October 30, 2021
12 mins read

 የዐብይ አሕመድ መሰወርና የወያኔ ፕሮፓጋንዳ – መስፍን አረጋ

አብናቶቻችን (አባቶቻችንና እናቶቻችን) እንደሚሉት፣ ዳር ሲደፈር መኻል ዳር ይሆናል፡፡   በዚህም ምከኒያት የሰሞኑ አንገብጋቢ ጥያቄ መኻል ደሴ ላይ ምን እየሆነ ነው የሚለው ነው?  አንዳንዶቹ ደግሞ ይህን አንገብጋቤ ጥያቄ አስታከው፣ የደሴ ሕዘብ በወሬ ብቻ ለምን ይሸበራል በማለት በተቻለው አቅሙ ከወያኔ ጋር የሚፋለመውን የደሴን ሕዝብ ተወቃሽ ለማድረግ ይዳዳቸዋል፡፡

ጥያቄው መሆን የነበረበት ግን የደሴ ሕዘብ ለምን ይሸበራል ሳይሆን የሚሸበርበት ምክኒያት ምንድን ነው የሚለው ነው?  የጥያቄው አጭር መልስ ደግሞ የደሴ ሕዝብ ባይሸበር እንጅ ቢሸበር አይገርምም ነው፡፡  ደሴን የወያኔ ስታሊንግራድ (Stalingrad) ለማድረግ ባለው አቅም ሁሉ ወያኔን እየተፋለመ ያለው ሰፊው የደሴ ሕዝብ፣ ፍልሚያህ ከንቱ ነው፣ መከላከያ ጥሎህ ሊሸሽ ነው፣ ወያኔ ደሴ ገብቷል ወይም ሊገባ ነው፣ በወልድያ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ሻጥር፣ ባንተም ላይ ሊደገም ነው እየተባለ ተቀናቃኝ የሌለው ሰፊ ፕሮፓጋንዳ ሲነዛበት በደንብ ይሸበር እንጅ ለምን አይሸበር?

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ነኝ የሚለው ዐብይ አሕመድ ይህ ሁሉ መዓት በአማራ ሕዝብ ላይ ሲወርድ ደምጹን አጥፍቶ ቤተመንግስት ቁጭ ብሏል፡፡  ምናልባትም ደግሞ የአማራ ሕዝብ ሰቆቃ በቪዲዮ ተቀድቶ እየተላከለት፣ በወለጋ ጭፍጨፋ ያልረካውን ስሜቱን በወሎ ጭፍጨፋ እያረካ፣ ኦሮሞ ሦሰት ሺ ዓመት ይገዛል ብሎ ከፎከረው ከቅርብ አማካሪው ከሌንጮ ባቲ እና ከመሰሎቹ ጋር አሸሸ ገዳሜ እያለ ይሆናል፡፡

አንድ ዘፋኝ ሞተ ብሎ ባፋጣኝ መግለጫ ያወጣው፣ የጀዋር ሙሐመድ ደጋፊወች ተቀየሙኝ ብሎ ወደ ሐረር ለመብረር የተሽቀዳደመው፣ በእስክንድር ነጋ ላይ ጦርነት ለመክፈት ከወፍ የፈጠነው ዐብይ አሕመድ፣ የኢትዮጵያን የወደፊት ዕጣ የሚወስነውን ይህን ወሳኝ ትንቅንቅ በተመለከተ ምንም ላለማለት ምሎ የተገዘተ ይመስላል፡፡  ምንም ከማለት የተቆጠበው ደግሞ ድምጹን አጥፍቶ ጭጭ ምጭጭ በማለቱ ምክኒያት ቢያንስ ቢያንስ ሦስት መሠረታዊ ጥቅሞችን ስለሚያገኝ ነው፡፡

