ከይርጉ እንዳይላሉ
11/09/20
በሃገራችን ኢትዮጵያ ከለውጡ ጅማሮ አንስቶ ሕዝብን በወገነ አቅጣጫ እውን እንዲሆኑ የምንጠብቃቸው አጀንዳዎች ስላሉን የመንግሥት አመራር ባጠቃላይና በትረ ስልጣኑን የጨበጠው መሪ በተለይ የሚመዘኑት ከሕዝብ ፍላጎት( expectation )አንፃር በሚከናወን ተግባር እንጂ በራሳቸው ፍላጎት በሚያከናውኑት መልካም ሥራ አይደለም።ለምሳሌ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ከሚሰጣቸው አንዱ የሕገ መንግስት መሻሻል ጉዳይ ነው። ምክንያቱም በቋፍ ላለው ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ዋንኛው መሰናክል በሕገ መንግስት ማእቀፍ ውስጥ ያለው ቋንቋን መሠረት ያደረገው የአስተዳደር ክልል ጉዳይ ወዴት እየገፈተረን መሆኑን በውል ስለምንረዳ ነው።አሁን ባለንበት ሁኔታ ለፍትህ መታጣት፣ለህግና ስርዓት አለመከበር፣ ለሰብአዊና ዴሞኮራሲያዊ መብት ጥሰት ዋንኛውና ብቸኛው መነሻ ቋንቋን መሰረት ያደረገው ሕገ መንግስትና እሱን መነሻ አድርገው የታወጁ አግላይ የከልል መንግስት ሕጎች ለተከሰቱ ተከታታይ ችግሮች ቀጣይነት ገፊ ኃይል ሆነው እያገለገሉ በመሆኑ ነው።
ወደዚህ አብይ ጉዳይ ከመግባታችን በፊት መታወቅ ያለበት በበርካታ አጥጋቢ ምክንያቶች የተጠየቀው የአንቀጽ ማሻሻያ እንጅ የሕገመንግስት ለውጥ አለመሆኑን ነው።የሕገ መንግስትም ለውጥ ቢሆን ሕዝብን ወክለው በስራ ላይ ያለ የተወካዮች ምክርቤት ና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እስካለ ድረስ የሽግግር ሂደቱን በመጠኑ ለጥጦ የሲቪክ ማሕበራትን ፣እውቀት ተሰሚነትና ችሎታ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክክፍሎችን ባሳተፈ አደረጃጀት በሕዝብ ተወካዮች ውሳኔ የሚሰጥበት ረቂቅ ቢዘጋጅ ይመረጣል ምክንያቱም ሕጉም ቢሆን የፀደቀው በውሳኔ ሕዝብ ሳይሆን በውክልና ድምጽ በመሆኑ ነው።
በመሰረቱ “ተቆርቋሪ ” የበዛለት በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግስት እንዴትና በማን እንደተደራጀ ዓላማው ምን እንደሆነ የሚታወቅ ነው።የሕገ መንግሥት አር,ቃቂ ኮሚሽን ሰብሳቢ የነበሩት የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በመጽሐፋቸው እንደገለጹልን ጉዳዩ እነመለስ ሌሊቱን በጓዳ እያሴሩበት ቀን ለይስሙላ ውይይት እየተካሔደበት የፀደቀ ሕገ መንግስት መሆኑን ነው።[ለዝርር መረጃ በሕገ መንግስቱ አርቃቂ ኮሚሽን ቃለጉባዔ ላይ ተመስርቶ ጋዜጠኛ ተመስገን ደስአለኝ ያቀረበውን ጥናታዊ ዘገባ ይመልከቱ።]
የሚገርመው
መንግሥት “ሕገ መንግሥቱን ለመናድ ያሴሩ ኅይሎች “ይላል
ወያኔና ኦነግ “ሕገ መንግስቱ በመጣሱ” ይላሉ፣ በሌላ በኩል
በአንድ ወቅት
ከኢሕአዴግ ጋር ሲፋለሙ የነበሩ ሕገ መንግስቱን ሲኮንኑና ሲያብጠለጥሉ የነበሩ ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ “የሽግግር ወቅት ብቸኛ ሰነድ “አድርገው በመቀበላቸው የመጀመሪያዎቹ ሁለተ ሳይታክቱ በሚያስተጋቡት ሦስተኛው በወሰደው አቋም የለውጡን ኃይል ግራ አጋብተዋል።
