ጠላትን በአጭር ጊዜ ለማጥፋት በቅንጅት እየተሰራ ነው፡- ብ/ጄ ተፈራ ማሞ

tefera mamo

ጠላትን በአጭር ጊዜ ለማጥፋት የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ማሞ ገለጹ፡፡  አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል ወረራ ከጀመረ አንስቶ በተደጋጋሚ በመምታት እንዲዳከም የማድረግ ሥራ መሠራቱን የአማራ ልዩ ኀይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ ገልጸዋል፡፡ ወደ ጋይንት አቅጣጫ ያቀናው የጠላት ስብስብ በተለያዩ አካባቢዎች በተከታታይ ተመትቷል፤ በየቦታው በደረሰበት ምትም ሊቀጥል በማይችልበት ደረጃ ተዳክሞ ወደፊት የመግፋት አቅሙ ተገድቧል ብለዋል፡፡

የጠላት ፍላጎት የአማራ ክልልን ሙሉ በሙሉ በመያዝ ኢትዮጵያን መቆጣጠር ቢሆንም የወገን ኀይል ከሕዝቡ ጋር በፈጠረው ቅንጅት የጠላትን አቅም ማዳከሙን የገለጹት ዋና አዛዡ የወገን ኀይል የጀመረውን የማጥቃት ርምጃ አጠናክሮ ወደፊት ይቀጥላል ነው ያሉት፡፡

ጠላትን በአጭር ጊዜ ለማጥፋትም የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ በቅንጅት እየሠሩ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችም ግንባር ድረስ በመሠማራት እየታገሉ መሆኑንም ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ተናግረዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ በከፈተው ጦርነት በደረሰበት ምት ተበታትኖ ወደ ጫካ መግባቱንም ጠቅሰዋል፡፡

የአሸባሪው ቡድን ዋንኛ ዓላማ የአማራን ሕዝብ መበቀል፣ ዘረፋ መፈጸም እና ጠላቴ ብሎ የፈረጀውን አማራን ማዳከምና ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑን ገልጸዋል።

ሕዝቡ ከጀርባ ተሰልፎ ጠላትን በመምታት፣ ለሠራዊቱ በቋሚነት ምግብ በማቅረብና አጋርነቱን በማሳዬት ለወገን ኀይል ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

ወራሪው ቡድን የሕዝቡን በሬ፣ ፍየል እና በግ እያረደ ሲበላ፣ ጎተራ ዘቅዝቆ እህል ሲጭንና ሁሉን አቀፍ በደል ሲፈጽም በተግባር መታየቱንም አንስተዋል ብርጋዴር ጀነራሉ፡፡ ይህ ቡድን እያለ ሀገር በሰላም እንደማይቀጥል ያነሱት ዋና አዛዡ ዳግም እንዳይነሳ ተደርጎ መመታት እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ድምፅ የሚሰማባቸው ሰፈሮች ወቅታዊ ገፅታ

ጦርነቱ ሕዝባዊ ነው፤ አሸባሪው ቡድን ሕዝብ አሰልፎ እንደመጣ ሁሉ እንደ ሕዝብ እንታገለዋለን ነው ያሉት፡፡ ቡድኑ ከገባበት አካባቢ እንዳይወጣ ሕዝቡ በሁሉም መንገድ መሰናክል መፍጠር አለበት ብለዋል፡፡

አሸባሪውን ቡድን ለማጥፋት በሚደረገው ዘመቻ የሕዝቡ ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረውም ጠይቀዋል፡፡ ቡድኑ የዘረፈውን ይዞ ለመውጣት የሚያደርገውን ጥረት ለማክሸፍም ሕዝቡ ከወገን ኀይል ጋር በመሆን ሚናውን መወጣት አለበት ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ አካባቢውን በንቃት መጠበቅ እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

አሸባሪው ትህነግ በሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሕዝቡን ለማሸበር ጥረት ቢያደርግም ቡድኑ ወራሪና ሌባ መሆኑን ሕዝቡ ጠንቅቆ ያውቃል ነው ያሉት፡፡ በሚያሰራጫቸው የሐሰት መረጃዎች ሕዝቡ እንዳይሸበርም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ጠላት የሆነው አሸባሪ ቡድን ለመቅበር በጀመሩት አግባብ በጋራ ሊታገሉ እንደሚገባም ብርጋዴር ጀነራል ተፈራ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ባሕር ዳር፡ ነሐሴ 13/2013 ዓ.ም (አሚኮ)

1 Comment

  1. Top Urgent!!!

    ክብር ለጀግኖቻችን እና መስውዓት ለምትሆኑት፡፡ ሁሉንም በድል እስከምታጠናቀቁ እና የትህነግ ግባተ-መቃብሩ እስከሚፈፀም ግን ሳትዘናጉ ፍፀሚያቸውን ማፋጠን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እና ሰራዊቱ ታሪክ ዳግም እየሰራ ነው፡፡ ቢዘህ የትህነግ ፍፃሜ ሰዓት አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሰታት እና አጋሮቻቸው ዓላማቸው ስላልተሳከ የመጨረሻ ተፅዕኖ በአገራችን ላይ በመፍጠር አጋራቸውን ትህነግ ለማዳን እየተሯሯጡ ስለሆነ መንግስት አቋሙን ፍንክች ማድረግ የለበትም፡፡ ይህ ጉዳይ የመንግስት ጉዳይ ሳይሆን የህዝብ ጉዳይ ከሆነ ስለቆየ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በህልውናው ጉዳይ በታሪክ ተደራድሮ አያውቅምና ጠላቶች ከዚህ የህዝብ ማእበል ትምህርት ሊወስዱ ይገባል፡፡ መንግስት በዚህ መጨረሻ ሰዓት ከባድ መሳሪያ በመተኮስ እየተፍጨረጨረ ያለ ባንዳን በጀትና ድሮን ድምጥፋጡን ማጥፋት አቅቶት ነው??? ወታደራዊ ጦርነት ላይ ለጠላት አንድ ደቂቃም ቢሆን ጊዜ መስጠት መዘዙ የከፋ ስለሆነ አረ ፍጥነት ፍጥነት ያስፈልጋል፡፡ ደጋፊዎቻቸውም የሚያፍሩበት ጊዜ እየቀረበ ነው ለሊቱም ለብርሃን የሚስያስተላልፍበት ጊዜ እየቀረበ ነው፡፡

    ድል ለጀግኖቻን!!
    ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share