ገድሎባላይዜሽንን አንቀበልም – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

Blinken ገድሎባላይዜሽንን አንቀበልም    መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ
blinken

ጦርነት እንኳን ለሰው ለአጠቃለይ ለምድር እንሥሣት ና እፅዋት የማይበጅ ነው ።ጦርነት ህይወት ላላቸው ፍጡራን ይቅርና ለአጠቃላይ ለምድሪቷም አንዳች ጥቅም አይሰጥም ።ለምድርም ሆነ ለነዋሪዎቿ አጥፊያቸው እንጂ አልሚያቸው ከቶም አይሆንም ። ይህንን እርባና ቢሥነቱን እያወቁ ግን በጦርነት ውሥጥና ከውጤቱ በኋላ “እናተርፋለን ” ባዮች በረቀቀ ሴራ ጦርነትን ደጋግመው ሲጭሩ ህዝብን ከህዝብ ሲያጫርሱ እናስተውላለን ። በገድሎባላይዜሽን መረህ ።
በገድሎባላይዜሽን መርህ የሚመራ ፤ በጦር ኃይል ደካማ የሆነውን አገር ሀብት መቆጣጠር በጉልበት ና በቴክኖሎጂ ተተግኖ መዝረፍ ፣ ግቡ ነውና ይህ በቀማኞች የሚመራ ጦርነት ሰብዓዊ ፍጡርን በሙሉ ለጥቅሙ ሲል እንደሚጨርስ ትላንት በሄሮሺማና ናጋሳኪ እንዲሁም በማጨው ፣ ዛሬ ደግሞ በአፍጋኒስታን ፣ በሊቢያ በየመን ፣ በሶሪያ ፣ በፍሊስጤም ና በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ተረጋግጧል ።
የገሎባላይዜሽኑ ፊትአውራሪ የአንድ አገር ዜጋ እርስ በእርሱ ቢጫረስ ፣ ህዝብ ቢፈናቀል ከቶም ደንታ የለውም ።ግቡ እርስ በእርስ አጫርሶ ዳርክ ኮንትኔት የሚላትን አፍሪካ መዝረፍ ነው ። ዓላማው የተፈጥሮ ሀብት እና መአድናትን ማጋበስ ነው ። …
የለምለም ና በበርካታ ማዕድን የተሞለች አገር ባለቤት ለሆነው ባለ አገሩ ፣ አፍሪካዊ ደንታ የለውም ። በዛ ማዕደን በበለፀገ አገር ለሚኖሩ ባለአገሮች ህይወት አይገደውም ። ህሊና ቢሱ በዝባዡ ኃይል እውቀት ያልዘለቀው ፣ ተርታው ህዝብ በሙሉ አልቆ ፣ ጥቂት ሆዳም እርሱን አገልጋይ የሆኑ ዜጎች በምድሪቱ ቢተርፉለት ሥለሚመርጥ ” በመተላለቃችሁ ግፉበት ፤ በርቱ! ” እያለ የትጥቅና ሥንቅ አቅርቦት በገፍ ያቀርባል ። የራሱን ብዝበዛ ለማፋጠን የሚረዳውን የጦር መሣሪያ ማምረቻ በሰፊው ሥለገነባም ፣ የተለያዩ እጅግ የዘመኑ የጦር መሣሪያዎችን በማምረት እነዚህንም መሳሪያዎች በድብቅና በግልፅ ከሆድ የዘለለ ህልም ለሌላቸው ፣ አገር አፍራሽ ልሂቃን በመስጠት የአንድ አገር ዜጎች እርስ በእርሳቸው እንዲጨራረሱም ያደርጋል ።
የሰለጠነው በገሎባላይዜሽን መርህ ተቀሳቃሹ እና መሣሪያ አምራቹ አገር ፣ ለጥቅም ሲል መፋጨት ፣ መጋደል የጀመረው በራሱ እና በወረራ የራሱ ባደረገው አገር ነው ። የሮማ ፣ የኦቶማን ኢምፓየርን ና እና የአሜሪካንን አፈናቃይነትና የግዛት ወረራ ከታሪክ አንብቦ መረዳት ይህንን እውነት ለመመሥከር ያስችላል ። እያንዳንዱ አውሮፓዊ ትላንት ምን እንደነበር በመንገር የዛሬው የብዝበዛ ወረራ ከዛ ተመክሮ የመጣ መሆኑንን በተጨባጭ ያስረዳል ።
ፈረንሳይ ና እንግሊዝ በአዲሲቱ አሜሪካ ውሥጥ ለዓመታትት ተዋግተዋል ።ሌላ አገርን በጦርነት የመያዝ ሃሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ የተወሰደው ከዛ ይመሥለኛል ።ከአፍሪካ ሠራተኛ እጆችን በኃይልና በጭካኔ ጭምር በማጋዝ ። ጦርነትን በሴራ መልክ በትብብር በማከናወን የተጀመረው በአንደኛው ዓለም ጦርነት መሆኑንንም አትርሱ ።የአውሮፓውያኑ የእርስ በእርስ ጦርነት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ደግሞ እጅግ የባሰ ሆነ ። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የጦር መሣሪያ አምራች ና ባለቤት የሆኑ አገሮች ፊታቸውን ወደአፍሪካ አዞሩ።
