የሕግ ማስከበር ዘመቻው በሰሜናዊ ክልሎች አወቃቀር ረገድ የፈጠረው ግርታ (ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ)

  1. መግቢያ

ቅድመ-ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ኢትዮጵያችን መጀመሪያ በጠቅላይ ግዛቶችና ቀጥሎም በክፍላተ-ሀገር ተሸንሽና ስትመራ ነበር የምናውቃት፡፡ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ ሆና በተዋቀረች ማግስት ደግሞ በአምስት ራስ-ገዝና በሃያ አራት አስተዳደር አካባቢዎች ተከፋፍላ ትተዳደር እንደነበር አንዘነጋውም፡፡

ይህንኑ ታሪካዊ ኩነት ይበልጥ ለመከለስ ትንሽ የኋሊት ተጉዞ አግባብነት ያላቸውን የራስ-ገዝና የአስተዳደር አካባቢዎች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 14/1980 ዓ.ምና እርሱን ለማሻሻል የወጣውን የራስ-ገዝ አካባቢዎች፣ የአስተዳደር አካባቢዎች፣ ልዩ የአስተዳደር አካባቢዎችና የአውራጃዎች ክልል መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 26/1981 ዓ.ም በዋቢነት ይመለከቷል፡፡

ያ ሁሉ ቀርቶ ሌላ ዘፈን መጣና በተለወጠው አዲስ ቅኝት መሰረት የፈረደባት መከረኛ ምድር እንደገና መደራጀት አለብሽ ተባለች፡፡ በመሆኑም የወታደራዊው ደርግ አገዛዝ ቅጥያ የነበረው ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ፈርሶ በሀገሪቱ የሽግግር መንግሥት እንደተመሰረተ ለይስሙላ እንኳ ይሁንታችን በይፋ ሳይጠየቅ በአረብኛ ቁጥር ብቻ የሚታወቁ 14 ክልሎች እንዲኖሩን ታወጀ፡፡

  1. ሕገ-መንግሥታዊ እሳቤና ስሪት

ሀገራችን ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው ቅርጽ በግድ የተጫነባት በህዳር ወር 1987 ዓ.ም ነው፡፡ በስራ ላይ ያለው ሕገ-መንግሥት ‘አዲሲቷ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ’ እያለ በሀሰት የሚሸነግላት ሀገር ከማእከላዊ መንግሥት ሥልጣን የተባረረው ወያኔ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ግልጽነት በጎደለውና እምብዛም ባልተብራራ ሀረግ ‘ብሔሮች፣ ብሔረ-ሰቦችና ህዝቦች’ እያለ በሚያንቆለጳጵሳቸው ዘውግ-ተኮር ስብስቦች ፈቃድና ፍላጎት የተፈጠረች እንጂ ቅድመ-ታሪክ ተሻጋሪ የሆነ፣ ዘላቂ ህልውና የነበራትና የፖለቲካ ነጻነቷንም ሆነ የግዛት አንድነቷን ከባእዳን ወረራ ተከላክላ የኖረች ሉኣላዊት ምድር አይደለችም፡፡

በወርሀ-ህዳር 1987 ዓ.ም እንደጸደቀው እንደዚሁ ሕገ-መንግሥት መንደርደሪያ ከሆነ ሀገሪቱ አሁን ያገኘችውን ቅርጽ የያዘችው ቀድሞውኑ “የየራሳቸው አኩሪ ባህልና መልክአ-ምድራዊ አሰፋፈር በነበራቸው የተለያዩ ብሔር-ብሔረ-ሰቦችና ህዝቦች ነጻ ፈቃድና ውሳኔ” ነው፡፡ እነዚሁ ብሔሮች፣ ብሔረ-ሰቦችና ህዝቦች “በተለያዩ መስኮችና የግንኙነት ደረጃዎች በመተሳሰር አብረው የኖሩባትና የሚኖሩባት ከመሆኗ የተነሳ ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን” ብለው ስለሚያምኑ ብቻ እዚያ ማዶና እዚህ ማዶ ተጠራርተው በጥምር ሕብረ-ሀገርነት የቆረቆሯት በማስመሰል ተስላ መቅረቧን እንገነዘባለን፡፡

ይህንኑ ይበልጥ ለማፍታታት የታቀደ በሚመስል ግርድፍ አቀራረብ “መጻኢውየነዚሁ ብሔሮች፣ ብሔረ-ሰቦችና ህዝቦች የጋራ እድል ሳይቀር ከታሪካችን ወርሰነዋል የሚሉትን የተዛባ የርስበርስ ግንኙነት በማረምም ሆነ የጋራ ጥቅሞቻቸውን በማሳደግና በማበልጸግ” ላይ መመስረት ያለበትና የሚኖርበት እንደሆነ ተቀብሎ በአንድ ላይ ለመጣመር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ገልጸዉልናል፡፡ ሲያሻቸውም የየራሳቸውን እድል በየራሳቸው በመወሰን ስም በራሳቸው ጊዜ ከፌደሬሽኑ እያፈተለኩ ጓዛቸውን ጠቅለው በመውጣት ጥቃቅንና አነስተኛ መንግሥታትን ለመመስረት መወሰናቸውን ይኸው ሕገመንግሥት ያለሀፍረት ሊነግረን ይከጅለዋል፡፡

