የኢትዮጵያ አገር አድን ግብረኃይል
SAVE ETHIOPIA TASKFORCE
ዋሽንግተን ዲሲ
ሰሜን አሜሪካ
(August 19, 2021
ለሃያሰባት ዓመታት በሕወሃት የጭቆና ቀንበር ሲማቅቅ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕወሃትን እንዲታገል ቅስቀሳ ያስፈልገዋልን? ሕዝቡ በተለይም በአማራ ክልል አስታጥቁን እያለ ለመንግሥት ውትወታውን አቋርጦ በማያውቅበት ሁኔታ ተመችቶት እንደተኛ ሁሉ ለመቀስቀስ መሞከር ስሜት ይሰጣልን? በእውነት እንነጋገር ከተባለ መቀስቀስ ያለበት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀውና የአማራ ልዩ ሃይልና መከላከያ ከቁልፍ ቦታዎች እንዲያፈገፍጉ ትእዛዝ የሰጠው መንግሥት ነው ወይስ ከፍተኛ መስዋዕትነት በመክፈል ሕወሃትን ከኮረም ባሻገር ያሳደደው ሕዝቡ?
ለረዥም ጊዜ በመታሠር፣ በመገደል፣ ለከፍተኛ ስቃይ ተዳርጎ አካለ ጎደሎ በመሆን፣ በማንነቱ በመዋረድ፣ በመዘረፍና ከሃገር በመሰደድ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍሎ ሕወሃትን ከሦስት ዓመት በፊት ከስልጣን ያባረረው ሕዝብ በተለያየ መንግሥታዊና ግለሰባዊ አሻጥርና ሴራ እንደገና እንዲያንሰራራ የተደረገውን ሕወሃትን እንዲዋጋ ቅስቀሳ ሊደረግለት ይገባልን? ከአማራው ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለኝ ያለውን ሕወሃት ከተከዜና ከኮረም ወዲያ ለማሻገር በተለይ አማራው መቀስቀስ ያስፈልገዋልን? ሕዝቡ ለሃገሩ፣ ለወገኑና ለክብሩ ቅስቀሳ ያስፈልገዋል ብሎ ማሰብ አንድም ሕዝቡን በደንብ አለማወቅ ነው፤ ሌላም በመንግሥት በኩል በየጊዜው የተሠሩ ሴራና ስህተቶችን ለመሸፈን መሞከርና እንዲሁም የግል ዝና ለማትረፍ መባከን ነው ብለን እናምናለን።
ሕዝቡ በጋራ ሁኖ አባቶቹ በጋራ ያቆዩለትን ሃገር ዳር ድንበሯን ከጠላቶቿ በመጠበቅ ለሚቀጥለው ትውልድ ማስተላለፍ እንዳለበት ማንም ሊነግረውና ሊያስተምረው አይገባም። ቢሆንም በተለይም ፊት ለፊት ከጠላት ጋር ሲፋለም ከጀርባው ሴራ የሚጎነጎንበት ከሆነ፣ ያስለቀቀውን መሬት ለቀህ ውጣ የሚባል ከሆነ፣ ከጠላት የማረከው መሣሪያ ተሰብስቦ የሚወሰድበት ከሆነ፣ ሲደራጅ አትደራጅም የሚባል ከሆነ፣ አንተ ያልመከርክበት ሕገመንግሥት ለአንድ ክልል ብቻ ተብሎ አይለወጥም የሚባል ከሆነ፣ በስተሰሜን አማራው ከሕወሃት ጋር ሲፋለም ኗሪነታቸው በኦረምያ ክልል የሆኑ የአማራ ሚልሽያዎች ትጥቃቸውን በግድ እንዲፈቱ እየተደረገ የሆነኝ ተብሎ ለኦነግ ሸኔ እርድ የሚጋለጡ ከሆነ እንዴት ነው ሕዝቡ በተለይም አማራው በሕወሃት ላይ ያልተከፋፈለ ትኩረት ሊኖረው የሚችለው? ለመሆኑ በአፋር ክልል ለማንም የማፈግፈግ ትእዛዝ ሳይሰጥ በአማራ ክልል ግን ከኮረም፣ ከአለማጣና ከቆቦ የአማራ ልዩ ሃይልና ሚሊሽያ እንዲያፈገፍጉ ለተደረገበት ክስተት መልስና ማብራሪያ የሚሰጥ አካል አለን?
ለምንድን ነው ወገናችንን በተለይም በሃገሩ ዳር ድንበርና በወገኑ ህልውና የማይደራደረውን አማራውን በተደጋጋሚ በተወሳሰበ ሴራ ልቡን የምናደማውና ምሬት የምንፈጥርበት? በውጭ ሃገር በሰላማዊ ሰልፍ ላይ የአማራን መጨፍጨፍ ዓለም እንዳያውቀው የከለከለ ስብስብና በግለሰብ ደረጃ ብዙ ነገር የምንጠብቅባቸው የተወሰኑ ግለሰቦች ባዘጋጁት “ሕዝባዊ የትብብር ጥሪ” የውይይት ፕሮግራም ላይ በአማራው ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ላለመጥቀስ የዙሪያ ጥምጥም ሲሄድና በሃገር አንድነት ስም አማራው ለደረሰበትና እየደረሰበት ላለው ስቆቃ በከፊልም ሆነ በሙሉ መጠየቅ የሚገባውን አካል ላለማስቀየም ጥንቃቄ ሲደረግ ማየት እንዴት ልብ ይሰብራል!!!
