የወያኔ ነገር ለወግ አይመችም – ድራንዝ ጳውሎስ (ከባህር ዳር)

የብዕሬን ወግ ከሲሳይ ካሳ ዘቤጌምድር የማኅበራዊ ድረ ገጽ ባገኘሁት ግጥም ልጀምር
ተዉ አልተሸጠም ቢሉት ተሸጧል አለና፣
ተዉ አትግዛ ቢሉት ክላሹን ገዛና፣
ተው አትፎክር ቢሉት ፎክሮ ገባና፣
ተኩስ ሳይተኮስ መትረየስ ሳያጓራ
እማ ድረሽ አለ ዘራፉ ቀረና፡፡
እንታረቅ አለ ፉከራው ቀረና፡፡
“ከበናቸዋል” ብለው እንዳልተሳለቁ፣
ተከበናል ብለው አልቅሰው አለቁ፡፡
እንዲህ ነገሩ ድሮም ያጀገናቸው እኛው፡፡ የሾምናቸው እኛው፣ አገር እንዳቦ ቆርሰው ሲወስዱ፣ አገርን በክልል ሲለዩ፣ የብሔር ስም ሲያወጡልን፣ አገር ውስጥ የገባውን ተሽከርካሪ በክልል ሲሰይሙልን፣ አሁን ደግሞ ምርጫ አካሄደው መንግስት ሲያዋቅሩ፣… አገርን በቀን ሲዘርፉ…፣ የጦርነት ብቃታቸውን በመፍራት ዕድሜያቸው ለጡረታ ሳይደርስ በግፍ ጡረታ እንዲወጡ የተደረጉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ጀግኖች ሜዳ ላይ ሲጣሉ፣ በየክልሉ ትግሬዎች ሥልጣን ተሰጥቷቸው ለወያኔ ሲላላኩ ማን ምን አላቸው፡፡ በእነርሱ ፍርጃ የለም፡፡ እነርሱ ከወርቅ ዘር ነው የተፈጠርን ብለው በአደባባይ ሲያውጁና የእነርሱ እናቶች፣ እህቶችና ልጆች በወርቅ ሲንቆጠቆጡ፣ ልጆቻቸው ባህር ማዶ ተሻግረው ሲማሩ የአማራው፣ የኦሮሞው፣ የደቡቡ፣ የአፋሩ፣ የጋምቤላው የቤንሻንጉሉ፣ የሐረሪውና የሱማሌው አሁን ደግሞ የሲዳማው እናት የእርቃኗ መሸፈኛ ብጫቂ ጨርቅ አጣ፣ የአብራኳን ክፋይ የሆነውን ልጇን የአሸባሪነትና የተለያየ የእብሪት ስም በመስጠት ከጎኗ እየነጠቁ ላላፉት 30 ዓመታት በብሔሩና በዘሩ ለእስርና ለእንግልት በመዳረጉ የኢትዮጵያ እናት ማቃና ማቅ ለብሳ ሐዘኗን ሳትጨርስ ይኸው ዛሬ ደግሞ ራሳቸው ጦርነት አውጀውና አብሯቸው የኖረውን በሰሜን ዕዝ በሚገኙ አማራ አባላት ላይ የተፈፀመባቸው እጅግ ዘግናኝ ሰይጣናዊ ድርጊት የወያኔን መጨረሻ የሚያሳዩ ናቸው፡፡ በዕውነት እነኚህ ምስኪን ወታደሮች ለአባት እናቶቻቸው መተኪያ የሌላቸው ልጆች፣ ለሚስት ባል፣ ለልጆቻቸው አባት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ደግሞ ከፍተኛ ባለውለታዋ የሆኑ ዜጎች ናቸው።
ምን አይነት ሰይጣናዊ ሥራ ነው? እንዴትስ ይገለፃል? በተኙበት ይሄንን ሁሉ ወታደሮች መረሸን? እንዴት አንድ ወታደር አብሮት 20 ዓመት ምሽጉን የተጋራውን ጓዱን ሌሊት በተኛበት መብራት አጥፍቶ፣ የመገናኛ አውታሮቹን በጣጥሶ ሲገድል ያድራል? የክልሉስ ሕዝብ ይሄ ሁሉ ሰው ሲጨፈጨፍ ኧረ በህግ አምላክ እባካችሁ አይልም? ለካ ይሄን ያህል አጥንታችን ደርሷል ጥላቻችን? እነኚህ ዛሬ ከጀርባቸው የታረዱት ወታደሮች 20 ዓመት ሙሉ ማንን ሲጠብቁ ነው የከረሙት? ምናለ ብትማርኳቸውና የተወሰነ ቦታ አስቀምጣችሁ የራሳችሁን ኦፕሬሽን ብታካሂዱ?