  1. በፌደሬሽኑ የታቀፉት ክልሎች ስሪትና አወቃቀር

በኢ.ፌ.ደ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 46 ንኡስ አንቀጽ (1) አነጋገር “የፌደራሉ መንግሥት የክልሎች ተዋጽኦ ነው”፡፡ ክልሎች ሊዋቀሩ የሚገባቸው ደግሞ “በህዝብ አሰፋፈር፣ በቋንቋ፣ በማንነትና በነዋሪዎች ስምምነት ላይ በመመስረት”  እንደሆነ የተጠቀሰው አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (2) ድንጋጌ አስረግጦ ይናገራል፡፡

ሆኖም ቀድሞ ሰሜናዊት ክፍለ-ግዛታችን የነበረችው ኤርትራ ከመሃል አገር ከተሰናበተችና እንደአንድ ነጻና ሉኣላዊት ምድር ራሷን ችላ ከቆመች በኋላ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል በጊዜያዊነት ይተዳደርበት ዘንድ ወጥቶ በነበረው የሽግግር ወቅት ቻርተር ማግስት አንድ ሕግ ተደንግጎ ነበር፡፡ በርግጥ የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም በወጣው በዚህ አዋጅ ቁጥር 7/1984 ዓ.ም መሰረት የየራሳቸው መለያ ቁጥር እየተሰጣቸው የተደራጁትና እስከ14 የሚደርሱት የሀገሪቱ ክልሎች በዘፈቀደ ታጥፈውና ወደዘጠኝ ተቀናንሰው እንደገና የተዋቀሩበትና በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 47 ስር ተዘርዝረው በጉራማይሌ አጠራር እየተጻፉ የተሰየሙበት አመክንዮ ያን ያህል ግልጽነት ያለው ሆኖ አናገኘውም፡፡

አዳዲሶቹ ክልሎች የተዋቀሩበት መንገድ ራሱ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 46 ንኡስ አንቀጽ (2) ድንጋጌ ስር አስቀድመው የተቀመጡትን መመዘኛዎች ጠብቆና አሟልቶ የተከናወነ አይደለም፡፡ የተባሉት ሕገ-መንግሥታዊ መስፈርቶች ‘የህዝብ አሰፋፈር’፣ ‘ብሔራዊ ማንነት’፣ ‘የአፍ መፍቻ ቋንቋ’ና ‘የአካባቢ ነዋሪዎች ፈቃድ’ ሲሆኑ የትኛውም ክልል ቢሆን ታዲያ እነዚህን ጣምራ መስፈርቶች በትክክል አሟልቶ ስለመደራጀቱ በማስረጃነት የሚያገለግል ሰነድ አይገኝም፣ ወይም የምስክርነት ቃል የሚሰጥ ሰው የለም፡፡

ይልቁንም ገሚሶቹ ክልሎች በመልክአ-ምድራዊ አሰፋፈራቸው ሕብረ-ብሔራዊ ሆነው ሳለ ቁጥሩ በዛ ይላል ተብሎ የሚገመተውን የአንድ ብሔር ወይም ብሔረ-ሰብ አንጡራ ስም እያንጠለጠሉ በዘፈቀደ እንዲጠሩ ሲደረግ ቀሪዎቹ ደግሞ እርስበርስ ተሰበጣጥረውና አንደኛው ከሌላው ጋር ተጋምደው የሰፈሩበት መልክአ-ምድራዊ አቅጣጫ ወይም ቀጣና እየተጠቀሰ ‘ህዝቦች’ በሚል ተከታይ የማሽሞንሞኛ ቃል የሚታጀቡበት መጠሪያ ተሰጥቷቸው እናገኛለን፡፡

እንግዲህ የዛሬውን አያድርገውና በገዛ እጁ ውርደትን ተከናንቦ መቀመቅ የወረደው የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ) ከሰላሳ ዓመታት በፊት ‘አምጬ ወለድኳት’ የሚላት ኢትዮጵያ የአዲስ አበባና የድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደሮችን ሳይጨምር ከመነሻው ዘጠኝ ክልሎችን ይዛ እንደተዋቀረች የምናስታውሰው ሲሆን በ2012ና በ2013 ዓ.ም ደግሞ አስረኛውና 11ኛው የሲዳማና የደቡብ ምእራብ ክልሎች ተጨምረዉላታል፡፡ ተጨምረዉባታል ሊባልም ይቻል ይሆናል፡፡

 

