ባርነት ያረከሰውን አርነት አይቀድሰውም (ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ)

44

መግቢያ

አብዝቶ ለጀሮ የሚሻክረው ሰሞነኛው የታምራት ላይኔ የነተበ ንግግር ራሱ ‘ተአምር’ የሚያሰኝ ሆኗል፡፡ እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር ጁላይ 28 ቀን 2021 ለአባይ ሚዲያዋ ጋዜጠኛ፣ መኣዛ መሀመድ ትመስለኛለች፣ በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ሰጥቶታል ተብሎ ዩቲዩብ ላይ የተለቀቀውን አስደማሚ ቃለ-ምልልስ በአንክሮ ተከታተልኩት፡፡

አረጋዊው ጠቅላይ ሚኒስትር በዚያ ቃለ-ምልልሱ “የትግራይ ህዝብ ነጻነት ግንባር (“ት.ህ.ነ.ግ) ቀድሞውንም ቢሆን በአሸባሪነት መፈረጅ አልነበረበትም”” ሲል አስደምጦን አረፈው አይደል?

“እናያፍሬ መጡ፣ ማሕበሩን ሊጠጡ”፣ አለች አያቴ፡፡

አንድ ጊዜ ለባርነት ካደርክ እኮ መዳኛ የለህም ጎበዝ!!!

በጠንካራ ፕሬዚደንት ስር ድኩም ጠቅላይ ሚኒስትር

tamiratእኔ በበኩሌ እንደብዙዎች ሁሉ ታምራት ላይኔን ለወጉ ያህል እንኳ ‘ጠቅላይ ሚኒስትር’ ብሎ ለማስታወስና በተከበረ መአረጉ ለመጥራት በጣም ይቸግረኛል፡፡

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ የመለስ ዜናዊ ታማኝ ባለሟል እንጂ እውነተኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር ለማለት አያስደፍርም፡:፡ ለአንባገነኑ የሽግግር ወቅት ፕሬዚደንት ከመላላክና ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቦችን አዘጋጅቶ ለፊርማ ከማቅረብ የዘለለ ሥልጣን ያለው ሰው አልነበረም፡፡ ይህንን ሀቅ ካላበደ በስተቀር ራሱም ቢሆን ፈጽሞ አይክደውም፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ከርሱ ይልቅ በፕሬዚደንት መንግሥቱ ሀይለ-ማርያም ስር ያገለግል የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ-ስላሴ ወግ-ደረስ የተሻለ መብት ነበረው ብዬ አምናለሁ፡፡

ለነገሩ ህዝብ በቀጥታ የመረጠው ወይም በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የተሰየመ ካልሆነ በስተቀር አንድ ርእሰ-መንግሥት ለራሱ አላማ የሾመው የትኛውም ጠቅላይ ሚኒስትር ተብዬ ግለሰብ ቢበዛ የፕሬዚደንቱ ጽህፈት ቤት ኀላፊ ሆኖ ከማገልገል የበለጠና ትርጉም ያለው ሥልጣን እንደምን ሊኖረው ይችላል?

ለዚህ እኮ ነው ብልጣብልጡ መለስ ዜናዊ የሀገሪቱን ሕገ-መንግሥት ባወጣ ማግስት ከብዙዎቹ የአፍሪካ አንባገነኖች በተለየ ሁኔታ የፕሬዚደንትነቱን የስራ ድርሻ ሲበዛ አኮስምኖ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን በጁ ያደረገው፡፡

ያም ሆኖ ዶ/ር አቢይ አህመድ መንበረ-ሥልጣኑን በጨበጡ ማግስት ‘ቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎች’ ነበሩ ያሏቸውን ጡረተኞች በታላቅ ክብር ጠርተው በቤተ-መንግሥት ባስተናገዱበት ወቅት ውለታቢሱን ታምራት ላይኔን ጭምር አልዘነጉትም ነበር፡፡