የዚህ አይነቱን አድርባይነት ወይም በዘመኑ ቋንቋ መተጣጠፍን እንደፖለቲካ ጥበብ የሚቆጥሩ ፣ በቋንቋ ላይ የተመሠረተው ፌዴራሊዝም ያሚያስከተለውን የዘር ፍጅትና የሰብአዓዊ መብት ጥሰት አስቀድመው ያሳሰቡትን የለውጥ ኃይሎች ለእሥር ሲዳረጉ በፍርድቤት ውሳኔ ከተፈቱ በኋላ ለደረሰባቸው እንግልት አንኳን ተቃውሞ ያላሰሙ፣ በተካሄደው የዘር ፍጅትና የሰብአዊ መብት ጥሰት ዝምታን የመረጡ ነውረኞች፤ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ድርጊቱን ሲኮንኑና ሲያጋልጡ ለማዘናጋት የሄዱበት አቅጣጫ አላዋጣ ሲል እጅግ በጣም ከረፈደ ማውገዛቸው ሕዝብን ከመናቅ ካልሆነ ሌላ ምን ምትክ ምክንያት ይገኝለታል።
ቋንቋን መሠረት ያደረገው የአስተዳደር ክልል ይህንኑ ተንተርሶ በየክልል የወጣው አግላይ ሕግ አንዱ መገለጫው የመሬት ይዞታ ላይ የተመሰረተው ግንኙነት ነው
በአገራችን ኢትዮዮጵያ ታሪክ አያሌ ማሕበረሰቦች በተለያዮ ስፍራዎች በተለያዮ ምክንያቶች (በወረርሽኝ፣በተፈጥሮ አደጋ በጦርነት በሕዝብ ብዛት) ሰፍረዋል ፣ተፈናቀዋል ፣ተሰደዋል።
ከኢትዮጵያ የረጅም ዘመን ታሪክ አንፃር ከመቶ አመታት በማይበልጥ ግዜ በክርስቲያን ማእከላዊ መንግስትና ከመኃመዳውያን ጋር በተካሄደ ፲፭ አመታት የዘለቀ በሰውም በንብረትም አያሌ ጉዳት ያስከተለው ጦርነት ተካሂዳል። ሁለቱም ተፋላሚዎች እጅግ በጣም በተዳከሙት ወቅት የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ የኦሮሞ ማሕበረሰብ የሕዝብ ብዛት ንረትና የተፈጥሮ ኃብት ውስንነት መነሻ ምክንያት ሆኖ ተስፋፍቷል። በአጭር ጊዜ ውስጥ በተወሰነ የግዜ ቀመር በፈረቃ ባካሄደው ጦርነት ለዘመነ መሳፍንት ማንሰራፋት ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባለፈ የማእከላዊ መንግስትን መልሶ ለማቋቋም በተደረገው ትግል የማይበገር መሰናክል ሆኖ ቆይቷል። የኦሮሞ ፍልሰት በታሪካችን ኃይማኖትን ሰበብ በማድረግ ከታዩ እልቂቶች በተለየ ያለ ምንም ማጋነን ከፍተኛው የሕዝብ ፍጅት የታየበት ክስተት ነበር። ፍልሰቱ በደረሰበት ቦታ ሁሉ የሕዝቦች ማንነት መገለጫ የሆነውን ቋንቋ ፣ባሕልንና የአስተዳደር ስርአትን ወይም ዘይቤን በመደፍጠጥ የኋልዮሽ በሆነ ፣እድሜና ፆታን መሰረት ባደረገ ማሕበራዊ የስራ ክፍፍል የተካ ስርአት ነበር። የኦሮምን ፍልሰት ያነሳሁበት ምክንያት በቁጭት ወይም በቁልጭት ሳይሆን የኦሮሞ ማሕበረሰብ በታሪካችን ውስጥ ከሚሸፍነው ድርሻና በመሬት ይዞታና በተፈጥሮ ኃብት አጠቃቀም ረገድ በየማሕበረሰቡ ግንኙነት ላይ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ በማሳየት ለአያሌ መሰናክሎች የምንጋለጥበት አደጋ ከፊታችን የተጋረጠ በመሆኑ የችግሩን ምንጭና አራማጅ ኃይል በውል ተረድተን የማያዳግም መፍትሄ ማቅረብ ወይም መቅረብ ስለሚኖርበት ነው።
አሁን ባለንበት ሁኔታ ሳብ ረገብ እያለ የሚሄደው የሽግግር ሂደት “ተኃድሶ” በተወሰኑ ወቅቶች ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎች የታየበት፣ ለቀጣይነቱ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ና የለውጡ አጋሮችን መስዋእትነት የጠየቀ ቢሆንም የተኃድሶው ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ቀልብ የሳበና ትኩረት የተሰጠው በመሆኑ ባለፍት ሁለት ተኩል አመታት እየተውተረተረም ቢሆን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ለመዝለቅ ችሏል። በመሆኑም የለውጡ አመራር አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገባ ጉዳዮችን መፈተሽ ይኖርበታል። ስለዚህ እደግመዋለሁ በቁርጠኝነት ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ሕግ ና ስርዓትን ማስከበር፣ የሰብአዊ ና ዲሞክራስያዊ መብቶችን የሚፈታተኑ ተግዳሮቶችን ለመግታት ፈጥኖ መገኘትና የችግሮች ሁሉ መፈልፈያ የሆነውን ቋንቋ መሠረት ያደረገው”ሕገ መንግሥትታዊ ፌደራሊዝም” በዚህም ሳቢያ የተፈጠሩ “አግላይ የክልል ሕጎችን” መፈተሽና የእርምት እርምጃ መውሰድ ለተኃድሶው ቀጣይነት አማራጭ ሆነው ከፊታችን ተደቅነዋል።በመሆኑም ከስሜታዊነት በፀዳ አኳኋን በነዚህ ጉዳዮች ላይ የምንወስደው አቋም የምንጓዝበትን አቅጣጫ እንደሚወስኑ እሙን ነው።