  1. የ’ሕግ ማስከበር’ ዘመቻው ተዋናዮች አበረታች ጥምረት

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አስተዳደር የትግራይን ክልል ሕገወጥ በሆነ መንገድ ይገዛ ከነበረው የደደቢት አጼ በጉልበቱ ጋር ከጥቅምት 24 እስከህዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ሲያካሂደው የሰነበተውን እልህ-አስጨራሽ ፍልሚያ ‘የሕግ ማስከበር ዘመቻ’ በማለት ነው የሚጠራው፡፡ በርግጥ የሀገሪቱን ሉኣላዊነት በተዳፈረና የግዛት አንድነቷን ከባድ አደጋ ላይ በጣለ ሁኔታ ያልተጠበቀ ትንኮሳ በመፈጸም የሕገ-መንግሥታዊ ስርአቱን ቀጣይነት እስከመገዳደር ደርሶ በነበረው ከሀዲ ቡድን ላይ የተወሰደው መሪር የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድም ቢሆን ሕግን ከማስከበር ተግባር ጋር ተያይዞ ቢገለጽ እምብዛም ላያስገርም ይችላል፡፡

እናማ አበው “አይጥ ለሞቷ የድመት አፍንጫ ታሸታለች” በሚሉት አይነት ት.ህ.ነ.ግ ሲያቀብጠው በፍጹም ሀኬት ተነሳስቶ የማይደፈረውን ተዳፈረና ባሰበው ቀርቶ ባላሰበው እንዲውል ተገደደ፡፡ እነሆ ለስድስተኛ ጊዜ ‘ተመረጥኩ’ ሲል አውጆ አለም-አቀፉን ሕብረተ-ሰብ  ለማወናበድ በሞከረ ማግስት ራሱ በጫረው የጦርነት ነበልባል ክፉኛ ከመለብለቡም ባሻገር ዘግይቶም ቢሆን ከሀገሪቱ የፖለቲካ ድርጅቶች ካርታ ሳይቀር እስከመሰረዝ ደርሷል፡፡

ይህ እኩይና ክልፍልፍ ቡድን ባለፈው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን እዝን ብቻ አልነበረም በግፍ ለማጥቃትና ለመበተን በለየለት እብደት ታውኮ የተወራጨው፡፡ ለትግራይ ተዋሳኝ የሆኑትንና  እንደሰሮቃና ቅራቅር ያሉትን የአማራ ክልል ግዛቶች ሳይቀር በተለያዩ አቅጣጫዎች ወሮ ለመያዝ ተንደፋድፎ እንደነበር የምናስታውሰው ነው፡፡

ከዚህ አንጻር በድንገት የተጠቃው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የከሀዲውን ቡድን ወረራ በጀግንነት ለመመከትና በመልሶ ማጥቃት እርምጃው በመደምሰስ የዶግ አመድ ለማድረግ ብቻውን አልነበረም፡፡ ከራሱ ክልል ደህንነት አልፎ ለሀገሪቱ ሉኣላዊነት መጠበቅ ጭምር ዘብ በመቆም ጨርሶ የማይታሙት የአማራ ልዩ ፖሊስ አባላትና የሚሊሻው ሀይሎች ከጎኑ የተሰለፉበትና በጠላት ላይ የተባበረ ክንዳቸውን ያሳረፉበት አጋጣሚ ለዓመታት የጓጓንለትን ድል የተፋጠነ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በዚያ ላይ ገና ከጅምሩ ሲጠነሰስ ‘ምነው ውሃ ሆኖ በቀረ’ ሊሰኝ የሚገባው ት.ህ.ነ.ግ አማራን እንደማሕበረ-ሰብ ከምድረ-ገጽ ለማጥፋት ከመነሻው ቃል ገብቶና ራሱን የቻለ ማኒፌስቶ ቀርጾ ሲምልና ሲገዘት የኖረ ድርጅት መሆኑን ስናጤን በሕግ ማስከበር ዘመቻው የታየውን አመርቂ ቅንጅት ተገቢነትና ባለዋጋነት ለመገንዘብ አያቅተንም፡፡

እንደእውነቱ ከሆነ ት.ህ.ነ.ግ ለአማራው ማሕበረ-ሰብ ብቻ ሳይሆን ሀይማኖት አበው ለሁሉም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ዜጎች አብሮነትና ተቻችሎ -ነዋሪነት የጋራ ደህንነት ሲባል በተባበረ ክንድ መመታትና ከናካቴው መወገድ የነበረበት ጸረ-አንድነትና ጸረ፼-ሠላም ሀይል ስለመሆኑ አገር ያወቀውና ፀሃይ የሞቀው ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ባልተገመተ ፍጥነት እየሆነ ያለው ይኸው ሲሆን ከእንግዲህ በBኋላ ነበር ለማለትም ይቻላል፡፡

በዚህም ሳቢያ ከሶስት ዓመታት በፊት ከማእከላዊው መንግሥት በቅሌት የተባረረው የት.ህ.ነ.ግ አመራር በጊዜያዊነት ተጠልሎባት የቆየችውን የመቀሌን ከተማ ብቻ ሳይሆን ራሱ ባቀጣጠለው የጦርነት እሳት ተበልቶ ይህንን አለም እስከወዲያኛው ተሰናብቷል፡፡ ይኸው ሰበብ ሆኖ ታዲያ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲደራጅና የተለመደው መንግሥታዊ አገልግሎት መሰጠቱን እንዲቀጥል መደረግ ነበረበት፡፡ ውሳኔው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሲሆን ትእዛዙን ያወረደው ደግሞ የፌደሬሽን ምክር ቤት ነው፡፡

