February 2, 2021
22 mins read

ስለሥርዓታዊ ለውጥ ዕድሎችና ሁኔታዎች ስናስብ – በተስፋዬ ደምመላሽ

በተስፋዬ ደምመላሽ
ጥር 25 , 2013 ዓ.ም.

በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ዘመናዊ ታሪክ ለአገርና ሕዝብ የሚበጁ የመዋቅራዊ ለውጥ ዕድሎች በየጊዜው ተክስተው አምልጠዋል? ለምሳሌ የአፄ ኃይለ ሥላሴ “ባላባታዊ” ሥርዓተ መንግሥት በደርግ “አብዮታዊ” መዋቅር ሲተካ፣ ተኪው ደርግ ደግሞ መልሶ በዘረኛ አብዮተኛ ነኝ ባይ ወያኔ ተገዶ ቦታ ሲለቅ፣ በኢትዮጵያ ዘላቂ የነፃነትና የዲሞክራሲ ለውጥ አጋጣሚዎች ተግኝተው ጥቅም ላይ ሳይውሉ ቀርተዋል ሲባል ብዙ ጊዜ የደመጣል።

በአገሪቱ የፖለቲካ ሊህቃን ዘንድ በዚህ የተለመደ አባባል ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች አንድ መሠረታዊ የአነሳስ ችግር አላቸው። ዋናው እንከን የዘላቂ ለውጥ ዕድሎችን ለይቶ ተገንዝቦ ሥራ ላይ ማዋል ከሃሳቦች አረዳድ፣ አያያዝና አፈጻጸም ጋር ያለውን ትስስር ጠለቅ ብሎ አለማስተዋል ነው።

የአባባሉ አይነታ ችግር “ነፃነት”፣ “ዲሞክራሲ”፣ “የህግ የበላይነት” እና ሌሎች ተዛማጅ ዓለም አቀፍ የፖለቲካ ሃሳቦች በረቂቁ  እንደተሰጡ ጽንሳዊ ትርጉማቸውን ወይም መርሃዊ ይዘታቸውን በቀጥታና ባንዳፍታ ሊለቁ ይችላሉ የሚል ቅድመ ግንዛቤ ወይም ግምት ነው። ሃስቦች በድፍኑ ወይም ቃል በቃል እንደተነገሩና እንደተገለጹ የሥርዓታዊ ቅየራ መሠረትና መጠቀሚያ ሊሆኑ ይችላሉ ከሚል አመለካከት የተነሳ መሆኑ ነው።

በእውነቱ ግን የሃሳቦቹ አቀባበል፣ አያያዝና አጠቃቀም ምንጊዜም ከተወሰኑ የፖለቲካ ወገኖች አቀራረቦች፣ እቅዶችና መላ ቅጦች እንዲሁም ከአገር አቀፍ ታሪካዊና ባህላዊ ሁኔታዎች ተነጥለው የሚታዩ አይደሉም። ቢያንስ በእምቁ ለድርድር ክፍት ከሆኑ ተለዋዋጭ የአጸናነስ፣ የአተረጓጎምና የአፈጻጸም አቀራረቦችና ልምዶች ጋር የተያያዙ ናቸው።

ስለዚህ በማንኛውም አገር፣ አገዛዝ ወይም የፖለቲካ ውቅር ዙሪያ የሥርዓታዊ ለውጥ ትግሎች ሲደረጉ በረቂቁ ከሰማይ የሚወርዱ፣ ባንዳፍታና በቀጥታ ሥራ ላይ ሊውሉ የሚችሉ የፖለቲካ ዕድሎች ወይም ምርጫዎች (ለምሳሌ “ዲሞክራሲ” እና “የህግ ገዥነት”) ሊኖሩ አይችሉም። ለምሳሌ ወያኔዎች እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በግልጽ አስቀምጠው የተነሱበትን፣ ለረጅም ጊዜ የታገሉለትን፣ በብዛት የሞቱለትንና በመጨርሻም ከሥልጣን የተባረሩበትን አብዮታዊ የተባለ “የትግራይ ነፃ አውጭ” እቅዳቸውን ለቅጽበት እንመልከት።

