በዓለም የምናየው እውነት ከብርሃን ጋር ይጋጫል ፡- መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

1 ፣ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ ፡፡   2 ፣ ምድርም  ባዶ  ነበረች  ፤ አንዳችም  አልነበረባትም ፤ ጨለማም  በጥልቁ ላይ ነበረ የእግዚአብሔርም  መንፈስ  በውሃ  ላይ  ሰፎ፟  ነበር።

3፤ እግዚአብሔርም ፣ ብርሃን ይኹን አለ ፤ ብርሃንም  ኾነ ፡፡

( ኦሪት  ዘፍጥረት ምዕራፍ 1፤ 1-3 )

መልካም አባት የእርሱን ሸክም ወይም ቀንበር ከላዩ ላይ ለማንሳት ሲል ብቻ ልጁ የራሱን ህልም ትቶ የእርሱን የልቡን መሻት እንዲከተል በነጋ በጠባ አይነዘንዘውም ። ልጁ በልቡ ውስጥ ባቀጣጠለው ብርሃን አማካኝነት ወደግቡ እንዲደርስ ፤ ዘወትር በጥሞና ይመክረዋል እንጂ !                 መልካም አባት፣  የሥኬት ና የውድቀት ጉዞውን በመተረክ ልጁ ከውድቀቱ እንዲማር ፤ ከስኬቱም ጠቃሚውን ብቻ እንደ እውቀት እንዲወስድ ፣ ዘወትር ከማሳሰብ ና ከማስገንዘብ ውጪ ፤ የልጁን ህልም በማጨናገፍ ፣ በእርሱ ያልተሳካ ህልም ለመቀየር ከቶም አይተጋም ፡፡

መልካም አባት ፣ የእኔን አመለካከትና ሃሳብ ካልወረሥክና እኔን ካልሆንክ ሞቼ እገኛለሁ አይልም ። ማንም የማንም ቅጂ መሆን እንደማይችል ያውቃል ። በግድ ካልመሠልከኝ እያለም ልጁን አያሥጨንቀውም ። እርሱ ያልሆነለትን ወይም ያልጨረሰውን የህይወት ጉዞ በእርሱ እግር ተተክቶ እንዲራመድም በነጋ በጠባ አይቸቀጭቀውም ።ልጁን በሚፈልገው መንገድ እንዲራመድ የልጁ የተለኮሰ የተስፋ ሻማ ፣ ብርሃኑ እንዳይጠፋ ና ከእርሱ ስኬት የላቀ ስኬት እንዲኖረው  በብርቱ ያግዘዋል እንጂ !

አባቶች ና እናቶች የልጆቻቸው የልብ ብርሃን ፣ የበለጠ እንዲደምቅ ከህፃንነታቸው ጀምሮ ልባዊ እገዛና የሞራል ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል ፡፡ ልጅ አይራበው ፤ አይጥማው እንጂ ፣ተገቢ እንክብካቤና የአእምሮ ምግብ አያስፈልገውም ፡፡ የሚሉ እናትና አባቶች ትላንት ብዙ ነበሩ ፡፡ ዛሬም በልጅ ቆዳ ማን ተቀበረ ባይ ወላጆች ትቂቶች ናቸው ብሎ መመስከር አይቻልም ፡፡ እርግጥ ነው ለልጆቻቸው ሲሉ ራሳቸውን የሚያስርቡ ፤ በእነሱ ጥጋብ ቁንጣን የሚይዛቸው ፍቅር የሆኑ ወላጆች እንዳሉ ሁሉ ፤ ከእውቀት እና ከደረሰባቸው ስቃይ የተነሳ ፣ ለልጆቻቸው ክፉ የሆኑ ወላጆችም ይኖራሉ  ፡፡ እርግጥ ነው አብዛኛው ወላጅ ለልጁ ስኬት የሚጥር ሆኖ እናገኘዋለን ፡፡