ሁለቱም አካላት ለወሰዱት እርምጃ የሕግ መሰረት አላቸው፡፡ የሕገ-መንግሥቱን አንቀጽ 62 ንኡስ አንቀጽ ፺(9)ና የፌደራሉ መንግሥት በክልሎች ጣልቃ ሊገባ የሚችልበትን ስነ-ስርአት ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 359/1995 ዓ.ም አንቀጽ 13 ንኡስ አንቀጽ (4) ድንጋጌዎች በዋቢነት ይጠቅሷል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ አያሌዎችን ከማጀት እስከአደባባይ አብዝቶ ሲያከራክር የምንታዘበው በአማራ ልዩ ፖሊስና የሚሊሻው ሀይሎች አይተኬ ተሳትፎ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ነጻ የወጡት ቀደምት የቤጌ-ምድርና የወሎ ክፍለ-ግዛቶችና ከአስከፊው የት.ህ.ነ.ግ አገዛዝ መዳፍ የተላቀቁት ነዋሪ ማሕበረ-ሰቦቻቸው እጣ ፈንታ ምን ይሁን የሚለው ነጥብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

በርግጥ ድሉ እንደተገኘ አለቅጥ ፈጦ የወጣው ይህ ጥያቄ በርካታ መልሶች ያሉት ቢመስልም ትክክለኛውን ምላሽ ማግኘቱ ግን ያን ያህል ቀላል አይሆንም፡፡

አንዳንድ ወገኖች ‘ት.ህ.ነ.ግ እንኳን ተወገደ እንጂ’ ወደትግራይ የተጠቃለሉት ቀደምት የቤጌ-ምድርና የወሎ ክፍለ-ግዛቶች እስካሁን በቆዩበት ሁኔታ መተዳደራቸውን ቢቀጥሉና በነዚሁ ክፍለ-ግዛቶች ውስጥ የሚነሱ የአማራ ማንነት ይከበርልን ጥያቄዎች ካሉ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ተጣርተው ተገቢውን ምላሽ ቢያገኙ ይሻላል ሲሉ ይመክራሉ፣ ይከራከራሉም፡፡

በርግጥ እነዚህ ወገኖች የሚስቱት አቢይ ቁም-ነገር አወዛጋቢዎቹ የዎልቃይት-ጠገዴ፣ የዳንሻ፣ የጠለምት፣ የሰቲት-ሁመራ፣ የራያ-አላማጣና የዎፍላ ክፍለ-ግዛቶች ቀድሞ ነገር ከነባሮቹ ጠቅላይ ግዛቶች በጉልበት ተወስደው ወደታላቋ ትግራይ በማናለብኝነት የተጠቃለሉ አካባቢዎች እንጂ ዘግይቶ የወጣው የኢ.ፌ.ደ.ሪ ሕገ-መንግሥት እንደሚደነግገው ለይስሙላ የተቀመጡትን መስፈርቶች አሟልተው የተካለሉ አለመሆናቸውን ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ከዘመቻው ማግስት ነጻ የወጡት እነዚህ አካባቢዎች በጥንቃቄ ተለቅመው በፌደራሉ መንግሥት ስር እየተዳደሩ ተጠሪነታቸው ለርሱ ብቻ እንዲሆን የሚወተውቱ ወገኖች አሉ፡፡ ራሳቸውን ችለው ይተዳደሩና ተጠሪነታቸው ግን ለፌደራሉ መንግሥት ቢሆን ሲሉ ጥሪ የሚያደርጉም አልታጡም፡፡ የራሳቸው ያልሆነ ባእድ ማንነት ተጭኖባቸው የኖሩት ማሕበረ-ሰቦች በማንነት-ለበስ ጥያቄያቸው መሰረት ወደአማራ ክልል ተመልሰው ሊካተቱ ይገባል የሚል ጠንካራ ሀይል ያለ መሆኑ አይካድም፡፡

አመሻሹ ላየተሰራጨው የብልጽግና ፓርቲ ድርጅታዊ መግለጫ

በቅርቡ ማለትም ታህሳስ 10 ቀን 2013 ዓም የወጣውና “ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው የሀገረ-ብሔረ-መንግስት የግንባታ ሂደት የተለያዩ የፖለቲካ ሃይላት አስተላለፍ ይታዩበታል” የሚለው ይህ የገዢው ፓርቲ መግለጫ በሶስተኛው ተራ ቁጥር ላይ “በሀገራችን የሚታየውን ውስብስብ ብዝሃነት የሚያስተናግድ ሀገራዊ አንድነትን ከመገንባት አንጻር በወንድማማችነት እሴት ላይ የተመሰረተ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያረጋግጥ የፌደራል ስርዓት ግንባታ እውን እንዲሆን የፓርቲው አመራሮችና አባላት በቁርጠኝነት እንዲታገሉ” አቅጣጫ መሰጠቱን አስተጋብቶ ነበር፡፡

