“በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታውን ለማሳለጥ ከመንግሥት ጋር እንሰራለን”፦ ተመድ

በትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታውን ለማሳለጥ ከመንግሥት ጋር በቅርበት እንደሚሰሩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸኃፊ ሥር የሰብዓዊ ጉዳዮችና የድንገተኛ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊት ገለጹ።
አስተባባሪው በኢትዮጵያ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
አስተባባሪው በተለይም ላለፉት ሁለት ቀናት በትግራይ እየተካሄደ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ በተመለከተ በክልሉ በአካል ተገኝተው የድጋፍ አሰጣጥ ሂደቱን መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ መንግሥት የሰብዓዊ እርዳታ ወደ ክልሉ በፍጥነት እንዲደርስ እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቅርቡም እህል የጫኑ 120 ከባድ ተሽከርካሪዎችን ለአብነት አንስተዋል።
በቀጣይም ይህንን ፈጣን የድጋፍ አሰጣጥ ሥርዓት አጠናክሮ ለመቀጠል ተመድ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ይበልጥ ተቀራርቦ ለመሥራት ቁርጠኛ መሆኑን አስተባባሪው በመግለጫቸው ጠቁመዋል።
በቆይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር በክልሉ የሰብዓዊ እርዳታው በሚፋጠንበት ሁኔታ ላይ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ጎን ለጎንም የአፍሪካ ኅብረት የማኅበራዊ ጉዳዮች ኮሚሽነር፣ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶችና ዓለም አቀፍ የረድኤት ተቋማት ተወካዮችንም በጉዳዩ ዙሪያ ማነጋገራቸውን ጠቁመዋል።
መንግሥት ላለፉት ስምንት ወራት በትግራይ ክልል ለሚገኙ ከ4.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ለሰብዓዊ እርዳታ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጿል።
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በማሳለፍ ሰራዊቱን ከትግራይ ሲያስወጣ ሰብአዊ ድጋፉ እንዳይቋረጥ በማሰብ 400 ሺህ ኩንታል የምግብ እህልና አልሚ ምግቦችን በመቀሌ መጋዘን ትቶ መምጣቱ ይታወሳል።
በዚሁ መጋዘን 2.5 ሚሊዮን ሊትር ዘይትና ሌሎች አልሚ ምግቦች መኖራቸውም ተገልጿል።
በክልሉ መንግሥት ከሚያቀርበው የሰብዓዊ እርዳታ በተጨማሪ የተለያዩ የረድኤት ተቋማት ያከማቹት የምግብ አቅርቦት እንዳለ ተገልጿል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.