❝ሁሉም ወደ ወሎ ይትመም፣ ይዝመት❞ ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ

246809762 3249503241953652 6787353081420082838 n

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም አሸባሪው የትህነግ ኃይል ያለማቋረጥ በርካታ ወገን ገድሏል፣ ሕዝብ አፈናቅሏል። መንግሥትና ሕዝብ የሠራውን መሠረተ ልማት አውድሟል ነው ያሉት። ጥቃቱን መመከት የሚቻለው ራስን በማደራጀትና በአንድነት በመነሳት ነውም ብለዋል።
የጥቃቱ ዓላማ ኢትዮጵያን ማፍረስና ምሥራቅ አፍሪካን ማተራመስ መሆኑን ገልጸዋል። ትግሉ የአማራና የአፋር ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ መሆኑን ነው ነው የተናገሩት።
የክልሉ መንግሥት አስቀድሞ ባደረገው የክተት ጥሪ የጠላትን ኃይል በተለያዩ አካባቢዎች መግታት መቻሉን ነው የገለፁት።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሻ ጋር በመሆን በተለያዩ አካባቢዎች መመከት መቻሉንም አስታውቀዋል።
በቅርብ ጊዜ የጠላት ኃይል ከጀርባው ብዙ ሕዝብ በማስከተል ትኩረቱን ደሴና ኮምቦልቻ ላይ በማድረግ ጥቃት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።
ጥቃቱን ለመመከት ጀግናው መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻ ከጀግናው የአካባቢው ሕዝብ ጋር ጠላትን እየተፋለመው መሆኑን ገልጸዋል። አኩሪ ጀብዱ እየተፈጸመ መሆኑንም አንስተዋል።
የደቡብ ወሎ ሕዝብ በአንድነት በመትመም ከሠራዊቱ ጋር በመሰለፍ ስንቅ በማዘጋጀት እና ሞራሉን በማነሳሳት የጀግንነት ደጀንነቱን እያረጋገጠ ይገኛልም ነው ያሉት።
ጠላት አሁንም ሕዝብ አሰልፎ እየመጣ ስለሆነ ጠላትን ለመደምሰስ ሁሉም መተባበር ይገባል ነው ያሉት። ቀደም ሲል የተጠራውን የክተት ጥሪ መነሻ በማድረግ ሁሉም የመንግሥት እና የግል ታጣቂ ሁሉ ወደ ወሎ ይትመም፣ ይዝመት ብለዋል።
ሁሉም በጀመረው አግባብ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።
ተፈናቃይ ወገኖችን በመደገፍ ረገድ በውጭና በሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ነው የጠየቁት። አማራና አፋር ክልል ተጠቅቶ የሚተርፍ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ የለምም ብለዋል። መላው የሀገሪቱ ሕዝብ በአንድነት የሚነሳበትና ጠላትን ከሀገር የሚያጠፋበት ጊዜ መሆኑን ገልጸዋል።
የክልሉ ሕዝብ ቀደም ሲል የያዘውን አቋም የበለጠ በማጠናከር እና በመደራጀት እንዲዘጋጅም ጠይቀዋል። የተራዘመ ትግል ስለሚጠይቅ በፅናት እንዲታገልም ጠይቀዋል።
የሕዝባችን እንባ በጀግኖች ትግልና መስዋእትነት ይታበሳል ብለዋል። ጠላትን እንደምናሸንፈው አልጠራጠርም ነው ያሉት።
አሚኮ

ተጨማሪ ያንብቡ:  የደቡብ ክልል ተወላጆች ባቱ (ዝዋይ) ከተማን ለቀው እየወጡ ነው

2 Comments

 1. እነሱ ጦርነቱን ህዝባዊ አድርገውታል የኢትዮጵያ ህዝብም ነፃነቱን የሚያግኘው ሁሉም በመዝመት ነው ውጪ ያለነው በእካል መርዳት ባንችልም በገንዘብና ቁሳቁስ ወሎን መርዳት እንችላለን:: እንበርታ

 2. ወሎ ወሎ ወሎ
  ምን አጥፍቶ ይሆን? ከቶ ምን በድሎ?
  በወለጋ ጫካ ተከትፎ ተጥሎ
  በመተከል ቆላ በጅምላ ተገድሎ
  ደቡብ ጉራ ፈርዳ በግፍ ተፈናቅሎ
  ዛሬ በአጽመ ርስቱ
  የሚለመጠጠው በእሳት አሎሎ
  በምን አበሳው ነው ላኮመልዛ ወሎ?
  ካማራ ኦሮሞ ከአገው ተወልዶ
  ከአፋር ከትግሬ ከሌላም ተዛምዶ
  ተጠምቆና ሰልሞ ዱአ አርጎና ሰግዶ
  ከሁሉ እንደ እምነቱ የኖረው ተዋዶ
  ባራቱ ማእዘን እሳት ላዩ ነድዶ
  ምንድነው በደሉ
  የተፈረደበት እንዲኖር ተዋርዶ?
  ወሎ ‘ሚወርድበት
  የመከራ ዶፉ በቀንና በሌት
  ቢሆን አይደለም ወይ
  የኢትዮጵያ ማንነት ጭማቂ ተምሳሌት?
  ወሎ ላይ የከፋው መከራው ግነቱ
  ሌላ እዳ የለውም ይሄው ነው እውነቱ
  ኢትዮጵያ ስለሚል ነው ውሕድ ማንነቱ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.