ፖለቲካ በሕብረተሰብ ውስጥ የሚከሰትን ማናቸውንም ጉዳዮ በመደገፍም፣ በመቃወም ወይ በገለልተኝነትም አቋም የሚወሰድበት ፣ለተግባራዊነትም ተያያዥነት ያላቸውን ነባር ና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመፈተሽና ውጤቱን ታሳቢ በማድረግ የሚንቀሳቀሱበት አቅጣጫ ነው ማለት ይቻላል። ይህም አቅጣጫ ነባራዊና ህልናዊ ሁኔታዎችን በመመርመር የእድገት ህግጋቶችን ሚዛን ጠብቆ መተግበርን የግድ ይላል። ከዚህ አንፃር አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግስት የሚያካሂደው
* “የጥልቅ ግምገማ ውጤት” ከሆነ ነባሩን አቅጣጫ ከታየበት ችግርና ድክመት አጥርቶ ማራመድ፣
*” ተኃድሶ ከሆነ ” የተኃድሶውን ፈለግ አስቀድሞ በማሳየት ለውጥ ማካሄድ ይጠበቅበታል፣ ምክንያተቱም “ጊዜ ና ለውጥ የሚያስተናግዱት የሚጠቀምባቸው ብቻ በመሆኑ ነው”።
በጊዜ ሂደት ለመረዳት እንደተቻለው ግን ሁኔታዎችን ማረጋጋት ባለመቻሉ ወይም ከሁለቱ ባንዱ አቅጣጫ ለመሄድ ባለመወሰኑ እጅግ በጣም አዝጋሚና አዘናጊ በሆኑ እርምጃዎች መንስኤነት በተፈጠሩ ምስቅልቅሎሽ ሳቢያ ለውጡ በሚያሳዝን ሁኔታ በተረኝነትና ፣በተኃድሶ መሃል አጣብቂኝ ውስጥ ተቀርቅሯል ።
እንደሕዝባዊነት የሚያዋጣው ተኃድሶ ማካሄድ ነው። አማራ ጠል ዘረኝነት ተፈትሾ አያሌ መስዋእት ተከፍሎበት ወያኔን ለአበሳ የዳረገ በመሆኑ ፣ ቀደም “ኢሒዴን “በኋላ “ብአዴን ” አሁን ” ብልጽግና ” በሚል ስያሜ የሚጠራው የአድር ባይነት ጥግ መለኪያ ድርጅት ያለምንም የእርማት ንቅናቄ በአዲስ ስያሜ ግራ የሚያጋባ አቋሙን ይዞ በተመሳሳይ ከፍታና መድረክ ላይ መታየቱን ቀጥሎበታል፣ያልተረዳንለት ችግር ካለ ሕዝብን አለኝታ አድርጎ ለመውጣ ወገቡን አቅንቶና ወድሮ በአባላት ንቁ ተሳትፎ በአዲስ ጉልበት (በትኩስ ኃይል) አመራሩንና አካሉን ማጠናከር ይኖርበታል፤ አለበለዚያ በሽብልቅ ተኃድሶ ውስጥ የገባው ጽንፈኛው የኦነግ ክንፍ በተናጠል “በተረኝነት” ኦሮሚያን በሌሎች ሰላም እጦትና ኪሳራ ለመገንባት በሚያደርገው ጥረት ለመቋቋም የሚወረወርለትን የሚቀበል ብቻ ሳይሆን በሕብረቱ ውስጥ አንፃራዊ ነፃነቱን የጠበቀ ከውስጥ በመነጨ ጥንካሬ በሁለት እግሩ የቆመ ኅይል ሆኖ መገኘት አለበት።
የችግሩ ምንጭ ምንድነው ?እንዴትስ ይወገዳል ? የሚሉትን ጥያቄዎች በውል ተገንዝበን የማያዳግም መፍትሄ መቅረብ ይኖርበታል። የበኩሌን የመፍትሄ ኃሳብ ከማጋራቴ በፊት አንድ ተዛማችነት ያለው ምሳሌ ላቅርብ እንደሚታወቀው የቋንቋ ፌደራሊዝም ከፈጠረው አንዱና ዋንኛው ችግ ር የመሬት ይዞታ ነው። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአገራችን ኢትዮጵያ በምድሯ አያሌ ማሕበረሰቦች በየትኛውም መልክአ ምድር ምክንያቱ ወረርሽ፣ የተፈጥሮ አደጋ ጦርነት እና ሌሎችም ታክለውበት ከአንዱ ስፍራ ወደሌላው ተሰደው ኖረዋል፤ በታሪክ አጋጣሚ በወረራ የሌሎችን ስልጣኔ ባሕል ና ቋንቋ እየደፈጠጠ ባለይዞታ የሆነው የኦሮሞ ማሕበረሰብ የፖለቲካ ምሁራን ነን ተብየዎች መሬትን ጠፍጥፎ የሰሩትን ያህል ሌሎች ነዋሪዎችን በጭካኔ በታገዘ ለማየትም ለመስማት በሚዘገንን እርምጃ ሲያፈናቅሉ ከምን አይነት አግባብነት ተነስቶ እንደሚያከናወን ማሰብም መገመትም መክበዱ ነው።