ለቸኮለ! ረቡዕ ጥቅምት 10/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

ዘግይቶ ባገኘነው ዜና

ተመድ በትግራይ ያሉትን የዕርዳታ ሠራተኞቹን በቅርቡ በግማሽ ለመቀነስ ማቀዱን አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል። ድርጅቱ በክልሉ ያሉትን 530 የዕርዳታ ሠራተኞች ወደ 220 ዝቅ እንደሚያደርግ የድርጅቱ ሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቃል አቀባይ ተናግረዋል። ድርጅቱ የዕርዳታ ሠራተኞቹን ለመቀነስ ያሰበው፣ በእርዳታ ሥራው ላይ ያሉት እክሎች ባለመፈታታቸው እና የጸጥታው ሁኔታ በማሽቆልቆሉ እንደሆነ ገልጧል።

1፤ ዛሬ ረፋዱ ላይ በመቀሌ የአየር ድብደባ እንደተፈጸመ የአማጺው ሕወሃት ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የድብደባው ዒላማ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ኩባንያ እንደሆነ ያመለከቱት ዘገባዎቹ፣ በጥቃቱ በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ ገልጠዋል። የጥቃቱ ዒላማ መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ኩባንያ መሆኑን ሮይተርስም የረድዔት ድርጅቶች ምንጮችንና ሌሎች ዓይን ምስክሮችን ጠቅሶ ዘግቧል። የአማጺው ሕወሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካዔል ግን፣ በድብደባው የተመታው መስፍን ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ሳይሆን በቅርብ ያለ የግል ኩባንያ ነው ሲሉ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

2፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዛሬ በመቀሌ የፈጸመው የአየር ድብደባ ዒላማ የአማጺው ሕወሃት የጦር መሳሪያ ማምረቻ፣ ማከማቻ እና የጦር ትጥቅ መጠገኛ ጣቢያዎች መሆናቸውን የኢትዮጵያ ወቅታዊ መረጃ ማጣሪያ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

3፤ የአማጺው ሕወሃት ታጣቂዎች በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በምትገኘዋ ውርጌሳ ከተማ 13 ሰላማዊ ሰዎችን እንደረሸኑ የመንግሥት ዜና አውታሮች ዘግበዋል። ጥቃቱ መቼ እንደተፈጸመ ግን ዘገባዎቹ አልገለጹም። በሰሜን ጎንደር ዞን አድርቃይ ወረዳ ደሞ የአማጺው ታጣቂዎች የዛሪማ ከተማን መስጅድ እንዳወደሙ የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መግለጹን የክልሉ ቴሌቪዥን ዘግቧል።

4፤ ቴሌግራፍ ጋዜጣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ የዕርዳታ እህል ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ አግዳለሁ በማለት ዝተዋል በማለት የሰራው ዘገባ የተዛባ መሆኑን የኢትዮጽያ ወቅታዊ መረጃ ማጣሪያ ግብረ ኃይል በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ጋዜጣው አዛብቶ አቀረበው የተባለው፣ ዐቢይ ባለፈው ሳምንት “የዕርዳታ ስንዴ ማስገባት ብናቆም 70 በመቶው የኢትዮጵያ ችግር ይቃለላል” በማለት የሰጡትን አስተያየት ነው። ዐቢይ ይህን የተናገሩት ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን እንድትችል ከመፈለግ እንጅ የዕርዳታ ስንዴን ከማገድ አንጻር አይደለም ያለው መረጃ ማጣሪያው፣ ዘገባው የሚያሳየው ጋዜጣው ቀድሞ በኢትዮጵያ ላይ የያዘውን አጀንዳ ማራመድ መፈለጉን ነው ብሏል።

