debre
debre
1፤ ሕወሃት ማረኳቸው ያላቸውን ከ1 ሺህ በላይ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በነጻ መልቀቁን የድርጅቱ ሊቀመንበር ደብረ ጺዮን ገ/ሚካዔል ለሮይተርስ ተናግረዋል። ደብረ ጺዮን ለቀቅናቸው ያሏቸው ተራ ወታደሮችን መሆኑን የገለጠው ዘገባው፣ ሌሎች 5 ሺህ ምርኮኛ ወታደሮች ግን በእጃችን ይገኛሉ ማለታቸውን ጠቅሷል። ምርኮኞቹ ትናንት በደቡባዊ ትግራይ በኩል ወደ አማራ ክልል እንዲሻገሩ መደረጋቸውን ከደብረ ጺዮን መስማቱን የገለጸው ሮይተርስ፣ መረጃውን ግን ከገለልተኛ አካል ማጣራት አልቻልኩም ብሏል።
2፤ የሕወሃት ኃይሎች ከአፋር ክልል ወደ መቀሌ ሲጓዙ የነሩ 60 ሰብዓዊ ዕርዳታ የጫኑ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ጉዞ ማስተጓጎላቸውን ኢዜአ ማምሻውን ዘግቧል። የተሽከርካሪዎቹ ጉዞ የተስተጓጎለው የሕወሃት ተዋጊዎች በክልሉ ዞን አራት ውስጥ ባሉ የፍተሻ ኬላዎች ላይ ዛሬ የከባድ መሳሪያ ድብደባ በመፈጸማቸው እንደሆነ ዘገባው አመልክቷል። የአፋር ክልላዊ መንግሥትም ሕወሃት ጦርነት ከፍቶብኛል ሲል በኮምንኬሽን ቢሮው ማኅበራዊ ትስስር ገጽ ባሰራጨው መግለጫ ገልጧል። የሕወሃት ተዋጊዎች በክልሉ ላይ ጥቃት የከፈቱት ፈንቲ ረሱ ያሎ በተባለ ወረዳ በኩል መሆኑን መግለጫው አመልክቷል።
3፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማዋ ከሕወሃት ጋር ግንኙነት አላቸው ብሎ የጠረጠራቸውን 323 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዳዋለ እና አንዳንድ ንግድ ቤቶችንም አሽጎ ምርመራ እያደረገ መሆኑን ማምሻውን ለመንግሥት ዜና አውታሮች ተናግሯል። ተጠርጣሪዎቹ ለሕወሃት ድጋፍ በማድረግ፣ ሰንደቅ ዐላማን በማዋረድ፣ ሕገወጥ ጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት እና ሌሎች ተያያዥ ወንጀሎች ጠርጥሬያቸዋለሁ ያለው ፖሊስ፣ እስሩ ግን ማንነት ላይ ያነጣጠረ አይደለም ሲል ሰሞኑን የወጡ አንዳንድ ዘገባዎችን አስተባብሏል።
4፤ በአዲስ አበባ የትግራይ ተወላጆች በጅምላ እየታሰሩ ስለመሆኑ መረጃዎች ደርሰውኛል ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ሪፖርት ከሷል። ፖሊስ ጣቢያዎች በትግሬኛ ተናጋሪዎች ስለመጨናነቃቸው ታስረው ከተፈቱ ግለሰቦች መስማቱን የገለጸው አምነስቲ፣ ፖሊስ መታወቂያ እየጠየቀ በማሰሩ እስሩ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ይመስላል ብሏል። መንግሥት ጅምላ እስሩን ባስቸኳይ እንዲያቆም እና የታሰሩት ላይም ክስ እንዲመሠርት ወይም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታቸው አሳስቧል።
5፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ስለ ትግራይ ተወላጆች በብዛት መታሰር በትዊተር ገጹ ካወጣው መረጃ ጋር አብሮ የማይሄድ አሳሳች ፎቶ ተጠቅሟል የሚል ከኢትዮጵያ መንግሥት ወቀሳ ቀርቦበታል። አምነስቲ የተጠቀመው ፎቶ የፈረንሳዩ ዜና ወኪል ፎቶ አንሽ በኢትዮጵያ ጠቅላላ ምርጫ ዕለት ፖሊስ ድምጽ ለመስጠት የተሰለፉ ሰዎችን ሲፈተሽ ያነሳው እንደሆነ ታውቋል።
6፤ ሕወሃት በሀገሪቱ ብሄራዊ ደኅንነት ላይ ለደቀነው አደጋ የክልሎች ጸጥታ ኃይሎች የሚሰጡት ምላሽ በፌደራል መንግሥቱ እና በመከላከያ ሠራዊት ዕዝ ስር የሚመራ መሆን እንዳለበት ኢዜማ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል። መንግሥት ግጭቱ የክልሎች ግጭት ብቻ ተደርጎ እንዲታይ ማድረጉ አስደንጋጭ እንደሆነበት ፓርቲው ጠቅሷል። መንግሥት ሕወሃትን ከማሸነፍ በዘለለ ለግጭቱ ዘለቄታዊ መፍትሄ በመገለግ ላይ ሊያተኩር እንደሚገባ ፓርቲው አሳስቧል። ሕወሃትን ደግፋችኋል በሚል ጸጥታ ኃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን እስር ባስቸኳይ እንዲያቆሙ እና እስካሁን ያላግባብ የተፈጸሙ እስሮችም ተጣርተው መንግሥት በአጥፊዎች ላይ ርምጃ እንዲወስድ ፓርቲው አክሎ ጠይቋል።
7፤ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ከተመድ የሰለም ማስከበር ተልዕኮ ድጋፍ ሰጭ ዋና ሃላፊ አትዋል ካሬ ጋር ስለ ኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች እንደተነጋገሩ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ አመልክቷል። ተመድ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ለዓለማቀፍ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ማሰማራት የለበትም በማለት የአሜሪካው ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ ሃላፊ ሜኔንዴዝ ለድርጅቱ ደብዳቤ በመጻፋቸው ኢትዮጵያ ማዘኗን ደመቀ ለዋና ሃላፊው ነግረዋቸዋል። ዋና ሃላፊው በበኩላቸው ኢትዮጵያ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን በሚወዛገቡባት አቢዬ ግዛት እና በሱማሊያ በሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች እየተጫወተች ያለችውን ቁልፍ ሚና አድንቀዋል ተብሏል። የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ከአቢዬ ግዛት እንዲወጣ ሱዳን ቀደም ሲል በተናጥል ለተመድ ጸጥታው ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቧ ይታወሳል።
[ዋዜማ ራዲዮ]