ምን ይሉታል ይህን በደል
አለመታደል ወይስ መጉደል ?
ሰው ሆኖ ተፈጥሮ
በስም አብሮ ተቆጥሮ
ሥጋውን መልሶ የሚበላ
ያልቻለውን የሚያባላ
ከፍጥረታት መሐል ቢፈለግ
የዚህ ዓይነቱን ድርጊት የሚያደርግ
በጭራሽ !!!!
የለም በዚህ ዘመን
ማንም ቢጠቅስ ታሪክን
ምን ይሉታል ይህን በደል
አለመታደል ወይስ መጉደል ?
ምናልባትም በዘመነ ዲኖሳውሪየር (Dinosaurier)
ይታሰብ ይሆን የኖረና የሚኖር
አይመስለኝም
አልገምትም
ወይም አልገባኝም
መላ ምትም የለኝም
የተናቁት እንስሳት
ከሰው ያንሳሉ የሚባሉት
ያገኙትን ምግብ ሲበሉ
ምንም በስግብግብነት ቢጣሉ
የተረፈውን ለመብላት
ጉልበታሙ በልቶ ሲነሳ
ቦታውን ሲለቅ እያገሳ
ይቀርባሉ በተራቸው
ትርፍራፊ ቢደርሳቸው
ምን ይሉታል ይህን በደል
አለመታደል ወይስ መጉደል ?
ማተብ የሚባል ነገር ነበር
አስተማምኖ ህዝብን የሚያኖር
አቻችሎና አስተሳስቦ የሚያሳድር
ያልተፃፈ ቃልኪዳን
ዋቢ በማድረግ ማተብን
አደራን የማያስበላ
አስተማምኖ ያለመሃላ
ሞት እንኳን አንዱን ቢቀድም
ቀሪውን የማያሳብል
ዳኛና ሽማግሌ የማይፈልግ
ቃልን በቃል የሚታደግ
ነበር አንድ ዘመን
አብሮ ያኖረ ህዝቦችን
በደል እንኳ ድንገት ቢኖር
ጥላቻ በጥላቻ ቢነባበር
ማተብ አብሮ አኑሮ ነበር
ምን ይሉታል ይህን በደል
አለመታደል ወይስ መጉደል ?
ትንሽነት
አረመኔነት
ስም ቢፈለግ የማይገኝለት
ከአውሬ በታች መሆን
ሰብዓዊነትን ማጣት
ሁሌም ክህደት
መታመንን አለማግኘት
ይህ ነው የሞት ሞት
ወጭት መስበር
በህሊና መታወር
የተኛን
ያንቀላፋን
አብሮ የበላን
አብሮ የጠጣን
የተዋለደን
የተጋመደን
አብሮ የደማን
አብሮ የሞተን
አብሮ የተራበን
አብሮ የታረዘን
የጠበቀን
ደጀን የሆነን
ድኃውን
ምንም የሌለውን
ምንም ያልበደለውን
ያመነውን
ያልጠረጠረውን
የሀገርን አንጡራ ሀብት
የወገንን ደጀንና ኩራት
የመከላከይውን ሠራዊት
እሱ እየሞተ እኛን የሚያኖረውን
የውጭና የውስጥ ሰላም ጠባቂውን
በግፍ መግደል
ምን ይሉታል ይህን በደል
አለመታደል ወይስ መጉደል ?
2020-11-10