“ለወራት የዘለቀው ጦርነት በታላቂቱ አገር በውጊያ የማይሽር ብርቱ መከራ እና መከፋፈል አምጥቷል” ሲሉ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሱሊቫን የልዩ መልዕክተኛውን ጉብኝት ይፋ ባደረጉበት የትዊተር መልዕክታቸው ጽፈዋል። ጄክ ሱሊቫን “ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ ወደ ድርድር እንዲመጡ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።
41650861 303
የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ ድጋሚ ሊጓዙ ነው። የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ወሳኝ ባሉት በዚህ ወቅት ጄፍሪ ፌልትማን በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ እንዲጓዙ መጠየቃቸውን የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪያቸው ጄክ ሱሊቫን ትናንት ሐሙስ ዐስታውቀዋል።
ልዩ መልዕክተኛው ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙት ዘጠኝ ወራት የዘለቀው የትግራይ ውጊያ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተሻግሮ አሳሳቢ በሆነበት ወቅት ነው።
“ለወራት የዘለቀው ጦርነት በታላቂቱ አገር በውጊያ የማይሽር ብርቱ መከራ እና መከፋፈል አምጥቷል” ሲሉ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን የብሔራዊ ጸጥታ አማካሪ ጄክ ሱሊቫን የልዩ መልዕክተኛውን ጉብኝት ይፋ ባደረጉበት የትዊተር መልዕክታቸው ጽፈዋል። ጄክ ሱሊቫን “ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ ወደ ድርድር እንዲመጡ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።
ጄፍሪ ፌልትማን ባለፈው ሚያዝያ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ከተሾሙ በኋላ በግንቦት መጀመሪያ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ተወያይተው ነበር።
ከሚያዝያ 26 እስከ ግንቦት 5 ቀን፣ 2013 ዓ.ም. በምሥራቅ አፍሪካ ባደረጉት የመጀመሪያ ጉዟቸው ግብጽ፣ ኤርትራ እና ሱዳንን ጎብኝተው ከአገራቱ መሪዎች ጋር ተነጋግረዋል።
በሁለተኛው ዙር ጉብኝታቸው ወደ ኳታር፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ኬንያ አቅንተዋል። ከግንቦት 23 እስከ 29 የዘለቀው ሁለተኛ ዙር የፌልትማን ጉብኝት “የተረጋጋ እና የበለጸገ የአፍሪካ ቀንድ በትብብር መደገፍ በሚቻልበት መንገድ ላይ ለመወያየት” የታቀደ የሚል ነበር። በዚህ ጉብኝት ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የሚወዛገቡበት የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ጉዳይ ሌላው አጀንዳ ነበር።
ልዩ መልዕክተኛው ከነሐሴ 9 እስከ 18 ቀን፣ 2013 ዓ.ም. ባሉት ቀናት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ጅቡቲ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እንደሚጓዙ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ዐስታውቋል።
DW