ይህን እቅድ አጥብቀው በመከተል በሻብእያ ድጋፍ ደርግን አሸንፈው አዲስ አበባን ሲይዙና አገር አቀፍ የመንግሥት ኃይል ሲጨብጡ የመላ ኢትዮጵያን ህዝብ አንድነትና ነፃነት የሚያስከብር ዲሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት የማቋቋም “አማራጭ” ውይም “ዕድል” ነበራቸው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ይህ ተጨባጭ ትርጉም የሌለው ኢታሪካዊ እሳቤ ነው። በምክንያታዊ ተስፋ የተቃኘ ሳይሆን ዝምብሎ ምኞታዊ አስተሳሰብ ነው።

የወያኔዎች ለውጥ የማምጣት “ምርጫ” በዘረኛ አማራ ጠል ተክለ ርዕዮታቸውና ፖለቲካቸው፣ ብሎም በአፓርታዪድ መሰል አስከፊ የአገዛዛ ቁመናቸው በጥብቅ የተወሰነ እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም። “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” አስቀያሚ የፈላጭ ቆራጭ አገዛዛቸውን ማቆንጂያ ስያሜ ከመሆን ያለፈ ምንም የዲሞክራሲ ሽታ አልነበረውም፣ በስም ይክሱ እንዲሉ።

ባጭሩ፣ የዘላቂ መዋቅራዊ ለውጥ ተቻይነቶችና ዕድሎች መፈጠር፣ እንዲሁም ጥቅም ላይ የመዋላቸው ወይም ያለመዋላቸው ነገር፣ በቅጡ ሊቀመር የሚችለው በታሪካዊ አውድ ነው። ካርል ማርክስ በዝነኛ አባባሉ እንደገለጸው፣ የሰው ልጅ እርግጥ ታሪክ ሠሪ ነው፣ ግን ሠሪ ፈጣሪ የሚሆንባቸውን ሁኔታዎች መምረጥ አይችልም። የዘላቂ በጎ ድርጊቶች ባለቤት የሚሆነው፣ የመዋቅራዊ ለውጥ ዕድሎች የሚያገኘውና እነዚህን በሚገባ ጥቅም ላይ ሊያውል የሚችለውም ታሪክ የፈጠራቸውን ተጨባጭ እውነታዎች በመገንዘብና ከዚህ ግንዛቤ ተነስቶም በመንቀሳቀስ ነው።

ወያኔዎች ያቋቋሙትና በዳርቻዎቹ ተጠጋግኖ እስከዛሬ የቀጠለው ጎሠኛ የአገዛዝ ሥርዓት የኢትዮጵያን አገራዊ እውነታዎች በቅጡ መገንዘቡ ቀርቶ እውነታዎቹን በመሠረቱ የካደና የተጻረረ ነው። ሐቀኛ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሌለው ወይም የራቀው መሆኑን በዲስኩሩም ይሁን በተግባሩ፣ በሚያደርጋቸውም ሆነ በማያደርጋቸው ነገሮች በተደጋጋሚ አሳይቷል።

እርግጥ አንዳንድ ጊዜ የፖለቲካ ወይም የማኅበራዊ ንቅናቄ መሪ ወጥ የሆነ የለውጥ ዕድሎች አስተውሎ ሊያሳይ ይችል ይሆናል፤ እድሎችን የመጠቀም ከፍተኛ የግል አቅም ሊኖረውም ይችላል። አገርን ግልጽ የመዋቅራዊ ሽግግር አቅጣጫ የሚያስይዝ ራዕያዊ አመራር ይሰጥም ይሆናል። በኢትዮጵያ ግን አለመታደል ሆኖ ከአፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የደርግንና የወያኔን አምባገነናዊ አገዛዞች አቆራርጦ ዛሬ ኢትዮጵያን የአብይ “ንግሥና” ላይ ያደረሰው የፖለቲካ ልምድ ይህ አይነት የአመራር አስተውሎና አቅም ኖሮት አያውቅም።

ያም ሆነ ይህ፣ በላቀ አስተዋይ መሪነት ደረጃም ቢሆን ፍጹም ግላዊነት የለም። መሪዎች የለውጥ ገድ የሚያጋጥማቸውና ወጥ አመራር ሊሰጡ የሚችሉትም ከታሪካዊ ሁኔታዎች ውጭ ተነስተው ሳይሆን በሁኔታዎቹ ዉስጥ ነው። ተጨባጭ አኳኋኖችን በምር ታሳቢ አድርገው በስልታዊ አስተውሎ በመንቀሳቀስ ለውጥ ሲያመጡም ታሪክን ከውስጥ እየኖሩ ነው።