“ታሞ የተነሳ እግዜርን ረሳ” እንዲሉ ይህ ተጋባዥ እንግዳቸው ነው እንግዲህ ዛሬ ላይ በቴሌቪዥን ብቅ ብሎና አይኑን በጨው አጥቦ በለውጡ ጉሮሮ ላይ አጥንት ሊሰኩ በህቡእም ሆነ በአደባባይ ከሚውተረተሩት ግንባር-ቀደም አሸባሪዎች ጋር ለማሴር አብሮ ሲንከላወስ በትዝብት የምናስተውለው፡፡

“ያዲያቆነ ሰይታን ሳያቀስስ አይለቅም” አሉ እማ ፈንታ፡፡

“ስንት ማንኪያ ‘ታምራት’ ላርግልህ?

የዛሬውን አያድርገውና ታምራት ላይኔ በትግል ጓዶቹ የከረረ ግምገማ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ዙፋኑ ወርዶ የተንኮታኮተ ሰሞን በሥልጣን ብልግና ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ይመላለስ በነበረበት ወቅት ‘ስኳር’ የሚል ተለዋጭ የተጸውኦ ስም ወጥቶለት ነበር፡፡

እንዲያውም ከዚሁ ስያሜ ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ኢትዮጵያ ሆቴል በረንዳ ላይ ተሰባስበን ቡና ስንጠጣ ሾካካነት አብዝቶ የሚያጠቃው አንድ መናጢ ጓደኛችን በተሟሟቀው ጨዋታ መሃል ገብቶ የተቀዳልኝን ቡና ስኒ ወደፊቴ እያስጠጋ “ጋሽ መርሓ፣ “ስንት ማንኪያ ‘ታምራት ላርግልህ””? እንዳለኝ አስታውሳለሁ፡፡

ሹፈቱ በቶሎ ያልገባኝና ከወደገጠሪቱ ኢትዮጵያ የመጣሁት እርጥብ ባላገር ታዲያ በሁኔታው ግራ እንደተጋባሁ የተመለከቱት ሌሎች ሳቢሳ ጓደኞቻችን ወዲያውኑ ቀበል አድርገው “ስንት ማንኪያ ስኳር ያስፈልግሃል”? ማለቱ እኮ ነው “አልገባህም እንዴ”? ያሉኝ ጊዜ አካባቢውን በማያቋርጥ ሳቅና ሁካታ እንደቀወጥነው ብዙዎቻችን ዛሬም ድረስ አንዘነጋውም፡፡

ለካስ በያኔው የመዲናችን የአነጋገር ዘዬ ‘ታምራት’ ማለት ‘ስኳር’ ማለት ኖሯል፡፡

ይታወስ እንደሆን ነውር የማያውቀው የወያኔ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ነበር የታምራትን መጠሪያ ስም ሳይቀር ወደሥኳርነት የቀየረው፡፡

ታምራት ላይኔ ለአስከፊው የወያኔ አገዛዝ አድሮ ለስርአቱ ቀጣይነት የግል ሰብእናውን ሳይቀር በመስዋእትነት ከማቅረብ ያልተመለሰ መሸ በከንቱ ፍጡር ይመስለኛል፡፡

ያኔ ገና በወጣትነቱ እንኳ በቀልኩበት ለሚለው ገናና ማሕበረ-ሰብ ይቅርና ለራሱና ለቤተ-ሰቡ ቅንጣት ታህል ክብር መስጠት የተሳነው ይህ የድሮ ጠቅላይ ሚኒስትር እነአቶ መለስ ከብላቴናነቱ አንስቶ ከጫኑበት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተምህሮ አፈንግጧል በማለት ወንጅለዉት ሳለ እርሱ እንደሚለው የቆመለትን ህዝባዊ አላማ ዘንግቶ በከፋ ንቅዘት መበላሸቱንና የኪራይ ሰብሳቢነት ሰለባ መሆኑን በይፋ አምኖ በአደባባይ ሲናዘዝና ለተመለከተው ሁሉ የመጨረሻ መሳለቂያ ሲሆን በጊዜው ሁላችንም አዝነንለት፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ አፍረንበት ነበር፡