መግለጫው በዚህ ሳይወሰን “በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ማሕበረ-ሰቦች የሚያነሷቸው የማንነት ጥያቄዎች ተገቢነት ያላቸውና ፍትሃዊ የህዝብ ጥያቄዎች መሆናቸውን ማእከላዊ ኮሚቴው ያምናል፡፡” ካለ በኋላ እነዚህ ጥያቄዎች “ነባራዊ ሁኔታውን መሰረት በማድረግ የህዝቦችን ወንድማማችነትና አብሮነት እንዲሁም የህዝቡን ነጻ ፍላጎት ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ ሕጋዊ አሰራርን ተከትለው ምላሽ ይሰጣቸው” ዘንድ በአጽንኦት ያሳስባል፡፡

እነሆ ከመግለጫው ክፍል ውስጥ አለፍ አለፍ በማለት ጥቂት ሀይለ-ቃሎችን እየመዘዝን በመጠኑም ቢሆን ለመተንተን እንሞክር፡-

የፓርቲው መግለጫ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ት.ህ.ነ.ግ) ይሰኝ የነበረው የዎንበዴዎች ስብስብ ጫፍ በወጣ ክህደት ተነሳስቶ በሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት ሰሜናዊ እዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ከከፈተበት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የሰነበተውን የመልሶ ማጥቃትና የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ የወጣ እንደመሆኑ መጠን በዋነኝነት ስለየትኞቹ ማሕበረ-ሰቦች ማንነት-ለበስ ጥያቄ በደምሳሳው ለማውሳት እንደፈለገ መገመት እምብዛም ከባድ ሊሆን አይችልም፡፡

ይህ ቀማኛ ቡድን ከቀድሞዎቹ የቤጌ-ምድርና የወሎ ክፍላተ-ሀገር በጉልበተኝነት ነጥቆ የወሰዳቸውንና በፍጹም ማናለብኝነት ከትግራይ ጋር ቀላቅሎ ያቆያቸውን የወልቃይት-ጠገዴ፣ የዳንሻ፣ የጠለምት፣ የሰቲት ሁመራ፣ የራያ አላማጣ፣ የወፍላና የመሳሰሉትን ግዛቶችና በነዚሁ አካባቢዎች የሰፈሩትን አማራዊ ማንነት ያላቸው ማሕበረ-ሰቦች እንደሆነ አንድና ሁለት የለውም፡፡

እንግዲህ ትንሽ ምጸት ቢመስልም ለራሱ ለት.ህ.ነ.ግ ምስጋና ይግባውና እነሆ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ተቋቁሞ ስራ ጀምሯል፡፡ ይሁን እንጂ ከፍ ብሎ የተጠቀሱትን አካባቢዎች ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በኋላ ማን እንደሚያስተዳድራቸው እስካሁን በግልጽ ተወስኗል ለማለት አያስደፍርም፡፡

በአሁኑ ወቅት በመሬት ላይ የሚታየውን ሀቅ ለመቃኘት ስንሞክር ግዛቶቹ ወደአማራ ክልል እየተመለሱ ስለመሆናቸውና በርሱ ስር መተዳደር ስለመጀመራቸው መጠነኛ ፍንጭ ይሰጠን ይሆናል፡፡ የየማሕበረ-ሰቦቹ ስነ-ልቡናዊ መነሳሳትም ቢሆን ይህንኑ ምልከታችንን ይበልጥ የሚያጠናክር ነው የሚመስለው፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አማራዊ ማንነታቸውን በኩራት አውስተው የማይጠግቡት የዎልቃይት-ጠገዴና የራያ-አላማጣ ማሕበረ-ሰቦች በሀይል ከተወሰደባቸው በኋላ ውድ ህይወታቸውን ሳይቀር ከፍለው የማታ ማታ ከወያኔ መዳፍ በማላቀቅ በእጅ ያደረጉትን ለም የመሬት ሀብትና ሰፊ የተፈጥሮ በረከት እንዲህ በቀላሉ መልሶ ለጠላት ለማስረከብ ት.ህ.ነ.ግን በጊዜያዊነት ከተካው አካል ጋር ፈቅደው ለድርድር ይቀመጣሉ ብሎ ለማመን ይቸግራል፡፡ ይልቁንም የማንነትና የውስጥ አስተዳደር መብት ጥያቄውን አበክረው ሲያነሱ የቆዩት እነዚህ ወገኖች ለተራዘመ ጊዜ ባካሄዱት መሪር ተጋድሎና በተቀበሉት መከራ ለተከፈለው መስዋእትነት ተገቢውን እውቅና የማይሰጥ ማናቸውም አይነት ምላሽ ምናልባትም ግፉኣኑን ከወትሮው የበለጠ እንዳያስከፋቸውና እንዳያበሳጫቸው ያሰጋል፡፡