በኢትዮጵያ የመሠረታዊ ለውጥ ዕድሎችን ለይቶ ተገንዝቦ በሚገባ መጠቀም እንግዲህ በአንድ ጎኑ የአመራር ሰጪ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ችሎታና ድርጊት ብቻ ሆኖ የሚታይ አይደለም። ይልቅስ ኢትዮጵያዊ ራስነታችን፣ ባህላችን፣ እሴቶቻችን፣ ክንውኖቻችን እና ጸጋዎቻችን ከዛሬ አድራጊ ፈጣሪነታችን ጋር ተገናኝተው የሚወራረሱበትና የሚመጋገቡበት ታሪካዊ ልምድ ውስጥ በንቃት ገብቶ ተንቀሳቃሽ አገራዊ ኃይል መሆን ነው።

እዚህ ላይ ሲወርድ ሲወራርድ የመጣው ብሔራዊ ተሞክሯችን እና ዛሬ የሚሆኑ ወይም የምናደርጋቸው ነገሮች በግንኙነታቸው ስለሚፈጥሩት ተወርዋሪ (ተንቀሳቃሽ) ኃይል ወይም በመካከላቸው ስላለው ትስስር ግልጽ መሆን ይጠቅማል። በረጅም ዘመናት ሂደት የዳበረው ብሔራዊ ባህላችን መገለጫ በቤተ መዘክርና በገዳማት በሚታዩ ቅርሳ ቅርስ አይወሰንም፤ ህያው ተንቀሳቃሽ ገጽታ አለው። ባለፈ ታሪክ ጎኑ ብቻ የሚከሰትና የሚያቅፈን ሳይሆን ዛሬ በጥልቅ የሚሰማን፣ የምንኖረውና አዙረን አስበን የምናዳብረውም ነው። በጦር ሜዳም ይሁን በባህልና ልማት ክንውኖቻችን ሁሉ ተከሳች ነው። ትውልድ ተሻጋሪ ኢትዮጵያዊነት ያንቀሳቅሰናል፤ መልሰንም እናንቀሳቅሰዋለን ወይም ልናንቀሳቅሰው እንችላለን።

በዚህ ሕያውነቱ አገራዊ ልምዳችን ወቅታዊ የመዋቅራዊ ለውጥ ዕድሎች ሊፈጥርና ዘመናዊ ሥርዓት ለዋጭ ሃሳቦች ሊያስተጋባና ሊያስተናግድ የሚችል እንደሆነ እንረዳለን። እንዲያውም ዘር ዘለሉ አገራዊነታችን የመዋቅራዊ ለውጥ ወሳኝ ግብአት ወይም መነሻ ነው ማለት ይቻላል። ከኢትዮጵያዊነት የራቀ ጠባብ ጎጠኛ ፓርቲ ወይም ጎሠኛ አገዛዝ ይህን አይነት ሰፋና ጠለቅ ያለ ሥርዓታዊ ለውጥ አስፈጻሚ መሆኑ ቀርቶ በቅጡ ታሳቢ ማድረግ እንኳን አይችልም። ምክንያቱም በርዕዮታዊ፣ ድርጅታዊና አገዛዛዊ ቁመናው ሃሳቡም ሆነ ምኞቱ ሁሉ የሚያተኩረው ብቸኛ የማንነት ፖለቲካ ላይ ነው።

በኢትዮጵያ የሥርዓታዊ ሽግግር ዕድሎች ወይም ክፍተቶች ልናገኝ የምንችለው እንግዲህ የተለያዩ የኢትዮጵያ ህብረተሰብ አካላትና ትውልዶች በተለያዩ ታሪካዊ ጊዜዎች በጋራና በቅብብሎሽ ካቆዩዋችው የተከማቹ አገራዊ  እውነታዎች፣ ሁኔታዎች፣ እሴቶችና ክንውኖች ተነስተን እንደሆነ እንገንዘባለን።

እነዚህ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ሁኔታዎች ዉስጥ የተለያዩ አብዮተኛ ወገኖችና አገዛዞች እየገቡ የሆኑ ያልሆኑ የለውጥ እቅዶች ተፈጻሚ ለማድረግ ሞክረዋል። ተራማጅ ተብዬ ኃይሎቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፣ በፉክክርና ግጭትም ይሁን በተጨባጭ ትብብር፣ አገሪቱ እስከዛሬ ለምትታመስበት ዘረኛ የፖለቲካ ሥርዓት ቀጣይነት አስከፊ አስተዋጽዎ አድርገዋል።