በመጀመርያ ደረጃ ጦርነቱ የኢትዮጵያ ጦርነት ሳይሆን የአማራና የትግሬ ጦርነት ነው፣ እኔና የኦሮሞ ሕዝብ ባይተዋሮች ስለሆንን ከደሙ ንጹሕ ነን የሚለውን መልዕክት ያስተላልፋል፡፡  ጦርነቱ የኢትዮጵያ ሳይሆን የአማራና የትግሬ ነው ማለት ደግሞ በተዛዋሪ መንገድ ሐበሻ ኢትዮጵያዊ አይደለም ማለት ነው፡፡  ይህ ደግሞ የራሳቸውን መጤነት ለመሸፈን ሐበሻ መጤ ነው የሚሉት የዐብይ አሕመድ ኦነጋዊ አማካሪወች ጥርሳቸውን የነቀሉበት ትርክት ነው፡፡   በተጨማሪ ደግሞ የአማራን ሕዝብ መጤ ነው ካለው ከብርሃኑ ነጋ፣ እንዲሁም አማራ የሚባል ሕዘብ የለም ካለው ካንዳርጋቸው ጽጌ፣ ባጠቃላይ ደግሞ ሰሜን ጠል ፖለቲካ ከሚያራምዱት፣ ለኦነጋውያን ካደሩት ከኢዜማውያን አጀንዳ ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆነው የዐበይ አሕመድ ድምጽ መጥፋት፣ ወያኔ በጌታቸው ረዳ፣ በደብረጽዮንና በጀነራሎቹ አማካኝነት የሚነዛውን ፕሮፓጋንዳ ተአማኒነት ከፍ ያደርገዋል፡፡  አለበለዚያማ፣ ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ስለሚብስ፣ በጥያራ መደብደብ የነበረበት መስፍን ኢንዱስትረያል ኢንጂነሪግ ሳይሆን፣ ትግራይ ቲቪ ነበር (እስራኤሎች የሐማስን ሬድዮ ጣቢያ የሚገኝበትን ሕንጻ በቦንብ አጋይተው እንደደረመሱት)፡፡

በዚህ ረገድ ደግሞ በወያኔ ዘመን የቀርብ ጓደኞች የነበሩት ጌታቸው ረዳና ዐብይ አሕመድ ሥራቸውን የሚሠሩት እየተናበቡ ይመስላል፡፡  እነዚህ ሁለት ግለሰቦች፣ ጀዝባ፣ ገሪባ የመሳሰሉትን ቃሎች የሚያዘወትሩ፣ የዱርየነት ባሕሪ የተጠናወታቸው፣ ዐራዳ ነን ባይ ግለሰቦች መሆነቸውን መዘንጋት አያስፈልግም፡፡  ጌታቸው ረዳ ዐብይ አሕመድን ከፍ ዝቅ እያደረገ የሚሰድበው፣ ሊሰድበው ፈልጎ ሳይሆን ወያኔ ዐብይ አሕመድን የሚጠላው ለማስመሰል ሲል ብቻ ነው ብሎ መጠርጠር ያስፈልጋል፡፡  ወያኔ ዐብይ አሕመድን የሚጠላው እንዲመሰል የሚፈለግበት ምክኒያት ደግሞ፣ የአማራ ሕዝብ ዐብይ አሕመድን እንዲወደውና፣ በዐብይ አሕመድ በመተማመን እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ በወያኔ እንዲቆራረጥ ነው፡፡  የአማራ ሕዝብ ከታች በሸኔ፣ ከላይ በወያኔ ተቆራርጦ ቢያልቅ ደግሞ ጥቅሙ ለወያኔም ለኦነግም  ነው፡፡

በሶስተኛ ደረጃ ዐብይ አሕመድ ጦርነቱን በተመለከተ ድምጹን ሲያጠፋ፣ ኢሳት፣ ዜና ቲዮብና የመሳሰሉት ለሱ ያደሩትን ዐብይ አሕመዳዊ ሚዲያወች ከፍተኛ ጥቅም ያገኛሉ፡፡  የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆነው ግለሰብ ጦርነቱን በተለመከተ ድምጹን በማጥፋቱ ምክኒያት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ የወደፊት ዕጣውን ስለሚወስነው ስለዚህ ወሳኝ ጦርነት ለማወቅ ሲል ብቻ፣ የጦርነቱ ብቸኛ ምንጮች እንዲሆኑ የተደረጉትን ዐብይ አሕመዳዊ ሚዲያወች አምርሮ ቢጠላቸውም እንኳን ሊመለከታቸው ግድ ይሆንበታል፡፡

