ለቸኮለ! ሐሙስ መስከረም 20/2014 ዓ.ም የዋዜማ ዐበይት ዜናዎች

1፤ መንግሥት በሀገሪቱ ውስጣዊ ጉዳይ እጃቸውን አስገብተው የተገኙ በተመድ ድርጅቶች የሚሠሩ 7 የውጭ ዜጎችን በ72 ሰዓታት ከሀገር እንዲወጡ ማዘዙን ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። ከሀገር እንዲወጡ ከታዘዙት መካከል፣ በኢትዮጵያ የተመድ ሕጸናት ድርጅት ተወካይ አደል ኮደር እና በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ሜርሲ ቪጎዳ ይገኙበታል። ቀሪዎቹ በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ እና በተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያየ ሃላፊነት የሚሠሩ ናቸው። ግለሰቦቹ ከሀገር እንዲወጡ የታዘዙት፣ በሀገሪቱ ውስጣዊ ጉዳይ እጃቸውን በማስገባታቸው እንደሆነ ተገልጧል።

2፤ አዲሱ የአማራ ክልል ምክር ቤት በአገኘሁ ተሻገር ምትክ ይልቃል ከፋለን ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ እንደመረጠ የክልሉ ብዙኀን መገናኛ ኮርፖሬሽን ዘግቧል። አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር የካቢኔያቸውን አባላት ለምክር ቤቱ አቅርበው አስሹመዋል። የተቃዋሚው አብን ከፍተኛ አመራር ጣሂር ሞሐመድ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሆነው ተሹመዋል። የሲዳማ እና ጋምቤላ ክልል ምክር ቤቶች ደሞ ነባር ርዕሰ መስተዳድሮቻቸውን በድጋሚ መርጠዋል።

3፤ ዛሬ በሱማሌ፣ ሐረሬ እና በደቡብ ክልል የተወሰኑ ምርጫ ክልሎች የክልል እና ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ምርጫ ሲካሄድ ውሏል። በደቡብ ክልል ምርጫ የሚካሄደው በ11 ዞኖች እና በሁለት ልዩ ወረዳዎች ነው። በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የሚኖሩ የሐረሬ ብሄረሰብ ተወላጆች ለክልሉ ብሄረሰብ ምክር ቤት አባላት ድምጽ ሰጥተዋል።

4፤ በሱማሌ ክልል በሞያሌ ምርጫ ክልል በሚገኝ አንድ ምርጫ ጣቢያ ዛሬ የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ እንደተቋረጠ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ዛሬ ለጋዜጠኞች መናገራቸውን ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘግቧል። የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የተቋረጠው፣ ምርጫ አስፈጻሚዎች በምርጫ ጣቢያው አካባቢ የአጋራባቹ ኦሮሚያ ክልል ጸጥታ ኃይሎች ሲንቀሳቀሱ አይተው የደኅንነት ስጋት ስለተፈጠረባቸው እንደሆነ ብርቱካን ገልጸዋል።

5፤ ዛሬ ምርጫ ቦርድ በደቡብ ክልል ምዕራባዊ ዞኖች የክልልነት ሕዝብ ውሳኔ አካሂዷል። የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ከደቡብ ክልል ተነጥሎ የደቡብ ምዕራብ ክልልን ለማቋቋም ወይም በደቡብ ክልል ውስጥ ለመቀጠል የሚያስችል ይሆናል። በሕዝበ ውሳኔው የተሳተፉት፣ የካፋ፣ ቤንች፣ ጋሞ፣ ሸካ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ እና ዳውሮ ዞኖች እና የኮንታ ልዩ ወረዳ ሕዝቦች ናቸው።

6፤ ኢዜማ ገዥው ፓርቲ ባቀረበልኝ የአብረን እንስራጥያቄ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ለማሳለፍ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርቻለሁ ሲል በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል። የፓርቲው ብሄራዊ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከገዥው ፓርቲ የቀረበውን የአብረን እንስራጥያቄ ሲወያይበት መቆየቱን ያወሳው ኢዜማ፣ አንዳንድ የክልል መንግሥታት ከወዲሁ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችን በሃላፊነት መሾማቸውን ጠቅሷል። ጉባዔው የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በሚያቀርበው መነሻ ሃሳብ ላይ የሚወያየው በቀጣዩ ቅዳሜ እና ዕሁድ ነው።

7፤ ወደ ትግራይ ክልል ምግብን፣ መድሃኒትን፣ የሕክምና ቁሳቁሶችን እና ነዳጅን ጨምሮ ሰብዓዊ ዕርዳታ ባስቸኳይ እና ያለገደብ እንዲገባ የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኻኖም በትዊተር ገጻቸው ጠይቀዋል። በክልሉ 5 ሚሊዮን ሕዝብ የርሃብ አደጋ እንደተጋረጠበት የገለጹት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ ከርሃብ ጋር በሽታ እና ሞት ተከትሎ ይመጣል ሲሉ አስጠንቅቀዋል። [ዋዜማ ራዲዮ]

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.