5፤ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የሰዓት እላፊ አዋጅ እንዳወጀ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። ከዛሬ ጀምሮ በከተማዋ ከጸጥታ እና ጤና ተቋማት ውጭ ያሉ ተሽከርካሪዎች ከምሽቱ2:30 እስከ ንጋቱ 11 ሰዓት ድረስ እንዳይንቀሳቀሱ ያገደ ሲሆን፣ ከምሽቱ 4 ሰዓት ጀምሮ ደሞ የሰዎችን እንቅስቃሴ አግዷል። አስተዳደሩ በከተማዋ መውጫና መግቢያ ጥብቅ ጥበቃ እና ፍተሻ እንደሚያደርግ፣ ወጣቶችን ለጸጥታ ጥበቃ ሥራ አደራጅቶ እንደሚያሰለጥን፣ የግል ታጣቂዎችን እና የመከላከያ ሠራዊት ተመላሾችን እንደገና መልምሎ ወደ ሥራ እንደሚያስገባ እና ሌሎች ርምጃዎችን እንደሚወስድ አክሎ ገልጧል።

6፤ አማራ ክልል በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ከባድ የበጀት ጫና ውስጥ እንደገባ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ጥላሁን መኻሪ ለሸገር ተናግረዋል። ጦርነቱ በክልሉ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ የገለጡት ሃላፊው፣ ፌደራል መንግሥቱ ከመጠባበቂያ በጀቱ ቀንሶ ለክልሉ ልዩ የበጀት ድጋፍ እንዲያደርግ የክልሉ መንግሥት በይፋ መጠየቁን ጠቁመዋል። ክልሉ ከፌደራል መንግሥቱ የጠየቀው የበጀት ድጋፍ ምን ያህል እንደሀነ ግን ዘገባው አልገለጸም። ከዓመታት በፊት የክልሉ የዕድገት ምጣኔ አሳማኝ ባልሆነ ሁኔታ ዝቅተኛ ሆኖ በመሰላቱ እና በሕዝብ ቆጠራ ላይ በተፈጸመው ስህተት የተነሳ፣ ፌደሬሽን ምክር ቤት እስካሁንም ለክልሉ የሚደለድለው የበጀት ድጎማ አነስተኛ ሆኖ መቀጠሉ ችግሩን እንዳባባሰው ሃላፊው አክለው ገልጠዋል። ፌደሬሽን ምክር ቤት ከጥቂት ዓመታት በፊት የተደረገውን የዕድገት ምጣኔ ማሻሻያም ገና ተግባራዊ እንዳላደረገ ሃላፊው አስታውቀዋል።

7፤ የፌደራሉ ዓቃቤ ሕግ ዛሬ በባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፓርቲ አመራሮች ለመሠረተው የሽብር ክስ ዛሬ በግልጽ ችሎት ምስክሮቹን ማሰማት መጀመሩን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል። ዓቃቤ ሕግ ለዛሬ ከጠራቸው 9 ምስክሮች ዛሬ ችሎት ያቀረበው ሁለቱን ብቻ ነው። ከዘጠኙ ምስክሮች ሁለቱ የሚመሰክሩት በፓርቲው ሊቀመንበር እስክንድር ነጋ ላይ እንደሆነ ዓቃቤ ሕግ ለችሎቱ አስረድቷል። ዓቀቤ ሕግ የቀሪዎቹን 12 ምስክሮቹን ስም ዝርዝር ዛሬ ለመገናኛ ብዙኀን በይፋ እንዲገልጽ ትናንት በችሎቱ ታዞ የነበረ ቢሆንም፣ ስም ዝርዝራቸውን ግን ዛሬ ሳይገልጽ ቀርቷል።

8፤ ምርጫ ቦርድ በመጭው ታኅሳስ 21 በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምርጫ እንደሚያካሂድ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰራጨው መረጃ አስታውቋል። በሰኔ እና መስከረም በሌሎች ክልሎች ጠቅላላ ምርጫ ሲካሄድ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በጸጥታ መደፍረስ ሳቢያ የክልል ምክር ቤት እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ እንዳልተደረገ ይታወሳል። በታኅሳስ ምርጫ የሚካሄድባቸው ምርጫ ክልሎች 17 ናቸው። [ዋዜማ ራዲዮ]

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.