ሆሎዶሞር! የስታሊን ፍሬ! – ገለታው ዘለቀ 

geletaw
ገለታው ዘለቀ
         ሆሎዶሞር የሚለው ቃል ዩክሬንኛ ነው። ዩክሬን ውስጥ በ1932 እና በ 1933 አመተ ምህረት መካከል በሚሊዩን የሚቀጠር ሰው በረሃብ አለቀ። በኣለማችን በጣም አሰቃቂ ከሚባሉት የረሃብ እልቂት ውስጥ አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል። ሆሎዶሞር ማለት በዩክሪኖች ቋንቋ ሆን ብሎ አስርቦ መግደል ማለት ነው። ይህ የዩክሬኖች የታሪክ ጠባሳ የተከሰተው በወቅቱ በነበሩ መሪዎች ጭካኔ ነበር። ረሃቡ እንዲደበቅ በማድረግ፣ የተራበው ሰው ከኣንዱ ክፍለ ሃገር ወደ ሌላው እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ፣ አለማቀፍ እርዳታ እንዳይደርስ መንገድ በመዝጋት በወቅቱ የነበሩ መሪዎች ሚሊዩን ሰው በረሃብ  ጨረሱ። ዩክሬን ውስጥ ህጻናት ዋይ ዋይ እንዳሉ፣ ሽማግሌዎች እንዳቃሰቱ ተሰቃይተው ይህቺን ኣለም የተሰናበቱት ሰው ሰራሽ በሆነ ረሃብ ነው። ዛሬ የዩክሬን ህዝብ ያንን ታሪኩን ሃውልት ተክሎለት ሲጸጸት ይኖራል።
ከእለታት አንድ ቀን አንዲት ቦስተን ውስጥ የምትኖር ዩክሬናዊት ሴት ቤት ከጓደኞቼ ጋር ራት ተጋብዘን በልተናል። የዚህች ሰው ቤተሰቦችም ነበሩ። ታዲያ ይህቺ ዩክሬናዊት ራት በልተን ስናበቃ የተራረፈውን በመሰብሰብ ተጠምዳ ሳለች ጨዋታ ጀመርን። “በኛ ባህል የተረፈ ምግብ ኣይጣልም። ምግብ በጣም የተከበረ ነው” አለችኝ። ታሪካዊ ዳራውን ስታጫውተኝ “ዩክሬን ውስጥ ያ ሁሉ ሰው በረሃብ ያለቀው በእስታሊን የሚመራው መንግስት የፈጸመው ሆሎዶሞር ( አስርቦ መግደል) ነበር::  በዚያን ጊዜ ዩክሬን ከባድ ድንጋጤ ወደቀባት:: ህዝቡ ደንገጠ:: ስለሆነም እስካሁን ድረስ ለምግብ ትልቅ ክብር አለን፣ የተረፈንን አንጥልም፣ ጥንቅቅ አድርገን እንበላለን…..ቤተሰብ እንደዚያ ነው ያስተማረን ….. አለችኝ ጸጸትን ከፊቷ እያስነበበችኝ። ታሪኩን ቀደም ብየ የማውቅ ቢሆንም ባለታሪኳ ስታነሳው ደግሞ ልቤ ተነካ። እኔም ወደ ሃገሬ በምናብ ተጓዝኩና የወሎን ረሃብ ኣሰብኩ። የኢትዮጵያውያን ሆሎዶሞር እያልኩ ተካከዝኩ። ወሎ ያ ሁሉ ህዝብ ያለቀው ድርቁ ከአቅማችን በላይ ከአለም እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች አቅም በላይ ሆኖ አልነበረም። ጭካኔ የተሞሉ መሪዎች መረጃውን ደብቀው ስላቆዩት ነው ብዙ ህዝብ ያለቀብንና የታሪክ ጠባሳ ያወጣነው። ያ ጊዜ አለፈ ቢባልም ኣያልፍም። በህሊናችን ውስጥ ሁሌም አለና…..
ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ረሃቦች በሙሉ ሰው ሰራሽ ናቸው። በተፈጥሮ አደጋ የሚገለጹ አይደሉም። የምንራበው ዝናብ የለም ብለን ይሆናል፣ ነገር ግን ከፍተኛ የከርሰ ምድር ውሃና አያሌ ጅረት ያለን ሰዎች ነን። የምንራበው መሬት አነሰ ብለን ይሆናል፣ ነገር ግን መታረስ የሚገባውን መሬት ግማሹን ያላረስን ሰዎች ነን። የምንራበው በጦርነት ውስጥ ገብተን ነው ብለን ይሆናል፣ ነገር ግን አንድ ላውንቸር በብዙ ሺህ ዶላር እየገዛን፣ ታንክና ዲሽቃ በሚሊዩን ብር እየገዛን፣ በየቀኑ ለምንተኩሰው ጥይት ሚሊዩን ብር እያወጣን ነው የምንራበው። ስለዚህ ሃገራችን ውስጥ የተፈጥሮ ረሃብ የለም:: ሰው ሰራሽ ረሃብ ነው ያለው። በብዙ ብር መሳስሪያ እያስገባን ህዝቡ ረሃብ ላይ ነው አለም ርዳታህን ዘርጋ ስንል ህፍረት የሚባል የማይሰማን ኣይናችንን በጨው ያጠብን ፈጣጦች ሆነን ነው ህዝቡ መከራ የሚያየው።
በአሁኑ ወቅት የወሎው ወገናችንና የትግራዩ ወገናችን ረሃብ ላይ ነው። የወሎው ረሃብ ኣሁንም ተደብቆ ዜናው ሁሉ ኣይሰማም። በታሪካችን ላይ ሌላ ጠባሳ እየከተብን ነው። ይህ ነገር በፈጣሪም ዘንድ ይቅርታ የለውም። ሆሎዶሞር ይቅርታ የሌለው ሃጢያት ነው።