ከደርግ የግዛት ዘመን ጀምሮ ተራማጅ ነን ባይ አገዛዛዊም ተቃዋሚም በተባሉ ወገኖች መካከል ኃይለኛ፣ ደም አፋሳሽ ልዩነቶችና ግጭቶች እንደነበሩ፣ ዛሬም እንዳሉ፣ ሊካድ አይችልም። ሆኖም በአፋኝ አምባገነናዊ የለውጥ ፖለቲካ ቁመናቸው ወገኖቹ ጥልቅ እንከናማነትን ይጋራሉ። የፖለቲካ ባህላቸው በጠቅላላ የዘላቂ ለውጥ ዕድሎች ፈጣሪ ወይም ተጠቃሚ ሳይሆን አጨናጋፊ፣ ይባስ ብሎም በንኡስ ጎጠኛ ብሔርተኝነት ታላቅ አገርን እንዳለ አመሳቃይ እንድሆነ አይተናል።

የፖለቲካ ባህሉ እንከናማነት ዝምብሎ የዚህ ወገን ወይም የዚያ ጎሣ፣ የአንድ አገዛዝ ወይም የሌላ የሚባል አይደለም። ባህሉ በተለያዩ የዘር ስብስቦች፣ ፓርቲዎችና እና አገዛዞች ለያይተን ወይም ከፋፍለን የምናየው ሳይሆን በጎሣ ወገንተኝነትና አገዛዝ ወሰኖች ተሻጋሪነቱ የምንጨብጠው ነው። ማለትም፣ በሥርዓታዊ ወርድና ስፋቱ የምንቋቋመውና የምንፈነቅለው ነው።

የመፈንቅለ ሥርዓት ተግዳር

ባለፉት ጥቂት አመታት የጎሣ አገዛዙ የገጠመው ዉጥረት ወይም አስጊ ወቅት የተወሰኑ ቅየራዎች አስከትሏል። መጀመሪያ ሕወሐት ለረጅም ጊዜ በበላይነት ይዞት የቆየውን አምባገነናዊ የመንግሥት ሥልጣን ለቆ ወደ ትግራይ ገዢነት ዝቅ እንዲልና ይበልጥ ጎጠኛ እንዲሆን አደረገው። አስጊ ወቅቱ አያይዞም አብይን በሥርዓት ጥገና አድራጊ ፈጣሪነት አገር አቀፍ ሥልጣን ላይ አወጣው። ዉጥረቱ በኋላ ሕወሐትን በጦር ሜዳ የሚገባውን ሙሉ ሸንፈትና አይወድቁ ዉድቀት አከናነበው።

ከነዚህ እውን ቅየራዎች አልፎ የጎሣ አገዛዙ የነበረበትና ዛሬም የቀጠለበት የሚያሰጋ አገር አወዛጋቢ ሁኔታ የመዋቅራዊ ለውጥን አስፈላጊነትና ተቻይነት አሳሳቢ ነው። መሠረታዊ ሕጋዊነትም ሆነ ሐቀኛ የሕዝብ ቅቡልነት ኖሮት የማያውቅ አሮጌ አገዛዝ የሚያጋጥመው ዉጥረት ምንጊዜም አዲስ የፖለቲካ ሥርዓትን በተጨባጭ ያመላክታል። የውጥረቱ ቀጣይነት ወይም ተደጋጋሚነት የመዋቅራዊ ለውጥ ዕድሎችንና ክፍተቶችን ይጠቁማል። አሁን በአገራችን ያለው ሁኔታም ይኸው ነው። ተግዳሩ ዕድሎቹን በስልታዊ መንገድ አገር አቀፍ የሥርዓታዊ ለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ማዋሉ ነው።

የሚፈለገው ማኅበራዊ (ብሎም ፖለቲካዊ) የለውጥ እንቅስቅሴ በርካታ ነባርና ወቅታዊ እንቅፋቶች ተደቅነውበታል። እዚህ የጎሣ ሥርዓቱን ቀጣይነት የሚደግፍ አንድ መሰናክል በመጠቆም ላብቃ። ይህም እንቅፋት የአብይ የግል አመራር ነው።

አብይ ወገንተኝነትንና ጎሠኝነትን አልፎ ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት መሪነት ባሻገርም በግል ሰውነቱ ዙሪያ የፖለቲካ ስበት መሃል ፈጥሯል። ወደ ሥልጣን የመጣ ሰሞን በነበረበት ደረጃ ዛሬ ደምቆ የሚያበራ የፖለቲካ ኮከብ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፤ ደብዝዟል። ሳቢነቱ ወይም የህዝብ ቅቡልነቱ በግልጽ ቀንሷል። ይሁን እንጂ፣ በኢትዮጵያ ጉዳዮች የአብይ ግላዊ አመራር ዛሬም ቢሆን ጎልቶ ይታያል። ስለዚህ የግል አመራሩ ለሥርዓታዊ ለውጥ ትግሉ አንድምታ አለው።