ታዲያ ጨዋታን ጨዋታ ያመጣዋል እንዲሉ ያችን የታምራትን የ’ተበላሽቼ ነበር’ አዋራጅ ኑዛዜ በወቅቱ የሀገሪቱ ፕሬዚደንት የነበሩት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በአንድ ቀዝቃዛ ምሽት ከመኖሪያ ቤታቸው ሆነው በቀጥታ ቴሌቪዥን የመከታተል አጋጣሚ ነበራቸው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ በአይናቸው በብረቱ የሚያዩትን ለማመን እስኪቸግራቸው ድረስ ራሳቸውን እየነቀነቁ፣ “ወቸው ጉድ፣ ምን አይነት ዘመን ላ ደረስን እናንተዬ”?… እያሉ አብዝተው ሲደነቁና ሲደመሙ በድንገት ከወደጓዳ ብቅ ብለው የተመለከቷቸው የውጭ ዜጋ ባለቤታቸው፣ “አዎይ አለመታደልህ፣ ይህንንም አልነገሩህ እንዴ”? ሲሉ እንደተዘባበቱባቸው በጊዜው ስለመቀለዱ አንድ ሌላ ከይሲ ወዳጄ የሰማውን አጫውቶኛል፡፡

ለመሆኑ የት.ህ.ነ.ግ በሽብርተኝነት መፈረጅ ታምራት ላይኔን ለምን ያን ያህል አበሳጨው?

ሰውየው በርግጥ ለዚህ ቁጭቱ መንታ ምክንያቶችን ሲሰጥ አድምጠነው ይሆናል፡፡

እንደቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አስተያየት ከሆነ ት.ህ.ነ.ግ በአሸባሪነት ለመፈረጅ የበቃበት አንደኛው ምክንያት አስቀድሞ ለ27 ዓመታት ያህል የመንግሥቱን ሥልጣን ጨብጦ የቆየበትን እድልና አጋጣሚ እየተጠቀመ በዜጎች ላይ ሲፈጽመው ከኖረው አረመኔያዊ ግፍና ሰቆቃ የተነሳ በብዙኃኑ ዘንድ አስቀድሞ የተጠላ በመሆኑ ያንኑ ለማጠናከርና እዚያው ላይ “ምስማር ለመምታት” በማሰብ ነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በሕግ ማስከበር ስም የሚካሄደው ደም አፋሳሽ ግጭት በሠላማዊ ውይይትና ድርድር እልባት ሊያገኝ ይገባዋል ሲል አለም-አቀፉ ሕብረተ-ሰብ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ መንግሥት ላይ በጊዜው ሲያሰማ የነበረውን ጩኸትና ይኸው እያሳደረ የመጣውን ጫና ለመቋቋም ያመች ዘንድ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር አልደራደርም የማለት ሰበብ ለማግኘት ነው ሲል የውክልና መላምቱን አስተጋብቶልናል፡፡

መኣዛ ከዚህ አልፋ ጥያቄዎቿን ትንሽ ዘለግ በማድረግ “ለመሆኑ መጀመሪያ በትግራይ ክልል ለተፈጠረውና አሁን አሁን ወደሌሎች አጎራባች ክልሎች እየተዛመተ ለመጣው አደገኛ ቀውስ መነሻ ተደርጎ የሚወሰደውንና ከስምንት ወራት በፊት በሰሜን እዝ ላይ የሰነዘረውን ወታደራዊ ጥቃት እንዴት ይመለከቱታል”? ስትል ታምራት ላይኔን ጠይቃው ነበር፡፡

ጉደኛው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን በተለመደው ተንበርካኪነቱ ይበልጥ ሲገፋበት ተደምጧል፡፡

