ሰሞኑን በመተከል ጉዳይ ፓርላማው ከፓርላማው ያልለመድነው ዓይነት ለሚጨፈጨፍ ሕዝብ ተቆርቋሪነት ያዘለ ውይይትና ውሳኔ ሲያስተላልፍ በሚዲያ ተመልክተናል። ያ የምናውቀው ኢህአዴግ መቶ ፐርሰንት የተቆጣጠረው ፓርላማ ነው ሌላ? ከምር ነው ሴራ? ከዚህ በፊት እንዲህ ዓይነት ተቆርቋሪነት ያሳየበት ወቅት መቼ ነበር? ብለን መጠየቃችን አይቀርም።
ፓርላማው ደራሲ አያልነህ ሙላቱ
እሱ በራሱ ላይ ቅንጣት እምነት ያጣ
…ዝፈን ሲሉት ዘፋኝ ሊቀ መኳስ ዋጣ
አልቅስ ሲሉት አልቃሽ ጣምራ እንባ እያወጣ
ብሎ የገለጸው ዓይነት የካድሬ ስብሰብ ነው። በራሱ ነጻነት የሚሠራ ሳይሆን የገዢው ፓርቲ ወይም የጠቅላይ ሚንስትሩ አሻንጉሊት ነው የሚያስብል ታሪክ ነው ያለው። ፓርላማው ከዚህ በፊት በዘር ተለይተው ስለሚጨፈጨፉት ተቆርቋሪነት ያሳየበት አንድ ክሥተት ነበር። መቼ ነበር? አዎ ሰኞ ጥቅምት ሃያ ሦስት ነበር። ከጦርነቱ አንድ ቀን በፊት።
ብልጽግና በሕወሃት ላይ አማራውን ለማዝመት በፈለገ ጊዜ ጉሊሶ ላይ ቅዳሜ የተጨፈጨፉትን አማሮች እሁድ ጠ/ሚ ለመጀመሪያ ጊዜ የዘር ጭፍጨፋን የዘር ጭፍጨፋ ብለው ሲጠሩ፣ ሰኞ ፓርላማው በእንባ እየተራጨ ሸኔና ሕወሃትን የማውገዝ ድራማ መደረከ። ማክሰኞ ፋና ይሁን ዋልታ የኦሮማራ ነጠላ ዜማ (ወይም ዶክዮመንታሪ) ሲለቅ ዋለ። እሮብ ፋኖና አማራ ሚሊሺያ ሶሮንቃ ላይ ከወያኔ ጋር ጦርነት ገጠሙ። እንግዲህ የፓርላማው በዓይነቱ የመጀመሪያ የነበረው የለቅሶ ትእይንት አማራውን ‘ያንተም መንግሥት ነን፤ የሚያሳድድህም ሕወሃት ነው፤ ተረዳድተን እናጥፋው’ የሚል መደለያና ለዘመቻ መቀስቀሻ የፕሮፓጋንዳ ድራማ ነበር ማለት ነው።
በዚያን ጊዜ ገናም ጦርነቱ ሳይጀመር ብዙ ሰው ባልተለመደው የፓርላማ ተቆርቋሪነት ተገርሞ ነበር። እንዲህም ተገጥሞ ነበር
ይቺ —– የዛሬው ፓርላማ
የለቀቃት —– ነጠላዋ ዜማ
በዘር ጭፍጨፋ እልቂት ለራደው ጨለማ
የእፎይታ ብርሃን መፈንጠቂያ ሻማ?
ወይንስ
ከአስመሳዮች ማማ
ለትህነግ ማብሰያ ማገዶ ለቀማ
የተሰማች ——- ሙዚቃዊ ድራማ?
እውነታው ከዚህ የፓርላማ ድራማ ወራትም በኋላ በወለጋና በመተከል ዘር ተኮር ጭፍጨፋው ተጧጡፎ መቀጠሉ ነው። ያኔ ፓርላማው ተላቅሶ ሕዝቡንም ቀስቅሶ ነበር።
ከዚያም ወዲህ ብዙ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ በአማራው ላይ ተከሥቷል። ፓርላማው ግን ልክ እንደ በፊቱ ጭጭ ነው ያለው። ለቅሶ የለ፣ የሐዘን መግለጫ የለ፣ የሐዘን ቀን ይታወጅ የለ። ዝም እንደ ወትሮው ልማዱ።
አሁን ሰሞኑን ደግሞ ድንገት ለኢህአዴግ ፓርላማ እንግዳ የሆነ፣ ከትክክለኛ ፓርላማ ግን በዜጎች የሚጠበቅ ዓይነት ውሳኔና ውይይት* በዘር ተኮር ጭፍጨፋው ላይ ፓርላማው ሲያካሄድ ታይቷል። ይቺ አሁንም እንቆረቆርልሃለን የሚል ድራማ በመመድረክ ለሌላ ዘመቻ የማመቻቸት ሥራ ናት ወይስ የምር? እንግዲህ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ወርራ ቁጭ ብላለች። የገባችው አማራ ተብሎ በተከለለው ክልል በኩል ቢሆንም የደፈረቸው የሀገርን ሉዐላዊነት እንጂ ያንድ ክልልን ድንበር አይደለም። ይህን ጥቃት መከላከል ያለበት ሁሉም የኢትዮጵያ የመከላከያ እና የጸጥታ መዋቅር በቅድሚያ፣ ከዚያም ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ በደጀንነት ነው እንጂ የአማራ ክልል በተባለው ውስጥ የሚገኙ ፖሊስና ታጣቂዎች ብቻ አይደሉም። ልዩ ኃይል የሚሳተፍ ከሆነም ከሁሉም ክልል የተውጣጣ ልዩ ኃይል ከመከላከያው ጎን ሊገባ ይገባል። ለፍትሐዊነትና ለፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ለታሪክም ሲባል።