ለዚያውም ከታሪካችን እጅግ ቅርብ ለሆነ ግዜ በወረራ የሰፊ ይዞታ ባለቤት ሆኖ የዚህ ችግር ምንጭ መሆን አስነዋሪ ነው። የአሜሪካን ቀይ ሕንዶች ምናልባት በዚህ አይነቱ የመሬት ቅርምትና የባለቤትነት ይዞታ የሚፈጥረውን ስስታምነት በአስተዋይነት በማያዳግም ሁኔታ ያስዎገዱበት በኃላፊነት ስሜት መሬትን በጋራ ለመንከባከብ የቀየሱት ዘዴ ይመስለል አንድ ምሳሌዊ አባባል አላቸው።
” ይህን መሬት ከልጅ ልጆቻችን የተበደርነው ነው እንጂ ከቀደምቶቻችን የወረስነው አይደለም,”
በማለት በማይናወጥ አቋም “የሚያደፈርስ ባእድ አፈናቃይ” እስከመጣ ድረስ ተግብረውታል ተጠቅመውበታል ።
እሩቅ ሄድኩ እንጂ በታሪካችን በወላይታ ስርወ መንግሥት (Dynasty) በፍልሰት ሄደው ከማሕበረሰቡቡ ጋር ተዋህደው ይኖሩ የነበሩ ትግሬዎች የነበረውን ሥርወ መንግሥት ገልብጠው በዘመኑበት የመጨረሻ ወቅት በካዎ ጦና ላይ ማሕበረሰቡ አምጾ በለዘበ የመማክርት ጉባኤ አገሩን እንዲገዛ እስከተወሰነበት ድረስ .”በመሬትም በሕይወትም የመወሰን ፎጹም ስልጣን ነበረው”። ከዚህ የምንገነዘበው ወረራውም ሆነ ፍልሰቱ የሚሸፍነው እርቀትና በመሬት ይዞታ ላይ ያለው ግኑኝነት ነባሩን ስርአት በመናድ ለሰላም እጦት ለፍትህ መዛባት ምክንያት መሆኑን ነው።
ታዲያ የኛዎቹ መዘዙን ለማየት የተሳናቸው ምንደኞች ቋንቋን ፡መሠረት ያደረገ ፌዴራሊዝም ሕገ መንግስታዊ እውቅና እንዲያገኝ በማድረጋቸው በበቂ ታሪካዊ ምክንያት፣ የሕዝብ ክምችትና የእድገት አቅጣጫ ጠብቆ በመደራጀት ላይ የነበረውን,”የኢሕድሪ” አስተዳደር መዋቅር አሻሽሎ እንደመቀጠል ጣሊያን በአምስት አመት ቆይታው ተጠሪነቱን ለሮም በማድረገ ሊተገብረው የነበረውን የቋንቋ ፌደራሊዝም መጠነኛ ለውጥ በማድረግ ተገበሩት።
። የዛን እለት የአሣራችን የመጀመሪያ ቀን ተበሰረ። “አይን አጠገብ ያለች ቅጠል ተራራ ትጋርዳለች “እንዲሉ የአገራችን የፖለቲካ ምሁራን”ከብልኮ ጥብቆ “ተሽሏቸው ጠባቡን ጎጆአቸውን አደራጅተው ለመሞቅ ምስኪኑን የማሕበረሰቡን አባላት እየሰው በክልላቸው አዲስ የገዢ መደብ ሆነው ” ፈጣሪያቸውን” ወያኔን ተገዳደሩት።ይሄ እውን እንዲሆን ለዘመናት አብሯቸው የኖረን የአማራውን ማሕበበረሰም ነፍጠኛ በማለት በጠላትነት ፈርጀው ተደራጁበት ጭካነ በተሞላበት አካሄድ ጨፍጭፈው ቀሪውን አፈናቀሉት አሰደዱት በይዞታው ስር የነበረችን ኩርማን የእርሻ መሬት ተቀራመቱት።ለዚህ ና ለማንኛውም ችግር ለሕግና ፍትህ ጥሰት ፣ለዴዴሞክራሲና ሰብአዊ መብት መረገጥ መነሻውም መድረሻውም በቃንቋ ላይ የተመሠረተው ፌደራሊዝም በመሆኑ መፍትሄውም ቋንቋንና ፣ የሕዝብ ብዛትን መልክአምራዊ አቀማመጥን ፣የአስተዳደር ቅልጥፍናንና ሌሎች መስፈርቶችን አካቶ “የአስተዳደር ክልልን” ” በአስተዳደር ወሰን”መተካት በአብሮነት ለመኖር ከታሪክና በመስዋእትነት ከደረስንበት ብቸኛው ተምክሮ መገንዘብ ይቻላል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳሁኑ ዘመን አንድነቱን የሚፈታተን ብክለት ሳይጠናወተው ቀደም ባሉ ጊዜያት ለተወሰነም ጊዜ ቢሆን ሁኔታዎች እስኪመቻቹ ያለመንግስት ቆይቷል። በጣሊያን ወረራ ወቅት፣በደርግ የመጀመሪያ ዓመታት አካባቢ እና ኢሕአዴግ ስልጣን