ያም ሆኖ የቀድሞው የተጠቂነትና የአሁኑ ድል አድራጊነት ስሜት ክፉኛ የተጫጫነውና እልህ የተቀላቀለበት መስሎ የሚታየው ይህ አይነቱ የሰለባዎች ቁርጠኝነት ብቻውን ለችግሩ ዘላቂና የተሟላ መፍትሄ ሊያመጣ እንደማይችል ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

ስለሆነም አፈር ልሶ ላይነሳ ድባቅ የተመታው ት.ህ.ነ.ግ ራሱ ተመልሶ ላያንሰራራ እስከወዲያኛው ተወግዷልና ዘመቻውን ተከትሎ እንደገና በቁጥጥር ስር የዋሉት ክፍለ-ግዛቶች ወደቀድሞው ባለይዞታ ያለተጨማሪ ደም መፋሰስ ሊመለሱ የመቻላቸውን አጋጣሚ ቀላል ያደርገዋል፡፡

በየትኛውም የአለማችን ክፍል የሀይል አስተላለፍ ሚዛን ሲለዋወጥ እንዲህ ያለውን ክስተት መታዘብ ያን ያህል ያልተለመደ ነገር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ኒኪታ ክሩስቼፍ የቀድሞዋ ሶቪየት ሕብረት መሪ ነበሩ፡፡ በትውልድ ሀረጋቸው ሩስያዊ ሆነው ሳለ በጊዜው አፍቃሬ ዩክሬን የነበሩት እኝሁ አንባገነን መሪ ዩክሬንን በተለየ ሁኔታ ያስፋፉ ወይም የጠቀሙ መሰላቸውና የሩስያ ክፍለ-ግዛት አካል የነበረችው ክሪምያ እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በ1954 ዓ.ም በዩክሬን ስር ትጠቃለል ዘንድ ጉዳዩን ሕገ-መንግሥቱ ከሚያዘው ውጭ ለከፍተኛው የሶቪየት ፕሬዚዲየም አቅርበው አስወስነዋል፡፡ በዚህ እርምጃ ለዘመናት ስትበግን የኖረችው ሩስያ ታዲያ ሶቪየት ሕብረት በፈረሰችና ወደአስራምስት የተለያዩ ሪፓብሊኮች በተበታተነችበት ወቅት ከዩክሬን ጋር በሀይለኛው ተፋልማ በአሸናፊነት መልሳ ስትይዛት ከጊዜያዊ ኩርፊያ በስተቀር አጥብቆ የገሰጻት አገር ወይም አለም-አቀፍ ተቋም እንኳ አልነበረም፡፡

እነሆ ክሪምያ እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር ከ2015 ዓ.ም ወዲህ የደካማዋ ዩክሬን ሳይሆን የሀያሏ የሩስያ ፌደሬሽን ክፍልና አካል ሆናለች፡፡ አለም-አቀፉ ሕብረተ-ሰብ፣ በተለይም የምእራብ አውሮጳ ሀገሮችና ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካም ቢሆኑ ሳይወዱ በግዳቸው በመሬት ላይ የተለወጠውን ሁኔታ ወደመቀበሉ ከማዘንበል የተሻለ አማራጭ እንዳልነበራቸው ተስተውሏል፡፡

ወደያዝነው የራሳችን ርእሰ-ጉዳይ ስንመለስ እንደሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 48 ንኡስ አንቀጽ (1) ከሆነ በሠላም ወቅት ቢሆን ኖሮ “የክልሎችን ወሰን በሚመለከት የአከላለል ለውጥ ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ መቋጨት ያለበት ጉዳዩ በሚመለከታቸው ተጎራባች ክልሎች የሁለትዮሽ ውይይትና ስምምነት ነው፡፡ የሚመለከታቸው ክልሎች የቱንም ያህል ተቀራርበው ቢወያዩ ተጠባቂው ስምምነት ላይ ለመድረስ ካቃታቸው ብቻ የፌደሬሽን ምክር ቤት አግባብ ያላቸውን ማሕበረ-ሰቦች አሰፋፈርና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ተገቢውን ማጣራት አካሂዶ የመጨረሻ እልባት መስጠት ይኖርበታል፡፡ ይልቁንም በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (1) መሰረት የሚቀርብ ጉዳይ ከሁለት ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በተጠቀሰው ምክር ቤት አማካኝነት የማያዳግም ውሳኔ ሊሰጥበት እንደሚገባ ነው በግልጽ ተደንግጎ የምናገኘው፡፡

ይሁን እንጂ በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል አስተዳደራዊ ወሰኖችን በተመለከተ አለመግባባት ቢፈጠርና ሕገ-መንግሥቱ በሚለው አይነት የአከላለል ለውጥ ጥያቄ ቢነሳ በስራ ላይ ካለው ሕገ-መንግሥት ትክክለኛና የተፋጠነ ፈውስ መጠበቁ ‘ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ’ ይሆናል፡፡

