ይድረስ ለኢትዮጵያ መንግስትና አገር ወዳድ ወገኖቼ – የመጨረሻው ደወል – ከ አባዊርቱ

abiy
abiy

መንደርደርያ!

በመጀመርያ ጊዜ ደጉ ብዙ አሳየንና በህይወት እያለሁ፣ ያ በወያኔ አሻጥር በለጋ እድሜው ገና ከመሬት ከፍ ሳይል አገሩንና ወገኑን በጥርጣሬ እንዲያይ ተቀነባብሮበት የነበረው ቄሮ የአያቶቹንና የቅድመ አያቶቹን ሰንደቅ ሰንቆና አይኑ እምባ አቅሮ ለኢትዮጵያችን ሊዘምት ከአባገዳዎች ቃለ ቡራኬ ሲቀበል ያሳየኝ ፈጣሪ ክብር ምስጋና ይግባው። የዖሮሞ ልጅ እንዲህ እንደዋዛ እንዳልነበር ልቦናዬ ቢያውቀውም፣ ለነዚህ የፅልመት ውላጆች “ምስጋና” ይግባቸውና ልጆቻችንን ወደ አንድ ማእድ እያመጡልን ነው። መቼ ይህ ብቻ፣ የሲዳማው ነሽ፣ የሀድያው፣ የሱማሌው ነሽ የአርጎባው፣ የአማራው ነሽ የጋምቤላው ማንንስ ጠርቼ ማንንስ እተዋለሁ። እንደው በደፈናው የኢትዮጵያ አምላክ ይክበር ይመስገን ከማለት ውጭ። ይህን ካልኩ በሁዋላ በትግራይ የሚቀጠፉትን ጨቅላ ህፃናትን ሳስብ ደግሞ ሀዘኔ መራር ነው። የትግራይ ወላጆች ፈጣሪ ከናንተ ጋር ይሁን። በልጅነት አይቼዋልሁ የትግራይን ህዝብ ባለማተብነት። ምነው ፈጣሪ እነዚህን አጋንንት ጣለባችሁ ይሆን። ጦርነቱን አናቆመው ነገር እነዚህ ተምቾች አይተኙልንም። በግልፅ ከውጭ ጠላቶች እየተመሳጠሩ አገራችንን ጭራሽ ወደ ገደል ሊከቱብን ሌት ተቀን የሚተጉ ነቀርሳዎች ናቸው። ያለው አማራጭ ወላጅ የሆንክ ሁሉ ህይወትህ እዛው ከልጅህ ጋር ይለፍ እንጅ ልጅህን አትስጥ። ወዲህም ወዲያም ያው ሞት ነውና። ይህው ነው።
ይድረስ ለዶር አቢይ መንግስት!
መቼስ ያለባችሁን አበሳ ሳስበው እንቅልፍ ይነሳኛል። ይቺ ሳማንታ ሴትዮ ለምን እንደምትመጣ ይረዳኛል። ፃድቃን የተመኛትን የሱዳን ኮሪዶር ለማስከፈት የጫና መፍጠርያ ተልእኮ መሆኗን አባመላው አቢይ አይጠፋህም መቼስ። ለዚህም በደንብ መዘጋጀት ነው። እንዴት? እስቲ የመሰለኝን እንደ አንድ  ስለ አገሩ እንቅልፍ እንዳጣ ዜጋ ልሞነጫጭር።
፩) ወይ ፍንክች ፣ የፈለጋቸውን ጫና ያምጡ እንጅ ለነፃድቃን ይህን በር መክፈት ማለት አንደኛውን ነጭ ባንዲራ አውለብልበን ለወያኔ እንደ ማደር ይሆናል። የ አሜሪካንን ጫና ለመቋቋም ከ ቻይናና ሩስያ ከሌሎችም ያለንን ትስስር ከፍ ማድረግ ነው። የአስቸካይ ስብሰባም ግድ ይላል
፪) ከኤርትራ ተመካክረን ለ ራሺያና ቻይና የጥምረት ቤዝ አሰብና ምፅዋ ላይ ማቀድ ። ገፍተው ከመጡ ለምን ሰቲቱመራ አይሆንም ቤዛቸው። ይህው ነው። ለጥጋበኛ አስተንፋሽ አለና አይዞን። ኤርትራውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጥቃታችንን እንደማይቀበሉ በደማቸው አሳይተውናልና እተማመናለሁ።
፫) ኢትዮጵያዊው ወገን ከፍተኛ አገራዊ ተሃድሶ ስሜት  ላይ ነው ያለው። ስሜቱ እጅግ ከፍ ብላል። ይህም ይቀጥላል። የዛሬ ፪-፫ አመት ህዝባዊ ሚሊሻ በየክልሉ ይዋቀር እልም የነበረው እንዲህ አይነት ሁኔታ ይከሰት ይሆናል ከሚልም ነበር። ፈጣሪ በራሱ ጊዜ የነዚህን የሳጥናኤል ውላጆች ልብ አይቶ እነሆ የወዶ ዘማቹ ቁጥር ከገመትኩት በላይ ሆነ። ታድያ የኢትዮጵያ አምላክ የምንለው የዋዛ እንዳልሆነ በአይናችን እያየነው ነው። ይህ በይበልጥ እንዲቀጣጠል ማበረታታት።
