ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ለአምባሳደሯ ነግረዋቸዋል። አምባሳደር ባሲ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካዎቹን የጎበኙት፣ መንግሥታቸው ኢትዮጵያን ከአፍሪካው የቀረጥ ነጻ ዕድል (አጎዋ) እንደሚያግድ እያስጠነቀቀ ባለበት ወቅት ነው።
8፤ ዛሬ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናዊያን ባለፈው ስምንት የተደረገውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በመቃወም በመላ ሀገሪቱ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ ማድረጋቸውን ዓለማቀፍ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። ሰልፈኞቹ ከሥልጣኑ የተወገደው ሲቪል የሽግግር መንግሥት ወደ ቦታው እንዲመለስ የጠየቁ ሲሆን፣ ጸጥታ ኃይሎች ሁለት ተቃዋሚ ሰልፈኞችን በጥይት እንደገደሉ ታውቋል። በሰልፉ ሳቢያ በሀገሪቱ የስልክና ኢንተርኔት መስመሮች በሙሉ ተቋርጠው ውለዋል።
[ዋዜማ ራዲዮ]
ተጨማሪ ያንብቡ:  ኮምቦልቻ አሁን በከባድ ተኩስ እና ተቃውሞ ተናጠች ቪዲዮ/ወሎ በጀት ተጀመረ ተባባሰ/አዲስ አበባ እና መቀሌ ሹመቱ ተፈጸመ/አብይ አስደንጋጭ ብድር ጠየቀ

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share