ታምራት “በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ ላይ ተሰንዝሯል የተባለው ጥቃት በርግጥ ወንጀል አይደለም ብዬ አልከራከርም” ሲል ቀስ በቀስ እየተንኳተተም ቢሆን ወደእውነታው ለመጠጋት ይሞክር እንጂ “ዝርዝር ሁኔታው ወደፊት የበለጠ መጣራት ይኖርበታል” ሲል አንዳች ሀፍረት ሳይሰማው በአደባባይ ለማላገጥ ፈጽሞ አልከበደውም፡፡

ይኸው አነጋገሩ አግራሞት የጫረባት በሚመስል ድምጸት፣ ትንታጓ ጋዜጠኛም ቀጠል አድርጋ “ቡድኑ ጥቃቱን በቀጥታ ራሱ እንደፈጸመው በአደባባይ እያመነ ምኑ ነው የሚጣራው?፣ ማንስ ነው የሚያጣራው? በማለት ኮስተር ብላ ባፋጠጠችው ጊዜ መፈናፈኛ ስላጣና ጭራሹን ስለተምታታበት “ለፍትህ ሲባል ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ሊታይ ይገባዋል ማለቴ ነው እኮ” ሲል በወገናዊነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ ማሰሪያ ውሉ በጠፋበት አነጋገር ሲንተባተብ አድምጠነዋል፡፡

ብራቮ መኣዛ፣ በሙያሽ እደጊ፣ ተመንደጊ ብያለሁ፡፡

እንደመውጫ

የሽብርተኝነት ወንጀል በጠባዩ አለም-አቀፍ ወንጀል ከመሆኑም በላይ ዘርፈ-ብዙ ደረጃዎች እንዳሉት መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ የሽብርና ተዛማጅ ወንጀሎችን በቀጥታ መፈጸም ብቻ ሳይሆን ይህንኑ ወንጀል ከሚፈጽሙት ግለሰቦች ወይም ቡድኖችም ሆነ ሥልጣን ባለው የመንግሥት አካል አማካኝነት በሽብርተኝነት ከተሰየሙት ድርጅቶች ጋር በማናቸውም አይነት መንገድ መተባበ ወይም እነዚያኑ ወገኖች በአደባባይ መደገፍ፣ ማሞገስም ሆነ ማሞካሸት በራሱ የሚያስጠረጥር፣ ምናልባትም የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ተሻሽሎ የወጣውን የሽብርና ተዛማጅ ወንጀሎች መከላከያና መቆጣጠሪያ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ዓ.ም አንቀጽ 3ና አንቀጽ 9 ድንጋጌዎች በዋቢነት ይመለከቷል፡፡

“ማንም ሰው ፖለቲካዊ፣ ሀይማኖታዊ ወይም ርእዮተ-አለማዊ ግቦችን ለማራመድ አስቦ አንድን ህዝብ ወይም የተወሰነ የሕብረተ-ሰብ ክፍል ለማስፈራራት ወይም መንግሥት፣ የውጭ አገር መንግሥትም ሆነ አለም-አቀፍ ድርጅት አንድን የሆነ ተግባር እንዲፈጽም ወይም እንዳይፈጽም ለማስገደድ ወይም በዚሁ ኣካል ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ለማሳደር በተወጠነ እቅድ በማንኛውም ሰው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰ ወይም እንዲደርስ ያደረገ፣ የሰውን ህይወት አደጋላ የጣለ፣ የጠለፋ ወይም የአፈና ድርጊት የፈጸመ፣ በንብረት፣ በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በአካባቢ ላይ ጉዳት ያደረሰ ወይም ህዝባዊ ወይም ማሕበራዊ አገልግሎትን ከክፉኛ ያስተጓጎለ እንደሆነ የሽብር ወንጀል እንደፈጸመ ተቆጥሮ ከአስር ዓመት በማያንስና ከ18 ዓመት በማይበልጥ ጽኑእ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል” የአዋጁ አንቀጽ 3 ንኡስ አንቀጽ (1) በማያሻማ ቋንቋ ይደነግጋል፡፡

