አቶ ዳኘው ወልደ ስላሴ  እና አቶ ፍትህአዬ አሰጉ ለአቶ መለስ ዜናዊ ስለ ወልቃይት ጠገዴ፣ ሰቲት ሁመራ እና ጠለምት የፃፉት ታሪካዊ ደብዳቤ

በኅዳር 11 ቀን 1984 ዓ/ም፣
ይድረስ ለክቡር አቶ መለስ ዜናዊ
የኢትዮጵያ ሽግግር መንግስት ፕሬዜዳንት
አዲስ አበባ
welkeit 768x597 1
ክቡር ፕሬዜዳንት፡
ከአክሱም ምስረታ በፊት ጀምሮ የትግራይና የጎንደር ህዝብ በዘር፣ በቋንቋ፣በባህል፣ በጋብቻ፣በስም፣ በሀይማኖት፣ በሀገር ፍቅር ስሜት፣በጆግራፊና በኢኮኖሚ በጠቅላላው አነጋገር በታሪክ፣ በኑሮና በባህል ተሳስሮ የተከዜን ወንዝ በጋራ እየጠጣ ደንበር ሳያፈርስ ከጥንት የወረሰውን የአበውን ታሪክና ቅርስ አክብሮና ተደጋግፎ በመኖር ኢትዮጵያን የብዙህ ሺ አመታት የታሪክ ባለሀብት ያደረገ ሲቀር ቢውል ከአንድ አያት የሚቆጠር አንድ ወጥ ህዝብ ነው።
በመሆኑንም የጎንደርና የትግራይ ህዝብ አንድ ብሔረሰብ እንጂ ሁለት ብሄረሰብ ተብሎ መታየትና መቆጠር አልነበረበትም። አንዱ በተመቸውና በተሟላለት ጊዜም ሌላውን ማበረታታትና መደገፍ እንጂ ማባረርና መናቅ ባህሉ ሁኖ አያውቅም። በንቀትና በእብሪት አገዛዝ ምክኒያት ግዙፍ ሰራዊት የነበረው የመንግስቱ ኀይለ ማሪያም መንግስት ተንኮታኩቶ ሲወድቅ ታይቷል።
ትግራይና ጎንደር ባለፉት 17 አመታት የጨለማ ዘመን ውስጥ የሰው ህይዎት መስዋትነትና በኢኮኖሚ ውድመት በኩል ያላቋረጠና ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል። አብረው በመነሳታቸውና በመታገላቸው ኢትዮጵያን ከጭቆና አገዛዝ ነፃ አውጥተው አሁን ካለቺበት የፖለቲካ ነፃነት እና የኢኮኖሚ ተስፋ ጭላንጭል ላይ ሊያደርሷት ችለዋል።
የእነዚህ ህዝቦች የታሪክና አንድነት እውነተኛ ገፅታ ይህ ሁኖ ሳለ ሰሞኑን “Africa Confidentional” የሚባለው የ15 ቀን መፅሄት ባወጣው እትም ከኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት አገኘውት ብሎ የፃፈው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የአስተዳደር ክልል ካርታ ለጎንደር ለጎንደር ታሪክና ቅርስ ቀዳሚ ባለቤት የሆኑትን ለም ቦታዎች ማለትም ሰቲት ሁመራን፣ ወልቃይትን፣ ጠገዴንና ጠለምትን ከተፈጥሮዊና ታሪካዊ አካላቸው ከጎንደር ለይቶ የተከዜን ድንበር በመጣስ የትግራይ አስተዳደር አካል በማድረግ ቦታችን የትግራይ ልማት ማዳበሪ ህዝቡን ሁለተኛ ደረጃ የትግራይ ዜጋ ለማድረግ መታቀዱን ስለተረዳን በተቃጣብን የውርደት ብትር እጅግ በጣም ተደንቀናል/ አዝነናል።
በተጨማሪ ቴዎድሮስ የተወለደበትን ቋራን፣ አፅሙ ያረፈበትን ማህበረ ስላሴን፣ ዮሐንስ የተሰዋበትን መተማን አስመልክቶ ቆላማውን ሀገር በሙሉ ዘሩንና ስሙን አካባቢውን ሰምቶት ለማያውቀው “ቤኔሻንጉል” ለተባለ እዚያ አካባቢ ለማይኖር ጎሳ ለመስጠት መታቀዱን ካርተው አሳይቷል። ይህ እቅድ ከኦሜድላ እስከ መተማ ባለው ቆላማ መሬት ላይ ከዝንተ አለም ጀምሮ ከብቱን እንደልቡ ከቦታ ቦታ እያዘዋወረ የሚያሰማራውን ደገኛ የቋራ፣ የአለፋ፣ የጣቁሳ፣ የተከል፣ የጫቆና አዳኝ አገር ህዝብ እስከ አሁን ፀንቶ የኖረበተን ህጋዊ መብት የሚጋፋ ነው።