አሁን ኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆም አለብን። ረሃብ ያለባቸውን አካባቢዎች መርዳት፣ ማጋለጥ አለብን። ከመቼውም ጊዜ በላይ ንቁ መሆን ያስፈልጋል። ሃገራችን ከዚህ በሁዋላ ይህንን ኣሰከፊ ነገር እያየች መኖር የለባትም። የፖለቲካ ችግራችንን በፍጥነት በድርድርና በእርቅ እንፍታ፣ የገበሬውን የእርሻ ማንቆ እንፍታለት። ያለንን የተፈጥሮ ሃብት ተጠቅመን ቢያንስ ከረሃብ መላቀቅ አለብን። የለብንም?
የሰሜን ገበሬ በኣማካይ ስድስት ቤተሰብ ይዞ የሚኖረው ከአንድ ሄክታር መሬት በታች በሆነች መሬት ላይ ጥገኛ ሆኖ ነው። መሬት ከገበያ ላይ የሌለባት ሃገር ከመሆኑዋ የተነሳ ኑሮው ሁሉ በዚህች የበሬ ግንባር በምታክል መሬት ላይ ነው። በየኣመቱ እየተነሳ ሲገጥባት ቢኖር የሚያገኘው ምርት የትም አያደርሰውም። ስለሆነም ገበሬው የሚያመርተው ምርት አመት እንደማይቀልበው ስለሚያውቅ እንዲህ የሚል ስነ ቃል ይቀኛል።
ነሃሴ ቁልቁለቱ
መስከረም ዳገቱ
ጥቅምት አግድመቱ
ህዳር ገደርዳሬ
ታህሳስ ሆይ ጀብራሬ- እንጀራውን ይዘህ ምነዋ እስከዛሬ!
ይላል ገበሬው:: እነዚህ ወራት ከባድ የምግብ እጥረት የሚታይባቸው ጊዚያት ናቸው:: ገበሬው መከራ የሚያየው በፖሊሲ ችግር በመሆኑ ነው  የኢትዮጵያን ረሃብ ሆሎዶሞር ነው  የሚያሰኘን።
የሚያሳዝነው ሚራበው ገበሬው ብቻ ሳይሆን ዋና ከተማችን ያለው ህዝብም ነው። በኣሁኑ ሰኣት ከመቶ ሺህ ህዝብ በላይ አዲስ አበባ ውስጥ በረሃብ እየተሰቃየ ነው። ህዝባችን ርቦታል። ይህ ህዝብ የእለት ጉርሱን ማግኘት አልቻለም። በታሪካችን ተሰምቶ የማይታወቅ ነው ይሄ ደግሞ።
አሁን በቃ!  ይበቃል። አሁን ረሃብ ከምድሪቱ መጥፋት አለበት። ለዚህ ደግሞ ብሄራዊ መግባባት የሽግግር ጊዜ ያስፈልጋል። በጣም አጣዳፊ የሆነው የወሎና የትግራይ የኣዲስ አበባ ረሃብ ጉዳይ መፍትሄ ይሻል። መንግስት ይህንን ረሃብ እያየ እንዳላየ ከሆነ በሰውም በእግዚኣብሄርም ፊት ይቀጣል።
በብሄር ብሄረሰብ መብት ትምህርት ተማርኪያለሁ የሚለው እስታሊን  ዩክሬን ውስጥ በረሃብ የገደላቸው ዜጎች ከሶስት ሚሊዩን ይበልጣሉ ይባላል። ብሄር ማለት የራሱ መሬት ያለው ነው እያለ እያስተማረ የዜጎችን ንቅናቄ ገድቦ ያን ያህል ሰው አስጨርሷል። ዛሬ ዩክሬን ያንን ትምህርት አትከተልም። የስታሊንን ትምህርት እንደ ኣውሬ ነው የምታየው።  ዩክሬን ውስጥ ለስታሊን የተቀመጠለት ሃውልት ሆን ብሎ በረሃብ የጨረሰ ጨካኝ መሪ….. የሚል ነው። ሃገራችን ኢትዮጵያ ብቻ ናት እስካሁን የዚህን ሰው ትምህርት ይዛ የምትራበው። የመሬት ፖሊሲው የዚህ ገዳይ ሰው ትምህርት ነው። የብሄር ብሄረሰብ ትርክቱ የዚህ  ገዳይ  ሰው ሃሳብ ነው። ስለምን ሃገራችን ኢትዮጵያ በዚህ ሰው ትምህርት ትራባለች? ለምን በዚህ ሰው ትምህርት እንፈናቀላለን? ለምን የኔ….የኔ..የኔ……በሚል እንዋጋለን? ለውጥ ያስፈልጋል።
ኢትዮጵያውያን በአንድነት እንነሳ። የሰው ልጅ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በረሃብ ሊሞት አይገባም። ሳይንስ ቴክኖሎጂ አድጎ ሰው በረሃብ የሚሞትበት ዘመን አልፉዋል።
ገለታው ዘለቀ
እግዚአብሄር ይርዳን!
ተጨማሪ ያንብቡ:  ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ - መላ መላ ብለው ኅሊናዎን አበርትተው ለንሥሃ ይብቁ! - ከበየነ

1 Comment

  1. You can’t contrast that historical junction with on going ETHIOPIAN cause & effect complete different. ETHIOPIA in national just war agnist the junta Wayanee tgrie group & emansupate forign power. Thanks

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share