ወላጆች ለልጆቻቸው ሥኬታማነት መጣር ና መጋራቸው ተገቢ ነው ። ይሁን እንጂ ከ18 ዓመት በኋላም በአንቀልባ ሊያዙሏቸው ከሞከሩ ፣ ልጆቻቸውን አቅመ ቢሥና ልፍሥፍሥ ያደርጓቸዋል ።ከ 18 ዓመት በኋላ የወላጆች ግዴታ የልጆቻቸውን ህልም ማለም አይደለም ። ልጆች የሚገባቸውን የቀለም ትምህርት ከቀሰሙ በኋላ  የራሳቸውን ህልም በማለም ፣ የራሰቸውን ህይወት ራሳቸው መኖር አለባቸው ።

ወላጆች ለልጆቻቸው ፣ በልጅነታቸው ዝቅ ብለው የሰሩ ሰዎች ፣ በጎልማሳነታቸው ስኬታማ መሆናቸውን በማመላከት በህይወታቸው ስኬታማ እንዲሆኑ ባላሰለሰ ምክር የመንገዳቸውን ጋሬጣ ሊነሱላቸው ግን ይገባቸዋል ፡፡ የሐብታምነት ምሥጢሩ ዝቅታን መውደድ ነው  ። በትህትና  ጎንበስ ማለት ነው ፡፡ በማለትም ምክር ሊለግሷቸው ይገባል ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የማያለቅስ ልጅ - ከዳንኤል ክብረት (ዲ/ን)

በነገራችን ላይ ናዝሬት ( አዳማ )  ውስጥ ፣ ሁለት የጎጃም ወጣቶች ቤት ተከራይተው እንጀራ በመጋገር ህይወታቸውን ለመቀየር በመስራት ላይ ይገኛሉ ፡፡ የእንዚህን ወንዶች በእንጀራ መጋገር ና ለሆቴል ቤቶች ማቅረብ ሥራ  ላይ መሰማራት  ጥቂት የማይባሉ ሴቶችን እና ወንዶችን አስገርሟል ፡፡ በበኩሌ ግን ሊስትሮ የሆኑ ሴቶች እጅግ የሚደነቁና ዝቅ በማለት ፣ ትህትናን አስተምረው ለከፍታ እንደሚጥሩ ሁሉ ፤ እነዚም ወንዶች በተመሳሳይ ድርጊት የስራን እኩልነት በማስተማራቸው ሊወደሱ ይገባል ፡፡ በትህትናቸውና ዝቅ ብሎ ከፍ ለማለት በመሻታቸውም የልባቸውን ፍላጎት ፈጣሪ እንደሚያሳካላቸው አትጠራጠሩ ፡፡

ፈጣሪ በማንኛውም ቀና መሻት ና ጥረት ውሥጥ አለ ። ከሰው የልቅ በፈጣሪ የሚመካ በወንድ ወይም በሴት ሤጣናዊ ምላሥ የማይሸወድ ወጣት ምንጊዜም ሥኬታማ ነው ። በወንድ ወይም በሴት ያልፍልኛል የሚል ወጣት ግን ዘላአለም ዓለሙን አያልፍለትም ። እናም ቆም ብለው ወጣቶች እንዲያስቡ   ለታላቅ ሥኬትም እንዲያልሙ ወላጆች የማበረታት እና የማንቃት ምክርን ከመለገሥ ባሻገር በአንዳንድ ወጣቶች ሥንፍና ፣ ድብቅ ልብ ፣ ሸፍጥ ና ውሸት በመማረክ የሐሰተኛ ትርክቶቻቸው ተባባሪ መሆን የለባቸውም ። እነዚህ ባልተጨበጠ ህልመና ሃሰብ የሚያምኑ ወላጆች ፣ ለልጆቻቸው  ከሚመኙት ና ከሳሉላቸው  ህልምም ወጥተው ፣ ነባራዊውን ዓለምና የልጆቻቸውን ድብቅ ህይወት ፈጥነው መረዳት ከሚመጣባቸው ውድቀት ያድናቸዋል ፡፡

ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እንዲሉ ፣ ጥቂት የማይባሉ ወላጆች በልጆቻቸው የውሸት ወሬ በመሸወድ ፣ ያልተገባ መሠዋትነት ይከፍላሉ ። የልጆቻቸውን እውነተኛ ማንነት ሲያውቁ ግን ልባቸው ይሰበራል ።

በአጠቃላይ በጥፋት ጎዳና የሚከላወሥ ልጃቸውን የማያውቁ ና ልጃቸውን እንደፃድቅ የሚቆጥሩ ወላጆች በጣም ያሳዝናሉ ። እነዚህ ወላጆች የልጆቻቸውን ሥንፍና እና የምላሥ ጉልበት በማሥተዋል የውጪ ህይወታቸውን ከወዲሁ  ካልፈተሹ ፣ ወይም ካላሥፈተሹ በሥተቀር ፣ ልጆቻቸውን ሣያውቋቸው ይሞታሉ ። ወይም እውነተኛ ማንነታቸውን ባወቁ ጊዜ በንዴት በግነው ለበሽታ ሊዳረጉ  ይችላሉ ።

ይኽ የማይቀር እውነት ነውና ወላጆች ዛሬውን  በተጨባጭ የልጆቻቸውን ማንነት ለማወቅ መትጋት ይጠበቅባቸዋል ።

በተለይም ብዙውን ጊዜያቸውን ከልጆቻቸውን ጋር የሚያጠፉት እናቶች ናቸውና ፣ በተጨባጭ የልጆቻቸውን ማንነት ለማወቅ መትጋት አለባቸው ።

” እውን ልጆቻቸው እነሱ እንደሚያሥቡት ብሩህ አእምሮ እና ራእይ ያላቸው ናቸው ? ወይሥ በህልም አለም ኗራዎች ። ”

የኢትዮጵያውያን እናቶች አብዛኛዎቹ ርሁሩሆች ናቸው ። የልጆቻቸው ሥኬት በእጅጉ ያሥጨንቃቸዋል ። እናም አንዳንደ እናቶች ለልጆቻቸው ሥኬት ሲሉ  የማይፈነቅሉት ዲንጋይ ፣ የማይቧጥጡት ተራራ የለም ።

ተጨማሪ ያንብቡ:  ክልል መፍትሔ አይደለም! - አንዱ ዓለም ተፈራ

እርግጥ ነው ” እናት  ጎሽ ፣ ለልጆ ብላ ተወጋች ፡፡ ” እንደሚባለው ፤ የኢትዮጵያ  እናቶችም በታላቅ መሥዋትነት ነው ፤ ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት ። ብዙዎቹ እናቶችም ፈጣሪ የልጆቻቸውን ህልም እነዲሳካ ይፀልዩላቸዋል እንጂ መዝጊያውን እንዲያንኳኩ አይመክሯቸውም ፡፡ ዝም ብሎ በፀሎት ብቻ መኖር ተጎልቶ አበሳ መቁጠር ነው ፡፡ ሲጀምር ” ጥረህ ግረህ ብላ ፡፡ ” ተብለህ ነው ከገነት ወደምድር በጥፋትህ ተባረህ የመጣኸው ፡፡ ሲቀጥል ደግሞ የምትሻውን ለማግኘት ፤ ወደምትሻው በመሄድ የምትሻውን ለማግኘት በሩን ማንኳኳት እንደሚጠበቅብህ  ካልተገነዘብክ ለዘመናት ቆመህ መቅረትህን ማወቅ አለብህ ፡፡ ይህንን ከተረዳህ በቁም መቃዠትህ ያከትማል ፡፡