በአማራ ማንነት መብት ተቆርቋሪዎች እምነትና አቀራረብ ነገሩ በአጎራባች ክልሎች መካከል የተፈጠረን የወሰን አለመግባባት እርስበርስ ተወያይቶ በሠላማዊ መንገድ ከመጨረስ ወይም ያንኑ ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርቦ ሕጋዊ ዳኝነት ከመጠየቅ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ አይደለም፡፡  ጉዳዩ ሕገ-መንግሥት ተብዬው ገና ሳይወጣና ክልሎቹ ራሳቸው የተሟላ እውቅና አግኝተው ሳይደራጁ ሕግን ባልተከተለ መንገድ አስቀድሞ በጉልበት የተወሰደን ለም መሬትና በግዴታ የተነጠቀን ሰብኣዊ የቡድን ማንነት ተመጣጣኝ ሀይል ተጠቅሞ ከማስመለስ ወይም በእጅ ከማድረግ ያነሰም የዘለለም አይደለም፡፡ ጥያቄው ራስን ከመከላከል ተፈጥሯዊ መብት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ሆኖ በአፈና ሀይሎች የተደፈጠጠን ማንነት ከወደቀበት የማንሳትና ራስን ከዘላለማዊ ተገዢነት ነጻ የማውጣት ነው ተብሎም በወጉ ሊገለጽ ይችላል፡፡

ስለሆነም ‘የቄሳርን ለቄሳር’ እንዲሉ ት.ህ.ነ.ግ ለማእከላዊው መንግሥት መንበረ-ሥልጣን ከመብቃቱ በፊት ገና በትግል ሜዳ እያለ በጉልበት ነጥቆ በማናለብኝነት ወደትግራይ ያጠቃለላቸው አወዛጋቢ ግዛቶች በሕገ-መንግሥቱ መሰረት እንደተካለሉ ተቆጥሮ በአከላለል ለውጥ ስም በአጎራባች ክልሎች መካከል አንዳች ድርድር ሊካሄድባቸው ወይም የፌደሬሽን ምክር ቤት ዳኝነት ሊጠየቅባቸው ከቶ አይገባም፡፡

  1. ማጠቃለያ

የዛሬይቱን ኢትዮጵያን በባለቤትነት የቆረቆሩ ያህል የሚሰማቸውና ገና ከዋዜማው በሀሰት የተዘመረላቸው ጉራማይሌ ክልሎች እንዴትና በምን አይነት መስፈርት እንደተዋቀሩ በትክክል አይታወቅም፡፡ በርግጥ የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር (ት.ህ.ነ.ግ) በትረ-ሥልጣኑን እንደጨበጠ በብሔር-ወለድ ፌደራሊዝም የተቃኘውን ሕገ-መንግሥት በመሳሪያነት ተጠቅሞ የሀገሪቱን መልክአ-ምድር በብሔር እየሸነሸነ እንደገና ሊያደራጅ ሞክሯል፡፡

ሆኖም ከማለዳው የጨነገፈውን ይህንኑ ያልተቀደሰ ፕሮጀክት እስከፍጻሜው ሊያደርሰው ባለመቻሉ ሂደቱን በግማሽ ለማቋረጥ ተገዷል፡፡ ለምሳሌ ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ፣ ኦሮምያ… በማለት ሲዘረዝር ከቆየ በኋላ ወዲያውኑ ማርሹን ያለይሉኝታ ቀይሮ የደቡብ፣ የጋንቤላ  ወዘተ. ብሔሮች፣ ብሔረ-ሰቦችና ህዝቦች… በማለት ያለበቂ እውቀትና ብልሃት በጀመረው የግዛት ሽንሸናና ድልድል መልሶ ሀፍረት ሲሰማውና አብዝቶ ሲሽኮረመም እናገኘዋለን፡፡

መላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ይሁንታችን እንኳ አስቀድሞ ሳይጠየቅ የመጣንበት ብሔርና የምንናገረው ልሳን ብቻ በመደበኛነት ተወስዶ ያለምርጫችን በዘፈቀደ በተጠረነፍንባቸው ክልሎች ሁሉ በአመዛኙ እርስበርስ ተሰበጣጥረን እንደምንኖር ነው አለም በሙሉ የሚያውቀን፡፡ ለምሳሌ የኦሮምያ ክልል በኦሮሞ ስም ይከለል እንጂ በውስጡ ሌላ አይነት ብሔራዊ ማንነት ያላቸው አያሌ ማሕበረ-ሰቦች እንደሚገኙበት እሙን ነው፡፡

በቤኒሻንጉል-ጉምዝ፣ በሃራሬና በጋንቤላ ክልሎችማ የየአካባቢዎቹ ባለቤቶች ናችሁ ተብለው በሕገ-መንግሥት ደረጃ ከሚሞካሹት ብሔረ-ሰቦች ይልቅ አሃዛዊ በሆነ መረጃ የላቀውን ቁጥር ይዘው የሚገኙት ሌሎች ማሕበረ-ሰቦች ናቸው፡፡ እንደአንድ አብነት ጠቅሰን ብንመለከተው የመተከል ዞን ዛሬ በውስጡ ካቀፋቸውና ማለቂያ የሌለው የመከራ ዶፍ በየእለቱ ከሚወርድባቸው በርካታ ወረዳዎቹና ቀበሌዎቹ ጋር በቤኒ-ሻንጉል-ጉምዝ ስር ተካሏል ይበሉን እንጂ መልክአ-ምድራዊ ቁርኝቱም ሆነ ማሕበረ-ሰብኣዊ ዝምድናው ከጎጃም አማራ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ስለመሆኑ ማን ይዘነጋዋል?