የ19ኛው ክ/ዘ የለየለት የቅኝ ግዛት አገር የመያዝ እሽቅድድም አውሮፓውያን በአፍሪካ አካሂደዋል ። ቤልጄም እንግሊዝ ፣ ፈረንሣይ ፣ጀርመን ኢጣሊያን አፍሪካን ለመቀራመት በአፍሪካ ምድር ተርመሥምሰዋል ። የአፍሪካን ህዝቦችም በጎሣ እየከፋፈሉ አጫርሰዋል ። ለአንዱ መሣሪያና ጥይት በመሥጠት ለአንዱ በመንፈግ የአንድ አገር ህዝብን አፋጅተዋል ። ቂም እንዲያያዝም አድርገዋል ። እነሱ በአንደኛውና ሁለተኛው ዓለም ጦርነት የተጨራረሱትን ያህል አፍሪካዊያንን በወረርሺኝ ፣ በኤችአይቪ ፣ በችጋር ፣ በቸነፈር ወወተ ጭምር እንደቅጠል እንዲረግፍ አድርገዋል ።
በአንደኛውና በሁለተኛው ዓለም ጦርነት 65 ሚሊዮን የሚጠጋ ሰው እንደሞተ ይገመታል ። ከፍተኛው ሞት የተመዘገበው ማለትም 56.4 ሚ ( ከ1939_1945 እኤአ ) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲሆን በአንደኛው የዓለም ጦርነት ( 1914_1918 ዓ/ም ) 8.5 ሚ ህዝብ ነው ያለቀው ።
ዛሬ ደግሞ በገድሎባልአይዜሽን ( ግሎባላይዜሽን ) ዘመን ፣ የአፍሪካን ህዝብ እርስ በእርሱ በማጫረስ ፣ ሁለንተናዊ ድህነት እንዲወራው በማድረግ ፣ ለእለት ጉርሱ ብቻ በማሰብ ኗሪ እንዲሆን በኬሚካል የታሸ ሥንዴና ዱቄት በማቅረብ ፣ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ ዜጎች ለአገረቸው ደንታ እንዳይኖራቸው በማድረግ የ19 ክ/ዘ ቅኝ ገዢዎቻችን በእጅ አዙር ዛሬም ጀግኖቻችንን በመግደል በጉልበታቸው የእጀራ አባት ሆነውብናል ። ( ወዳጄ ግድሎባላይዜሽን ማለት ትርጉሙ ይኸው ነው ።)
በጦር መሣሪያቸውና በሀብታቸው በመመካት ዛሬም ብዝበዛቸው እንዳይቋረጥ በብርቱ በመፈለግ፣ አውሮፓ ና አሜሪካ አፍሪካን ሠላም አልባ ና የአምባገነኖችና የሽብርተኞች መፈንጫ እያደረጓት ነው ። ይህም ብቻ አይደለም ሞት ምን መሆኑንን ከቶም የማይገነዘበውን ፣ የእለት ምግቡን ካገኘ ያለአቅሙ መሣሪያ ተሸክሞ ለጦርነት ለመማገድ ወደኋላ የማይለውን ፣ በድህነት ሰበብ የሆዱ እሥረኛ የሆነውን ለአቅመ አዳም ያልደረሰውን ዕድሜው በ12 እና በ15 ዓመት መካከል የሚገኘውን ፣ በሃሺሽ በማጦዝ ዛሬ ና አሁን የአፍሪካ ወጣቶች በከንቱ እንዲያልቁ እያደረጉ ነው ።
ዛሬ በአገሬ በኢትዮጵያ ይህ ግፍ በአውሮፓ ና በአሜሪካ ተባባሪነት ፤ በአሸባሪው ህወሃት ፊት አውራሪነት በገሃድ እየተፈፀመ ነው ። ይህ ግፍ ደግሞ ቢዘገይም ዋጋ ያሥከፍላቸዋል ። የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታት ለብዝበዛ ሲሉ የሰሩት ግፍ እንሆ ዛሬ ዋጋ እንደሚያሥከፍላቸው እያየን ነው ። የሰሞኑ ጎርፍ ና ውድመትም የእግዚአብሔር ልምጪን ኃይለኝነት እያሳየን ነው ። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከጥንት እስከዛሬ የምንመካው በፈጣሪያችን በእግዚአብሔር ነውና ጠላቶቻችን በፈጣሪ ልምጪ እንደሚሸነቆጡ እናምናለን ።
እኛ ኢትዮጵያዊያን የምንመካው በፈጣሪያችን ነውና ፈጣሪያችን እግዚአብሔር ከቶም አያሳፍረንም ። እናም ገድለውን በአገራችን ላይ አዛዥ ናዛዥ እንሁን የሚሉትን የምእራቡን ዓለም ና የአሜሪካ ቱጃሮችን የድፍረትና የጭካኔ ተግባር እጃችንን አጣምረን አንቀበለም ። ተላንትም አልተቀበልንም ። ዛሬም አንቀበልም ። አዎ ገድሎባላይዜሽንን አንቀበልም ።

2 Comments

  1. እጅግ ገራሚ ሀሳብ ነው ያመጡት። እውነትም ግሎባላይዜሽን ሶስተኛውን አለምህዝብ በድህነት እንዲማቅቅ እና የኘሱ መጽዋት ጠባቂ ማድረግ ነው። ገድሎባይላዜሽን ልክ እንደ cocacolinization and macdonalization አካዳሚ ቋንቋ ውስጥ መካተቱ አይቀሬ ነው።

  2. ትክክለኛ የአሜሪካና የአውሮፓውያን ሤራ አመላካች ነው ከዚህ ሌላም ለቀጣይ ቀጣይ ያሤርዋቸው የማፋጃ ስልቶችም እንደሚኖሯቸው አውቀን እንጠንቀቅ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.