በእኛ አገር ም ሆነ በሌላው ዓለም ፣ ጥቂት የማይባል  ሰው በቁም ቅዘት ውስጥ ሲኖር ይስተዋላል  ። የቁም ቅዠቱም  ከንቃተ ህሊናው ዝቅተኝነት የሚመነጭ ነው ። በንቃተ ህሊናው ዝቅተኛነት ና ለማወቅ ባለመትጋቱ ፈጣሪ ( እግዛብሔር = GOD ) ለእርሱ ብቻ የሚያደላ የሚመስለው ጥቂት አይደለም ። እርግጥ የፈጣሪያችንን  የየቀን ተአምራት ፣ በግለሰብ ደረጃ ካየነው ፣ ፈጣሪ ለግለሰብ የሚያዳላ ይመሥለናል ። ከዚህ የተነሳ ነበር እኮ ፣ ነፍሱን ይማረውና እውቁ ጋዜጠኛ ሃያሲና ደራሲ  ሥህብሐት ለአብ ገብረእግዛብሔር ” እኔ እና እግዛብሔር  ሽርክ ነን ። ” በማለት በድፍረት የተናገረው ። በየዕለት ህይወቱ ከደስታ እምብዛም  ባለመራቁ ፣ ፈጣሪ ለእርሱ ብቻ የሚያደለ መሥሎት  ። …

እንዲህ ዓይነቱ ህሳቤ የሚመነጨው በመምሸት ና በመንጋት ውሥጥ በሚፈጠሩ ተደጋጋሚ የልብ መሻቶች መከወን ነው ፡፡ ሆኖም እነዚህ ከንውኖች ለሁሉም ሰው አልጋ በአልጋ ሆነው አይገኙም ፡፡ ስለዚህም አንዳንዶች እኔ እና ፈጣሪ ሽርክ ነን ቢሉ ልንገረም አይገባንም ፡፡ እንደሰዉ ገጠመኝ ክንውኖቹ ይለያያሉ እንጂ ሁላችንም ከፈጣሪ ጋር ሽርክ ነን ፡፡ እንደ አዲስ ስለሚታይ ነው ፡፡…በፈጣሪ ዘንድ አዲስ ነገር ባይኖርም ፡፡ …

በዚህ ዓለም ፣ በጎና ክፉ ፤ አሥደሳች ና አሥከፊ ፤ መራራና ጣፋጪ ፤ ጥላቻና ፍቅር ፤ ማግኘትና ማጣት ፤ መጥገብና መራብ ፤ ሐዘን ና ደስታ ፤ ወዘተ ። ሁሉም ያሉ ና የነበሩ ናቸው ፡፡ አንዳንድ የገዘፈ ምናብ ያላቸው ሰዎች ፣ በየደቂቃው በህይወት ጉዟቸው የሚያጋጥማቸውን ፣ ማንኘውንም ክስተት እና ገጠመኝ ፣ ከፈጣሪ ፍላጎት ጋራ የሚያገነኙ በመሆናቸው ሥለምንም ነገር የማይደንቃቸው ሆነው የምናገኛቸው የመፀሐፍ ቅዱሱ የሰባኪው መክብብ ሐሳብ በቅጡ ስለገባቸው ነው ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  አንድ ሕዝብ ነን ወይስ አይደለንም - nፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

በእርግጥ እነዚህ አራት ዐይና ሰዎች ህይወትን ጠንቅቀው በማወቃቸው አብዝሃኛው የዓለም ነገር አይደንቃቸውም ፡፡ አይገርማቸውምም ። አይሞቃቸውም ፤ አይበርዳቸውም ፡፡ ብዙዎቻችንን ግን ፣ ህይወት የምታሥደምመን በሌላው ህይወት ላይ ሥትጨክን ወይም ደግ ሥትሆን ብቻ ነው ። ለምን ብለን ብንጠይቅ እሥከዚህ አስደንጋጭ ክሥተት ጊዜ ድረስ ዐይናችንን ቸፍነን በጭለማ ውስጥ ሥለነበር ነው ፡፡

ዐይናችን ተጨፍኗል ሥል ፣ ሥለተዘጋ ዐይን ማውራቴ አይደለም ።ሥለ ውሥጣዊ አይናችን እያወራሁ ነው ፡፡ ሥለ ውስጣዊው  ልቦናችን እያወራኋቸሁ ነው ።ታቃላችሁ ፤ ልቦናችን ሥለ ሌላ በጥልቀት እያሰበ ሣለ ፣ ዐይናችንን ዙሪያ ገባውን እንዲያይ ለማዘዝ አንችልም ። ዐይናችን  የሚታዘዘው ፣ በልቦናችን ነውና !