በዚህም ምክኒያት የነዚህ ዐብይ አሕመዳዊ ሚዲያወች ገቢ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል፡፡  ጦርነቱ እስከቀጠለ ድረስ ደግሞ መጨመሩን ይቀጥላል፡፡  እነዚህ ሚዲያወች ለዐብይ አሕመድ ስላደሩ፣ ዐብይ አህመድ ደግሞ ሐበሻ የሚጨፋጨፍበትን ጦርነቱ እየሸጡ ትርፍ እንዲያገኙ በማድረግ ወሮታቸውን እየከፈላቸው ነው፡፡  ለሱ ለራሱ ደግሞ ባንድ በኩል አማራን በማዳከም ኦነጋዊ ሕልሙን እውን ለማድረግ እየተቃረበ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አማራ ከሚዳከምበት ጦርነት ትርፍ እንዲያገኙ በማድረግ ለኢዜማዊ ሎሌወቹ ወሮታቸውን እየከፈለ ባንድ ዲንጋ ሁለት ወፍ ይመታል፡፡

ስለዚህም ኦነጋዊው ዐብይ አሕመድ፣ እንዲሁም ለሱ ያደሩት ዐብይ አሕመዳዊ ሚዲያወች ጦርነቱ በተቻለው መጠን እንዲራዘም እንጅ በወያኔ ተሸናፊነት ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ የሚፈልጉበት አንዳቸም ምክኒያት የላቸውም፡፡  የዐብይ አሕመድን መከላከያ ሚኒስትር ቤታቸው፣ የዐብይ አሕመድን ጀነራሎች ጓደኞቻቸው ያደረጉት እነዚህ ዐብይ አሕመዳዊ ሚዲያወች፣ ያልተያዘውን ተያዘ፣ ያልተደረገውን ተደረገ፣ ያልሆነውን ሆነ እያሉ የውሸት ቱልቱላ ቀን ከሌት የሚቶለቱሉት፣ የአማራ ሕዝብ እውነታውን አውቆ ከመጋፈጥ ይልቅ፣ ዐብይ አሕመድን ተማምኖ ላቱን ከውጭ እንዲያሳድር ለማድረግ ብቻና ብቻ ነው፡፡

በሌላ በኩል ግን፣ ጌታቸው ረዳ የአማራን ሕዝብ ሰቆቃ የሚያሳጥር ትልቅ ነገር ተናግሯል፣ ምንም እንኳን ነገሩን የተናገረው ወያኔ ዐብይ አሕመድን የሚጠላው እስከዚህ ድረስ ነው ለማስባል ብቻ ቢሆንም፡፡  የተናገረው ደግሞ ኦነጋዊ ጀነራሎች ተሰባስበው ዐብይ አሕመድን እንዲያስወግዱት ነው፡፡  ጌታቸው ረዳ የተናገረው ነገር ለአማራ ሕዝብ የሚጠቅመው ደግሞ፣ የአማራ ሕዝብ ይህን የሕልውና ጦርነት ባሸናፊነት ሊወጣው የሚችለው፣ የኦነግ ጀነራሎች ሳይሆኑ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው፣ ሳይረፍድ በፊት ዐብይ አሕመድን ባፋጣኝ ካስወገዱት ብቻና ብቻ በመሆኑ ነው፡፡

የአማራ ሕዝብ በከፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት ድባቅ ተመትቶ የነበረውን ወያኔን ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲያንሰራራ ያደረገውን፣ ቀጥሎ ደግሞ ያማራን ሕዝብ ፍዳ እያስበላ ባጭር ጊዜ ውስጥ የደሴን በር እንዲያንኳኳ ያስቻለውን ኦነጋዊውን ዐብይ አህመድን የጦር ጠቅላይ አዛዥ አድርጎ ከወያኔ ጋር ጦርነት መግጠም፣ ውጤቱ የአማራን ሽንፈትና እንደ ሕዝብ መጥፋት ማፋጠን ብቻና ብቻ ነው፡፡

መስፍን አረጋ

mesfin.arega@gmail.com

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Go toTop

Don't Miss

Abiy Ahmed and Demeke Mekonnen

የዐብይ አሕመድ የድርድር ተውኔትና የደመቀ መኮንን ሚና – መስፍን አረጋ

የዐብይ አሕመድ ዋና አማካሪ ኦቦ ሌንጮ ባቲ እንደፎከረው ከሆነ ‹‹ኦሮሞ

የቱ ነው ኦሮሞ? – መስፍን አረጋ

መንደርደርያ ያማራ ሐለወት አደጋ ላይ ወድቆ እየተቀበረ በማሽን ተዝቆ፣ ጽንፈኛ