፬) ያለንበት የጦርነት ጊዜ ላይ ስለሆነ ብሪፊንግ ወሳኝ ነው ከሲቪሉም ከሚሊተሪውም ክፍል ። የነ ግስላው ባጫ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሲቭል ቃል አቀባዮችም በጥሩ ቋንቋ ተርትሮ የሚገልፅ/የምትገልፅ ቃል አቀባይ ያስፈልጉናል። ለዚህ በ international relations የተካኑ የዳያስፖራ ልጆች አይጠፉምና ቢታሰብበት? ይህ/ይህች ግለሰብ ከዶር አቢይና ቢለኔ ስዩም ጋር አንድ ሳምንት ያህል ሻዶው ቢያደርግ/ብታደርግ የመንግስትን አቅጣጫና ፍላጎት ለመረዳት አይቸግርም። ከዛም በየቀኑ አብረውም ስለሚሰሩ ተንትኖ ምድረ ምቀኛ በፍራንክ የተገዛን የ ማርቲንን አይነት ድኩም አፍ ማዘጋት አይቸግርም። ኸረ ብዙ አሉን የናት አገር ልጆች። ዳያስፖራ ወላጆችም ዝም አትበሉ። ልጆቻችሁን የምታውቁ እናንተው ናችሁና ጠቁሙ። አገራችን ከምንጊዜም በላይ እርዳታችንን ትፈልጋለች – በሁሉም መስክ።
ይድረስ  ለአገር ወዳድ ዳያስፖራ ምሁራን ወንድሞቼና እህቶቼ!
መቼስ ለአገራችን ያላችሁ ስሜት በቅርበት ለተከታተለ ያስደምማል። ወቅቱ ከምንጊዜውም በላይ አንድነታችንን ይፈልጋል ። ከመንግስት ጋር ያለንን ሂሳብ ፣ ቢኖር እንኳ ለማወራረድ አልደላንም። ወጥሩና አንድነታችንን ከአፅናፍ እስከ አፅናፍ እናስተጋባ። በዚህ ዘመን ለኢትዮጵያ ያልሞገተ በእውነት የተረገመ ቢሆን ነው። ወያኔ ሰላሳ አመት ቀልዳብን፣ ልጆቻችንን አኮላሽታ ዛሬም ከመቃብር ተነስታ ጭራሽ የሱዳን የጓዳ በር ይከፈትልኝ ስትል የማይቆጭ ኢትዮጵያዊ አብሯት ሲበላና ሲያባላ የኖረ ድኩም ብቻ መሆን አለበት። ምን እናድርግ?
፩) ለመከላከያው ብቻ ሳይሆን አንጀቱን እስሮ ለሚዋደቀውም የሚሊሻ ገበሬና ከየአቅጣጫው ወደ ሰሜን እየተመመ ያለውን ወጣት አርበኛ በማቴርያልም፣ ሞራልም ድጋፉን ማጠናከር። በየ ዳያስፖራው ከተሞች የእራት ምሽት እያዘጋጀን ገንዘብ መሰብሰብ። በውጭ የምትኖሩ አርቲስት እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በዚህ ጉዳይ ምክር ማድረግ። ይህ የአንድ ወር ወይም ሳምንት ጉዳይ ሳይሆን ፣ ዘላቂ ወይም ጦርነቱ እስኪያከትም መሆን አለበት።
፪) ምሁራኖቻችን አይምሯችሁን ሰብሰብ አድርጉ በኢትዮጵያ አምላክ። እንደው ለመቃወም ተብሎ መለቅለቅ ያስገምት ካልሆነ በቀር በየጥሻውና በረሃው ለሚዋደቀው ወገናችን ወይም በለጋ እድሜአቸው ልጆቻቸው ለተቀነጠሱባቸው የትግራይ እናቶች የሚፈይደው አይኖርም ። ኢትዮጵያዊ ጠረን የምትሸቱትን ምሁራን ማለቴ ይሰመርበት። ባንዳማ ባንዳ ነው