እዚህ ላይ በውል ልናስተውል የሚገባን ከዲያብሎስ ጋር የተጣባው የወያኔ አገዛዝ በሕግም ሆነ ያለሕግ ሀገሪቱን በነገድ፣ በቋንቋና በሀይማኖት  እየሸነሸነ በየጎጡ ሊያደራጀን የሞከረው እኛን በመከፋፈል የራሱን ዘላቂ ህልውናና ያልተገባ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥና በሽዎች ለሚቆጠሩ ዘመናት እርስበርስ ተጋምደን የኖርነውን ድንቅ ማሕበረ-ሰቦች ዘወትር በሚያናቁር መንገድ መሆኑን ነው፡፡ ስለሆነም ያለአግባብ የተጠረነፍንባቸውንና እዚህ ግባ የማይባሉ ምክንያቶች በየጊዜው እየተፈለጉ በሰበብ አስባቡ የምንተራመስባቸውን ትናንሽና ትላልቅ ክልሎች መቸውንም ጊዜ ቢሆን በራሳችን ምርጫና ፍላጎት መልሰን እንዳንከልስና እንዳናስተካክላቸው ልንከለከል ከቶ አይገባም፡፡

ይልቁንም አወዛጋቢነታቸው ለተራዘመ ጊዜ ቀጥሎ የምናየው የአንዳንድ ተዋሳኝ ክልሎቻችን አስተዳደራዊ ውቅር ወትሮውኑ የተሰራው ፌደራላዊው ሕገ-መንግሥት ራሱ ከመታወጁ በፊት እንደመሆኑ መጠን የስርአቱ አፈ-ቀላጤዎች አበክረው ሲያቀነቅኑለት እንደምንሰማው ያን ያህል ሕገ-መንግሥታዊ ፍተሻና ብያኔ የሚያሻው እንኳን አይደለም፡፡ ስለሆነም የብልጽግና ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው ላይ እንዳተተው የማንነት ጥያቄዎቹ ተገቢነትም ሆነ ፍትሃዊነት እውን የሚታመንበት ከሆነ ህዝባዊነታቸውን ከማጣራትና ቅቡልነታቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ “ሕጋዊ አሰራሩን በመከተል ምላሽ ይሰጥባቸዋል” ሲል አብሮ ያንጠለጠለው የግርጌ ሀረግ ተጨማሪ ብዥታን ከመፍጠር ባለፈ አንዳች ውሃ የሚቋጥር ትርጉም ያለው መስሎ አይታይም፡፡

እነሆ ከት.ህ.ነ.ግ የአገዛዝ መዳፍ የተላቀቁት የዎልቃይት-ጠገዴና የራያ ማሕበረ-ሰቦች ከትግራይ ክልል ጋር ተፋትተዋል፡፡ በዚያ ከተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ጋርም ጨርሶ አይተዋወቁም፡፡

በመሬት ላይ እንደሚታየው ከሆነ በአሁኑ ወቅት አማራዊ ማንነት ያላቸው እነዚህ ማሕበረ-ሰቦች በስሱም ቢሆን እንደሚተዳደሩ የሚታመነው በአማራ ክልላዊ መንግሥት ስር ነው፡፡ ይህ ግን የተጠቀሰውን ክልላዊ መንግሥት ልበ-ሙሉነትና የፌደራሉን መንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ ያለጥርጥር ይጠይቃል፡፡

እዚህ ላይ አንድ ግዙፍና በተባበረ ጥረት ብቻ ልንቋቋመው የሚገባን ፈተና ከፊታችን መደቀኑን መካድ አይቻለንም፡፡

በሕግ ማስከበር ዘመቻው ነጻ የወጡት ማሕበረ-ሰቦች በየትኛውም ክልል ስር ይተዳደሩ እንደሁላችንም ቀጣይነት ያለውና በአቅርቦቱም ሆነ በጥራቱ ለድርድር የማይቀርብ መንግሥታዊ አገልግሎት ማግኘት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በማንነታቸው ምክንያት በሀይል የተፈናቀሉትና ሲሳደዱ የኖሩት ወገኖችም ያለተጨማሪ መዘግየት ወደቀያቸው ሊመለሱ፣ እንደገና ሊቋቋሙና ሠላማቸው ተጠብቆ አካባቢያቸውን በማልማት ኑሯቸውን ሊያሻሽሉ ይገባል፡፡ ከድሉ ማግስት በሁሉም የአገልግሎት ዘርፎች ፈጥኖ ደራሽነታችን የሚያስፈልገውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡

አበቃሁ፡፡

1 Comment

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.