የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከየት ተነስቶ ምን ደረሰ?


ከእውነቱ በለጠ

ኢትዮጵያ በአንድ ወቅት ገናና ሀገር ነበረች፡፡ የኢትዮጵያም ሙዚቃ በጥንት ጊዜ ጅማሮው ላይ ታላቅ ነበር፡፡ ‹‹ታላቅ ነበር›› ብቻ ብለን ሳናሳድገው ቀረን እንጂ፡፡ የዜማው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ለሰራቸው ዜማዎቹ ምልክቶችን በማድረግ ተማሪዎቹ ዝማሬዎቹን መረዳት እንዲችሉ ቀድሞ የኖታን ፅንሰ ሀሳብ ያሰበ እና ያበረከተ ታላቅ ሰው ነበር፡፡ የእርሱ ምልክቶች (ኖታዎች) የሚያሳዩትና የሚያመለክቱት ነገሮች ውሱንነት ቢኖርበትም ከአውሮፓውያኑ የኖታ ዘዴ መጀመሪያ ከ400 ዓመታት በፊት ግን ቀድሞ ሙከራውን አድርጎ ነበር፡፡ እርሱ ፈጠረው ከሚባለው ውጪ ምንም ሳያድግ እና ሀሳቡም ሳይሰፋ ባለበት ቀረ እንጂ፡፡

ሙዚቃን ከአንድ ትውልድ ወደ ሌላ ትውልድ ለማስተላለፍ አሁን እንዲህ ቴክኖሎጂ እና ቅጂ (ድምፅ ቀረፃ) ባልነበረበት ጊዜ እንዴት አስቸጋሪ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡ እንኳን ለሌላ ሰው በአፍ ብቻ የነገርነውን ዜማ ቀርቶ ራሳችን የያዝነውን ዜማ በሌላ ጊዜ ለመድገም አስቸጋሪ ነው፡፡ የግድ ቀድተን ወይንም በኖታ ፅፈን ካልሆነ ማስታወስ ከባድ ነው፡፡ የኖታ መጀመር በሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ከታዩ ክስቶች ትልቁን ቦታ ቢይዝ የሚያስገርም ነገር አይደለም፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ የት ተጀመረ? የት ደረሰ? ሙዚቃችን አድጓል ወይስ ወድቋል?›› የሚሉት ጥያቄዎች ሰሚውንም ይሁን ጠያቂውን ያሰለቸ እንዲሁም አጥጋቢ መልስ ያልተገኘላቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡

አሁን ስላለንበት ‹‹ዘመናዊ›› ሙዚቃ አስተሳሰብ ከመግባታችን በፊት የኢትዮጵያ ሙዚቃ መንገድ ወይም ጉዞ ምን ይመስል እንደነበር እንመልከት፡፡

ጥንት

ኢትዮጵያ በአክሱም ስርወ መንግስት ወቅት ከ350 ዓ.ም በፊት (ክርስትናን ከመቀበሏ በፊት) በአገራችን ውስጥ የነበሩት የእምነት ስርዓቶች የአይሁድ እምነት እና የባህል አምልኮ ስርዓቶች ነበሩ፡፡ ሙዚቃ ደግሞ ከአምልኮ ጋር ብዙ ጊዜ ቀጥተኛ ተያያዥነት ያለው በመሆኑ የእነዚህ ሃይማኖቶች የአምልኮ ስርዓት ላይ ጭፈራዎች፣ ዜማዎች እና የተወሰኑ ስርዓቶች ይደረጉ እንደነበር መገመት ይቻላል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ታሪካዊው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት በአዲስ አበባ ተካሄደ

በአክሱም ዘመነ መንግስት ከተፈጠሩ ክስተቶች መካከል አንዱና ትልቁ የክርስትና እምነት ወደ አገራችን መግባት ነው፡፡ ክርስትና ከገባ 250 ዓመት በኋላ የኖረው ቅዱስ ያሬድ በዝማሬው በኩል በተለይ ስርዓቱን የጠበቀ የሙዚቃ /የዜማ ዘዴ እንደዘረጋ ይታወቃል፡፡ በኢትዮጵያ የሙዚቃችን ታሪክ ያን ጊዜ እንደተመሰረተ ይታመናል- አሁን የደረሰበት ቢደርስም፡፡