፫) በትዊተርና በመሳሰሉት እስከ ክጆቻችንና ልጅ ልጆቻችን ወጥረን የአሜሪካንና አውሮፓን ፖሊሲ ሜከርስ ፋታ ማሳጣት። ካስፈለገም ከዳያስፖራው ፈንድ በትንሿም ብትሆን ቀንጭበን በሎቢ መወጣጠር። አንዱ ወንድሜ ይህ የአሜሪካ ሎቢ ጉዳይ ከዬት ያመጣኸው ሳይንስ ፣ ያልተፃፈ ትደግማለህ ይሉኛል። እንደው ትንሽ ፊደል የቆጠረ አሜሪካ ከ 70’ዎቺ ጀምራ ሎቢ ማድረግ በህግ መንግስት የተፈቀደና ዋናው የጉዳይ ማስፈፀሚያ ለመሆኑ መቼስ ሚስጥር አይሆንም። የምን ቲዎሪና ሳይንስ እንደሚያወሩ እሳቸው ያውቁታል። ለማንኛውም ወያኔን የሚያክል ቋጥኝ ጀርባችን አዝለን በማይረባ እንካስላንትያ ጊዜን ማባከን በየቀኑ በሚሰውት ወገኖቻችን – በሁለቱም ወገን – ላይ እንደመሳለቅ ይሆናልና እየተሰተዋለ ለማለት ያህል ነው። ዘመቻው ይቀጥላልና እንበርታ ወገን።
፬) የዚች ሳማንታ ፓወርስ ወደ ኢትዮጵያን ጉዞ አስመልክቶ  ምን ይዛልን እንደመጣች ባይታወቅም መጠርጠር የበጎ ነው። እነ ፃድቃንን የመተንፈሻ ሳንባ በምእራብ ሱዳን በኩል ልታዘን ከሆነ ካሁኑ ምሁራን የተባለ ሁሉ ማንኛውንም የመገናኛ ዘዴህን ቀርፀህ አድፍጠህ ጠብቅ። ወገኖች ኢትዮጵያን እንደ ጨርቅ ኳስ ነው እያዩዋት ያሉት – ለላስቲኩ እንኳ ወጉ አልደረሰንምና በንቃት እንጠብቅ። መንግስትም የሚከናወነውን ሁሉ ህዝባችንን ብሪፍ ማድረግ የግድ ነው። እስካሁንም ብዙ ጉድለቶች ይታዩኛል። በጦርነት እንዲህ ተወጣጥረን፣ ህዝባችን ምን ይፈጠር ይሆን እያለ በጭንቀት እየተናጠ ከሚሊተሪ ብሪፊንግ ተጨማሪ ቢያንስ በእንግሊዘኛ አጠር ያለች ሳምንታዊ ብሪፊንግ ያስፈልግ ነበር። በአገርኛውም ቢሆን ትክክል ወቅታዊ መረጃ ከመንግስት ቢኖር ብዙ ሰው በሱቅበደረቴ የዩቱብ ጡረተኛ አይወናበድም ነበር (የጁንታ ትክለኞቹን ማለቴ ነው) ሆኖም ያለውን ችግር ከሩቁ እገምታለሁ። ስንት በአይን የማይታይ፣ በእጅ የማይዳሰስ ውስጣዊ ጦርነትና ሳቦታጅ ከጁንታው ርዝራዥ እያለ እዬዬ ሲደላ አይነት እንደሆነበት ለመንግስት እጠረጥራለሁ።
በመጨረሻም!
ይህ ጦርነት በአንዲት ጀምበር ቢጠፋ ደስታውን አልችለውም ነበር። ሆኖም እነዚህ ከይሲዎች ህፃናትን ማግደው ሊያንበረክኩን ስለከጀሉ ድራሻቸውን ማጥፋቱ ለራስ ህልውና ነው። እስቲ ተመልከቱ፣ ገና ሳማንታ እግሯ አዲሳባ ሳይረግጥ የፃድቃን ፉከራ ምንን ያሳያችሁዋል ወገኖች? የታቀደልን ጉዳይ ስላለ እናት አገራችንን ለመታደግ በማንኛውም መንገድ ለመሰለፍ መዘጋጀት ብልህነት ነው። አንድ በጣም ወሳኝ የምለው ባለፈው ምርጫ የተሳተፋችሁ የተቃዋሚ ድርጅቶች በሙሉ በዶር ብርሃኑ ወይም ሌላ ሰው ሰብሳቢነት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርታችሁ ቢቻል ሴትዮዋን በአካል ማግኘት፣ ካልሆነም በፔቲሺን መልክ አሜሪካ ረጃጅም እጆቿን ከኢትዮጵያችን ላይ እንድታነሳ በአፅንኦት ማሳሰብ ወቅቱ የሚጠይቀው ሆኖ ይሰማኛል። አይናችን እያየ እንዴት ዝም ይባላል? አሜሪካ ይሁን አውሮፓ ለቅልውጥ ወዲያ ወዲህ የሚሉትን ልጥፍ ፌዴራሌ ተብዬዎችንም እርቃናቸውን የሚቀሩት እንዲህ ለኢትዮጵያ አንድ ላይ ታጥቀን ስንነሳ ብቻ ነው። ፈጣሪ ይርዳን ። አሜን!!!
ተጨማሪ ያንብቡ:  ይድረስ ለሁላችን! - ---ፊልጶስ