ባግባቡ እስኪቆናጠጥ ማለት እጁ ያልደረሰባቸው ብዙ አካባቢዎች በነበሩበት ወቅት፤ይህንኑ አስመልክቶ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ በአንድ አጋጣሚ ይመስለኛል የሕገመንግስቱን ሰነድ ሲረከቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ “ውለታውን” ላለ መዘንጋት ስለሕዝቡ ጨዋነት መስክረዋል።ለዚህ ዋናው ምክንያት እንደዛሬው ሳይሆን ተቻችሎ የመኖርን ባሕል የሰላምና መረጋጋትን ጠቀሜታ አጣጥሞ የሚያውቀው ሕዝብ ምግባረ መንግስት የተዋሃደው ስለነበረ ነው።
በመሰረቱ መንግስት ለሕዝብ አገልጋይ እንጂ ተገልይ ሊሆን የሚያስችለው ምንም አመክንዮ የለም።የተቋቋመው ስለሕዝብ ሕልውናው የሚረጋገጠው በሕዝብ እስከሆነ ድረስ እራሱን አድራጊ ፈጣሪ አድርገው ማየት የለበትም
በታዳጊ አገሮች እኛንም ጨምሮ ሁኔታዎችን ብንፈትሽ ግንኙነቱ የተገላቢጦሽ ሆኖ እናገኘዋለን።የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመንግስትም ሆነ ከተቋማት ጎን የሚቆመው ሕልውናውንና ጥቅሙን እስካስከበሩለት ጊዜ ብቻ
በመሆኑ መንግስትም ሆነ ተቋማት አገግሎት ለመስጠት ቀደምትነት ማሳየት ብቻ ሳይሆን በገቡት ቃል መሰረት ኃላፊነትን በቆራጥነት መወጣት አለባቸው።
ይሄን ማድረግ ባልቻለ መንግስትም ሆነ ተቋም ሕዝብ በውለታ የገባበትንም ሆነ በመግባባት የተፈጠረን ቋጠሮ ለመፍታት ጊዜው ሲደርስ ፈቃድ የማይጠብቅበት ተፈጥሮአዊ መብቱ በመሆኑ በተናጠል ውሳኔ ሲያደርግ አይተናል ።
መታወቅ ያለበት የሕዝብ ውሳኔ የሚከተለው ባለፉት እና የእዛ ድምር ውጤት በሆነው ወቅታዊ ሁኔታዎች ላይ በመመስረት እንጂ ስለሚመጣው ተስፋ በማድረግና በመጨነቅ አለመሆኑን የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ምሥክር ነው።
ስለዚህ በአገራችን ሁኔታ የመንግስትና የሕዝብ ግንኙነት ምጣኔን በተመለከተ በጥቂቱ ይህል ካልኩ ስለሃገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ማንሳት ተገቢ ይመስለኛል።
ሃገራችን የምትገኝበትን ሁኔታ ካወቅንበት ወደ ተሻለ ከፍታ በምናደርገው ጉዞ የተሻለ እርከን ላይ የምንገኝ ቢሆንም ተቀጣጣይ ሁኔታዎች የበዙበትና ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ሁኔታ ውስጥ በመሆናችን ከመቸውም ጊዜ በላቀ በጋራ ጉዳይ ላይ መረባረብን የሚጠይቅ መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ለኒህ ጋባዥ የሆኑ ምክንያቶችን በሁለንተናዊ መልኩ ከዚህ እነደሚከተሐው ማየት ይቻለል ።
በቅርቡ የተገኘው ድል ወያኔ በተሳሳተ ስሌትና አጠቃላይ ዝግጅቱን ለግብ ለማብቃት በሰሜን እዝ ሰራዊታችኝ ላይ አስቦና አልሞ በማዘናጋት የወሰደው ዘግናኝ ወታደራዊ እርምጃ ለመንኮታኮት እንጅ ለጠበቀው ድል ዋስትና አልሆነውም። በመከላከያ ሠራዊት ፣በአማራ በአፋር ልዮ ኅይልና ከሰለባ የተረፈው የሰሜን እዝ ጦር በወሰደው መልሶ መቋቋምና ማጥቃት የወያኔ አመራር በጉራ ከተኮፈሰበት ከፍታ ተፈነገለ።
በውጤቱም ሁለት መሰረታዊ ትኩረት የሚሹ ጉዳዳዮች ተከሰቱ፣
ሀ/በተሃድሶው መሪ ኃይሎች ውስጥ የተመጣጠነ ግንኙነት መፈጠሩ ፣
ለ/ በሁለቱም አቅጣጫ ተጠቃሚ ለመሆን በተሃድሶ ኃይሎች ውስጥ የሽብልቅ ገብቶ ውጤቱን ወደራሱ ግብ ለማቃናት ሚጣደፈው አክራሪ የኦነግ ክንፍ ቦታ መያዙ ናቸው።
አሁን የተገኘው ድል በወሳኝ መልኩ የወያኔን አመራር ቢያንኮታኩትም ይሄ ድል ለተረኝነት ሳይሆን የተኃድሶ አለኝታ ለመሆኑ ሳውል ሳያድር በሚወሰዱ ተከታታይ እርምጃዎች መረጋገጥ አለበት።
ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው ይገባ የነበር ሕገ መንግስት የማሻሻል ወይም የመለወጥ ተግባር ቀድሞውንም በተሃድሶ አመራር አጀንዳ ውስጥ ያልተካተተ መሆኑ በወረደ መልኩ ቢነገርም ማለት “ለአንድ ክልል”ብለን ሕገመንግስ አንለውጥም መባሉ እና ቀደም ብሎ በጥሪ ወደአገር ቤት የገቡ የኦነግ ድርጅቶች ፍለጎት በ አቶ ሌንጮ ለታ ሲገለጥ “ጥሪውን ተቀብለን የመጣነው የኤትኒክ ፌደራሊዝምን” ይበልጥ ለማጠናከር ነው ማለታቸው ፣ ከዚህም በላይ ሕገ መንግቱን ማሻሻልም ሆነ መለወጥ የአንድ” ሕዳጣን ብሄረሰብን ቬቶ ስልጣን” ፈቃደኝነትን የሚጠይቅ መሆኑን ተስቶን ወይም አንዱ ከልካይ ሌላው አጠናካሪ መሆናቸው አተነው ሳይሆን በሥራ ላይ ካለው ፖርላማ ሥልጣን በላይ እንዳልሆነ ስለምናውቀው ነው። ካለፍት ስርአቶች በተለየ በሕገ መንግሥቱ ከለላ የጎሳ ፌደራሊዝ በይዘቱ በፈጠረው ችግር ሉአላዊነታችን ተጋላጭ በመሆኑና ከመቸው ጊዜ ለውጭ ጣልቃ ገብነት የተደላደ ሁኔታ መፍጠሩ አሳሳቢ በመሆኑም ጭምር ነው።
የሚገርመው አቶ ልንጮ ከተከፈለው መስዋእትነትና ከወደመ ንብረት ባሻገር ገዝፎ የታያቸው ህውሃትና ኦነግ የዘውግ ፌደራዝም መስራች በመሆናቸው የአንዱ ካስማ መነቀል ለሕገ መንግስቱ ሕልውና ያሳሰባቸው ሙሆኑ ነው። ሌላው ጉዳይ ወያኔ በምግባሩ ከሥልጣን ተወግዶ እንኳ ሕገ መንግስቱ መሻሻል ሳይደረግበት አገልግሎት ላይ መሆኑ ድፍረት ስጥቷቸው ይሆን ወይስ ኦቦ ሌንጫ ሊረዱት ተስኗቸው ከወያኔ አመራር መንኮታኮት በኋላ “ሕውኃት ቀደምት ቦታውን እንዲይዝና ለድርድር የሚቀርብበት ሁኔታ እንዲመቻች” ማሳሰባቸው አጃኢብ የሚያሰኝ ነው።ሞክንያቱም ደራሽ ወንዝ የወሰደውን ቁሳቁስ በአመዛኙ በዝርዝር ማወቅ ቢቻልም በቀድሞ ይዞታው ወደነበረበት ቦታ መመለስ ጨርሶ የማይታሰብ መሆኑን ዘንግተውት ይሆን ???
እዚህ ላይ ሊያስታውሱ የሚገባ አንድ ጉዳይ ኦነግ የሽግግር መንግስት መስራች የተወካዮች ምክሮ ቤት አባል በነበረበት ወቅት አቋሙን ለማጽናት ባላስቻለው ቁመና ውስጥ እያለ በምርጫ ስርአት በተፈጠረው ውዝግብ ምክር ቤቱን ለቆ በመውጣቱ ወያኔ አስቀድሞ ባዘጋጀለት ወጥመድ ውስጥ ገባ ቀደም ሲል በተደረገው ስምምነት ከኢሕአዴግ ሠራዊት በስተቀር ለዋስትናው የሻአቢያ ጦር ጥበቃ እንዲያደርግ ሆኖ በ፲ሽዎች በላይ የሚገመቱ የኦነግ ታጣቂ ኃይል ሑርሶና ዲዴሳ ከተተ፣ ኦነግ ከሽግግር ምክር ቤት ሲወጣ ሻአብያ ጥበቃውን አነሳ ኦነግ ባልተመቻቸ ሁኔታ ወያኔን በወቅቱ በሚመፃደቅበ የትግል ዘዴ ለመፋለም በመወሰኑ በሑርሶና ዴዴሳ ከተው የነበሩ በቅጡ ያልተጀራጁ ታጣቂዎችን ለእስራትና ምርኮ አጋለጦና የቀሩት በመበተናቸው የድርጅ አካላትና አባላት ከፍተኛ መናጋትና ቀውስ ውስጥ ገቡ፤ ወያኔ ባስተማኝ ስጋቱን አስወግዶ የበላይነቱን አረጋገጠ።ኦቦ ሌንጮ አሁን ያለንበትን ትግል እንደከዚህ በፊቱ ቦሌ ላይ ቪዛ አስመትቶ የመውጣትን ያህል አቅለው ከሆነ ማስተዋሉ ይበጃል ያስቡት።
ሌላው ትኩረት የኢዜማ የአደረጃጀት ቁመና ያሰባሰበው የሰው ኃይል እንደተጠበቀው ሆኖ አባላቱ ላልተወሰነ ጊዜ በማቆያ ሥፍራ እንዲከርሙ የተወሰነባቸው ይመስል አጠቃላይ ፣ ተለዋዋጭ እና አደገኛ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በገረገራ አጥር እጨነቁረው እንደሚያይ አቋም የሚሚወስዱት መግለጫ የሚያወጡት እጅግ በጣም ከረፈደ ነው። አንዳንዴ ግዜ በአንደበት የሚገለጡ አቋሞች የግሌ አቋሜ ነው የሚል ተቀጥላ ቢሰጠውም በፈለገው አኳኋን ይቅረብ አነጋጋሪ አቋሞችን መተቸት ያስፈልጋል ለምሳሌ “የመጀመሪያ ስራችን እነአብይ የጀመሩትን ለውጥ ተጋግዘን