ካለበለዚያ ሌላ ክልል ነው በሚል ፌዝ መተከል ገብቶ የወገኖቹን ጥቃት ማስቆም የተከለከለ ልዩ ኃይል በምን ስሌት ነው ከሌላ ሉዓላዊ ሀገር ጋር ብቻውን ተለይቶ እንዲሰላለፍ ሊደረግ የሚችለው? የአማራ ልዩ ኃይል ተለይቶ ሱዳንን መግጠም አግባብ ነው ከተባለ ለአማራ ልዩ ኅይል መተከል ገብቶ በጉሙዝና በኦነግ ተለይተው የሚጨፈጨፉትን የአገውና የአማራ ንጹሐን መታደግ ይበልጥ አግባብነት ይኖረዋል።
ስለዚህ የፓርላማው ሰሞነኛ እንቅስቃሴ ለመተከል ጨለማ፣ ብርሃን ሰጪ ሻማ ነው? ወይስ የአማራን ታጣቂ ለሌላ ዘመቻ የማድሪያ የኮንቪንስና የኮንፊውዝ ድራማ? ብለን ለመጠየቅ እንገደዳለን። ይህም ከከንቱ ተጠራጣሪነት የመነጨ ሳይሆን የአማራ ብልጽግና አባላት በተለያየ ቦታና በሚዲያ እየተከሠቱ ተጨፍጫፊውን ሕዝብ በሐሰት ከመደለል ውጪ ወገንን የሚታደግ ሥራ ለመሥራት አለመቻላቸውን በተደጋጋሚ ስላስተዋልን ነው። ኦህዴድ መቼም ኦህዴድ ነው። እንዲያውም ‘ኦህዴድ መቼም ኦነግ ነው’ ቢባል ተግባሩን ይበልጥ ይገልጸው ይሆናል። የፓርላማው ተቆርቋሪነት የምር ከሆነም ሁሉንም በቀጣዩ በተግባር የምናየው ይሆናል።
ብልጽግና የሚሠራቸውን ነገሮች ሁሉ በሁለት መክፈል ይቻላል ብዬ ነበር ከዚህ በፊት
- የምርጫ ቅስቀሳ
- የምርጫ ክስከሳ
አሁን ሳየው ሦስተኛና ግዙፍ ነገር እንደረሳሁ ይገባኛል። የሥልጣን ማስከበርና የሥልጣን ጥቅለላ። እነዚህ ሥራዎች የሚደጋገፉና የሚመጋገቡበት ጊዜ ይበዛል። ለምርጫ ክስከሳ ብሎ የሚያጠፋቸውን ፓርቲዎች ሲያጠፋ የምርጫ ቅስቀሳ የሚሰራበት የፕሮፓጋንዳ እድል ያገኛል። ለሥልጣን ማስከበር ብሎ የሚሠራውን ሥራ ለምርጫ ከስከሳም ለቅስቀሳም ይጠቀምበታል። እንግዲህ ከነዚህ ሦስቱ አንዱን ፍላጎት እስካልተቃረነ ድረስ በመተከልም ደም እንደጎርፍ መፍሰሱ፣ ሕዝብ መፈናቀሉ ይቀጥላል፣ ሱዳንም ቢፈልጋት ጎንደር ገብታ መቀመጥ ትችላለች፣ ብልጽግና ጉዳዩ አይሆንም። ባጭሩ ብልጽግና የሚንቀሳቀሰው ጉዳዩ ከነዚህ ሦስት ትኩረቶቹ አኳያ ፋይዳ የሚያስገኝ ከሆነ ብቻ ነው።
የሆነ ሆኖ ጦርነት ባልታወጀበት ለስድስት ወር ያለማቋረጥ በመተከል የፈሰሰው የንጹሐን ደም ከዘመኑ ባለሥልጣኖች፣ ፖለቲከኞችና የሃይማኖት ተቋማትም አልፎ በዚህ ዘመን የምንኖር ኢትዮጵያውያንን ሁሉ የሚያስጠይቀን ነው። ሰው ታርዶ አካሉ ሲበላ ይህንን ሰምቶ በዝምታ መቀጠል ከወገን ቀርቶ ከማንም የሰው ልጅ የሚጠበቅ ተግባር አይደለምና።
ግድያው ባስቸኳይ መቆም አለበት፣ የተፈናቀሉ ወደ ቦታቸው ሊመለሱ ይገባል፣ እስከዚያው ባሉበት ጊዜያዊ እርዳታ ይድረስላቸው።
የሞቱትን ነፍስ ይማር፣ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናትን ለተሰደዱት የኔ የሚላቸው መንግሥትን እንመኝላቸዋለን። ሆን ተብሎ በሽብር እንዲኖሩ ለተደረጉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁሉ ፈጣሪ የእፎይታቸውን ቀን እንዲያቀርበው እንማጸናለን።
አርብ ጥር 14፣ 2013
*ውሳኔና ውይይቱ ትክክለኛና ችግሩን በቅልጥፍናም ይሁን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ብቸኛ አማራጭ ነው ለማለት ሳይሆን ቢያንስ ፓርላማው ትኩረት ሰጥቶ፣ አስጠንቶ ውይይት ማካሄዱ ተገቢ ሥራ ነው ለማለት ነው።