2 Comments

  1. አባ ዊርቱ አገር አማን ነው? ጽሁፉ መልካም ነው አሜሪካ እንዲህ ያለ ቀጭን ትእዛዝ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ኢትዮጵያ የአሜሪካ 51ኛው ግዛት ሁና ነው ወይንስ መንግስቱ ደካማ ነው ብላ ነው? መግለጫን በተመለከተ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በሰለጠነ መልኩ ያቀርባሉ አድናቆቴ ታላቅ ነው ለሳቸው።

    ዲና ሙፍቲ ወያኔ ከሚያደርስባቸው ጫና በላይ እነ ሌንጮዎችና ሱሌማን ደደፎ የሚያበላሹትን ማስተካከልም ከባድ የስራ ጫና አድርሰውባቸዋል።

    ብርሀኑ ላሉት ህዝብ ሊያገለግለኝ ብቃት የለውም ብሎ የተወውን ስልጣን መስጠትዎ በዲሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብ ያለ ማመን ወይም ደግሞ እኔ አውቅልሀለሁ እንዳይሆን እፈራለሁ። በተረፈ ወያኔን ኮንነው ዶር አብይን በወያኔ ኢሉሚናቲ ባንዲራ ማውጣት ሊታሰብበት ይገባል በዛ ባንድራ ስር ብዙ ኮተቶች አሉ።
    ሰላም ላገራችን መቼም ይህ ህገ አራዊት እስካለ ድረስ ሰላም አይመጣም።

  2. የወያኔ ፅረ ህዝብነት፣ ዘረኝነት ፣ ሀገር በታይነት፣ ባንዳነት፣ሌሎችም የክፋት ክምሮች አስኩዋል የሚገኘው በህገ መንግስቱ ነው ።ሌላው ቀርቶ ምእራባዊያን ወያኔን ከሞት ለማስነሳት ህገ መንግስቱን እየጠቀሱ ሲሙዋገቱን ይስተዋላል። ታዲያ ለዚህ ህገ መንግስት የአንድ ቀን አዳር እንዴት እንፈቅድለታለን? የወያኔን ዱካ ለመከተል ላሰፈሰፉ ዘረኞች ወይስ ለምእራቢያውያን ፍጆታ ???
    ለኢትዬጽያ እናቴ እሰዋለሁ ብለህ በግንባር ደምህን የምታፈስ፤ አጥንትህን የምትከሰክስ ሁሉ ፡ -የሚገዛህ ህገ መንግስት ኢትዬጽያን ብትንትኑዋን ለማውጣት በውጭ ጠላቶቻችን የተቀየሰእና በውስጥ ባንዳዎች አስፈፃሚነት በተግባር የዋለ መሆኑን ከምንግዚየውም በላይ አሀን በምታየው እና በምትሰማው ሊገለጥልህ ይገባል። የጊዜው አጀንዳ ህገ መንግስቱ መሆን የግድ ነው።
    ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይባርክ !

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share