እዳር ማድረስ ነው። ከዚያ በኋላ ነው የፖለቲካ ፍክክር የሚደረገው ፣አገር ስትኖር አገር እንደአገር ስትቆም ነው በፖለቲካ ይዋጣልን የምንለው” የሚል የፕሮፌሰሩ ብርሃኑ ነጋን ምልከታ አንብባለሁ በኔ አረዳድ እስካሁን የነአብይ ብቻ የሆነ እስኪጠናቀቅ ድጋፍ የሚሰጠው ለውጥ እንዴት ይገለጣል? እስከምናውቀው ድረስ ሕዝብም ሆነ የፖለቲካው ኤሊት ድጋፍ የሰጣቸው ያለፈውን የነበሩበትን አስከፊ ስርአት ተቃውመው ፣ ወስነው በመምጣታቸውና እና ሕዝብ የታገለለትን አጀንዳ በመቀበላቸው እንጂ የሚሄዱበትን አቅጣጫ ደጋፊው ኃይል በውል ተረድቶት አይደለም። ስለዚህ መንታ መንገድ ትይዩ ያሉ በመሆኑ እስካሁን የተለኩት ወደፊትም የሚለኩት በሚፈጠሩ መሰናክሎች ላይ በሚወስዱት አቋምና እርምጃ ነው። በዚህ አንፃር በጎ ሥራዎቻቸውን ማንሳት ቢቻልም እንደመንግስት ሕግና ሥርዓትን በማስከበር ረገድ ጥርጣሬ የሚያጭር ዳተኝነት ማሳየታቸው እንደአስፈላጊነቱ ከትችትም ከውግዘትም ነፃ አያደርጋቸውም ።
ለምሳሌ በትግራይ የመጀመሪያውን ምእራፍ በሦስት ሳምንት ያጠናቀቀ መንግስት በደቡብ፣ በደቡብና በደቡብ ምእራብ ሃገራችን ላለፍት ሁለት አመታት እና ከዚያም በፊት ዘር ተኮር የሆነ ግድያ ማፈናቀልና ስደት ሲካሄድ ስርአት የማስከበር እርምጃ አለመወሰዱ የድክመቱ ግዙፍ አካል የሚገለጥበት ነው።በርግጥ ለዚህ ድክመት ጉዳዮን በለዘብተኛ አቋም ያልታገሉትን ኢዜማን ጨምሮ ለጊዘው እንለፋቸውና ለድብቅ አጀንዳቸው ስኬት አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ድጋፍ የሰጡና የተደራጁ ጽንፈኛ የፖለቲካ ድርጅቶች ከመንግስት ጋር የሚኖራቸው የኃላፊነት ድርሻ መጠን የሚለያይ ሆኖ በውጤቱ ለተፈጠረው ቀውስ ቅድሚያ ተጠያቂው የሚሆነው መንግስት ነው።ሌላው ፕሮፌሰሩ ያነሱት ኃሳብ “አገር ስትኖር አገር እንደአገር ስትቆም ነው “የፖለቲካ ይዋጣልን የምንለው ብለዋል ይሄ አባባል ጉድለት ያለው ነው ከላይ ስለትብብሩ ያቀረብኩት ትችት እንደተጠበቀ ሆኖ የአገርን ህልውና የማስከበር ና ፖለቲካውን የማዘመን ተልእኮ ያለው ተሃድሶ የፖለቲካ ትግሉን “ከሃገር መረጋጋት በኋላ” ማለታቸው በቀረበው ሃሳብ ውስጥ እምኑ ላይ ነው የተኃድሶ ፖለለቲካውን የማዘመን ተግባር የሚታየው? ምክንያቱም የነአብይ ተልእኮ እዳር መድረስ በፖለቲካ ትግሉ ልቀው እንዲገኙ ከማድረግ ተነጥሎ የሚታይ ባለመሆኑ ነው። ስለዚህ ላይ ላዮን ሲታይ ስሜት የሚሰጥውን “ውስጡን ለቄስ” የሆነ ቅንብርን ወደጎን ትቶ መታወቅ ያለበት የትግሉ መሳለመሳ የሚካሄድ እንጂ በወረፋ ቅደም ተከተል ተይዞለት የሚከናወን አለመሆኑን ግንዛቤ ይሻል። ይህብቻ ሳይሆን መሰናክል የበዛበትን ለሁሉም ፖለቲካ ድርጅቶች እኩል የመጫወቻ ሜዳና የጨዋታ ሕግ መተግበሩ ላይ ትኩረት መስጠቱ ይበጃል።
አሁን ያለውን የምርጫ አስፈፃሚ ኮሚሽን የአፈፃፀም መመሪያና የምርጫ መርሐ ግብር ተቀብላችሁ መሰናዶ በምታደርጉበት ወቅት አንደናንተው ተመሳሳይ አደረጃጀት የሚከተሉ ድርጅቶች መሪዎችን መንግስት
ከውድድር ውጭ ለማድረግ ያለ ተጨባጭ ምክንያት ሲያሥር ፣ በችሎት ተሰምቶ የማይታወቅ እንግልት በፖለቲካ መሪዎች ላይ ሲያደርስ፣ ለመስማት በሚከብድ አሳፋሪ ምክንያቶች ችሎት ሲራዘም ምን አላችሁ? በአዲስ አበባ ላይ ተወዳዳሪ ሆኖ የቀረበን ድርጅት አስቀድሞ የመንግስትም የፕሮፓጋንዳ ሰለባችሁ ሲሆን ውጤቱን በምን ያህል እንደምትጋሩት ማወቅ ባይቻልም በምርጫ አሸናፊነትን ለብልጽግና በሚስጥር ስለማወጃችሁ ቋሚ ተሰላፊ ይቅርና አላፊ መንገደኛ በቆረጣ አይቶ የሚረዳው ሴራ መሆኑን ሳትረዱት ቀርታችሁ ይሆን??