“የተፈጸመው የሽብር ወንጀል በሰው ላይ የሞት አደጋን ያስከተለ፣ ወይም ታሪካዊ ወይም ባህላዊ ቅርሶችን ያበላሸ፣ በንብረት፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ ወይም በህዝባዊ ወይም ማሕበራዊ አገልግሎት አውታሮች ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጉ የተረጋገጠ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ቅጣቱ ከ15 ዓመት እስከእድሜ-ልክ በሚዘልቅ ጽኑእ እስራት ወይም በሞት እንደሚያስቀጣ” የአዋጁ አንቀጽ 3 ንኡስ አንቀጽ (2) በአጽንኦት ያስጠነቅቃል፡፡

ለመሆኑ በተጠቀሰው አዋጅ አንቀጽ 18 ንኡስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ስር የተመለከቱትን መስፈርቶች ስለማሟላቱ በሚገባ ተጣርቶ በሽብርተኝነት የተሰየመው የት.ህ.ነ.ግ ቡድን የመንግሥቱን ሥልጣን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ድፍን 27 (ሃያ ሰባት ዓመታት ቀደም ሲል ከተዘረዘሩት አስከፊ ወንጀሎች ውስጥ በአጋጣሚም ቢሆን ያልፈጸመው የትኛውን የወንጀል ድርጊት ይሆን?

ሕጋዊ ሰውነት ያለው ማናቸውም ድርጅት በሽብርተኝነት ሊሰየም የሚችለው ቀድሞ ነገር “የሽብር ወንጀልን አላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስ ወይም የዚሁ ድርጅት ሥራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጪ አካል ወንጀሉን በአሰራርም ሆነ በግልጽ የተቀበለው ወይም አፈጻጸሙን የመራ ወይም ተፈጽሟል ተብሎ በሚታመነው ወንጀል ውስጥ በየትኛውም ደረጃ እጁ ያለበት ወይም የተሳተፈ መሆኑ ሲረጋገጥ፣ ወይም በአሰራር ወይም በአፈጻጸም ወንጀሉ የድርጅቱ መገለጫ ሆኖ ሲታይ ወይም አብዛኛው የድርጅቱ ሠራተኞች ወንጀሉን አስቀድመው በሚያውቁበት አኳኋን የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ” ነው፡፡

በሌላ አነጋገር የድርጅቱ ስራ አመራር አባላት ወይም ሰራተኞች ወንጀሉን መተዳደሪያ ሙያቸው አድርገው የያዙት መሆኑ ሲታወቅ ወይም ድርጅቱ ወንጀሉን በአሰራርም ሆነ በውጤት ደረጃ በጸጋ የተቀበለው ወይም የራሱ አድርጎ የወሰደው ሲሆን “የህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ያንን ድርጅት በሁለት ሶስተኛ የአብላጫ ድምጽ በአሸባሪነት ሊሰይመው” ይችላል፡፡

በመሰረቱ ሕግ አውጪው “ምክር ቤት የአንድን ድርጅት በፍርድ ቤት በኩል በወንጀል መከሰስ ወይም መቀጣት የግድ መጠበቅ ሳያስፈልገው በአሸባሪነት የመሰየም፣ የማፍረስና ሀብቱን መንግሥት እንዲወርስ የመወሰን መብት” እንዳለው ጭምር ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

እንግዲህ ከአባይ ሚዲያ ጋር ያካሄደውን ዝርዝር ቃለ-ምልልስ በውል ተከታትሎ የአቶ ታምራትን ትክክለኛ ስፍራ ለጉዳዩ አግባብነት ባለው በዚሁ የልዩ ወንጀል ሕግ ማእቀፍ ውስጥ አበክሮ መፈለጉ የጠቅላይ አቃቤ-ሕግ መስሪያ ቤት የቤት ስራ ይሆናል፡፡

የኔን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.