መካከለኛው ዘመን

ከዚያም በዛግዌ ስርወ መንግስት እንዲሁም በመቀጠል ባሉት ጊዜያት ከመንፈሳዊው ዓለም ውጪ ሙዚቃን እንደመተዳደሪያቸው አድርገው የተነሱ እንደነ አባውዴ (አሚናዎች) በተለምዶ ላሊበሎች የሚባሉትን በኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ማንሳት እንችላለን፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ደግሞ የአዝማሪዎች ድርሻ እና በኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የነበራቸው ተፅዕኖ ከፍተኛ ነበር፡፡ በአንዳንድ የቤተ መንግስት ክፍሎች ውስጥ ተቀጥረው መስራት መጀመራቸው ደግሞ ሌላው በሙዚቃችን ታሪክ ውስጥ የምናነሳው ጉዳይ ነው፡፡

ከአክሱም ስርወ መንግስት ጀምሮ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ የዜማ ትምህርት ይሰጥ የነበረው በቤተክርስቲያን ውስጥ ብቻ ነበር፡፡ ለብዙ ዓመታት ቤተክርስቲያን የዜማ /የሙዚቃ ምንጭ ነበረች፡፡

ዘመናዊ ጊዜ

ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ ትልልቅ ክስቶች የታዩበት ወቅት ነው፡፡ ለዕድገት እና ‹‹ዘመናዊነት›› ትልቅ ፍላጎት የነበራቸው አፄ ምኒልክ በጊዜያቸው የሙዚቃ ትምህርት እንዲሰጥ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ ከሩሲያ የመጡ ሙዚቀኞች አገራችን ውስጥ ሙዚቃን እንዲያስተምሩ አድርገዋል፡፡ ሙዚቀኞቹ ወደ አገራቸው ሲመለሱም ከአገልጋዮቻቸው የተወሰኑት ወደ ሞስኮ ሄደው ሙዚቃን እንዲማሩላቸው በዚያን ጊዜ ለነበሩት ጀነራል ብላሶፍ ደብዳቤ እንደፃፉ ጳውሎስ ኞኞ በታሪክ መፅሐፋቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡

አፄ ኃ/ሥላሴም አልጋ ወራሽና የአገሪቱ ባለሙሉ ስልጣን ከነበሩበት ወቅት አንስቶ በጥበቡ ዘርፍ ታላላቅ ተግባራትን ፈፅመዋል፡፡ ንጉስ ከመሆናቸው በፊት በአውሮፓ ባደረጉት ጉዞ ከኢየሩሳሌም ያስመጧቸው ከአርባዎቹ የአርመን ልጆች ብንነሳ እንኳን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር ዜማ የደረሱት ከአርባዎቹ አንዱ የሆኑት ኬቮርክ ናልባንድያን (kevork nalbandian) ነበሩ፡፡ ግጥሙን ደግሞ ዮፍታ ንጉሴ ፅፈውታል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  ታዋቂው የሙዚቃ ሰው ቴዲ ምትኩ በጠና ታሞ ሆስፒታል ገባ

ከኢየሩሳሌም ያመጧቸውን አርባዎቹን የአርመን ዜግነት ያላቸው ሙዚቃኞች የኢትዮጵያ ኦፊሻላዊ የማርሽ ባንድ አድርገው ቀጥረዋቸዋል፡፡ በዚያን ጊዜም እነዚህ ሰዎች በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለአገራችን ወጣቶች ሙዚቃን ያስተምሩ ነበር፡፡ የምኒልክና ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤቶች ዋና ተጠቃሽ ቦታዎች ናቸው፡፡

አፄ ኃ/ሥላሴ ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ቴአትር ቤቶችን በማቋቋም ለአገራችን የጥበብ ዕድገት ትልቅ ሚና ተጫውተዋል፡፡ የቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ቴአትር ቤት (የአሁኑ ብሔራዊ ቴአትር) የማዘጋጃ ቴአትር ቤት፣ ራስ ቴአትር የመሳሰሉት በንጉሱ ዘመን የተሰሩ ነበሩ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በየዓመቱ እነዚህ ቴአትር ቤቶችና የተለያዩ ኦርኬስትራዎች የሙዚቃ ውድድር ያደርጉ ነበር፡፡ በሠራዊቱም ውስጥ የነበረው የሙዚቃ እንቅስቃሴ ትልቅ ደረጃ የደረሰ ነበር፡፡ የእነክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ፣ የፖሊስ ኦርኬስትራ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡

የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤትም የተመሰረተው በዚሁ በንጉሱ ስልጣን ዘመን ወቅት ነው፡፡ በተቋም ደረጃ በአገራችን የመጀመሪያው የሙዚቃ ትምህርት ቤት እንዲከፈት እንዲሁም ጥበቡ እንዲስፋፋ ንጉሱ እገዛቸው ታላቅ ነበር፡፡

በደርግ ጊዜ የነበረውን የሙዚቃ ሂደት ብንመለከት ከሚነሱ ደካማ ጎኖች ውስጥ ሁልጊዜ  ምርመራ (ሳንሱር) መደረጉ፣ እንዲሁም እያንዳንዱ አልበም ውስጥ ቢያንስ አንድ ስለ ሀገር ሙዚቃ መስራት የሚያስገድድ ህግ መኖሩ በራሱ ጥቂትም ቢሆን አሉታዊ ጎን ቢኖረውም በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደግሞ ትልቅ የተባለው የባህል ቡድን ‹‹ህዝብ ለህዝብ›› በዓለም ዙሪያ ትርዒቱን ያቀረበው በዚሁ ወቅት ነው፡፡ የባህል ቡድኑ አላማ ምንም ይሁን ምን ባህላችንንና ሙዚቃችንን ለውጪው ዓለም በሰፊው አስተዋውቋል፡፡

በጊዜውም የግል ባንዶች መበራከትም የምናነሳው ሌላ አብይ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ ባንዶች በተለያዩ ሆቴሎች እና ምሽት ክበቦች ውስጥ ስራቸውን ያቀርቡ ነበር፡፡ ለምሳሌ ዳህላክ፣ ዳዲሞስ፣ ሮሃ፣ ኢትዮ ስታር፣ ዋሊያስ የመሳሰሉት ባንዶችን ማንሳት እንችላለን፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  "የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲያውቅልኝ የምፈልገው ነገር አለ" ድምፃዊ ደሳለኝ ብርሃኑ (Video)

አሁን ያለንበትን ጊዜ እንደ ታሪክ ሳይሆን እንደ ተጨባጭ ሁኔታ ስንመለከተው ከዚህ ቀደም ከነበረው በላይ ብዙ ሙዚቀኞችና ድምፃውያን የበዙበት ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡ የሙዚቃ ት/ቤቶች መብዛት፣ ከሌሎች ጊዜያት በተሻለ ለጥበቡ ትልቅ ስፍራ እየተሰጠ ያለበት ጊዜ ላይ እንገኛለን፡፡

በጥበቡም በኩል ጥሩ ጥሩ የሆኑ ቅንብሮች የሚቀርቡበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቴክኖሎጂው ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ እያደረገ ያለውን ጥሩ እና መጥፎ ጎን መመልከት ያለብን ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙ ጊዜ ይወስድ የነበረው የቀረፃ ሂደት ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ቀላል እየሆነ መጥቷል፡፡ ድምፃችንና የሙዚቃ መሳሪያዎችን በጥራት መቅረፅ ተችሏል፡፡ ቀረፃዎች ዲጅታላይዝድ መሆናቸው በሙዚቃችን ላይ ጥራትን ይጨምራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አብዛኛውን ነገር በኮምፒውተር ላይ ተደግፎ ማድረግ እንደ ጥበብ ሰዎች ተወቃሽ የሚያደርገን ጉዳይ ነው፡፡ አልበሞች የሚሰሩበትን ስቲዲዮዎች ማስፋት እና ደረጃውን የጠበቀ ማድረግ የባለሙያዎች ግዴታ ነው፡፡ ለጥበቡ እንደ ጥበበኛው ማንም ሌላ ግድ የሚለው የለምና፡፡ S

Share