ማጠቃለያ
የመጭው ምርጫ ውጤት የግብ ሳይሆን መጠነኛ የስልት ልዮነት በሚታይባቸው ከመቸውም ግዜ በበለጠ በተጠናከረ ሁኔታ በዘውግ ትጥቅ የደረጁ ኃይሎች የሚሳተፍበት እንደሚሆንና በሚኖራቸው አብላጫ መቀመጫ ሕግን በማውጣት በመሻር የሚኖራቸውን አቅም እንደሚጠቀሙበት በርግጠኝነት መናገር አዳጋች አይሆንም ።
የሚያሳዝነው ግን አሸናፊ ለመሆን ካለ አባዜ መንግስት፣ኢዜማና የምርጫ ኮሚሽ የግጥምጥምሽ ይሁን የታሰበበት ጉዳይ ለግዜው ባይታወቅም ድርጅቶች መክሰም ወይም ከጫዋታ ውጭ መሆን ቢኖርባቸውም ተፈጥሮአዊ ሂደቱን ጠብቆ መሆን ሲገባው ህልፈታቸውን ለማፋጠንና ቀብራቸውን ለማጠናቀቅ በምታደርጉት ጥረት የአንድ ወቅት በዳይና ተበዳይም ተቀናጅቶ መስራት የሚያስመሰግን ቢሆንም ባለፈው በጽኑ የተተቸ ተግባር አምሳያ ሲፈፀም ማየቱ ለማመን ይከብዳል ።
እኛ ባላባራ ፈተና ውስ ያለን ተደጋግፈን የቆምን ሕዝብ ነን እንጂ እንደ በለፀጉት አገሮች በጠንካራ መሰረት ላይ ያለን አይደለንም ፣ማንነታችንን እና የአንድነታችንን ጥንካሬ የፈጠረው መንፈሳችን ነው ማለት ይቻላል፤ እሱም እልህ አስጨራሽ በሆነ አካሄድ በዘውግ ፌደራሊዝም ምክንያት እየተቦረቦረ ነው።ስለዚህ የአስተዳደር ዘይቤያችን አደረጃጀቱ ቋንቋ ጨምሮ የሕዝብ ብዛትን፣የአስተዳደር ቅልጥፍናን ፣የመልክአምድር አቀማመጥን ና ሌሎችንም መስፈርቶች ያካተተ ፌደራሊዝም ቢሆን አድነታችንን በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት ከማስቻሉም በላይ
በማንኛውም መስክ ጣልቃ ለመግባት፣ ተጽእእኖ ለማድረግ በማይታክቱ አጎራባች አገሮችንና ምእራብያኑን በመግታት የአያቶቻችን ቅርስ የሆነውን ሉአላዊነታችንን እናስከብራለን…።
ቸር ይግጠመን
፪ተኛው መጣጥፍ
በፍርሃት ወይ በብልሃት
ከይርጉ እንዳይላሉ
07/26/2020
ፖለቲካ በሕብረተሰብ ውስጥ የሚከሰትን ማናቸውንም ጉዳዮ በመደገፍም፣ በመቃuወም ወይ በገለልተኝነትም አቋም የሚወሰድበት ፣ለተግባራዊነትም ተያያዥነት ያላቸውን ነባር ና ወቅታዊ ሁኔታዎችን በመፈተሽና ውጤቱን ታሳቢ በማድረግ የሚንቀሳቀሱበት አቅጣጫ ነው ማለት ይቻላል። ይህም አቅጣጫ ነባራዊና ህልናዊ ሁኔታዎችን በመመርመር የእድገት ህግጋቶችን ሚዛን ጠብቆ መተግበርን የግድ ይላል። ከዚህ አንፃር