ኧረ ጌታ ሆይ?
መንግስት መረጃውን ተንትኖ በዝርዝር ያውጣው የምትሉ ሰዎች እባካችሁን ተው። እንደውም መንግስት እንደዚህ ጊዜ በሳል ውሳኔ አልወሰነም። መረጃዎቹ ቢለቀቁ ለመቆጣጠር የሚከብዱ ብዙ ተያያዥ ችግሮች መምጣታቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።
ከዚህ በኋላ የምንጠይቀው፦
1. ኦፕሬሽኑን በጀመረበት ፍጥነትና ጥራት ቶሎ ጨርሶ ለወንጀለኞቹ ፍርድ መስጠት። (ምን አይነት በቂና ተመጠጣኝ ፍርድ ሊሰጥ እንደሚችል ማሰቡ እንኳን ይከብዳል)
2. ይህ ሐገር ውስጥ ያለ ሕግ የማስከበር ሂደት ስለሆነ ድርድር ምናምን የሚባለውን ቅዠት ለደቂቃ እንኳን ቦታ ሊሰጠው አይገባም። ወንጀለኞት ተይዘው ተገቢውን የፍርድ ቅጣት ካልተቀበሉ ዋናው የሐገር መከላከያ ጦር ጠቅላይ አዛዥ (ጠቅላይ ሚኒስትሩ) ለእነኛ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ ደማቸው ለፈሰሰ ወታደሮች እሱም ተጠያቂ ይሆናል።
3. በሃገርና አለም አቀፍ ደረጃ ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ የመረጃ መስጫ ስርዓት መዘርጋት። መረጃን በተናበበ መልኩ በወቅቱ ማሰራጨት።
4. ቀድመው የተዘረጉትን የንግድ ኔትወርኮች፣ የወንጀል ትስስሮችን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከስራቸው ነቃቅሎ መጣልና የሕዝብ ሐብት ሲዘርፉ የኖሩትን ድርጅቶች መውረስ።
5. እውነተኛውን መረጃ ለሕዝብ ኦፕሬሽኑ ሲጠናቀቅና ነገሮች ሲሰክኑ ማሳወቅ። ይሄንን ሁሉ መርዶ ለወታደሮቹ ቤተሰቦች እንዴት ተብሎ እንደሚነገር ማሰቡ ራሱ ያደክማል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ብለው “ወገናቸውን” ከውጪ ጠላት ሲጠብቁ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ የተሰው ወታደሮችን ነፍስ ይቀበልልን፣ ለቤተሰቦቻቸው እሱ በምህረቱ ማፅናናቱን ይላክላቸው። በእውነት ለመናገር ከልክ በላይ ታመናል፣ የጥላቻችን ጥልቀት በጣም ያስፈራል።
የህወሃት ስብስብ የሰዉ ሳይሆን የጭራቅ ስብስብ በመሆኑ የትግራይ ህዝብም ይህን አረመኔ ቡድን ቀሚስ ሆኖ ሊሸሽገዉ አይገባም፡፡
ቀስቅሰው ቀስቅሰው የተኛውን በሬ፣
ይኽው አደረጉት የጫካ ውስጥ አውሬ፡፡ እንዳለው የጎንደር ባለቅኔ ዛሬ ትዕግስታችን አይተው ቢደፍሩንም ዶሮ ጭራ ጭራ… ነውና ነገሩ በስነምግባርና በሞራል ልዕልና ታንፀን ያደግን። ጠላትን የምንገጥመው “ጠብቀኝ መጣሁልህ!” ብለን ቀጠሮ አስይዘን እንጂ አንደ ወያኔ እኛን አምኖ፣ በእኛ ተማምኖ የተኛን ወታደር በማንጅራቱ አናርድም። እኛ እኮ የአፄ ቴዎድሮስ፣ የአጼ ሚኒሊክ፣ የጀግናው በላይ ዘለቀ ልጆች ነን። እንኳን ለራሳችን ጉዶች ለጣሊያን ሽልጦና ውሃ አልከለከልንም። ምርኮኛን አብልተን፣ የተጎዳውን አክመን፣ የጠላትን ሬሳ እንኳን ለአሞራ ጥሎ ለመሄድ ህሊናችን የማይፈቅድ፣ ያልተበረዘ፥ ያልተደለዘ የሞራል ስብዕና ያለን ህዝቦች ነን። ምክንያቱም እኛ ኢትዮጵያዊያን ነን፡፡ ወያኔ ሞቱ ተቃርቧል- ወግ የለም፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.