“ሕዝቡ አሸባሪውን በመቅበር ራሱን ከሰቆቃ አገሩን ከዓለም አቀፍ ጫና መታደግ አለበት”

– አቶ ክርስቲያን ታደለ የአብን የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ

christian

ህዝቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በአንድነት ተነስቶ አሸባሪውን ህወሓት በማስወገድ ራሱን ከሰቆቃ አገሩን ከዓለም አቀፍ ጫና መታደግ አለበት ሲሉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ክርስቲያን ታደለ ገለጹ፡፡
አቶ ክርስቲያን በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፣ አሸባሪው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ አሰቃቂና አስነዋሪ ጥቃት ከፈጸም ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት በአማራና አፋር ክልሎች ንጹሃን ዜጎችን ኢላማ ያደረገ ጅምላ ጭፍጨፋዎችን ፈጽሟል፡፡
ወራሪ ቡድኑ አሁንም አገር ለማፍረስ ያለ የሌለውን አቅሙ ተጠቅሞ በከፍተኛ ሁኔታ እየተፍጨረጨረ ይገኛል፡፡ ህዝቡ አሸባሪውን ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመቅበር ራሱን ከሰቆቃ አገሩን ከዓለም አቀፍ ጫና መታደግ አለበት ብለዋል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ንጹሃን ዜጎችን እየጨፈጨፈ ቢሆንም በቅጥረኞቹ አማካኝነት በዓለም መድረክ ተበዳይ በመምሰል ኢትዮጵያ ላይ የውጭ ጫና እንዲደረግባት እየሰራ መሆኑን ያነሱት አቶ ክርስቲያን፣ ህዝቡ በአንድነት ተነስቶ ቡድኑንና እኩይ ድርጊቱን ካላስወገደ ሰቆቃው እንደሚቀጥልና በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ጫናዎችም እየበረቱ እንደሚሄዱ ገልጸዋል፡፡
“የሽብር ቡድኑ በአገሪቱ ላይ የፈጸማቸው በደሎችና ሴራዎች በአገሪቱ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ምዕራባውያንና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጭምር ይታወቃል ያሉት አቶ ክርስቲያን፤በአሁኑ ጊዜም ወራሪው ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ነፍሰጡር ሴቶችን፣ አቅመ ደካሞችና ህጻናትን በጭካኔ የጨፈጨፈ ቢሆንም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በዝምታ ማለፉ የሚያሳዝንና የሚያስተዛዝብ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በአንጻሩ ምዕራባውያን የንጹኃን ዜጎች ህይወት ለመታደግ የሚደረግ እንቅስቃሴን በማውገዝ ማዕቀብ ለመጣል መሸቀዳደማቸው የሚኮነን ተግባር መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
(ኢ ፕ ድ)
ተጨማሪ ያንብቡ:  Sport: አርሰን ቬንገር እያደኗቸው ያሉት 5 ወጣት ተጫዋቾች

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share