ከጥቂት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ድምፅ ራዲዮ የሽግግር መንግስት ምክር ቤት የኢትዮጵያን አስተዳደር በ14 ክፍሎች ብሎ አፅድቋል ብሎ ያልተላለፈው ዜና…አፍሪካ ኮንፊደንሻል… ካተመው ካርታ ጋር የተቆራኘ እንዳልሆነ ተስፋ አለን። ከሆነ ግን ይህ ንድፍ #የህገመንግስት_ረቂቅ አካል ሁኖ እረኛዬ #እንዲፀድቅ ወደፊት በህዝብ ለህዝብ ለሚመረጠው #ህገ_መንግስት አፅዳቂ ጉባኤ ማቅረብ እነዚህን ወንድማማች #የትግራይና_የጎንደር_ህዝቦች ካሁን ጀምረው #ለፍጅት እንዲሰላለፉ መጋበዝ ነው ከሚባል በቀር ሌላ ምክኒያትና ትርጉም አይኖረውም። በተጨማሪ በሽግግር መንግስት ምክር ቤት ውስጥ የጎንደር ህዝብ የመረጠው ተዎካይ ባለመኖሩ እኛ አሁን ለማስረዳት የሞከርነውን ቁስሎንና ታሪኩን በግንባር የሚያስረዳ አላገኘነም። በመሆኑን #ከዝንተ_አለም ጀምሮ የኖረውን #መብታችን እና #ታሪካችን በህዝብ የሚመረጥ ህጋዊ ምክር ቤት እንደማይነካብን እናምናለን።
ይህን እቅድ በተግባር ላይ ለማኖር ቢሞከር በገፊነት በሚመጠውና በተገፊነት በሚመከተው ወንድማማች ህዝብ መካከል የሚደርሰው እልቂት ቀላልና ቁስሉ ለብዙ ትውልድ የማይሽር ስለሚሆን ይህ በከባድ መስዋዕትነት የተገኘን ድልና የተስፋ ጭላንጭል በዚህ ምክኒያት እንደይጠፋብና እንደይወድቅብን “በራሱ የተከፋፈለ ቤት አይፀናም።” የሚለው የመፅሀፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደይደርስብን ያሰጋል።
ለ17 አመታት የተሰቃየው አልበቀው ብሎ ይህን ወንድማማች ህዝብ ለርዕስ በርስ ግጭት መዳረግ በወርቅ ቀለም ሊፃፍ የሚገባው ይህን ዓቢይ የትግራይ፣ የጎንደርና የወሎ ህዝብ የትግል ታሪክ ሂደትና የድል ውጤት የሀፍረት ማቅ መልበሻና የወደፊት ትውልዶች ዕርግማን እንዳይሆንብን ያሳስባል።
የአካባቢውን ልማት በተመለከተ ለምሳሌ ሰቲት ሁመራን ብንጠቅስ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ተንቀሳቅሶ በነበረበት ወቅት ከወልቃይትና ጠገዴ ተዎላጆች ቀጥሎ ከፍተኛ ተጠቃሚዎች የትግራይና የኤርትራ ወንድማማቾች ነበሩ። በዚህ ሁኔታ የጎንደር ህዝብ ይደሰትና ይበረታታ ነበር እንጂ ምንም አይነት ቅሬታ ወይም ማጉረምረም እንዳልነበረ በሁላችንም ልቦና ውስጥ የሚበራ ህያው ትዝታ ነው።
ይህ የሚያንፀባርቀው በጎንደር ህዝብ አይን የትግራይና የኤርትራ ህዝብ በድንበር ሳይገታ በአንድ ቤተሰብነት ተሳስሮ በክፉና በበጎው ጊዜ አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ ተባብሎ አብሮ የመኖር ዘላቂ ባህርይ ያለው መንድ ወጥ ህዝብ ነው።
የካርታውን ንድፍ መውጣትና መሰራት አንድነታችንን ለሚጠሉ ወገኖች አስደሳች ወሬ ሁኖላቸዋል።
ስለዚህ ይህ አሳዛኝ እቅድ በፍጥነት ካልታረመ ወሬው ከአሁን ጀምሮ በ2ቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል በቀላሉና በጥቂት ትውልድ ሊታረም የማይችል ቅራኔና እልቂት በመጋበዝ የተሰበከውን የዲሞክራሲ ፋና በአለም ፊት እንዳያጨልመው በመስጋት ይህን የተቃጣ የቅስፈት ሰይፍ በወቅቱ የመቅጨት ኅላፊነት በክቡርነትዎ ላይ የተቀመጠ እንደመሆኑ የበኩላችንን በቅን አስተሳሰብ ላይ የተመሰረተ ሀሳብ በጎንደር ተዎላጅነት ግዴታችን ተነሳስተንና ተገፋፍተን በትህትና አቅርበናል።
ከማክበር ሰላምታና ከበጎ ምኞት ጋር
ዳኘው ወልደ ስላሴ
ፖ.ሳ.ቁ 70556
ስልክ.ቁ 201351
አዲስ አበባ
ፍትህእየ አሰጉ
ፖ.ሳ.ቁ 26809
ስልክ.ቁ 513879
አዲስ አበባ
ግልባጭ:
ለክቡር አቶ ታምራት ላይኔ
የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት ጠቅላይ ሚኒስተር
አዲስ አበባ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.