እዚህ ላይ ዋናው ነገር የአብይ ጠባይ ወይም ተክለሰውነት ራሱ (ለምሳሌ አማላይ አንደበቱ ወይም ሁሉን እኔ አውቃለሁ፣ እኔ አደርጋለሁ ባይ ባሕሪው) አይደለም። ይልቅስ አነሰም በዛም ግላዊ የሰዎች ስሜት ሳቢነቱን እየተጠቀመ ለነባሩ ጎሠኛ የፖለቲካ መዋቅር ቀጣይነት የሚሰጠው የአመራር አገልግሎትና ድጋፍ ነው።

እርግጥ የአብይ ጠባይ እንዳለ ለመዋቅራዊ ለውጥ የሚመች ሳይሆን ለውጡን በቅጡ ታሳቢ የማድረግ ዝንባሌ እንኳን አይታይበትም። አብይ በገዛ አገራቸው በገፍ ለሚጨፈጨፉ ዜጎች፣ በተለይ አማሮች፣ ስብእና ማሳየት ይቸግረዋል፤ ሰምቶ እንዳልሰማ አይቶ እንዳላየ ይሆናል። ከቴክኖክራታዊ የእድገት እቅዶች ባሻገር ይህ ነው የሚባል የመሠረታዊ ለውጥና ልማት አላማ እምብዛም አይከተልም። ለፖለቲካ መርህ ታማኝነት ይጎለዋል፤ ሃሳቦቹ የተጣሩ፣ የተሳኩና የተደራጁ ሳይሆኑ ልቅምቅም ናቸው። እነዚህ የአብይ ተክለሰውነት መገለጫዎች እንዳሉ ለሥርዓታዊ ለውጥ ምቹ እንዳይደሉ እንረዳለን።

ይሁን ኢንጂ፣ የአብይን ወጥ የግል ፖለቲከኛነት ስናረጋገጥ ማተኮር የሚያስፈልገን ነባሩን የማንነት ፖለቲካ መዋቅር እየጠጋገነ በማስቀጠል የሚጫወተው ሚና ላይ እንጂ ዝምብለን የሰውዬው “ተክለሰውነታዊ” ገጽታዎች ላይ አይደለም። የአብይ ግላዊ አገዛዝ ላይ ላዩን ድርጅታዊ ቅጥና ሥነ ሥርዓት የተጓደለበት ቢመስልም በወያኔዎች ከተቋቋመው የዘር ፖለትካ መዋቅር ጋር በአስተሳሰብና አሠራር በመሠረቱ የተቆላለፈ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።

ይህ መቆላለፍ የሥርዓት ቅየራ ዕድሎችን አፋኝ ስለሆነ ያለፈውን የወያኔ ገዢ ወገን ከአሁኑ የአብይ ኦነጋዊ አመራር ጋር ያገናኘው ‘የሽግግር’ ዱካ ቀጥተኛ ነው። በወያኔም ሆነ በኦነጋዊ ገጽታው ነባሩ አምባገነናዊው ዘረኛ ሥርዓት በፍዘታዊ ኃይሉና በአመራሮቹ እቅድ ዲሞክራሲያዊ አማራጮችን የሚያሟሽሽ መሆኑን እንረዳለን። ይህ ግንዛቤ የአገር ወዳድ ሥርዓታዊ ለውጥ ኃይሎች የመጀምሪያ ስልታዊ እርምጃ መሆን አለበት።

[email protected]

Leave a Reply

Your email address will not be published.

Latest from Blog

ከነፃነት ዘገዬ የአራት ኪሎው ኦነግ ሸኔ ከቁጥር ጋር እንደተጣላ ዕድሜውን አገባደደ፡፡ ኦነግ/ኦህዲድ ዛሬም ሆነ ዱሮ፣ በቤተ መንግሥትም ይሁን በጫካ ቁጥር ላይ ያለው አቋም ምን ጊዜም ያስደንቀኛል፡፡ ደግሞም እየባሰባቸው እንጂ ሲቀንሱ አይታዩም፡፡ ጥቂት

80 ቢሊዮን ብር ስንት ብር ነው?