ውድ ወገናችን ሆይ! በተለይም ብዙ ስቃይ ያስተናገድከውና በማስተናገድ ላይ ያለኸው አማራ ወገናችን ሆይ! ፈተናዎችህ ከዕለት ወደዕለት እየከፉና እየጨመሩ ሲሄዱ እንጂ ሲቀንሱ እየታዩ አይደለም። ማንኛውንም ዓይነት ፈተና ለዘመናት ተወጥተሃል። ያለጥርጥር አሁን የገጠመህንም ትወጠዋለህ። ቢሆንም ጠንቅቀህ ማወቅ ያለብህ የስነልቦና ሰለባ ሊያደርጉህ የሚፈልጉት “ነፍጠኛ፣ ጨቋኝ፣ ሠፋሪና መጤ” እያሉ የሚከሱህና የሚያንገላቱህ ብቻ አይደሉም። ከአብራክህ የወጡ አማሮችም ከሌሎች ያለበቂ ምክንያት ከሚጠሉህ ጋር እየተናበቡ እያስጠቁህ መሆኑን ላፍታም መዘንጋት የለብህም። በማንነትህ ግድያ የሚፈጽሙብህ ሕወሃትና ኦነግ ሸኔ ቢሆኑም ካንተው አብራክ የወጡም ልጆችህ ባልተናነሰ ሁኔታ ጉዳት እያደረሱብህ እንደሆነ ማመንም ቢያቅትህ አምነህ ልትቀበል ይገባል እንላለን። ትናንት እያንዳንዱን ካፋቸው ጠብ የሚለውን ቃል ታከብርላቸው የነበሩ ግለሰቦች ዛሬ ላንተ ሳይሆን መጨፍጨፍህን ለማያምን መሪ የካድሬነት ሥራ እየሠሩብህ ነው። ጠላቶችህ ከውስጥም ከውጭም ስለሆኑ ከእስከዛሬ በተለየ መንገድ ልትደራጅ ይገባል እንላለን። ከፊትለፊትህ ረዥም ጉዞ ይጠብቅሃል። በጊዜያዊ ድል ሳትሳከር በምታምናቸው መሪዎች ዙሪያ እየተሰባሰብክ ለራስህና ለሃገርህ ህልውና የጀመርከውን ተጋድሎ ከግቡ እንድታደርስ ጥሪያችንን እናቀርብልሃለን!!!
ጀግናው ወገናችን ሆይ! ስለኢትዮጵያ አንድነት አስፈላጊነትና ስለሕወሃት ምድራዊ ገሃነምነት ማንም ሊደሰኩርልህ አይገባም። ከሌሎች አገር ወዳድ ወገኖችህ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር ስትታገል ለህልውናህም ጭምር እየታገልክ መሆን እንዳለበት ላንተ አንነግርህም። የአገርህ ህልውና ከአንተ ህልውና ጋር የተያያዘ ስለሆነ ዛሬ ከምንም የበለጠ ለራስህ ህልውና ቅድሚያ መስጠት እንዳለብህ እንደተገነዘብክ የሚያጠራጥር አይደልም። ለራስህና ለሃገርህ ህልውና የሞት የሽረት ተጋድሎ እያደርግክ ባለህበት ሰዓት “በሃገር ጉዳይ ዳር መቆም የለም” የሚል ጥሪ የሚያቀርቡልህን ለመሆኑ ዳር የቆመውን ለይታችሁ አውቃችኋልን ብለህ ልትጠይቃቸው ይገባል እንላለን።
ጀግናው የአማራ ሕዝብ ሆይ! ባንተ ላይ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በተለይም በላፈው ሦስት ዓመት የደረሰውን ሥቃይና ግፍ “ጥቃቅን የፖለቲካ ልዩነት” ተብሎ መጠቀስ ነበረበትን? ስቆቃህ የራስህ ጥፋት በሚመስል መልክ መቅረብ ነበረበትን? የራስህን ግብዝነት (Ego) ወደጎን ጥለህ እኛን ምሰል መባል ነበረብህን? ዲያስፖራ የምትገኝ ወገናችን ሆይ! በገንዘብህም፣ በዲፕሎማሲም፣ በእምባህም መቼ ነው ለወገንህ ያልደረስከው? ስቆቃውን ስቆቃህ ያላደረግከው? “በሃገር ጉዳይ ዳር መቆም የለም” ከመባልህ በፊት እንደወትሮህ የተቻለህን እያደረግክ አልነበረምን? ነው ወይስ ለወገንህ የምትዘረጋለት ሁሉ በተወሰኑ አካሎች እጅ ብቻ መድረስ አለበት?
አገር ወዳድ ወገናችን ሆይ! ለዘመናት አባቶችህ እንዳደረጉት ለውድ ሃገርህ ምንጊዜም በጋራ መቆም አለብህ። የአማራና የአፋር ክልል በከፊል በወያኔ ወረራ አኬልዳማ ከመሆናቸው በፊት የድረሱልኝ ጥሪ አቅርበህ ነበር። ግን ሰሚ አላገኘህም። ስለሆነም በጥብቅ የምናሳስብህ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በተሰገሰጉ ሴረኞችና ሆድ አደር ካድሬዎች በተደጋጋሚ በስልታዊ ማፈግፈግ ስም የሆነኝ ተብሎ ለአደጋ ስለተጋለጥክ ራስህን ከኋላህም ከፊትህም እንድትጠብቅ ነው። የአንተ ህልውና ለአገርህ ህልውና ዋስትና ነውና!
“ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!”
“አንድነት ሃይል ነው!”
የኢትዮጵያ አገር አድን ግብረኃይል
የኢትዮጵያ አገር አድን ግብረኃይል በሰሜን አሜሪካ
——————————————————————————————————–
Email- [email protected]
Phone – 8477224193