በልቦና የሚታዘዝ በመሆኑም ነው ፣ እያያን ሲመሥለን የማናየው ። ይህ እውነት የሚያሥረዳን ሰው ሰለራሱ ህሊና አሠራር የሚያውቀው እጅግ ጥቂቱን መሆኑንን ነው ። በሣይንቲሥቶቹ ደረጃ ሥለህሊና እና ፈጣሪ የገዘፈ ያለማወቅ ካለ ፣ በተርታው ሰው ያለው ያለማወቅ ደግሞ የትየለሌ ይሆናል ፡፡

ጥቂት የማይባል አማኝ  ሰው ፣ የፈጣሪን  ሁሉን ቻይነት በተሳሳተ መረዳት ተገንዝቦ  ፈጣሪን እንደ አንድ ግዙፍ ሰው ይቆጥረዋል ፡፤ ” ሰማይ መቀመጫው ምድር መረገጫው ነው ፡፡ ” የሚለውን አባባል ያዝልኝ ፡፡ ይህንን ሲል ፈጣሪን ሰው አደረገው ማለት ነው ፡፡ …

ጥቂት የማይባል አማኝ ሰው ፈጣሪን ከሰማይና ከምድር ጋር ግዝፈቱን ቢያመሳስለውም ፈጣሪያችን ግን መንፈሥ ነው ። ልንዳስሰውና ልትጨብጠው ከቶም አትችልም ። ፈጣሪ በአንተ እና ባንቺ ውሥጥ ብቻ ሣይሆን ገና ባልተወለደው ጨቅላ ውሥጥ ያለ መንፈሥ ነው ። ፈጣሪ እንደ ድር በሁሉም ሰው ውሥጥ ፣ በሁሉም ሥፍራ ፣ በየትኛውም ጊዜ ና ቦታ ያለ ነው ። ፈጣሪ በእያንዳንዷ የጠፈር ክፍል ውስጥ ያለ የነበረ ና የሚኖር ነው ፡፡…

ፈጣሪ በቦታ ፣ በጊዜ ፣ በሁኔታ እና በሥፍራ አይወሰንም ። ዛሬ ቻይና ነገ አሜሪካ እሄዳለሁ ብሎ እቅድ አያወጣም ። ፈጣሪ ሁሉም ቦታ ፣ ሁል ጊዜ ፣ በሁሉም ሥፍራ እና በአሥቸጋሪ ና በፈታኝ ሁኔታዎች ውሥጥ ሁሉ ፣ በድል አድራጊነት ፣ ሳይፈተን የሚገኝ ነው ። ለእኛ ለምድር ሰዎች ፣  ፈጣሪ እንደምንተነፍሰው አየር ነው ። …

እናም የእያንዳንዳችንን እሥትንፋሥ ለማሥረዘምም ለማሣጠርም የሚችለው ፈጣሪ ብቻ ነው ።

ዛሬ ና አሁን ፣ በዓለም የምናየው እውነት ግን ፈጣሪያቸውን ሰዎች የሚያሥታውሱት አየር ሲያጥራቸውና እሥትንፋሳቸው ልትቆረጥ ጉሮሯቸው ጋር ሥትደርስ ብቻ ነው  ።

 

1 Comment

  1. ይገርማል ግሩም ጽሁፍና አስተማሪ ከመሆኑ ባሻገር በማህደር የሚያዝ ነው።ጸሀፊው ይህን ምክር የሰጡን ሙያዎ በዚህ ያተኮረ በመሆኑ ነው ወይስ የመንፈሳዊ ህይወቶ የጎለበተ በመሆኑ ነው?እናመሰግናለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share