በላይነህ አባተ ([email protected]) መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ልጆች እያታለሉና እየደለሉ ከእምነታቸው ለመንጠቅ ሲቃጡ በ1951 ዓ ም ባሳተሙት ‘መድሎተ አሚን ወይም የሃማኖት ሚዛን ጥልቅ መጽሐፍ ሽፋን ላይ ሕዝብ ልቡናውን፣ ዓይኑን፣ ጀሮውንና

ሰው ሆይ!

“በአንደበቴ እንዳልስት መንገዴን እጠብቃለሁ፤ ኃጢአተኛ በፊቴ በተቃወመኝ ጊዜ በአፌ ላይ ጠባቂ አኖራለሁ።”  መዝሙረ ዳዊት 39:1 ወንድሙ መኰንን፣ ኢንግላንድ 15 January 2025 መግቢያ የአገር መሪ፣ በስሜታዊነት እንዳመጣለት አይዘረግፍም። እያንዳንዷ ንግግሩ እየተሰነጠቀች ትታይበታለች። ንግግሩ ቁጥብ መሆን

ከተዘራ ያልታረመ አንደበት የጠቅላይ ሚኒስትር አነጋጋሪ ንግግሮች

አስቻለው ፈጠነ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከዘመናዊ ተፅዕኖዎች ጋር በማዋሃድ ባሳየው ልዩ ችሎታ የተቸረው አርቲስት ነው ። ጥበባዊ ጥረቱ ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ጥልቅ ባህላዊ ትሩፋት እና የሙዚቃ ልምምዶች በልዩ ሚዛን፣ ዜማ እና ዜማ

አሞራው ካሞራ | አስቻለው ፈጠነ

January 15, 2025
ፈራ ተባ እያልን እንጂ ስለፋኖ ትግልና አደረጃጀት ብዙ የሚባል ነገር አለ፡፡ እንዳጀማመሩ ቢሆን ኖሮ እስካሁን ፋኖ ኢትዮጵያን በአጠቃላይና አማራን በተለይ ከታወጀባቸው የመፈራረስና የዕልቂት ኦነግ-ኦህዲዊ ዐዋጅ ነጻ ባወጣቸው ነበር፡፡ ይሁንና በምናውቀውም በማናውቀውም በምንገምተውም

ይድረስ ለፋኖ አደረጃጀቶች በያሉበት – ነፃነት ዘገዬ

የአማራ ሕዝብ የኅልውና ትግል፦ ዘርፈ ብዙ የጥቃት ሰለባ የሆነ መንግሥት መር፣ ማንነት ተኮር እልቂት ለታዎጀበት ሕዝብ በጥብአትና በጀግንነት የሚከናወን የዘመናችን ሐቀኛ አብዮት ነው። አማራው በዋለበት እንዳያድር፣ ባደረበት እንዳይውል ተወልዶ ያደገበት ቀዬ ድረስ

ከአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች የተሰጠ የጋራ መግለጫ!

January 14, 2025
ኤፍሬም ማዴቦ ([email protected]) ባለፉት ሁለት ወራት አገር ውስጥና በውጭ አገሮች ያሉትን የኢትዮጵያ ሚዲያዎች ካጨናነቁ ዜናዎች ውስጥ አንዱ ፓርላማው ይህንን ወይም ያንን የህግ ረቂቅ አጸደቀ የሚሉ ዜናዎች ናቸው። የኢትዮጵያ ፓርላማ ምንም ይሁን ምን

የኢትዮጵያ ፓርላማ ሲመረመር

 ፈቃዱ በቀለ(ዶ/ር)   ጥር 2፣ 2017(January 10, 2025) መግቢያ ባለፉት ሃምሳ ዓመታ በአገራችን ምድር ሲያወዛግበንና በብዙ መቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ህይወታቸውን እንዲያጡ የተደረገበት ዋናው ምክንያት በፖለቲካ ስም የተደረገው ትግል ነው። ይህ ብቻ

ፖለቲከኛ ማለት ምን ማለት ነው? ፖለቲከኛ ራሱን የቻለ ሙያ ነው ወይ? በምንስ ይገለጻል? ለአንድ ህብረተሰብ የሚሰጠው በተጨባጭ የሚታይና የሚመዘን ነገር አለ ወይ? ፖለቲካ ሲባልስ ምን ማለት ነው? አገርን መገንቢያ ወይስ ማፈራረሺያ መሳሪያ?

Go toTop