ሁሉም አማራ ወደ ግንባር እንዲሰለፍ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ጥሪ አቀረቡ

demeke
demeke

በዳንሻ ከተማ ዛሬ ታላቅ ሕዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል። የሰልፉ ዓላማ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ክብር ለመስጠት፣ ለሁለተኛው ዙር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት ደስታን ለመግለጽ፣ አሸባሪውን ትህነግ ማውገዝ እና ሕዝቡ የሕልውና ዘመቻው ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግ ነው ተብሏል።

ውስጣዊ አንድነትን በማጠንከር የጋራ ጠላትን በብቃት መመከት እንደሚገባ በሰልፉ ተነስቷል። ለዚህም ሕዝቡን መስለው ለጠላት የሚሠሩ አካላትን መምከር ይገባል፤ የማያርፉ ከሆነ ግን ለሕዝቡ ህልውና ሲባል የማያዳግም ርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ተመላክቷል።

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የሰላምና ደኅንነት መምሪያ ኀላፊው ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ “ዛሬ የተገናኘነው ዲስኩር ለማሰማት ሳይሆን የመጣብንን ወራሪ አውቀን የመጨረሻውን ፍልሚያ ለመግጠም ነው” ብለዋል። ኮሎኔሉ አሸባሪው ትህነግ አማራን ለማጥፋት መነሳቱን አንስተዋል፡፡ ይህንን ለመመከትም የአማራ ሕዝብ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት አድርጎ በነቂስ ወደ ግንባር እንዲሰለፍ ነው ጥሪ ያቀረቡት።

የህልውና ዘመቻው የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ በመሆኑ ራስን ለመከላከልና ለማስከበር መሰለፍ ይገባል ብለዋል። ለአማራና ለኢትዮጵያ መሞት ክብር ነው ብለን ቀድመን መሰለፍ አለብንም ብለዋል። ኮሎኔል ደመቀ ባስተላለፉት መልዕክት ዛሬ ቁርጥ ቀን በመሆኑ ማንኛውም የታጠቀና ትጥቅ የሌለው ኀይል ወደ ማክሰኞ ገበያ፣ ወፍ አርግፍና ሑመራ መክተትና በጋራ ዘምቶ ጠላትን ማሸነፍ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ክብራችንን ስለምንመርጥ ሁላችንም ለሀገራችን መሞት ይገባናል ያሉት ኮሎኔል ደመቀ የሃይማኖት አባቶችም ጦር ግንባር ድረስ ተሰልፈው በጸሎትና በዱአ ሊያግዙ ይገባል ብለዋል። አቅም ያለው ታጥቆ መግጠም ያልቻለ ደግሞ በሞራልና በስንቅ አቅርቦት ሊደግፍ እንደሚገባም አሳስበዋል። በርሃ ያለ ባለመሳሪያ ሁሉ ከነገ ጀምሮ ወደ ግንባር እንዲከትም መመሪያ ሰጥተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኦሮሚያ ክልል የተደረገው ሰልፍ እንደውም የዘገየ ነው

የከተማው ሕዝብ በሰልፉ ላይ “የማንነት ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ መብታችን ነው፤ የአማራ ሕዝብ በሀገር መከላከያ ሠራዊት አይደራደርም፤ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ለፋኖና ሚሊሻ እንዲሁም ለመከላከያ ክብር ይገባል፤ እኛ አማራዎች የምናወራርደው እንጂ የሚያወራረድብን ሂሳብ የለም፤” እና መሰል መልእክቶችን አንግቦ ነው አደባባይ የወጣው፡፡ አስተያየታቸውን ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የሰጡ የከተማው ነዋሪዎችም ስለ ክብራቸው፣ ስለ ነጻነታቸውና ስለ ሀገራቸው ሕልውና ሲሉ ግንባር ለመሰለፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። በሰላማዊ ሰልፉ የዞኑን አስተዳዳሪ ጨምሮ ሌሎች አካላትም ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ – ከዳንሻ  (አሚኮ)

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Share